1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰዎች ለሰዎች ዋ/ስራ አስኪያጅ መልቀቅ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 21 2006

ኢትዮጵያዊትዋ የሜንሺን ፎር ሜንሺን ወይንም የሰዎች ለሰዎች ግብርሰናይ ድርጅት የበላይ ኃላፊ ወ/ሮ አልማዝ በም በከፊል ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተሰማ። እዚህ ጀርመን የሚገኘው የሰዎች ለሰዎች ዋና መ/ቤትም ይህንኑ ኣረጋግጠዋል።

https://p.dw.com/p/1A9oE
ምስል picture-alliance/dpa

ይሁን እንጂ የድርጅቱ ቃል ኣቀባይ ለዶቸቬሌ እንደነገሩት ወ/ሮ አልማዝ በም ከነበሩበት

ኃላፊነት ቢለቁም የሰዎች ለሰዎች የስራ ኣመራር ቦርድ የበላይ ሆነው ይቀጥላሉ።

በኣሁኑ ጊዜም ወ/ሮ አልማዝ የድርጅቱን የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ እየመሩ ይገኛሉ ተብለዋል።

ታዋቂው የሰብዓዊ እርዳታ ሰው ሚ/ር ካርል ኃንዝ በም የመሰረቱት እና ለረጅም ዓመታት የመሩት የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት በኣፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ የኣስቸኩዋይ ጊዜ እርዳታን ጨምሮ በርካታ የልማት እና ማህበራዊ ግልጋሎቶችን በመስጠት ይታወቃል። በረጅም ጊዜ ኣገልግሎት ከኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ጋር በእጅጉ እየተቆራኙ የመጡት ሚ/ር ካርል በም በዚሁ ኣጋጣሚ ነበር ምስራቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ከኢትዮጵያዊትዋ ወ/ሮ አልማዝ በም ጋርም እስከመጋባት የደረሱት።

ድርጅቱ ሰዎች ለሰዎች ኣሁንም ድረስ በተለያዩ የኣገሪቱ ክፍሎች እየሰራ ሲሆን መስራቹ እና ኣንጋፋው መሪ ሚ/ር ካርል በም ግን ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ከመንበራቸው ላይ ገለል ብለው ቆይተዋል። በእሳቸው እግር ተተክተው ድርጅቱን ሲመሩ የቆዩት ደግሞ እኚሁ ባልተቤታቸው ወ/ሮ አልማዝ በም መሆናቸው ይታወቃል።

።በሰሞኑ ዜናዎች መሰረት ደግሞ ወ/ሮ አልማዝ ከስልጣን ተወግደዋል የሚል ዘገባ እየተናፈሰ ይገኛል። ይህንኑ ለማጣራት ወ/ሮ አልማዝን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ባይሳካም እዚህ ጀርመን ኣገር ሙኒክ ከተማ ከሚገኘው የሜንሺን ፎር ሜንሺን ዋ/መ/ቤት ቃል ኣቀባዩ ሚ/ር ሄርማን ኦርጌልዲንገር እንደሚሉት ወ/ሮ አልማዝ በከፊል ከስልጣን መነሳታቸው ትክክል ነው። ነገር ግን ወ/ሮ አልማዝ ስራ ኣስኪያጅነቱን ቢለቁም ኣሁንም የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ይቀጥላሉ ተብለዋል።

Der Schauspieler Karlheinz Boehm am Dienstag, 14. August 2007 in Hamburg. Boehm hat nach 26 Jahren Engagement in seiner Aethiopienhilfe rund 300 Millionen Euro an Spenden eingenommen. In den vergangenen Jahren seien Krankenhaeuser und fast 200 Schulen gebaut worden. 2,8 Millionen Aethiopiern hatte man seitdem helfen koennen. (AP Photo/Fabian Bimmer) Former German actor Karl-Heinz Boehm is seen during a photocall in Hamburg, Germany, Tuesday, Aug. 14, 2007. (AP Photo/Fabian Bimmer)
ምስል AP

ኣንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ወ/ሮ አልማዝ ከኃላፊነታቸው በከፊል የመነሳታቸው ምክኒያት ሙስናን ጨምሮ በስልጣን ያለአግባብ መገልገል ነውም ተብለዋል። ሚ/ር ሄርማን እንደሚሉት ግን ይህ ከእውነት የራቀ ነው።

ሚ/ር ሄርማን እንደሚሉት ወ/ሮ አልማዝ ኣሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ናቸው። በዚህ ሁኔታ ድርጅቱን እየመራ ያለው ማን እንደሆን ተጠይቀው ሲመልሱም ድርጅቱ በዋናነት ከጀርመን እንደሚመራ እና ጀርመን ላይም ሆነ ኢቲዮጵያ ላይ የዳይሬክተሮች ቦርድ መኖሩን የገለጹት ሚ/ር ሄርማን ወ/ሮ አልማዝ ኣሁን የኢትዮጵያውን ቡድን እየመሩ መሆናቸውንም ኣስረድተዋልቀደም ባሉት ዓመታትም ተመሳሳይ የስልጣን ሽኩቻ በድርጅቱ ውስጥ መከሰቱን እና ወ/ሮ አልማዝ በወቅቱ የበላይነቱን መያዛቸውን በመጥቀስ ኣሁን ከድርጅቱ ዋ/ስ/ኣስኪያጅነት ተነስተው ለጊዜው የኢትዮጵያን ቡድን እንዲመሩ ወይንም በቦርድ ሰብሳቢነት ብቻ እንዲወሰኑ መደረጉ ውሎ ኣድሮ ወ/ሮ አልማዝን በሂደት ከጫወታ ውጪ ለማድረግ ኣይመስልዎትም ወይ? የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው ሚ/ር ሄርማን ፈጽሞ ሊሆን ኣይችልም። ወ/ሮ አልማዝ የMFM ልብ ናቸው ሲሉ ኣስረግጠው ኣስተባብለዋል።

ኣንጋፋው የሜንሺን ፎር ሜንሺን ግብረሰናይ ድርጅት መስራች እና መሪ ሚ/ር ካርል ኃንዝ በም ከኃላፊነታቸው ገለል የማለታቸው ጉዳይ ከባለቤታቸውም ሆነ ከድርጅቱ በኩል በይፋ ባይገለጽም የእድሜ ጫናን ጨምሮ በጤና መጉዋደል ምክኒያት መሆኑን ግን የቅርብ ምንጮች ይናገራሉ።

በግብረ ሰናይ ምግባራቸው ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክተሬት ዲግሪ የተሸለሙት ሚ/ር ካርል ኃንዝ በም ከኦሮሚያ ክልል በተቸራቸው የመኖሪያ ፈቃድ መነሻነትም የኢትዮጵያን ዜግነት ማግኘታቸው ኣይዘነጋም።

ጃፈር ዓሊ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ