1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳኑ ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ የቤት ስራዎች

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 18 2011

ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ አሜሪካ «ሽብርተኝነትን ይደግፋሉ» ከምትላቸው አገሮች ዝርዝር ሱዳንን ማስወጣትን ጨምሮ ለአገሪቱ ምጣኔ-ሐብታዊ ቀውስ መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል። ለሱዳን ፖለቲካዊ እና ምጣኔ-ሐብታዊ ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት ግን በሉዓላዊ ምክር ቤቱ የተካተቱ የጦር ሹማምንትና የተቃዋሚዎች ተወካዮች ተስማምተው መስራት አለባቸው

https://p.dw.com/p/3OQTn
Sudans neuer Premierminister Abdalla Hamdok
ምስል picture-alliance/AP Photo

የሱዳኑ ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ የቤት ስራዎች

ባለፈው ሐሙስ ቃለ-መሐላ የፈጸሙት ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ ቅድሚያ ከሰጧቸው አበይት ጉዳዮች መካከል ነፍጥ ካነገቡ የሱዳን አማጽያን ጋር እርቅ ማውረድ አንዱ ነው። ለወራት ከዘለቀ እና የተቃዋሚዎችን ሕይወት ከቀጠፈ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል በኋላ ሐምዶክ የሽግግር ጠቅላይ ምኒስትር ሆነው ቃለ መሐላ የፈጸሙት ከአዲስ አበባ ወደ ኻርቱም እንደተመለሱ ነው። አብደላ ሐምዶክ ሱዳንን በጠቅላይ ምኒስትርነት እንዲመሩ የተመረጡት ለወራት ከጦር ሹማምንቱ ጥብቅ ድርድር ላይ የከረሙት ተቃዋሚዎች በእጩነት ካቀረቧቸው በኋላ ነው።

ጠቅላይ ምኒስትሩ ከአዲስ አበባ ተጉዘው ኻርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ አል-በሽርን በጣለው አብዮት በአገሪቱ ጎዳናዎች ከፍ ብሎ ይሰማ የነበረውን ነፃነት፣ ሰላም እና ፍትኅ የሚጠይቅ መፈክር የሚያሰሙ ደጋፊዎቻቸው ተቀብለዋቸዋል። እርሳቸውም በአደባባይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ እንደከረሙ የሱዳን ዜጎች «ዴሞክራሲያዊ እና ለፍትኅ የቆመ መንግሥት» ለማቆም ከጎናቸው እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። 

አብደላ ሐምዶክ "ያገሬ ሰዎች ባቀረቡልኝ ጥሪ መሰረት መጥቻለሁ። የመጣሁት አብረን እንድንሰራ፤ እኛና አገራችንም በኅብረት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድንሻገር ነው። በኅብረት ዴሞክራሲያዊ እና ለፍትኅ የቆመ መንግሥት እንገንባ። ልዩነቶቻችንን እንዴት መፍታት እንዳለብን እንስማማ፤ ነፃ ከወጣን ጀምሮ ሁሉም የሱዳን ዜጎች የሚስማሙበት ብሔራዊ መርሐ-ግብር መቅረፅ አልቻልንም። ሱዳን እንዴት መተዳደር አለባት በሚለው ላይ እንስማማ እና ውሳኔውን በሱዳን ዜጎች ለሚመረጥ መንግሥት እንተው» ሲሉ ተማፅኖ የተቀላቀለበት ጥያቄ አቅርበዋል። 

Sudan Abdel Fattah al-Burhan, Chairman Transitional Military Council (TMC) & Ahmad Rabie
ምስል Getty Images/AFP/E. Hamid

ሐምዶክ ቃለ መሐላ በፈሙበት ዕለት ቀደም ብሎ የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ተመስርቷል። በሉቴናንት ጄኔራል አብዱል ፋታኅ አል-ቡርሐን የሚመራው እና ከጦሩ እና ከተቃዋሚዎች የተውጣጣው ሉዓላዊ ምክር ቤት ለ39 ወራት ሥልጣን ላይ ይቆያል። የጦር መኮንኑ አብዱል ፋታኅ-አልቡርሐን ለ21 ወራት ተቃዋሚዎች ለ18 ወራት የሚመሩት ይኸው ምክር ቤት የሥልጣን ጊዜ ሲገባደድ በሱዳን ምርጫ ሊካሔድ ተወጥኗል። 

ሐምዶክ ከአዲስ አበባ ተጉዘው በሉቴናንት ጄኔራል አብዱል ፋታኅ አል-ቡርሐን ፊት ቃለ-መሐላ ከፈጸሙ በኋላ ባሰሙት ንግግር መንግሥታቸው ለሚጠብቁት ውስብስብ ችግሮች መፍትሔ ማፈላለግ ዋንኛ ሥራቸው መሆኑን ገልጸዋል። «በአብዮቱ ሥር የሰደደው እና 'ነፃነት፣ ሰላም እና ፍትኅ' የሚለው መፈክር የሽግግር ጊዜው ዋንኛ መርሐ-ግብር ይሆናል። የዚህን መርሐ-ግብር ዋና ዋና ነጥቦች ልንገራችሁ። ቀዳሚው ጉዳይ ጦርነቱን ማቆም፤ ሱዳንን መልሶ መገንባት፤ በውጭ አገራት እና በስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ዜጎቻችን መከራ መፍትሔ መሻት፤ የከፋውን ምጣኔ-ሐብታዊ ቀውስ ለመፍታት መሥራት እና በእርዳታ እና እገዛ ላይ ሳይሆን በአምራችነት ላይ መሠረት ያደረገ ኤኮኖሚ መገንባት ነው» ብለዋል ጠቅላይ ምኒስትሩ። 
 

አብደላ ሐምዶክ ማን ናቸው? 

አብደላ ሐምዶክ በሙያቸው የኤኮኖሚ ባለሙያ ሲሆኑ ትምህርታቸውን በኻርቱም ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል። በዩናይትድ ኪንግደም ከማንችስተር ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል። የ61 ዓመቱ ጠቅላይ ምኒስትር ባለፉት 30 ዓመታት የሱዳን ታሪክ ውስጥ ይኸን ሥልጣን የያዙ የመጀመሪያ ሲቪል ናቸው።

አል-በሽር ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ከሱዳን የፋይናንስ ሚኒስቴር ሰራተኝነታቸው ተባረዋል። ኋላም አል-በሽር የተቋሙ ምኒስትር እንዲሆኑ ያቀረቡላቸውን ግብዣ አሻፈረኝ ብለው ሳይቀበሉ ቀርተዋል። በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኤኮኖሚክ ኮሚሽንን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኃላፊነት ሰርተዋል።  በሙያቸው አንቱታን ካተረፉት ሐምዶክ ያገራቸው ሰዎች ብዙ ይጠብቃሉ። በሱዳን የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ የሆነው አልሳኖሲ አዳም እንደሚለው በተለይ አል-በሽርን ለውድቀት ላበቃቸው ምጣኔ-ሐብታዊ ምስቅልቅል መፍትሔ ከጠቅላይ ምኒስትሩ ይጠበቃል።

Abdalla Hamdok
ምስል picture-alliance/G. Dusabe

አልሳኖሲ አዳም «ከዚህ በኋላ ትልቁ ችግር ኤኮኖሚውን ከገባበት ምስቅልቅል እንዴት ማውጣት ይቻላል የሚለው ነው። ሐምዶክ በሙያቸው የኤኮኖሚ ባለሙያ ሆነው የጠቅላይ ምኒስትርነት ሥልጣን መያዛቸው በትክክለኛው ሰዓት በትክክለኛው ቦታ የተገኙ ያደርጋቸዋል። ብዙ ሰዎች በእጩነት ያቀረቧቸው እና የተስማሙባቸው ለዚህ ይመስለኛል» ሲል ተናግሯል። 
አል-በሽርን ገፍቶ የጣላቸው የሱዳን አብዮት የተጀመረው በዳቦ ዋጋ ማሻቀብ ሳቢያ ነው። ሐምዶክ የሚረከቡት የሱዳን ኤኮኖሚ ፈተና ግን የዋጋ ግሽበትን በማረጋጋት ብቻ የሚመለስ አይደለም። ጠቅላይ ምኒስትሩ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እና የሥራ አጥነትን ጨምሮ በአስተዳደር ጉድለት ከዓመት ዓመት ያደጉ ኤኮኖሚያዊ ችግሮች ከፊታቸው ተደቅነዋል። 
«የሱዳን ኤኮኖሚ ከአፍሪካ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በመጠኑ እጅግ ጠንካራ ነው። በትክክለኛው ርዕይ፤ በትክክለኛ ፖሊሲዎች ለምጣኔ-ሐብታዊው ቀውስ መፍትሔ እንፈልጋለን ብዬ አስባለሁ። ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ፈተናዎች በማገገሚያ መርሐ-ግብሮች አማካኝነት የዜጎቻችንን ችግሮች የሚቀርፍ ዕቅድ ይኖረናል። የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር፤ ነዳጅ፣ መድሐኒት እና የመሳሰሉትን የሸቀጦች እጥረት መፍታት ቅድሚያ ያገኛሉ» ሲሉ አዲሱ ጠቅላይ ምኒስትር ለሱዳን ዜጎች ተስፋ የሚያጭር መልዕክት አስተላልፈዋል። 

Sudan Khartum Machtabgabe Militär
የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎችን የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት በተፈራረሙበት ዕለት የአገሪቱ ዜጎች ደስታቸውን ሲገልጹ በአደራዳሪነት የተሳተፈችው ኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ታይተዋልምስል Getty Images/AFP/A. Mustafa

የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች እንደሚሉት ለ20 ዓመታት በዘለቀ የአሜሪካ ማዕቀብ ተገልላ የቆየችውን ሱዳን ወደ ዓለም ኤኮኖሚ መመለስ አንዱ የቤት ሥራቸው ይሆናል። ምንም እንኳ በሱዳን ላይ የተጣለው ማዕቀብ ከሁለት ዓመታት በፊት ቢነሳም አገሪቱ ዛሬም በአሜሪካ «ሽብርተኝነትን ይደግፋሉ» የሚባሉ አገሮች ከሰፈሩበት ዝርዝር ውስጥ አለችበት። በዚህ ሳቢያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የዕዳ ስረዛ አይደረግላትም፤ የውጭ መዋዕለ-ንዋይም ቢሆን የተገደበ ነው። ሐምዶክ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ያላቸው ተደማጭነት እና ግንኙነት አገራቸውን ከዝርዝሩ ለማስወጣት ገፋ ሲልም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ድጋፍ እንድታገኝ ማድረግ ይችሉ ይሆናል የሚል ተስፋ ያላቸው ባለሙያዎች አሉ። 

አብደላ ሐምዶክ «በአጭር እና ረዥም ጊዜ የሱዳንን የምርታማነት ችግሮች መፍትሔ ልናገኝላቸው ይገባል። ኤኮኖሚው ያሉበትን የውጤታማነት ችግሮች ካልፈታን በቀር ሌሎች አገሮች እና ወዳጆቻችን ምንም ያክል እርዳታ እና ብድር ቢሰጡን የሚፈይድልን ነገር አይኖርም። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እኛ ሱዳናውያን ጠንክረን መስራት ይኖርብናል። ከዚህ በተጨማሪ የበጀት አስተዳደር እና የፋይናንስ ፖሊሲውን መመርመር ይኖርብናል። በዋናነት ግን የባንክ ዘርፉ ወድቋል ማለት ይቻላል። ዕምነትን ወደ ባንክ አገልግሎት ዘርፍ መመለስ አለብን። በነፃነት እና ለውጥ ኃይል ውስጥ ከሚገኙ ባልደረቦቻችን ጋር በመሆን ከፍ ያለ ጥረት በማድረግ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ተጨባጭ ፖሊሲዎች እና  እቅዶች እናቀርባለን» ብለዋል። 

በእርግጥ ሐምዶክ እንዳሉት የሱዳንን ምጣኔ-ሐብትም ይሁን ፖለቲካዊ ችግሮች ለመቅረፍ እውቀት፣ ክህሎት እና ያላቸው የአመራር ብቃት ብቻቸውን በቂ አይደሉም። ከእንግዲህ በመንግሥታዊ ውሳኔዎች በሉዓላዊ ምክር ቤቱ የተካተቱ የጦሩ ከፍተኛ ሹማምንት እና የተቃዋሚ ተወካዮች መስማማት መቻል አለባቸው። 

እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ