1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳኑ ፕሬዝዳት የቤጂንግ ጉብኝት

ሐሙስ፣ ሰኔ 23 2003

የቻይናዉ ፕሬዝዳት ሁ ጁንታኦ «የቅርብ ወዳጃችን ሐገር መሪ» በማለት ደማቅ አቀባበል አደረጉላቸዉም።የሱዳንና የቻይና ምጣኔ ሐብታዊ ግንኙነት እጅግ ከፍተኛ ነዉ።

https://p.dw.com/p/RWmX
ሑ ና በሽርምስል dapd


30 06 11

የሱዳኑ ፕሬዝዳት ዑመር ሐሰን አል-በሽር ካለፈዉ ሮብ ጀምሮ ቻይናን በይፋ እየጎበኙ ነዉ።ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት በተገኙበት እንዲያዙ የበየነባቸዉ አል-በሽር ቤጂንግ እንደገቡ የቻይናዉ ፕሬዝዳት ሁ ጂንታኦ በክብር ዘብ የብረት ሠላምታ ደማቅ አቀባበል ነበር ያደረጉላቸዉ።አል-በሽር ባለፈዉ ቤጂንግ ከመግባታቸዉ በፊት ኢራንን ጎብኝተዉ ነበር። የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ጥናት ተቋም የሱዳን ጉዳይ ባለሙያ ፉዓድ ሒክማት እንደሚሉት የሱዳኑ ፕሬዝዳት የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ማዘዢያ ሳያግዳቸዉ ይሕን ያሕል ርቀት መጓዛቸዉና ቻይና በወንጀለኝነት የሚታደኑትን መሪ ማስተናገድዋ ለፍርድ ቤቱ ታላቅ ዉድቀት ነዉ።

«ፕሬዝዳንት በሽር የብዙ ሐገራትን የአየር ክልል አቋርጠዉ፥ ማንም ጉዟቸዉን ለማወክ ሳይሞክር ያንን ሁሉ ርቀት መጓዛቸዉ ለዓለም የጦር የወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት (ICC) ድቀት ነዉ።ይሕ በርግጥ ሊጤን የሚገባ ጉዳይ ነዉ።ለበሽር ባንፃሩ ብዙ እንቅፋት ሳይገጥማቸዉ ያን ያሕል ርቀት መጓዛቸዉ ትልቅ ድል ነዉ።»

ፕሬዝዳት አል-በሽር ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የእስራት ዋራንት ከቆረጠባቸዉ በሕዋላ ኬንያን ጎብኝተዉ ነበር።ያኔ የፍርድ ቤቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፥የተለያዩ ተቋማትና አንዳድ ምዕራባዉያን መንግሥታትም የኬንያ መንግሥት አልበሽርን እንዲያስር ከፍተኛ ግፊት አድርገዉ ነበር።ኬንያ አልበሽርን ባለማሰሯም ከፍተኛ ዉግዘትና ተቋዉሞ ገጥሟት ነበር።

በዩጋንዳ ላይም ከፍተኛ ግፊት በመደረጉ አልበሽር ባለፈዉ አመት ካምፓላ ላይ በተደረገዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል።አሁን ግን ያለፈዉ አይነት ተቃዉሞና ዉግዘት አልተሰማም። ምክንያቱም ግልፅ ነዉ።ሰዉዬዉ የጎበኙት ደካማ ሐገር አይደለም።ቻይናን እንጂ።

«የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ አባል የሆነችዉ ሐያል ሐገር ቻይና የICC አባል ባትሆንም አልበሽርን ለመቀበል መወሰኗ እና የሚጓዙበት የአየር መስመር ማመቻቸትዋ (የፍርድ ቤቱ) ዉሳኔ ተቀባይነቱ ምን ያሕል እንደሆነ የሚጠቁም ይመስለኛል።ይሕ ግን የሩዋንዳዉ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ከተፈፀመ በሕዋላ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ፍትሕን ለማስከበር መተባበር እንደሚገባዉ መስማማቱን የሚያፈርሰዉ አይመስለኝም።»

ያም ሆኖ ፕሬዝዳት አል-በሽር ከቴሕራን ቤጂንግ የሚገቡበትን ጊዜ ባንድ ቀን ማዘግየት ነበረባቸዉ።አዉሮፕላናቸዉ ወደ ቤጂንግ መብረር ከጀመረ በሕዋላ እንደገና ወደ ኢራን ተመልሶ የበረራ መሥመሩን መቀየር ነበረበት።የሱዳኑ ፕሬዝዳት የመዘግየት-መመላለሳቸዉ ሰበብ አንዳድ ሐገራት የአየር ክልላቸዉን ለአልበሸር በመከልከላቸዉ ነበር።

«የአል-በሽር አዉሮፕላን በአየር ክልላቸዉ ላይ እንዳይበር ያልፈቀዱ አንዳድ ሐገራት ነበሩ።በዚሕም ምክንያት አል-በሽር ቤጂንግ ለመድረስ መጀመሪያ ወደተነሱበት ወደ ኢራን ተመልሰዉ የጉዞ አቅጣጫቸዉን ዳግም ለማዘጋጀት ተገድደዉ ነበር።ሥለዚሕ አል-በሽር በየአር ክልላቸዉ እንዳያልፉ አንዳድ ሐገራት ከልክለዉ ነበር።»

China Sudan in Peking bei Wu Bangguo
አል በሽር ከ ዉ ባንጉኦ (የቻይና ምክር ቤት ሊ/መምስል dapd

ያም ሆኖ ቤጂንግ ደረሱ።የቻይናዉ ፕሬዝዳት ሁ ጁንታኦ «የቅርብ ወዳጃችን ሐገር መሪ» በማለት ደማቅ አቀባበል አደረጉላቸዉም።የሱዳንና የቻይና ምጣኔ ሐብታዊ ግንኙነት እጅግ ከፍተኛ ነዉ።የንግድ ልዉዉጣቸዉ ባለፈዉ የጎርጎሮሳዉያኑ ዓመት 2010 ፥ 8.6 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። አብዛኛዉን የሱዳን ነዳጅ ዘይት የምትገዛዉ ቻይና ናት።ሱዳን ደግሞ ከመጪዉ ሳምንት በሕዋላ በይፋ ሁለት ሐገር ትሆናለች።ሰሜንና ደቡብ።የቻይና ወዳጅነት ይቀጥል ይሆን? ፉዓድ ሒክማት «አዎ» ነዉ መስላቸዉ።ግን እንዴት፥-

«እንደሚመስለኝ ችይና ሥለ አፍሪቃና ሥለ ሌሎችም አዳጊ ሐገራት የምትከተለዉ መርሕ ተጨባጭ ነዉ።ሁል ጊዜ ቅድሚያ የምትሰጠዉ የራስዋንና የምትወዳጃቸዉን ሐገራት ጥቅም ማስከበር ነዉ።ከሱዳን ጋርም ቢሆን ቻይና ከደቡብም፥ ከሰሜንም ሱዳን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራት ነዉ የምትፈልገዉ።እንደሚታወቀዉ ለቻይና ከሚሽጠዉ ነዳጅ ዘይት ሠማንያ ከመቶ ያሕሉ በወደፊቱ ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ነዉ የሚገኘዉ።ሥለዚሕ ቻይና ከሰሜኑም ጋር ያለትን ግንኙነት እንደጠበቀች ከደቡብ ጋርም ጥሩ ግንኙነት ትመሠርታለች።»

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ


ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ