1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን፣የጠብ-ስምምነት ተቃርኖ አብነት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 14 2014

ሐምዶክ አዲስ አበባ በሚገኘዉ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪቃ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ምክትል ኃላፊ ሆነዉ በሚሰሩበት ወቅት የሚያዉቃቸዉ አንድ ባልደረባቸዉ «ዲፕሎማት፣ ትሁት፣ በሳል እና ሥነ-ሥርዓት አክባሪ» ይላቸዋል።

https://p.dw.com/p/43LXZ
Bildkombo | Abdel Fattah al-Burhan und Abdullah Hamduk
ምስል dpa/picture alliance

የሱዳን መሪዎች ጠብና ስምምነት

221121

እሳቸዉ በዕድሜ ታላቅ፣በፖለቲካዉ ቀልጠፍ፣ ከሃይማኖቱ ለቀቅ፣ በዉጪዉ ልምድ መጠቅ ያሉ ናቸዉ። ዶክተር አብደላ ሐምዶክ። በትምሕርት-የፖለቲካ ስልጣኑ እንደ ሳዲቅ አል መሕዲ፣ እንደ መሐመድ ሙርሲ ከፍ፣ ላቅ ያለዉን ስፍራ ይይዛሉ። በአስተሳሰብ ግን ከሱዳኑ-አልመሕዲ፣ ከግብፁ አል ሙርሲ ይልቅ ወደ ተማሩ፣ወደ ሰሩበት ያዳልሉ። ሲነጠል ብሪታንያ-ሲጠቃለል ምዕራብ አዉሮፓ ሲሰፋ-ዓለም። እኚሕኛዉ ከእሳቸዉ በ4 ዓመት ያንሳሉ። እንደ ፅኑ ሃይማኖተኛ ገራገር፣ አዛኝ ግን እንደ ወታደር ቆፍጣና ናቸዉ። ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን። ናስርስርን በስሚ-ስሚ ያደንቃሉ፣ አቡድን በሩቅ ዝና ያዉቃሉ። የአል በሽር ታማኝ ፣የአል-ሲሲ ስልት ከፊል ተጋሪ ናቸዉ። ፖለቲካን ግን መጥቶባቸዉ አወቁት እንጂ ሔደዉበት ወይም ፈልገዉት አያዉቁም። የዘመኗ ሱዳን ሁለት ገፅታዎች። ተስማሙ፤ ተጣሉ፤ ታረቁ። 

ተጣሉ፣ ተማረሩ። መፈንቅለ መንግሥት። ጥቅምት 25፣ 2021 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጠባቸዉ ሕዝብ ባደባባይ አሰለፈ፣አስፈከረ፣ አስጮኸም። ቢያንስ የአርባ አምስት የዋሐን ሕይወትን ቀጠፈ። ዓለምን አነጋገረ። አስደነገጠ። ተወገዘም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀኃፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱዢሪክ ባለፈዉ ሐሙስ።

*«ይሕ፣ ከጥቅምት 25ቱ መፈንቅለ መንግሥት ወዲሕ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር 37 ያደርሷል። በሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚወሰደዉን አለቅጥ የበዛ የኃይል እርምጃ አጥብቀን እናወግዛለን።» ዉግዘት፣ ወቀሳ፣ ክሱ፣ የአደባባይ ሰልፍ፣ ተቃዉሞዉም ቀጠለ።

«አብዮቱ የሕዝብ፣። አገዛዙም ሕዝባዊ መሆን አለበት። ጦሩ ወደ ምሽጉ----» ይልገባ ሰልፈኛዉ።

ሱዳን በ1964 ጥቅምት፣ በ1986ም። በ2018ም-በ2019ኝም እንዲያነበረች። የሲቢል ጦር ኃይል ፖለቲከኞች ፍትጊያ ምድር። ዘንድሮም እንደ ጥንት፣ ድሮዉ፣ እንደ ቅርቡም ቀጥላለች። ተረኞቹ ግን ሐምዶክና አል ቡርሐን ናቸዉ።

ሁለቱ የአንድ ሐገር ግን የሰሜን-ደቡብ ክፍለ ግዛቶች፣ የተቀራራቢ ዘመን ግን የተራራቀ ቤተ-ሰብ ዉልዶች ናቸዉ። ደቡባዊ ሱዳን ማዕከላዊ ኮርዶፋን ግዛት በ1956 የተወለደዉ አብደላ በ4 ዓመቱ ድክድክ ሲል፣ጋንዳሉ መንደር-ሰሜን ሱዳን የሚኖረዉ አብዱልረሕማን የሚመሩት የሱፊ ሃይማኖት አጥባቂ ሰፊ ቤተ-ሰብ አንድ ወንድ ልጅ ተጨመረለት።1960። ስሙንም አብዱልፈታሕ አሉት።

Sudan | Proteste nach dem Militärputsch
ምስል Marwan Ali/AP/dpa/picture alliance

ሐምዶክ ከደቡብ ወደ ሰሜን ሽቅብ፣አብዱልፈታሕ ከሰሜን ወደ ደቡብ ቁልቁል ግን ሁለቱም ኻርቱምን እያማተሩ ትልቁ ክፍልም-ቁርአንም፣ትንሽዬዉ ቁርዓን-ፊደል ሲቆጥር ትልቂቱ ከተማ  በታላቅ ሕዝባዊ አብዮት ትናጥ ያዘች።1964።

ሁለቱም የልጅነት ምኞታቸዉ በወጣትነታቸዉ ዘመን ተሳካ። ኻርቱም ገቡ። የየቅል የሕይወት ጉዟቸዉም ያኔ ተጀመረ። ታላቅየዉ የ1964ቱ ሕዝባዊ አብዮት ከተጠነሰሰበት ዩኒቨርስቲ፣ ታናሽዬዉ ደግሞ አብዮቱ ከሥልጣን ያስወገዳቸዉ እነ ጄኔራል ኢብራሒም አቡድ ከመሰረቱት የጦር ትምሕርት ቤት ገቡ።

ሐምዶክ ከኻርቱም በማንቸስተር ብሪታንያ ያደረሳቸዉን ትምሕርት አጠናቅወቀዉ፣ የሱዳን ገንዘብ ሚንስቴር ትልቅ ባለሙያ ሲሆኑ፣ አብዱልፈታሕ የጦር መኮንነቱን ማዕረግ ተራበተራ ይወጣጡበት ነበር። ሐምዶክ እንደ ዕዉቅ የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ከኻርቱም ለንደን፣ ከለንደን ሐራሬ፣ አዲስ አበባ እያሉ ትላልቅ ዓለም አቀፍ መሥሪያ ቤቶችን ሲያፈራርቁ፣ አል ቡርሐን ከኻርቱም አማንና ካይሮ በሚገኙ ምርጥ የጦር ትምሕርት ቤቶች የጦር  አዛዥነትን ዕዉቀት ቀስመዉ ደቡብ ሱዳንና ዳርፉር ላይ ይዋጉ-ያዋጉ ነበር።

ሐምዶክ አዲስ አበባ በሚገኘዉ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪቃ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ምክትል ኃላፊ ሆነዉ በሚሰሩበት ወቅት የሚያዉቃቸዉ አንድ ባልደረባቸዉ «ዲፕሎማት፣ ትሁት፣በሳል እና ሥነ-ሥርዓት አክባሪ» ይላቸዋል።

Sudan Unruhen Proteste
ምስል AFP

ጄኔራሉም እንደ ወታደር ቆምጨጭ፣ ቆፍጠን፣ ፈርጠም ያሉ ናቸዉ። ስማቸዉን መናገር ያልፈለጉ አንድ የሱዳን የጦር መኮንን በ2019 «ቡርሐን ከፍተኛ የጦር መኮንን ነዉ» አሉ «ግን በሳል ወታደር ነዉ። በፍፁም እዩኝ እዩኝ የሚል ሰዉ አይደለም» አከሉ።

ሐምዶክ እንደ ምጣኔ ሐብቱ ሁሉ ዲፕሎማሲዉን ኖረዉበታል። ፖለቲካዉንም ገባ ወጣ እያሉም ቢሆን ያዉቁታል። ጄኔራሉ ግን ፖለቲካ አያዉቁም። ወይም እንደሚያዉቁ አያሳቁዉም። እንደ 1964ቱ፣ እንደ 1986ቱ ሁሉ ኅዳር 2018 ኻርቱም ላይ የተጀመረዉ የአደባባይ ተቃዉሞ በ2019 ሲግም፣ ሒደት ዉጤቱን ሐምዶክ እንደ ሱዳናዊ ምሁር፣ አል ቡርሐን እንደ ባለጉዳይ ጄኔራል በቅርብ ይከታተሉት ነበር።

ሚያዚያ ላይ የያኔዉ የጦር ኃይሎች ኢስንስፔክተር ጄኔራል ካርቱም አደባባይ የተሰለፈዉን ሕዝብ አነጋገሩ። ከዕለታት በኋላ «ሶስት ሆነን ቀጠሮ ያዝንና አልበሽር ጋ ገባን» አሉ ጄኔራሉ  በቅርቡ «ከዚያ ሁሉም ነገር ያበቃለት መሆኑን ነገርኳቸዉ።» ቀጠሉ። አል በሽር ከሥልጣን በተወገዱ ሳልስት የወታደራዊ ሁንታዉን የመሪነት ሥልጣን እንደያዙም ጦራቸዉ ከለዉጥ ፈላጊዉ ሕዝብ ጎን መቆሙን መሰከሩ።

«የወታደራዊዉ ምክር ቤት ሚና ለሕዝባዊዉ አብዮት ድጋፍ መስጠትና ማጠናከር ነዉ። የኛ ሚና ሕዝባዊ ተቃዉሞዉንና የተቀደሰዉን አብዮት ማጠናቀቅ ነዉ። በዚሕ ሚናዉ ወታደራዊዉ ምክር ቤት ኃላፊነቱ ስልጣኑን ለሕዝቡ፣ ፍላጎቱን ለማሳካት ለተፋለመዉ ሕዝብ ማስረከብ ነዉ።»

የአልበሽር መወገድና የሕዝባዊዉ አመፅ ገሚስ ድል፣ አዲስ ፖለቲካዊ ምዕራፍ ሲቀድ ሁለቱን ያንድ ሐገር ዉልዶች ግን የሁለት የተራራቀ ሙያ፣ የሁለት ዓለም አስተሳሰብ አራማጆችን አገናኛቸዉ። አግባባ-አስማማቸዉም። በሐምዶክ ቋንቋ ለሁሉም ሱዳናዉያን እኩል ለመስረት ቃል ገቡ። ነሐሴ 21 2019።

 «የሽግግር መንግሥቱ መርሕ መሠረት ነፃነት፣ ሰላምና ፍትሕ የሚለዉ የአብዮቱ ስር የሰደደ መፈክር ነዉ። ይሕን መሰረታዊ ፍላጎት እንዳሳካ ፍቀዱልኝ። የተመረጥኩት በአብዛኛዉ በነፃነትና በለዉጥ ኃይላት ነዉ። ዛሬ ቃለ መሐላ ከፈፀምኩ በኋላ ግን የመላዉ ሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር ነኝ ብዬ አምናለሁ።»

ጄኔራሉ እንደ ርዕሠ-ብሔር ዶክተሩ እንደ እንደ መራሔ መንግሥት የሚመሩት የወታደር-ሲቢል ጥምር የሽግግር ምክር ቤት መመስረቱ የሱዳን ሕዝብን ፅናት፣ የጦር-ሲቢል ፖለቲከኞቹን አስተዋይነት፣ ማሕሙድ ዲሪሪ፣ መሐመድ ኤል ሐሰን ሌባቲን የመሳሳሉ የኢትዮጵያ፣ የአፍሪቃ ሕብረትና የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማቶችን ብልሐት ያስመሰከረ ነበር።

በስምምነቱ መሰረት የሽግግር መንግስቱ እስከ 2024 ድረስ መዝለቅ ነበረበት። ይሁንና ወትሮም ዘይትና ዉኃ የመሰሉት የሱዳን አዳዲስ መሪዎች የሕዝባቸዉን ጥያቄ ፈጥነዉ ከመመለስ ይልቅ አንዴ ከኢትዮጵያ ጋር ሲላተሙ፣ ሌላ ጊዜ ከእስራኤል ጋር ሲወዳጁ፣ደግሞ ሌላ ጊዜ ዋሽግተን፣ፓሪስ፣ በርሊን ሲሮጡ ሕዝባቸዉን ረስተዉ እርስበርስ ተላትመዉ አረፉት።

Sudan | Militärputsch | General Abdel Fattah al-Burhan
ምስል Marwan Ali/AP/dpa/picture alliance

ጄኔራል አል ቡርሐንም ፊልድ ማርሻል አብደልረሕማን ስዋር አል ዳሐብን ሳይሆን ኮሎኔል ዑመር ሐሰን አል በሽርን ወይም ጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ሲሲን መሰሉ። መፈንቅለ መንግሥት። «የሱዳን ጠባቂ ጦሩ ነዉ።»አሉ። ገራገሩ ጄኔራል ተቆጡም።ጥቅምት 25።

«ሐገሪቱን የሚጠብቁት እነዚሕ ኃይላት ናቸዉ። ለዉጡን ካደጋ የሚጠብቁት፣ የሚመሩትም  እነዚሕ ኃይላት ናቸዉ። ይሕን ለዉጥ ማንም አይመራዉም። እኛ በነፃና ትክክለኛ ምርጫ በሕዝቡ ፍላጎት ለሚሰይመዉ መሪ ሐገሪቱን እናስረክባለን።»

እስከ ዘንድሮ ጥቅምት ድረስ 5 የተሳከ፣ 12 የከሸፈ መፈንቅለ መንግሥት ያስተናገደችዉ ሱዳን አንድ መፈንቅለ መንግሥት ተጨመረላት ወይም ተጨመረባት። አዲስ ፖለቲካዊ ቀዉስ። ሌላ የአደባባይ ሰልፍ። መከራኛዉ ግን ፅኑዉ፣ ሰላማዊዉ ሕዝብ እንደገና ሕይወት፣ አካል ደሙን ይገብር ያዘ።

በሰልፈኛዉና በፀጥታ አስከባሪዎች መካከል በነበረዉ ግጭት በትንሽ ግምት 45 ሰዉ ተገድሏል። ሁለቱ የሱዳን የተቃርኖ አንድነት አብነቶች ግን ወር ሳይሞላቸዉ ትናንት ታረቁ። የሽግግር ሥርዓቱን ዳር ለማድረስ እንደገና ተስማሙ። ከቁም እስር የተለቀቁት ጠቅላይ ሚንስትር ስምምነቱን አወደሱት።

«ይሕ ስምምነት፣ የዉስጥና የዉጪ እንቅፋቶችን ለማስወገድ፣ የሽግግር ሒደቱን ወደ ተሳካ ዴሚክራሲ ለማራመድ ይረዳል የሚል ተስፋ አለን። ስምምነቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰላምና በምጣኔ ሐብቱ ረገድ ያስመዘገብናቸዉን ድሎች ለመጠበቅ ይረዳል።»

Sudan | Militärputsch | Regierungschef Abdullah Hamduk
ምስል Mohamed Khidir/XinHua/dpa/picture alliance

በስምምነቱ መሰረት ታስረዉ የነበሩ ፖለቲከኞች ተፈትተዋል። ይሁንና የጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ መንግሥት ከሥልጣን መወገዱን በመቃወም በተከታታይ የተደረጉትን የአደባባይ ሰልፎች ያስተባበሩት ማሕበራት ስምምነቱን አልተቀበሉትም።

ሰልፈኛዉም ዛሬም እንደመሰንበቻዉ «አብዮቴን» መልሱን እንደዘመረ፣ እንደተሰለፈ፣ ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር እንደተላተመ ነዉ። «እሱ (ጠቅላይ ሚንስትሩ) ከገዳዮች ጋር ለመቀመጥ መስማቱ አብዮቱንና  አብዮተኞችን መካድ ነዉ» ይላል ሰልፈኛዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ