1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ምርጫ በአንድ ቀን መራዘም

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 8 2007

ሱዳን ምርጫ ብታካሂድም የፕሬዝዳንት ኦማር አል በሺር የስልጣን ዘመንን የሚያቆም አይመስልም። በዋና ከተማዋ ካርቱም ግን የመራጮች ቁጥር አነስተኛ ነው ተብሏል። ለሶስት ቀናት ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ ለአራተኛ ቀን ተራዝሟል።

https://p.dw.com/p/1F9fi
Wahlplakat mit sudanesischem Präsidenten Omar al-Baschir
ምስል Ashraf Shazly/AFP/Getty Images

ሱዳን በሶስት የምርጫ ቀናት የመራጮች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ አራተኛ ቀን አስፈልጓታል። አራተኛው የምርጫ ቀን የተገቢነት ጉዳይ ግን አከራካሪ ሆኗል። ከምርጫው በፊት የአፍሪቃ ህብረት ባካሄደው ቅድመ ጥናት የምርጫው ግልጽነት፤ነጻ እና ፍትሃዊነት በቂ አይደለም ሲል ተችቶ ነበር። ደቡብ ሱዳን ከተገነጠለችበኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ምርጫ 16 ፕሬዝዳንታዊ እጩ ተወዳዳሪዎችና 45 የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሳተፉሉ። ስልጣንን ለፕሬዝዳንቱ ጠቅልሎ ይሰጣል ተብሎ በተተቸው በአዲሱ ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያ መሰረት የግዛት አስተዳዳሪዎች በዚህ ምርጫ አይመረጡም። ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሺር እና ፓርቲያቸው (National Congress Party (NCP) ይህን ምርጫ ያሸንፋሉ የሚል ቅድመ ትንበያ በርትቷል። ከ25 ዓመታት በላይ በስልጣን የቆዩት ፕሬዝዳንት ተፎካካሪዎች በአገሪቱ ህዝብ ዘንድ እምብዛም አይታወቁም። ፓርቲዎቹም ቢሆኑ በምርጫ ዘመቻው ወቅት ራሳቸውን በአግባቡ ለማስተዋወቅ የሚያስችል ገንዘብ ለማሰባሰብ ተቸግረዋል። በሱዳን ፕሬዝዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ የመራጮች ቁጥር ማሽቆልቆል አሳሳቢው ጉዳይ መሆኑን የአረብ ሊግ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ መሪ አላ አልዙሃይሪ ይናገራሉ።

Sudanesischer Präsident Omar al-Baschir
ምስል Ashraf Shazly/AFP/Getty Images

«ዳርፉር አሳሳቢው አካባቢ ነው። አካባቢውን የሚቃኙ አምስት ቡድኖች አሉን። እኔ ሰሜናዊውን አካባቢ ትናንት ጎብኝቻለሁ። የመራጮች ቁጥር አማካኝ ከሚባለው እጅግ በጣም ያነሰ ነው። ምርጫው በሰላም ይካሄዳል ብለን እንጠብቃለን።»

ቀድሞም በተዓማኒነቱ ላይ ከፍተኛ ጥያቄ ለሚነሳበት ፕሬዝዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ የመራጮች ቁጥር መቀነስ አሉታዊ ተጽዕኖው ይበረታል። የሱዳን መንግስት ግን በዚህ አይስማማም። የፕሬዝዳንት ኡመር ሀሰን አልበሽር አማካሪ የሆኑት ኢብራሂም ጋድኖር የመራጮች ተሳትፎ አመርቂ እንደሆነ ይከራከራሉ።

«የምርጫው ውጤት በብሄራዊ የምርጫ ኮሚሽን ይፋ ከመሆኑ በፊት ማንም ስለ መራጮች ቁጥር መቀነስ መናገር አይችልም። እንደ ፓርቲ በተለያዩ ግዛቶች በሚገኙ የራሳችን ጣቢያዎች ሁኔታዎችን እንከታተላለን። በመራጮች ቁጥር ደስተኞች መሆናችንን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።»

ያናቤ ለተሰኘ የሱዳን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ምርጫውን የሚታዘቡት አምና ኡመር አብደላ የመራጮች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም አሁንም መራጮች ይመጣሉ የሚል ተስፋ አሳድረዋል።

«ካለፈው ምርጫ ጋር ሲነጻጸር የመራጮች ቁጥር አነስተኛ ነው። ቢሆንም አሁንም መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያ ይመጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።»

Sudan Wahlkampf SPLM Tänzer der Nuba
ምስል DW/S. Foltyn

በካርቱም ሃጂ ይሱፍ በተባለ አካባቢ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ስሙን መግለጽ ያልፈለገ የምርጫ ስፈጻሚ በሶስቱ ቀናት ከተመዘገቡ ሱዳናውያን መካከል አስር በመቶ መራጮች ብቻ መምረጣቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። በሌላ የምርጫ ጣቢያ የሚገኝ የምርጫ አስፈጻሚ የመራጮቹ ቁጥር ከተመዘገቡት ከ10-20 በመቶ ብቻ መሆኑን ተናግሯል። የምርጫ ተሳትፎው በገጠራማ አካባቢዎች ከፍ እንደሚል ይጠበቃል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሳዲቅ አል መሃዲን የኡማ ፓርቲ ጨምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ ባለመሆኑ መራጮች በምርጫው ባለመሳተፍ ተቃውሟቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል። በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ2010 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ለተቃዋሚዎች የመወዳደሪያ ምህዳር የለውም ሲል የተቸው የካርተር ማዕከል ይህን ምርጫ በገንዘብ ከመደገፍም ሆነከመታዘብ ታቅቧል። የአውሮጳ ህብረትም ቢሆን «ይህ የአሁኑ ምርጫ ምንም ተዓማኒ ውጤት አያመጣም የሱዳን ዜጎች ከዚህ የተሻለ ይገባቸዋል» ሲል በፌዴሪካ ሞግሄሪኒ በኩል አስታውቋል። የሱዳን መንግስት በበኩሉ የካርተር ማዕከልንም ይሁን የአውሮጳ ህብረትን አቋም አይቀበልም።

የሱዳን ህዝቦች አርነት ንቅናቄ-ሰሜን(SPLM-North) ተብሎ የሚጠራው አማጺ ቡድን በኑባ ተራሮች አካባቢ ከመንግስት ጋር በሚያደርገው ውጊያ ሰበብ ሰባት የምርጫ ጣቢያዎች ተዘግተዋል። በግብጽ፤ሊቢያ እና ደቡብ ሱዳን ያለው ውጥንቅጥ ሱዳናውያን በአገሪቱ መረጋጋት እና ደህንነት ላይ እንዲጨነቁ አድርጓዋል።

ሲሞና ፎልቲን/እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ