1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ድርጅቱ ውሃ ለተጠሙ አዲስ መፍትሔ አለው

ረቡዕ፣ መጋቢት 27 2009

መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገ እና ቴክኖሎጂን ከኢንጂነሪንግ ጋር ያቀናጀ ድርጅት በኢትዮጵያ ያለውን የውሃ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት መፍትሄ ነው ያለውን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ መፍትሄው ከቧንቧ መስመር ዝርጋታ እስከ የውሃ ስርጭት ስርዓት ድረስ ያለውን ስራ በቴክኖሎጂ ታግዞ በአነስተኛ ወጪ መስራትን አላማ ያደረገ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/2al0Y
Ethiopian startup at Silicon Valley Challenge
ምስል 3BL Enterprise

የ‘ሲሊከን ቫሊን’ ቀልብ የሳበው ኢትዮጵያዊ ድርጅት

ጉግል፣ ፌስቡክ እና አፕል ለመቀመጫነት የመረጡት የአሜሪካው ሳንፍራንሲስኮ ሰርጥ በርካታ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ድርጅቶች ዋና መስሪያ ቤት የሚገኝበት ቦታ ነው፡፡ “ሲሊከን ቫሊ” በሚል ቅጽል ስያሜው ይበልጡኑ በሚታወቀው በዚህ ቦታ ከውሃ ጋር የተያያዙ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎችን የሚደግፍ ድርጅት አለ፡፡ “ኢማጅን ኤችቱኦ” ይሰኛል፡፡ ድርጅቱ በየዓመቱ አዲስ ነገር ፈጣሪዎችን እየጋበዘ ያወዳድራል፡፡ ውድድሩ ታዲያ በየትኛውም ክፍለ አህጉር ውስጥ ላሉ አላሚዎች ክፍት ነው፡፡

ከ30 ሀገራት የተውጣጡ 180 ገደማ አመልካቾች በዚህ ዓመት ውድድር ተሳትፈው ነበር፡፡ በውሃ ዘርፍ አንቱታ ያተረፉ ዳኞች ከመካከላቸው አስራ ሁለቱን ለመጨረሻ ዙር መረጡ፡፡ ሰባት ተወዳዳሪዎችን በማሳለፍ አሜሪካ ቀዳሚነቱን ስትይዝ ካናዳ በሁለት ተከትላለች፡፡ ብሪታንያ እና ስፔን አንዳንድ አዋጥተዋል፡፡ ከመጨረሻ ዙር ተሳላፊዎች ውስጥ የአንድ አፍሪካዊት ሀገር መገኘት አስገራሚ ነበር፡፡ ያቺ ሀገር ኢትዮጵያ ነበረች፡፡

Äthiopien
ምስል 3BL Enterprises

ኢትዮጵያን የወከለው “ስሪቢኤል ኢንተርፕራይዝስ” የተሰኘው ጀማሪ ድርጅት በዚህ ውድድር ለመጨረሻ ዙር ማለፉ ብቻ አይደለም ቀልብ ሳቢው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት በሳንፍራንሲስኮ በተካሄደ ዝግጅት ከሶስት ተሸላሚ ድርጅቶች አንዱ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያዊውን ድርጅት ለሽልማት ያበቃው እንዴት በአነስተኛ ወጪ የውሃ መስመር ዝርጋታ ማካሄድ እንደሚቻል የነደፈው ዲዛይን እና የሰራው አፕልኬሽን ነው፡፡

የምስራች ታደሰ አፕልኬሽኑ የተጠነሰሰበትን ቦታ በማቅረብ እና ለ“ስሪቢኤል ኢንተርፕራይዝስ” የቢዝነስ ምክር በመለገስ ሀሳቡ እውን እንዲሆን የረዳው “አይስአዲስ” የተሰኘን ድርጅት በስራአስኪያጅነት ከሚመሩት አንዷናት፡፡ ስለአፕልኬሽኑ እና አገልግሎቱ እንዲህ ታስረዳለች፡፡

“ሰዎች በጣም ብዙ ችግር አለባቸው፡፡ ውሃ ለማግኘት ብዙ ሰዓታት በእግር በመሄድ ነው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት፡፡ ስለዚህ ይህን የመሰረተው ክሪስ ሰው ለውሃ የሚያደርገውን ጉዞ እንዲቀንስ እና ቤቱ ድረስ ውሃ እንዲመጣለት ነው፡፡ ቤቱ ድረስ ከመጣለት በኋላ ደግሞ ያንን የመጣለትን መስመር እንዴት ነው ሲበላሽ መጠገን፣ ማስተካከል የሚችለው የሚለው ላይ ነው ስራው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ አፕልኬሽኑ ጥገናው ላይ ኢንስተራክሽኖቹን ይሰራል በዚያ ላይ ባንቧዎቹን በየቤቱ መግጠም ማለት ነው፡፡” ትላለች የአፕልኬሽኑን ዋና ዓላማ ስታብራራ፡፡

የአፕልኬሽኑ ፈጣሪ አሜሪካዊው ክሪስ ተርንቡል ግራይምስ ከ“ስሪቢኤል ኢንተርፕራይዝስ” ሶስት መስራቾች አንዱ ነው፡፡ በገጠር ያለውን የውሃ አቅርቦትን ማሻሻል ዓላማቸው ያደረጉ ሁለት አይነት አፕልኬሽኖችን ፍሎየስ በሚል መለያ ስር መስራቱን ይናገራል፡፡ የሁለቱን ልዩነት ይተነትናል፡፡

“ፍሎየስ ኮሌክት የሚባለው የመጀመሪያው አፕልኬሽ ስለህብረተሰቡ ዝርዝር ዕቅድ እንድናወጣ የሚረዳን ነው፡፡ በህብረተሰቡ ውስጥ ስትዘዋወር መረጃ ታገኛለህ፡፡ መረጃውን ሰብስበህ ስትከት የተቀናበረ መረጃ ይሰጣሃል፡፡ ከዚያ ኢንጂነሮቻችን የውሃ ፍሰት ስርዓቱን ይነድፋሉ ማለት ነው፡፡

ፍሎየስ ማኔጅ በሚባለው ሌላኛው አፕልኬሽን የሚረዳን ደግሞ ለተግባራዊ ስራዎች እና ለጥገና ነው፡፡ መከናወን የሚገባቸው የጥገና ስራዎች የትኞቹ እንደሆኑ ጥቆማ ያቀርብልሃል፡፡ የውሃውን ጥራት ደረጃ ማረጋገጥ ከፈለግህ አሊያም የሆነ ቦታ ላይ ያለን መቆጣጠሪያ መክፈት ከፈለግህ ወይም ሌላ ነገር መከወን ካሻህ ማስታወሻ ይልክልሃል፡፡ እነዚህን ስራዎቹን ማከናወን እንዴት እንደምትችል የሚያሳዩ የማስተማሪያ ቪዲዮዎች ይሰጥሃል፡፡ በዚህ ሰዎችን ማሰልጠን ይቻላል፡፡ ሌላው ደግሞ በየቤቱ እና እርሻው ውሃ ማግኘት የሚፈልግ ደንበኛ በየወሩ ለአገልግሎቱ መክፈል ይገባዋልና እነዚህን ደንበኞች እንድታስተናግድ ይረዳሃል፡፡ እንደዚሁም ስርዓቱ በአጠቃላይ እንዴት እንደሚተገበር፣ የውሃ ጥራቱን የተመለከቱ መረጃዎችን ይሰበስባል፡፡ ይህ ዲዛይናችንን እያሻሻልን እንድንቀጥል ያደርጋናል” ሲል ሁለቱ አፕልኬሽኖች ምን ምን ግልጋሎት እንደሚሰጡ ይዘረዝራል፡፡

Äthiopien Dürre Wassertransport
ምስል picture-alliance-akg-images/Y. Travert

“ስሪቢኤል ኢንተርፕራይዝስ” አፕልኬሽኖቹን ሰርቶ ብቻ ቁጭ አላለም፡፡ በተግባር ምን እንደሚመስሉ ለመፈተሽ በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ አቅራቢያ ያለች አንዲት መንደር መርጧል፡፡ ከቡታጅራ ከተማ ወጣ ብላ ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ይህች መንደር ዊታ ትሰኛለች፡፡ ክሪስ ስለዚህች መንደር የሰማው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአርክቴክቸር፣ ህንጻ ግንባታ እና ከተማ ልማት ተቋም ሰዎች ነው፡፡ ተቋሙ በሀገሬው የቤት አሰራር ዘዬ የተቃኘ የቤት ዲዛይን ሰርቶ በአካባቢው እንዲለመድ ለማድረግ እየሞከረ ይገኛል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሰዎች ጋር ሆኖ የዊታ መንደር ነዋሪዎችን የማነጋገር ዕድል የገጠመው ክሪስ ነዋሪዎቹ አጥብቀው ከሚሿቸው ነገሮች አንዱ ውሃ በቤታቸው ማግኘት መሆኑን ይረዳል፡፡ ከዓመት ተኩል በፊት እንዲህ የተጀመረው የክሪስ እና የዊታ ቁርኝት አድጎ ከሳምንት በኋላ በመንደሪቱ ለሚጀመረው የውሃ መስመር ዝርጋታ እና ግንባታ ደርሷል፡፡ የእነ ክሪስ “ስሪቢኤል ኢንተርፕራይዝስ” በአሜሪካው ውድድር ያገኘውን የአምስት ሺህ ዶላር ሽልማት ለግንባታው ለመጠቀም ወስኗል፡፡

በዊታ መንደር የሚዘረጋው የውሃ መስመር 700 ቤቶችን ለመድረስ እቅድ አለው፡፡ እንደ ክሪስ አባባል ከሆነ ዕቅድ ተግባራዊ ሲሆን ከአራት ሺህ እስከ አምስት ሺህ ሰዎች ውሃ ያገኛሉ፡፡ የእነርሱ የውሃ መስመር ዲዛይን እና ግንባታ አሁን እየተሰራበት ከሚገኘው የበለጠ የረከሰ መሆኑ ህብረተሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ክሪስ ያምናል፡፡

“ቀድሞ በሌሎች ሀገሮች የነድፍኳቸው ዓይነተኛ የአሠራር ስልቶች ለእያንዳንዱ ቤት 100 ዶላር ገደማ የሚያስወጡ ናቸው፡፡ እኛ በቤት ከ50 እስከ 60 ዶላር የሚፈጁ አሠራሮችን መንደፍ እንችላለን፡፡ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከከተማ የውሃ መስመር ጋር የተቀናጁ አነስተኛ የውሃ አቅራቢዎች አሉ፡፡ የእነርሱ ዋጋ ለእያንዳንዱ ቤት ከ75 እስከ 80 ዶላር ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ ዋጋ አሁን ካሉት ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ወይም በሁለት ሶስተኛ ያነሰ ነው” ይላል በአነስተኛ ወጪ ስለሚሰራው የእነርሱ የውሃ መስመር ዲዛይን ሲያስረዳ፡፡

የ“ስሪቢኤል ኢንተርፕራይዝስ” የውሃ ሲስተም ዲዛይን ወጪ ቆጣቢ በሆነ ሁኔታ በአንድ አካባቢ እንዲተገበር ከተፈለገ በትንሹ እስከ 200 ቤቶች በውስጡ መካተት እንዳለባቸው ክሪስ ይገልጻል፡፡ የድርጅቱ የውሃ ሲስተም ዲዛይን ለገጠር ቤቶች እና እርሻዎች እንዲስማማ ተደርገው የሚሰሩ ናቸው፡፡ ማስተግበሪያዎቹ አፕልኬሽኖችም ለተመሳሳይ አላማ እንዲውሉ በድርጅቱ ቢሰሩም በሌሎች አፕልኬሽኖች እንደተለመደው ለማንኛውም ግለሰብ አገልግሎት የሚሰጡ አይደሉም፡፡ ይልቁንስ “ፍራንቻይዝ” በሚባለው የንግድ ስርዓት ከ“ስሪቢኤል ኢንተርፕራይዝስ” ጋር የሚሰሩ የንግድ ድርጅቶች የሚገለገሉበት ነው፡፡ ክሪስ ስለ “ፍራንቻይዝ” አሰራር እና ስለ ድርጅቱ የውሃ ሲስተሞች ማብራሪያ አለው፡፡

Äthiopien Flüchtlingslager Flüchtlinge aus Eritrea
ምስል Reuters/T. Negeri

“የትኛውም ቦታ ላይ የሚገኙ የድርጅቱን ፍቃድ አግኝተው የሚሰሩ የራሳቸውን የንግድ ስራ ይሰራሉ፡፡ እኛ የምናቀርብላቸው ስራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸው ስልጠናዎች፣ ቁሳቁሶች እና ንድፎችን ነው፡፡ ሁለት አይነት ሲስተሞችን እንሰራለን፡፡ አንዱ ለመኖሪያ ቤት ጠቀሜታ የሚውል ሲሆን ሌላኛው ለመስኖ ስራ የሚሆን ነው፡፡

ለቤት ውስጥ አገልግሎት እና ለመስኖ የሚውለው የውሃ ጥራት እንደመለያየቱ ዲዛይኖቹም የተለያዩ መሆን አለባቸው፡፡ ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውለው ውሃ በአብዛኛው የሚቀርበውና የሚተዳደረው በመንግስት አማካኝነት ነው፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የህብረት ስራ ማህበራትም በባለቤትነት ሊይዙት ይችላሉ፡፡ አሁን ልንገነባ ለተዘጋጀነው የመኖሪያ ቤቶች የውሃ ሲስተም ዲዛይን ላደረግንበት እና ለግንባታ ከማስከፈል ውጭ በባለቤትነት አናስተዳደረውም፡፡ ነገር ግን ለግብርና መስኖ የሚውለውን ባለቤት መሆን እንችላለን፡፡ በኢትዮጵያ በዚህ መልኩ እየተሰራባቸው ያሉ ምሳሌዎች አሉ” ይላል ክሪስ፡፡  

የ“ስሪቢኤል ኢንተርፕራይዝስ” ለየት ያለ የውሃ መስመር የመዘርጋት እና የመቀየስ አካሄድ ለዓለም አቀፍ ዕውቅና የበቃው በንግዱ ዓለም እየተለመደ የመጣውን “ኢንኩቤሽን” የተሰኘ ሂደት አልፎ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ይህን አይነት አገልግሎት በመስጠት ረዘም ላሉ ጊዜያት የሰራው “አይስአዲስ” ለ“ስሪቢኤል ኢንተርፕራይዝስ” የመስሪያ ቦታ ከማቅረብ አንስቶ የምክር አገልግሎት እስከማበርከት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የ“አይስአዲሷ” የምስራች እንደዚህ አይነት ድርጅቶች በእንዴት ያለ ሂደት ውስጥ እንደሚያልፉ እንዲህ ታስረዳለች፡፡  

Äthiopien Mann wäscht seine Hände
ምስል Reuters/T. Negeri

“ኢንኩቤሽን ማለት አንድ ሰው የፈጠራ ሀሳብ ሲኖረው ወይም የቢዝነስ ሀሳብ ሲኖረው ያንን ከሀሳብ ወደ ተግባር እንዴት እንደሚለውጥ የሚረዳ የሚያግዝ ተግባር ነው፡፡ እኛ በጣም የምናተኩረው ቴክኖሎጂ ላይ ያለን ሀሳብ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ ላይ ሆኖ ግን በተለያየ አይነት ሴክተሮች ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡ በግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ በውሃ ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሀሳቦች ወደ ቢዝነስ መቀየር ለሚፈልጉ ሰዎች ነው የምንሰራው፡፡

አንድ ሀሳብ ከዳበረ በኋላ የበለጠ እንዲስፋፋ አክስለሬተር ውስጥ ይገባል፡፡ ስለዚህ ይሄ ድርጅት ከአይስ አዲስ ‘ኢንኩቤሽን’ በኋላ ‘አክስለሬተር’ የሚባለው ደረጃ ላይ ደረሰና ሲሊከን ቫሊ ባለው ‘ኢማጅን’ በሚባል ድርጅት ተመረጠ” ትላለች በቴክኖሎጂ ጀማሪ ድርጅቶች ዘንድ ስለተለመደው አካሄድ ስታብራራ፡፡  

የ“ስሪቢኤል ኢንተርፕራይዝስ” ዓለም አቀፍ ውድድር ማሸነፍ የፈጠራ ሀሳቦቻቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ለሚውተረተሩ የቴክኖሎጂ ሰዎች አንድ ማነቃቂያ ነው፡፡ የድርጅቱ መስራቾች ቀጣይ ህልም በሰርቶ ማሳያ እየሞከሩት ያሉትን የውሃ መስመር ዝርጋታ እና ቅየሳ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ማስፋፋት ነው፡፡ ውሃ ላይ ተቀምጣ ውሃ የተጠማችው ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይታደጓት ይሆን?  

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ