1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሳህል አካባቢ የገጠመው የምግብ እጥረት ችግር

ቅዳሜ፣ የካቲት 29 2006

በሳህል አካባቢ የተከሰተው ድርቅ፣ የሰብል መበላሸት፣ የዋጋ መወደድ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የረሀብ አደጋ አሰጋቸው። በተመድ የምግብ ይዞታ ተመልካች መስሪያ ቤት ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፣ በሞሪታንያ ብቻ ከየአምስቱ ነዋሪዎች መካከል አንዱ በምግብ እጥረት ተጎድቶዋል።

https://p.dw.com/p/1BM09
Zai in Mali
ምስል Chris Reij

በመዲናይቱ ኑዋክሾት አቅራቢያ በሚገኘው ትንሹ የዓሣ ገበያ ካለፉት 13 ዓመታት ወዲህ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ያጠመዱትን ዓሣ በመሸጡ ተግባር የተሠማሩት ነጋዴ ኦማር ባ ባለፉት ዓመታትይኸው ስራቸው ይበልጡን አዳጋች እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

« የምናጠምደው ዓሣ መጠን በያመቱ እየቀነሰ ነው። ይህንን በግልጽ ተመልክተናል። ድሮ በየቀኑ 100 ወይም 200 ቶን ዓሣ እናጠምድ ነበር። ዛሬ ግን ግማሹን ነው የምናጠምደው። »

ለዚህም የሚቀርበው ምክንያት በሞሪታንያ ባህር ጠረፍ ያለው የዓሣ መጠን እየተሟጠጠ ሄዶዋል የተሰኘው ነው። በዚሁ የባህር አካባቢ የሞሪታንያ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ከቻይና እና ከአውሮጳ ጭምር የሄዱ ግዙፎቹ መርከቦችም ናቸው ዓሣ የሚያጠምዱት። ይህም የሀገሪቱ ተፈጥሮ ሀብት እየተሟጠጠ ለሄደበት እና የምግብ ዋጋ ለተወደደበት ድርጊት አንዱ ምክንያት ሆኖዋል። ከዚህ ሌላምበሀገሪቱ የተከሰተው ድርቅ እና የሰብል መበላሸት በምግቡ አቅርቦት ላይ እጥረት አስከትሎዋል። በዚህ በተያዘው 2014 ዓም በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ሌሎች ስምንት ሀገራት፣ ማለትም፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ካሜሩን፣ ጋምቢያ፣ ማሊ፣ ኒዠር፣ ናይጀሪያ፣ ሴኔጋል እና ቻድ የረሀብ አደጋ እንደሚያሰጋቸው የተመድ የምግብ ይዞታ ተመልካች መስሪያ ቤት ባልደረባ ሮድሪግ ቪኔ አስታውቀል። ሥጋት የተደቀነባቸውን ሰዎች ብዛት ስንመለከት ሁኔታው ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑ ይታያል።

Fischer in Mauretanien
ምስል DW

« ከ20 ሚልዮን የሚበልጥ ሰው በምግብ እጥረት እየተሰቃየ ነው። ይህ በጣም ብዙ ነው። ከዚህ ጎን ልዩ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከአንድ ሚልዮን ስድስት መቶ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ባካባቢው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ወይም ተሰደዋል። ከዚህ ሌላም በአሁኑ ጊዜ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ሊቀርብላቸው የሚገባ ሁለት ሚልዮን ተኩል ሰዎች ይገኛሉ። »«

Hunger im Sahel Bildergalerie Senegal
ምስል picture-alliance/dpa

በሳህል አካባቢ ያሉት ሀገራት ከብዙ ዓመታት ወዲህ የምግብ እጥረት ቀውስ ይታይባቸዋል። ይህ በተለይ በግብርና እና በአርብቶ አደርነት ላይ ጥገኛ የሆኑትን ድሆቹን አብዝቶ ጎድቶዋል። ሮድሪግ ቪኔ እንዳስረዱት፣ እነዚህ ሰዎች ለክፉ ቀን የሚሆን የእህል ምርት የማከማቸት አቅም የላቸውም።

« የሕዝቡ መሠረታዊ ህልውና ተደጋግሞ በሚከሰተው ድርቅ፣ ጎርፍ ወይም የአንበጣ ወረራን በመሳሰለ የተፈጥሮ አደጋ ይነካል። የእህል እና የምግብ ዋጋ የሚወደድበት ዓይነቱ ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ፣ እንዲሁም፣ እንደምናየው፣ ባንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ አሳሳቢ ውዝግቦችም በመሠረታዊው የምግብ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ። »

የተመድ የምግብ ይዞታ ተመልካች መስሪያ ቤት እንደሚገምተው፣ በዚህ በተያዘው 2014 ዓም ብቻ በሳህል አካባቢ ሀገራት የምግብ እጥረት ችግር ያጋጠመውን ሕዝብ ለመርዳት ወደ አንድ ቢልዮን ተኩል ዩሮ ያሰፈልጋል። ምክንያቱም የምግቡ እጥረት በበረኃማዎቹ የገጠር አካባቢዎች ያሉትን ብቻ ሳይሆን፣ በከተሞች እና በባህሩ ጠረፍ አካባቢ ያሉትንም ይጎዳልና። በዓሣው ንግድ የተሠማራው ነጋዴ ኦማር ባ እንዳለው፣ የዓሣው መጠን እጅግ ቀንሶዋል።

« ዓሣ ለማጥመድ አንዳንዴ እስከ 20 ኪሎ ሜትር ርቀን መሄድ እንገደዳለን፤ አንዳንዴም የምንፈልገውን የዓሣ ዓይነት ለማስገር 30 እና 40 ኪሎሜትር እንጓዛለን። አንዳንዴ አንድ ሳምንት ሙሉ ጠብቀንም ምንም ሳንይዝ እንመለሳለን። »

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ