1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ናድያ እና ላምያ 

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 5 2009

የዘንድሮው የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ የሰብዓዊ መብቶች ሽልማት ለሁለት የዚድ የተባለው ሃይማኖት ተከታዮች ትናንት ተበርክቷል። ሳካሮቭ የተሰኘው ይኽው ሀሳብን በነጻ የመግለጽ ሽልማት የተሰጣቸው ሁለቱ ወጣቶች ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ቡድን ለወራት አፍኖ የወሲብ ባርያ አድርጓቸው ነበር ፣

https://p.dw.com/p/2UH8F
EU-Parlament Sacharow-Preis Nadia Murad und Lamija Adschi Baschar
ምስል Reuters/V. Kessler

Sacharow-Preis geht an zwei Jesidinnen - MP3-Stereo

ትናንት የሳካሮቭ ሽልማት በሽትራስቡርጉ የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ የተበረከተላቸው ኢራቃውያኑ  ወጣት ሴቶች
 የ23 ዓመትዋ ናድያ ሙራድ እና የ18 ዓመትዋ ወጣት ላምያ በሽር ናቸው። የመስዋዕትነት ታሪካቸው የሚጀምረው ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 3፣ 2014 ዓም ነው። በዚህ ዕለት ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን የየዚድ እምነት ተከታዮች የሚገኙበትን የሁለቱ ሴቶች መኖሪያ የሆነውን የትውልድ ስፍራቸውን ያዘ። የጽንፈኛው ቡድን አባላት በዚያ ነዋሪ የነበሩት ወንዶች እና በዕድሜ የገፉ ሴቶችን በሙሉ ገደሉ። ከተገደሉት መካከል የናድያ 6 ወንድሞች እና ወላጅ እናቷ ይገኙበታል። ታናሽ እህትዋ እና እርስዋ በቡድኑ አባላት ለባርነቱ አያያዝ ተፈነገሉ። ናድያ እንደተናገረችው ያኔ በሺህዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች የዚዶች ጋር በአፋኞቻቸው በአውቶብስ ከተወሰዱ በኋላ ለጽንፈኛው እስላማዊ ቡድን እንደ ስጦታ ተበረከቱ። ናድያንም አንዱ ቤቱ ወስዶ የወሲብ ባሪያ አደረጋት። ልታመልጥ በሞከረችበት ወቅትም ለጠበቃዎቹ አሳልፎ ሰጥቷት ራስዋን እስከምትስት እንደደፈሯት በጎርጎሮሳዊው 2015 በተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በተገኝችበት ወቅት ተናግራለች። ከጥቂት ወራት በኋላ ነበር ናድያ በሰዎች እርዳታ ከአፋኞቿ አምልጣ ጀርመን ለመግባት የበቃችው። ናድያና እንደ ናድያ ሁሉ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሚጠራው ቡድን ተመሳሳይ በደል የተፈፀመባት ላምያ ትንናት ሽትራስቡርግ ፈረንሳይ የሳካሮቭ ሽልማት ሲበረከትላቸው ሽልማቱ ምን ትርጉም እንዳለው ናድያ ተጠይቃ ነበር። 
« ይህ ሽልማት ለኛ በጣም አስፈላጊ ነው ፤ ለሁላችንም ፤ ለኔ እና ለናድያ ብቻ አይደለም ይልቁንም ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሚጠራው ቡድን ጥቃት ለተፈጸመባቸው እና ሰለባ ለሆኑት ሴቶች በሙሉ እንጂ። ዓለም ያየናል ድምጻችንን ታሪካችንን ይሰማል። እኛን ከጥቃት ለመከላከል እርምጃ ይወስዳል። »
ናድያ አሁን እንደ ርስዋ በአፋኞች በደል ስለተፈፀመባቸው ሰዎች የምትከራከር እና የምታስረዳ  የተመድ ልዩ አምባሳደር ናት። ከዚህ ሌላ ከሶሪያ እና ከኢራቅ የተሰደዱ ሴቶች እና ሕጻናትን የመርዳት ሙከራ ታደርጋለች። እንደ ናድያ ሁሉ የጽንፈኛው እስላማዊ ቡድን ሰለባ የነበረችው ላምያ እንደ ናድያ ብዙም አትታወቅም። ሆኖም እርሷም በጽንፈኛዎቹ ቡድኖች ለግዳጅ ጋብቻ ተዳርጋ ነበር። ሞሱል ውስጥም ተደፍራለች። በተለያዩ ጊዜያት ከአፋኞቿ የማምለጥ ሙከራ ብታደርግም በተደጋጋሚ ተይዛለች። ይሁንና በሚያዚያ 2016 ተሳክቶላት ብታመልጥም የIS ተዋጊዎች ተከታትለዋት ባደረሱት የቦምብ አደጋ አብረዋት የነበሩ ሁለት ሰዎች ሲገደሉ ላምያ ከባድ ጉዳት ደርሶባታል። በአደጋው የዓይን ብርሃንዋን ሙሉ በሙሉ እስከ ማጣት ደርሳ ነበር። ይህ ሁሉ በደል የተፈጸመባት ላምያ በመጨረሻ ጀርመን መግባት ችላለች ። ጀርመን ከገባች በኋላ የህክምና እርዳታ ያገኘችው ላምያ አሁን ጽንፈኞቹ የሚያደርሱትን በደል የማስተዋወቅ ዘመቻ ታካሂዳለች።  የሳካሮቭ ተሸላሚዋ ላምያ  የአውሮጳ ኅብረትአይ ኤስ ን እንዲዋጋ ጠይቃለች ። 
«የሳካሮቭ ሽልማት ለኛ ለጥቃት ሰለባዎቹ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ከአውሮጳ ኅብረት በኩል ለያዝዲን ማህበረሰብ የሚደረግ ትልቅ እገዛ ነው። ሆኖም የሳካሮቭ ሽልማት ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራውን ቡድን አያስቆምም። የአውሮጳ ኅብረት ቡድኑን መዋጋት አለበት። ቡድኑ አዋርዶን ነበር።  ሆኖም የሳካሮቭ ሽልማት ክብር እና ልዕልናችንን አስመልሶልናል። »
በአሁኑ ጊዜ 75 ሺህ የዚዶች ከኢራቅ ተሰደዋል። አሁን እዚያ የሚገኙትም ኑሯቸው አስተማማኝ አይደለም።
 

Bildkombo Nadia Murad Basee Lamija Adschi Baschar
ምስል picture-alliance/AP Photo/Y. Karahalis/B. Szlanko
Nadia Murad und Lamija Adschi Baschar
ምስል picture-alliance/dpa/F. Kraufmann

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ