1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ተመሳሳይ ሰልፎች በ600 ከተሞች ተካሄደዋል

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 18 2009

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች የበርካታ ሀገራት  ከተሞችን ጎዳናዎችን ሞልተው ነበር፡፡ ሰልፈኞቹ ለሳይንስ ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት የወጡ ነበሩ፡፡ ሰልፉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለሳይንስ እና ምርምር ተቋማት ይመደብ የነበረውን ገንዘብ ለመቀነስ ካላቸው ዕቅድ እና ለሳይንስ በአጠቃላይ ካላቸው አቋም ጋር የተያያዘ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/2bqHP
March For Science NYC
ምስል Reuters/A.Kelly

ሰልፍ ለሳይንስ እና የሳይንስ የምርምር ስራዎች

በአርባ አምስተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ከየአቅጣጫው የሚነሱ ተቃውሞዎች ከዕለት ዕለት እየበረከቱ መጥተዋል፡፡ የሚያሳትፉት የህብረተሰብ ክፍል እና የሀገራት ብዛትም የጨመረ ይመስላል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከተሳተፉበት እና በጥር ወር አጋማሽ ከተካሄደው “የሴቶች ሰልፍ” በኋላ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለሳይንስ ሲባል የተካሄደው ሰልፍ ብዙዎችን በአንድ ዓላማ በማሰባሰብ ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ 

Australien March for Science
ምስል Reuters/D. Gray

ሰልፉ ባለፈው ቅዳሜ ሚያዝያ 14 እንዲካሄድ የተወሰነው ከዓለም የመሬት መታሰቢያ ቀን ጋር እንዲገጣጠም ታስቦ ነው፡፡ የአሜሪካ መንግስት መቀመጫ ዋሽንግተን ዲሲ ደግሞ የሰልፉ ዋና ዝግጅት ማከናወኛ ተደርጋ በአዘጋጆቹ ተመርጣለች፡፡ በዋሽንግተን ዲሲው ሰልፍ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዕለቱ የነበረውን ዝናብ እና ብርድ ተቋቁመው አደባባይ ወጥተዋል፡፡ ሳይንስ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ሚና ለማጎላት እና ለማወደስ የተጠራው ሰልፍ እንደ ኒውዮርክ፣ ቺካጎ እና ሎስ አንጀለስ በመሰሉ ሌሎች የአሜሪካ ታላላቅ ከተሞችም ተከናውኗል፡፡ 
የአሜሪካንን ጎዳናዎች አጨናንቀው የዋሉት ሰልፈኞች ምንም እንኳ “ሳይንስ” በሚል አንድ ጥላ ስር ቢሰባሰቡም ምክንያታቸው ለየቅል ነበር፡፡

“እኔ እዚህ ያለሁት ስለተከፋሁ ነው፡፡ ሳይንስ ጥቃት እየተሰነዘረበት ይመስላል፡፡ ሀቅም እየተጠቃ ይመስላል” ይላሉ በዲሲው ሰልፍ የተሳተፉት ክርሰቲን ሳንቦርን፡፡ በዚያው በዋሽንግተን ሰልፍ የነበሩት ክሊኒካል ሳይኮሎጂስቱ ቲም ትሩምፐር ደግሞ ምክንያታቸው ይህ ነው፡፡ “የአየር ንብረት ለውጥ ለእኔ ትልቁ ስጋት ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ያስመዘግብነውን መሻሻል  ልናደናቅፍ አይገባም፡፡” ሌላዋ ሰልፈኛ አን ማሪ ፌትዝጀራልድ በበኩላቸው “ጡረታ የወጣሁ የባይሎጂ መምህር ነኝ፡፡ ሳይንስ ማስተማር ከመጀመሬ በፊት በህክምና ዘርፍም ሰርቼያለሁ፡፡ እዚህ ያለሁት በአሁኑ አስተዳዳር በሳይንስ ላይ የተቃጡት ሁሉም አደጋዎች ክፉኛ ስላሳሰቡኝ ነው፡፡ ስለሁኔታው የሚሰማኝን ማሰማት እንዳለብኝ በማመኔ ነው፡፡ ወጥቼ የሆነ ነገር ማድረግ አለብኝ” ብለዋል፡፡

Australien March for Science
ምስል Getty Images/AFP/P. Parks

ሰልፈኞቹ በተለያዩ ቃላት ይግለጹት እንጂ አደባባይ ያስወጣቸው ጉዳይ በፕሬዝዳንት ትራምፕ የሚመራው መንግስታቸው ለመውሰድ ያሰበው እርምጃ እና የሚከተለው አቋም ይመስላል፡፡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የትራምፕ አስተዳደር ለአካባቢ ጉዳዮች እና ለጤና ምርምሮች የሚመደበውን በጀት በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ማሰቡ ለብዙዎች በሰልፎቹ ላይ እንዲሳተፉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚህ በተቃራኒዉ ለሀገር ውስጥ ደህነነት እና ለመከላከያ መስሪያ ቤቶች ከፍ ያለ ተጨማሪ በጀት ለመስጠት መታሰቡ በርካቶችን አስቆጥቷል፡፡

ባለፈው መጋቢት ወር ይፋ የተደረገው የአሜሪካ መንግስት የበጀት ዕቅድ ለብሔራዊ ጤና ተቋም የሚመደበውን የገንዘብ መጠን በ18 በመቶ የመቀነስ ሀሳብ አለው፡፡ በገንዘብ ሲሰላ 5.8 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚሆነው የገንዘብ ቅነሳ ለበርካታ ምርምሮች የሚደረገው ድጋፍ እንዲቋረጥ ምክንያት ይሆናል በሚል ከተመራማሪዎች ትችት እየቀረበበት ይገኛል፡፡ ቅነሳው “አዳዲስ ወጣት ተመራማሪዎች ሊያገኙ የሚገባውን ድጋፍ ያስቀራል” የሚል ስጋትም ፈጥሯል፡፡

በኡታህ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ብራያን ጆንስ “ገና ካሁኑ የምርምር ቤተ-ሙከራዎች ሲዘጉ እያየን ነው” ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት ለታይም መጽሔት አስረድተዋል፡፡ የአሜሪካ ብሔራዊ ጤና ተቋም በገንዘብ ከሚደግፋቸው ውስጥ የዓይነ ስውርነት፣ የመዘንጋት (አልዛማየር)፣ የካንሰር፣ ስኳር እና የሰውነት መንዘፍዘፍ (ፓርኪንሰን) በሽታዎች ላይ የሚደረጉ ምርምሮች እንዳሉ በመጥቀስ ጉዳዩ ምን ያህል ከእያንዳንዱ ሰው ህይወት ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ 

በሰልፎቹ የትራምፕ አስተዳደር እርምጃ ክፉኛ መብጠልጠሉ በተለምዶ ይነገር የነበረውን “ሳይንስና ፖለቲካ የተለያዩ ናቸው” ይሉትን   ብሂል የጣሰ ሆኗል፡፡ አዘጋጆቹ ሰልፉ “ለማንም ያልወገነ የሳይንስ ማወደሻ” እንደሆነ ቢገልጹም ኩነቱ ፖለቲካ በሳይንስ ውስጥ ስላለው ሚና ክርክር ማስነሳቱን ግን አልካዱም፡፡ “ሰልፉ ተመራማሪዎች በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ አለባቸው ወይስ የለባቸውም የሚል ውይይት ቀስቅሷል” ሲሉ ጽፈዋል አዘጋጆቹ ይፋዊ ድረገጻቸው ላይ፡፡ ለጥቀውም “በሳይንስ የተደረሰባቸውን ስምምነቶች የማጣጣል እና ሳይንሳዊ ግኝቶችን የማቀብ አስደንጋጭ አካሄድ በሚታይበት ወቅት በምትኩ ይህን ጥያቄ እንጠይቃለን፡፡ ለሳይንስ ጥብቅና ለመቆም አለመናገር እንችላለን?”

March for Science in Tokio
ምስል picture alliance/Zumapress

ከአዘጋጆቹ አንዱ የሆኑት እና በሳይንሳዊ የቴሌቪዥን ዝግጅቶቻቸው የሚታወቁት ቢል ኔይ ይህንኑ በዋሽንግተን ዲሲው ሰልፍ አስተጋብተዋል፡፡ “አንዳንድ ሰዎችን ሳይንስን ፖለቲካዊ አደረጋችሁት ሊሉ ይችላሉ፡፡ ግን እኛ ይህን እያደረግን አይደለም፡፡ እየተሟገትንለት ነው” ብለዋል ቢል፡፡ 

ፖለቲካ ብቻውን የሚቆም ይመስል እንደ ሳይንስ፣ ስፖርት እና ሙዚቃ ከመሰሉ ዘርፎች ጋር መነካካት የለበትም የሚል ክርክር በኢትዮጵያ ተዋስኦ ውስጥም የሚስተዋል ነው፡፡ ሳይንስ እና ፖለቲካ ምንና ምን ናቸው? ለሚለው ጥያቄ የዋሽንግተን ዲሲው ሰልፍ ተሳታፊ የነበረው የቶሊ ሪንፐርግ አስተያየት ምላሽ ያለው ይመስላል፡፡ 

“እኔ በግሌ እንደማስበው ሳይንስ ለማንም አይወግንም ግን ፖለቲካዊም ነው፡፡ አንድ መቶ ሰዎች ይህን ከተረዱና እና ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ከገባቸው የዚህ እንቅስቃሴ ስኬት ነው፡፡”
እንቅስቃሴው ከጥቂት መቶ ሰዎች እና ከአንድ ሀገርም መሻገሩ የታየው የዚያው ሰልፉ የተጠራ ቀን ነው፡፡ ዓላማውን የደገፉ ተመሳሳይ ሰልፎች ለንደን እና በርሊንን ጨምሮ በመላው ዓለም ባሉ 600 የሚጠጉ ከተሞች ተካሄደዋል፡፡ ጉዳዩ የአሜሪካ ብቻ አለመሆኑንም አሳይተዋል፡፡ በዚህ በጀርመን በርሊን ለሰልፍ ከወጡ አስር ሺህ ገደማ ሰዎች መካከል የነበሩት ማርያ ፖህለ አደባባይ የወጡበትን ምክንያት ሲያስረዱ ይህንኑ ስሜት አንጸባርቀዋል፡፡

“ለሳይንስ፣ ለሀቅ እና ደግሞ ተለዋጭ ሀቅን በመቃወም ነው የወጣሁት፡፡ ለሳይንስ ስል፤ ሳይንስ በአሜሪካ ብቻ አይደለም አደጋ ላይ የወደቀው በአውሮፓ እና በመላው ዓለም ነው፡፡ ለሐቅ ስል፤ በሳይንስ የተፈተሸው በሚገባ እንደሚረጋገጥ ለማመልከት ነው” ይላሉ ማርያ፡፡

March For Science Washington, D.C.
ምስል picture alliance/ZUMAPRESS/A. Edelman

በሰልፉ ማጠናቀቂያ ላይ የነበረው ትልቁ ጥያቄ የሰልፈኞቹ ውርጅብኝ ያነጣጠረባቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት “ሚሊዮኖችን አድምጠው አቋማቸውን ይለውጡ አሊያም መለሳለስ ያሳዩ ይሆን?” የሚል ነበር፡ ፡ ይህ ጥያቄ የቀረበላት ወጣቷ ኤልዛቤት ከጓደኞቿ ጋር እየተሳሳቀች ይህን ብላለች፡፡ “ፕሬዝዳንታችን ይሰሙን ይሆን ብዬ አስባለሁን? አላስብም፡፡ ለእራሱ ያለው አመለካከት በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ይህ ጫፉም አይደርስ፡፡ ግን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይደርሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ስትል ምኞቷን አጋርታለች፡፡   

ኤልዛቤት ፕሬዝዳንቷ ምን እንደሚያስቡ ለማወቅ ብዙ መጠበቅ አላስፈለጋትም፡፡ እንደተለመደው መልሱን ከትራምፕ የትዊተር መልዕክት አግኝታዋለችና፡፡ ፕሬዝዳቱ ስለ ሰልፉ ምንም ሳይተነፍሱ በዚያው ዕለት ስለተከበረው የመሬት ቀን ተከታዩን ጽፈዋል፡፡ 

“ዛሬ በመሬት ቀን የሚያምሩ ደኖቻችንን፣ ሐይቆቻችንና መሬታችንን እናወድሳለን፡፡ የሀገራችንን የተፈጥሮ ውበት ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እንቆማለን፡፡ አየራችንን እና ውሃችን ንጹህ ሆኖ እንዲቆይ እተጋለሁ ነገር ግን ሁሌም ማስታወስ ያለባቸሁ የኢኮኖሚ ዕድገት የአካባቢ ጥበቃን ይበልጥ እንደሚያጎልብት ነው፡፡ ዋናው ስራ ነው!”    

ትራምፕ ሲቀኙ እንደዚያ ናቸው፡፡ ሊያውም ከ140 ቃላት ባነሰ፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ 

ነጋሽ መሐመድ