1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሴፕ ብላተርና ሚሼል ፕላቲኒ የስምንት ዓመታት እገዳ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 11 2008

የዓለም አቀፉ እግር ኳስ አስተዳዳሪ (ፊፋ) ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተርና የአውሮጳ እግር ኳስ ማህበሩ ሚሼል ፕላቲኒ ለስምንት ዓመታት ከእግር ኳስነክ ጉዳዮች ታግደዋል። በጀርመን ጋርዲዮላ እና ባየር ሙኒክ ግንቦት ላይ ፍቺ ይፈጽማሉ። ባርሴሎና በዓመቱ አምስተኛ ዋንጫውን በጃፓን ከፍ አድርጓል።

https://p.dw.com/p/1HRLF
Schweiz FIFA PK Blatter
ምስል Getty Images/P. Schmidli

[No title]

የሴፕ ብላተርና ሚሼል ፕላቲኒ ቅጣት

የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ በምሕፃሩ ፊፋ የስነ-ምግባር ኮሚቴ ሴፕ ብላተርና ሚሼል ፕላቲኒን ለስምንት አመታት ከማንኛውም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አግዷል።

ከጎርጎሮሳዊው 1998 ዓ.ም. ጀምሮ ፊፋን በዓለቅነት የመሩት የ79 አመቱ ሴፕ ብላተር በመጪው የካቲት በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደማይወዳደሩ ካስታወቁ ከራርመዋል። የአውሮጳ እግር ኳስ ማህበር የበላይ የ60 አመቱ ሚሼል ፕላቲኒ የሴፕ ፕላተርን መንበር ይወርሳሉ የሚል ተስፋ ተጥሎባቸው የነበረ ቢሆንም አልተሳካም። ሁለቱ ሹማምንት ከዚህ ቀደም ከፊፋ ካዝና ወጥቶ ለሚሼል ፕላቲኒ በተከፈለ 1.3ሚሊዮን ፓውንድ አሊያም 2 ሚሊዮን ዶላር ጉዳይ ተከሰው የ90 ቀናት የእግድ ቅጣት ተጥሎባቸው ነበር።

ሴፕ ብላተርና ሚሼል ፕላቲኒ የተቋሙን የስነ-ምግባር መርሆዎች በመቃረን በ'አግባብ ያልሆነ ክፍያ' ጥፋተኛ መባላቸውን የፊፋ የስነ-ምግባር ኮሚቴ አስታውቋል። ሁለቱ ባለስልጣናት ግን በጎርጎሮሳዊው 1998 ዓ.ም በተፈጸመ ስምምነት መሰረት ሚሼል ፕላቲኒ ከ1998-2002 ዓ.ም ለሴፕ ብላተር በአማካሪነት ላገለገሉበት የተከፈለ ነው ሲሉ አስተባብለዋል። ክፍያው ግን በስምምነቱ ላይ የሰፈረ ሳይሆን በቃል የተፈጸመ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ሴፕ ብላተርና ሚሼል ፕላቲኒ የጥቅም ግጭት በመፍጠር እና ከመርማሪዎች ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አለመሆንን ጨምሮ የ50 ገጽ ክስ ቀርቦባቸው ጥፋተኛ ሆነዋል።

የጋርዲዮላና ሙኒክ ፍቺ

ስፔናዊው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ከባየር ሙኒክ የእግር ኳስ ክለብ ጋር ያላቸውን የስራ ውል በአመቱ መጨረሻ ሲያጠናቅቁ ኃላፊነታቸውን እንደሚለቁ ተረጋግጧል። ጣልያናዊው ካርሎ አንቺሎቲ የባየር ሙኒክን የአሰልጣኝነት መንበር በሚቀጥለው አመት ይረከባሉ። «ጋርዲዮላ ለክለቡ ላበረክተው አስተዋፅዖ እናመሰግናለን።» ያሉት የባየር ሙኒክ ሊቀ-መንበር ካርል ሄንዝ ሩሚኒጌ አመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ሌሎች ስኬቶች በጋራ እንደሚጎናፀፉ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል። «ስኬታማው አሰልጣኝ አንቺሎቲ ወደ ባየርሙኒክ ሊመጣ ነው። አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን።» ሲሉም አክለዋል ሊቀ-መንበሩ ቢልድ ለተሰኘው የጀርመን ጋዜጣ በሰጡት ቃለመጠይቅ።

የባየር ሙኒክ የመሀል ሜዳ ሞተር ቶማስ ሙለር በበኩሉ የአሰልጣኙ ውሳኔ ምንም አይነት ተፅዕኖ እንደማያሳርፍ ተናግሯል።

«ምንም አይነት ጫና አይፈጥርብንም። ከአሰልጣኙ ጋር ስኬታማ ለመሆን ያለንን ሁሉ እንሰጣለን። አሰልጣኙ የሚለንን እንሰማለን።»

Fußballtrainer Pep Guardiola & Carlo Ancelotti
ምስል picture-alliance/dpa/J. Lizon

የ56 አመቱ ካርሎ አንቺሎቲ ከዚህ ቀደም ጁቬንቱስ፤ቼልሲ እና ሪያል ማድሪድን አሰልጥነዋል። የጨዋታ ፍልስፍናቸው ከባየር ሙኒክ ጋር እንደሚመሳሰልም ይነገርላቸዋል። አንቺሎቲ ሶስት የቻምፒዮንስ ሊግ እና ሁለት የዓለም እግር ኳስ ዋንጫዎችን በተጫዋችነትና አሰልጣኝነት ዘመናቸው አግኝተዋል።

ከሶስት አመታት በኋላ የተሰማው የፔፕ ጋርዲዮላ ስንብት የተጠበቀ ነበር። የ44 አመቱን የቀድሞ የባርሴሎና ተጫዋችና አሰልጣኝን ለመቅጠር የፈረጠመ የገንዘብ አቅም ያላቸው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ፍላጎታቸውን አሳይተዋል። በጎርጎሮሳዊው 2013 ዓ.ም. የባየር ሙኒክ አሰልጣኝ የሆኑት ፔፕ ጋርዲዮላ የጀርመን ቡንደስሊጋን ሁለት ጊዜ፤የጀርመን ዋንጫ እና የአውሮጳ ሱፐር ካፕ፤እና የዓለም ክለቦች ዋንጫን አሳክተዋል።

የጀርመን እግር ኳስ ማህበር ሌላ ቅሌት?

የጀርመን እግር ኳስ ማህበር በጎርጎሮሳዊው 2006 ዓ.ም የተካሄደውን የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት ለማግኘት ለቀድሞው የፊፋ ባለስልጣን ጃክ ዋርነር ጋር አስቀድሞ ስምምነት ፈጽሞ እንደነበር ዴር ሽፒግል የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። እንደ ጋዜጣው ዘገባ ከሆነ የጀርመን እግር ኳስ ማህበር የጃክ ዋርነርን ድምጽ ለማግኘት የተለያዩ ጥቅማጥሞችና 1,000 ውድ ትኬቶችን ለመስጠት አስቀድሞ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ለጃክ ዋርነር የተገባው ቃል አጠቃላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ዩሮ ይገመታል ብሏል የዴር ሽፒግል ዘገባ። ዋርነር በጊዜው የሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካና ካሪቢያን እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ነበሩ። ጃክ ዋርነር ከሌሎች 14 የፊፋ ባለስልጣናት ጋር በቀረበባቸው የማጭበርበር፤ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና እጅ መንሻ የመቀበል ክስ ጥፋተኛ ተብለው ከእግር ኳስ እድሜ ልካቸውን ታግደዋል።

ቡንደስሊጋ

በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄዱ የጀርመን ቡንደስሊጋ ጨዋታዎች ቅዳሜ ዕለት ሻልከ ሆፈንሄምን፤ኦግስበርግ ሐምቡርገርን፤ባየር ሙኒክ ሃኖቨርን እንዲሁም ባየር ሊቨርኩሰን ኢንግሎሽታትን በተመሳሳይ ውጤት አንድ ለምንም አሸንፈዋል።ኮሎኝ ደግሞ ዶርትሙንድን ሁለት ለአንድ አሸንፏል። ቬርደር ብሬመንን በሜዳው ያስተናገደው ኢንትራክት ፍራንክፈርት በበኩሉ የሁለት ለአንድ ባለድል ሆኗል። ቮልፍስበርግ በሽቱትጋርት ሶስት ለአንድ ተሸንፏል። እሁድ ሔርታ በርሊን ሜይንዝን ሁለት ለምንም ቦሩሲያ ሞንቼግላድባህ ዳርም ሽታትን ሶስት ለ ሁለት አሸንፈዋል።

Deutschland Fußball Bundesliga Borussia Mönchengladbach vs. SV Darmstadt 98
ምስል Getty images/Bongarts/L. Baron

የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላን ሊሸኝ ጉድ ጉድ የሚለው ባየር ሙኒክ በ46 ነጥብ ተቀምጧል። ቅዳሜ ዕለት አስደንጋጭ ሽንፈት የገጠመው ቡሩሺያ ዶርቱሙንድ በ38 ሁለተኛ፤ሔርታ በርሊን በ32 ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ሴሪ አ

በጣሊያን ሴሪ አ ትናንት መሪው ኢንተር ሚላን በላዚዮ 2 ለ 1 ተሸንፏል። ፍሮሲኖኔን የገጠመው ኤሲ ሚላን በበኩሉ 4 ለ2 አሸናፊ ሆኗል። ሮማ ጄኖን፤ፊዮሬንቲና ቼዬቮን በተመሳሳይ 2 ለምንም አሸንፈዋል። ናፖሊ ደግሞ አታላንታን ሶስት ለአንድ አሸንፏል። ጁቬንቱስ ካርፒን ሶስት ለሁለት በማሸነፍ በአመቱ ስምንተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ኢንተር ሚላን በ36 ነጥቦች ቀዳሚነቱን ይዟል። በአንድ ነጥብ ከኢንተር ዝቅ ያሉት ፊዮሬንቲና እና ናፖሊ በተመሳሳይ 35 ነጥቦች ግን በግብ ተለያይተው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ጁቬንቱስ በ33 አራተኛ ሮማ በ32 አምስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው።

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ ጎንበስ ቀና የበዛበት የራፋ ቤኒቴዙ ሪያል ማድሪድ ትናንት ምሽት 10 ግቦችን አስቆጥሮ ምሽቱን በድል ተወጥቷል። ሁለት ቀይ ካርድ የተመዘዘበት እና 12 ግቦች ከመረብ ያረፉበት ጨዋታ ግን እውነተኛውን የሪያል ማድሪድ የሜዳ ላይና የመልበሻ ክፍል ገጽታ የሚያሳይ አይመስልም። በጨዋታው ጅማሮ ቀሰስተኛ እንቅስቃሴ ያሳየው ሪል ማድሪድ ለአሸናፊነት የዳኞች እገዛ አስፈልጎታል። የሪያል ቫልካኖ አስራ አንዱም ተጨዋቾች ሜዳ ላይ በነበሩባቸው ደቂቃዎች ቀድመው ግብ ማስቆጠር ሁለት ለአንድ መምራትም ችለው ነበር። ከሳምንት በፊት በቪያ ሪያል አንድ ለምንም የተሸነፈው የዋና ከተማዋ ሪያል ማድሪድ ያንሰራራው ከመጀመሪያው ቀይ ካርድ በኋላ ነበር። በጨዋታው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሁለት፤ካሪም ቤንዜማ ሶስት ዳንኤሎ አንድ የጨዋታው ኮከብ ጋሬዝ ቤል ደግሞ አራት ግቦችን በሪያል ቫልካኖ መረብ ላይ አሳርፈዋል። በጨዋታው ጅማሮ እንደተለመደው የሪያል ማድሪዱ አሰልጣኝ በደጋፊዎቻቸው ተጮሆባቸዋል። ደጋፊዎቹ የክለቡ ፕሬዝዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ እንዲለቁ የሚጠይቅ መልዕክትም አስተላልፈዋል።

FIFA Club World Cup Finale - FC Barcelona vs. River Plate
ምስል picture-alliance/dpa/K. Ota

በሌሎች ጨዋታዎች አትሌቲኮ ማድሪድ በማላጋ አንድ ለምንም ተሸንፏል። ቪያ ሪያል ሪያል ሶሲዳድን፤ሴልታ ቪጎ ግራናዳን እንዲሁም አትሌቲኮ ቢልባኦ ሌቫንቴን ሁለት ለምንም አሸንፈዋል።

የፕሪሜራ ዲቪዥኑን የደረጃ ሰንጠረዥ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ባርሴሎና በ35 ነጥቦች ይመራል። በተመሳሳይ 35 ነጥቦች ነገር ግን በግብ ክፍያ የተበለጠው አትሌቲኮ ማድሪድ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሪያል ማድሪድ በ33 እንዲሁም ሴልታ ቪጎ በ31 ነጥቦች ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

የዓለም ክለቦች ዋንጫ

ባርሴሎና በዮካሃማ የኒሳን ስታዲየም የአርጀንቲናውን ሪቨር ፕሌት 3-0በማሸነፍ የዓለም ክለቦች ሻምፒና ዋንጫን አንስቷል። ይህ ዋንጫ ከላ ሊጋ፣ኮፓ ዴል ሬይ፤ቻምፒዮንስ ሊግና የአውሮጳ አሸናፊዎች ዋንጫ ጋር ተደምሮ በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም አምስተኛ ሆኗል። የልዊስ ኢንሪኬው ባርሴሎና በልጦ በታየበት የጃፓኑ የዓለም ክለቦች ዋንጫ ልዊስ ሱዓሬዝ ሁለት እንዲሁም ሊዮኔል ሜሲ አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

ፕሪምየር ሊግ

ዕለተ-ቅዳሜ በተካሄዱ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ኒው ካስል እና አስቶን ቪላ አንድ አቻ ተለያይተዋል። ቦርንማውዝ ዌስት ብሮምን፤ክሪስታል ፓላስ ስቶክ ሲቲን ሁለት ለአንድ አሸንፈዋል። ቶተንሐም ሳውዝሃምፕተንን 2 ለምንም አሸንፋል። የልዊስ ቫንጋል ማንችስተር ዩናይትድ በኖርዊች 2ለ1 ተሸንፏል። ከሳምንት በፊት የማንችስተር ዩናይትድ ቦርድ ሙሉ ድጋፍ አላቸው የተባለላቸው አሰልጣኝ ልዊስ ቫንጋል የመባረር አደጋ ከፊታቸው ተደቅኗል። ማንችስተር ዩናይትድ ከስቶክ ሲቲ የሚያደርጉትን የገና ሳምንት ጨዋታ ከተሸነፈ አሰልጣኙ እንደሚባረሩ የእንግሊዝ ጋዜጦች እየጻፉ ነው። ሌስተር ሲቲ ኤቨርተንን 3ለ2 በማሸነፍ ግስጋሴውን ቀጥሏል። ሊቨርፑል በዋትፎርድ የ3 ለምንም አሰቃቂ ሽንፈት ገጥሞታል። የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ በአዳም ቦግዳን ስህተት ናታን አኬ ያስቆጠራት ግብ መሻር ነበረባት ሲሉ ተናግረዋል። ክሎፕ ተጫዋቾቻቸው ለዋትፎርድ እንቅስቃሴ ተገቢውን ምላሽ ባለመስጠታቸው መሸነፋቸውን አምነዋል።

Großbritannien Manchester United Trainer Louis Van Gaal
ምስል picture-alliance/dpa/N. Roddis

አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆን ያባረረው ቼልሲ ሰንደርላንድን 3 ለአንድ አሸንፏል። የቼልሲ ደጋፊዎች ለቀድሞው አሰልጣኝ ድጋፋቸውን ለክለቡ ባለቤት ሩሲያዊው ቢሊየነር ተቃውሟቸውን ባሳዩበት የዕለተ ቅዳሜ ጨዋታ ኢቫኖቪች፤ፔድሮ እና ኦስካር ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል።

ቼልሲ እስከ አመቱ መጠናቀቂያ ድረስ ሆላንዳዊው ጉስ ሂድኒክን በአሰልጣኝነት ቀጥሯል። ካሁን ቀደም በተመሳሳይ ለአጭር ጊዜ ቼልሲን ያሰለጠኑት ሂድኒክ የኤፍ.ኤ. ዋንጫን ከክለቡ ጋር አንስተው ነበር። ሂድኒክ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ 15ኛደረጃ ላይ የተቀመጠውን ቡድን ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በርካታ ሥራ ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

UEFA Champions League Chelsea vs. Schalke 04
ምስል Reuters/Eddie Keogh

ተሰናባቹ የቼልሲ አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ በበኩላቸው ስራ ፍለጋ ጎርደድ ጎርደድ እያሉ ናቸው ተብሏል። እንደ እንግሊዝ ጋዜጦች የጭምጭምታ ወሬ ከሆነ ሞሪንሆ በማችስተር ዩናይትድ የልዊስ ቫንጋልን ወንበር ማማተር ይዘዋል።

በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ሌስተር ሲቲ በ38 ነጥቦች አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው አርሰናል በ33 ነጥብ ሁለተኛ ማንችስተር ሲቲ በ32 ሶስተኛ ቶተንሐም በ29 አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ማንችስተር ዩናይትድ ወደ አምስተኛ ደረጃ ሲንሸራተት ሊቨርፑል 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ