1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማዕከላዊ ወደ ሙዚየምነት ይቀየራል-ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 25 2010

ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ "በደርግ ጊዜ በርካታ ሰዎች ስቃይ ያዩበት እስር ቤት" ያሉት ማዕከላዊ እንዲዘጋ መወሰኑን ተናግረዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዛሬም በተጠርጣሪዎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምበታል የሚሉት ማዕከላዊን ለመዝጋት መወሰኑን በጎ ርምጃ እያሉ ነው። ግን ከሐቀኛ ለውጥ ጋር እንዲሆን ይሻሉ።

https://p.dw.com/p/2qJ7A
Amnesty International - Welcome to hell fire
ምስል Chijioke Ugwu Clement

ስቅየት ይፈጸምበታል የሚባለው ማዕከላዊ ሊዘጋ ነው

ከወደ ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጽ/ቤት የተሰማው ውሳኔ ለጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ "እምባ የሚያስመጣ" ሆኖበታል። "እንዴ የተሰቃየሁበት ቤት እኮ ነው።" አለ በፍቃዱ ስለምን እምባ እምባ እንዳለው ሲጠየቅ። "እኔ ቂሊንጦ መጀመሪያ ስገባ እኮ ፈርሶ እንደ አዲስ የሰብዓዊ መብትን የሚያከብር ተቋም ሆኖ መገንባት አለበት ብዬ ደብዳቤ ልኪያለሁ።" የሚለው ጦማሪ  ማዕከላዊ ተዘግቶ እንደማየት የሚያስደስተው ነገር እንደሌለ ፈርጠም ብሎ ይናገራል።   

በፍቃዱ የሚጠቅሰው ስቅየት በተለያዩ ምክንያቶች ማዕከላዊ ገብተው በወጡ ተጠርጣሪዎች ዘንድ በስፋት ይደመጣል። ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ሊቃነ-መናብርት ጋር ሆነው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "አሁን አዲስ አበባ ላይ ማዕከላዊ ተብሎ የሚታወቅ ማቆያ እስር ቤት አለ። ይኸ የምርመራ እስር ቤት በደርግ ጊዜ በርካታ ሰዎች ስቃይ ያዩበት እስር ቤት ነው።" ሲሉ ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ  "ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተካሔዱበት እስር ቤት ነው። ይኼ ማዕከላዊ የሚባለው ሲነሳ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያስቃይ ነው የሚነሳው። አዲሱ የምርመራ ቢሯችን እዛ ተቀምጦ ያ መንፈስ እና አተያይ ባለበት አካባቢ መቆየቱ በራሱ የሚፈጥረው ተፅዕኖ አለው። ያንን ግን ታሪካዊ የነበረውን መጥፎ ገፅታ መዝጋት አለብን። ዘግተን ሙዚየም መሆን አለበት።" ሲሉም አክለዋል።

ጠቅላይ ምኒስትሩ የሚመሩት መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በማዕከላዊ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ያልፈጸሙትን ወንጀል በግዳጅ እንዲያምኑ የሚያስገድዱ የስቅየት ተግባራት ይፈምባቸው እንደነበር ይከሳሉ። በኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) አባልነት ተጠርጥሮ ከሚሰራበት የጋምቤላ ክልል ወደ ምርመራ ቢሮው እንደተወሰደ የሚናገረው ቤኛ ገመዳ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው። ቤኛ እንደሚለው በአዲስ አበባ ማዕከላዊ ወንጀል ምርምራ ዋና መሥሪያ ቤት (ማዕከላዊ) ሲደርስ መጀመሪያ የታሰረው ከጭለማ ቤት ነበር።

"ወዲያው ቀጥታ በኢትዮጵያ መንግሥት አጠራር 84 ተብሎ የሚጠራ ወይ ደግሞ ጨለማ ቤት ምንም መብራት የሌለበት ውስጥ ገባሁኝ እና አራት ወር ሙሉ ታሰርኩኝ። እዛ እስር ቤት ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ወደ ቢሯቸው እየጠሩኝ የተለያዩ ሰቆቃ ግፍ ያደረጉብኝ ነበር። ጀርባዬን በኤሌክትሪክ ቶርች እያደረጉ እያቃጠሉ፤ጥፍሬን በከስክስ ጫማ እየረገጡ፤እየነቀሉ በጥፍር መቁረጫ እየጎተቱ ፤ውሐ እያርከፈከፉብኝ፤በኤሌክትሪክ ሽቦ እየገረፉኝ እኔ የማላውቀውን ነገር እመን፤ይሔን አድርገሃል፤የምታውቀውን ተናገር እያሉ እየደበደቡ ምርመራ ከሌሊቱ 7 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት እያደረጉብኝ ወደ ጨለማ ቤት እየመለሱኝ ነበር።"

ጦማሪው በፍቃዱ ኃይሉ በማዕከላዊ "ሁሉም አይነት የማሰቃየት ተግባሮች" ይፈጸማሉ ሲል ይናገራል። "ማዕከላዊ ውስጥ በተለይ የፖለቲካ እስረኛ ሆነህ ከገባህ ወይም ደግሞ በአመለካከት ልዩነትህ ከታሰርክ ምርመራ የሚደረግልህ በኃይል ነው። መብትህን በመተግበርህ ነው የምትገባው ግን ወንጀል እንድታምን ነው የምትደረገው። ስለዚህ ምርመራ አይደለም እዚያ ያለው። በታሪክም እንደተመዘገበው እኛም ገብተን እንደቀመስንው ከኛም የባሰ የቀመሱ አሉ ሁሉም አይነት የማሰቃየት ተግባሮች ማዕከላዊ ውስጥ ይፈጸሙ ነበረ። እየተፈጸሙም ነው በአሁኑ ሰዓት።"

Human Rights Watch Logo Flash-Galerie
ምስል Human Rights Watch

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሒውማን ራይትስ ዎችን የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ያወጧቸው ዳጎስ ያሉ ሰነዶችም ቢሆኑ ከጠቅላይ ምኒስትሩ ይልቅ የቤኛ እና የበፍቃዱን ሐሳብ ይደግፋሉ። ባለፉት 26 አመታት በፖለቲካ እስረኞች ላይ ተመሳሳይ የስቅየት ተግባር ይፈጸምበት ነበር ሲሉም ይከሳሉ። ከአምስት አመታት በፊት ሒውማን ራይትስ ዎች ባወጣው ምርመራዊ ዘገባ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የተቃውሞ ሰልፍ አደራጆች እና በትጥቅ ትግል ተሳትፈዋል የተባሉ ግለሰቦች በማዕከላዊ የምርመራ ቢሮ ታስረው ስቅየትን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚደርስባቸው ገልጾ ነበር። የሒውማን ራይትስ ዎች ዘገባ እንደሚለው መሐል አዲስ አበባ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን ከፍ ብሎ በሚገኘው ማዕከላዊ መርማሪ ፖሊሶች የተጠርጣሪዎችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል አስገዳጅ ስልቶች ይጠቀማሉ። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች አጥኚው አቶ ፍሰሐ ተክሌ እንደሚሉት "እስካሁን ድረስ በማዕከላዊ በተጠርጣሪዎች ላይ የጭካኔ ተግባሮች ለመፈጸማቸው በቂ መረጃ አለን" ሲሉ ያክላሉ።

ግፍ እና ማዕከላዊ

ማዕከላዊን ጠጋ ብለው ያጠኑት ሐንጋሪን፣ ሮማኒያን እና ዩክሬንን በመሳሰሉ አገሮች ከነበሩ የወንጀል ምርመራ ተቋማት ጋር ያመሳስሉታል። እነዚህ አገሮች በአስከፊነታቸው የሚታወቁትን የምርመራ ቢሮዎች ከሶሻሊዝም ውድቀት በኋላ ወደ ሙዚየምነት ለውጠዋቸዋል። በሐንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት የሚገኘው እና ጥቁሩ ቤት (ብላክ ሐውስ) ተብሎ የሚታወቀው ሙዚየም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ለማፈን ጥቅም ላይ ውሏል የሚባለው የአዲስ አበባው ማዕከላዊ በንጉሣዊው ሥርዓተ-መንግሥት ተቋቁሞ ለሦስት ሥርዓተ-መንግሥታት የዘለቀ ነው።

"በኃይለ ስላሴ ዘመን የፖሊስ ማዘዣ እዛ ነበር የነበረው። በትልልቅ ወንጀሎች የሚጠየቁ ሰዎች እዚያ ነበር የሚያዙት። ስለዚህ ማዕከላዊ ይባል ነበር። ምንም እንኳን ያሉት መረጃዎች በጣም ትንሽ ቢሆኑም በዛ ዘመንም ቢሆን ማዕከላዊ በተለይ የፖለቲካ እስረኞች ይታሰሩበት የነበረ ቦታ እንደነበር የሚያሳዩ ነገሮች ነበሩ። እነሱ መታሰራቸው ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሰዎች ላይ የተለያዩ የግፍ አያያዝ የጭካኔ አያያዝ ይካሔድባቸው እንደነበር አሰቃቂ በደሎች ይፈጸምባቸው እንደነበር ያኔ በነበረው ወፌ ላላ በሚሉት ባዶ እግራቸውን ውስጡን የሚመቱት የሚደበድቡት ነገር እንደ ነበረ ተፅፎ ያለ ነገር አለ። ይኼ ድርጊት ግን የበለጠ የተስፋፋው በደርግ ዘመን ነው። ደርግ በተለይ ከቀይ ሽብር ጋር በተያያዘ የሚይዛቸውን የሚያስራቸውን ሰዎች ከኢሕአፓ እና ከሌሎች ያፈነገጡ ቡድኖች ጋ በተያያዘ የሚያስራቸውን ወጣቶች ብዙዎቹን እዚያ ያስራቸው ነበር። ከመገደላቸው በፊትም እንደ ማቆያ ይጠቀምበት ነበር።"

ባለሙያዎች እንደሚሉት በማዕከላዊ ተፈጽመዋል የሚባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና የስቅየት ድርጊቶች በዓለም አቀፍ ልማዳዊ ሕጎች የተከለከሉ፣ ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ጋር የሚቃረኑ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት ማዕከላዊን ጨምሮ በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች ተፈፅመዋል የሚባሉ የመብት ጥሰቶችን አይቀበልም።

የማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ቢሮን መዘጋት በርካታ ኢትዮጵያውያን ሲናፍቁት ቆይተዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች መዘጋቱን ይናፍቁ እንጂ እንዲህ ድንገት ይሆናል ብለው የጠበቁ አይመስልም። ለበፍቃዱ የውሳኔው ገፊ ምክንያት "የሕዝብ ጫና ነው።"  

"ሁሉንም ሰው ቀስ በቀስ እቀጣለሁ እያለ ሁሉንም ሰው ያስቀየመ መንግሥት ነው ያለው። ስለዚህ አሁን ሁሉም ሰው ጋ ሆድ እና ጀርባ ነው። ለመታረቅ የሚደረግ ሙከራ ነው ብዬ ነው የማስበው። ስለዚህ የሁላችንም ጩኸት እምባ ነው እየተሰማ ያለው ብዬ የማስበው።" 

ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመሩት ኢሕአዴግም ይሁን መንግሥታቸው መረጋጋቱን በተከታታይ ተቃውሞች ከተነጠቀ አመታት ተቆጠሩ። በተለይ በኦሮሚያ ክልል በሚካሔዱ ተቃውሞዎች የበርካቶች ሕይወት ቢጠፋም የመብረድ አዝማሚያ አላሳዩም። የሰብዓዊ መብት ጥናት ባለሙያው አቶ ፍሰሐ ተክሌም በተቃውሞ ወቅት የተሰሙ ድምፆች የኢሕአዴግ ሹማምንቱን እንዳስገደዳቸው ያምናሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈመው በማዕከላዊ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ብቻ አይደለም የሚሉት አቶ ፍሰሐ ተክሌ ጅማሮው ግን የመጀመሪያው እርምጃ እንጂ የመጨረሻው አይደለም ሲሉ ተናግረዋል። ባለሙያው እንደሚሉት መንግሥት ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማስቆም፣ አስፈላጊም ሲሆን የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ተነሳሽነት ሊኖረው ይገባል። "በተለይም ደግሞ ለአገራቸው በጎ የሚሉትን አማራጭ ይዘው የመጡ ዜጎች ሲሰቃዩ የኖሩበት ነው። ስለዚህ ከዚህ በፊት እንደሚባለው የይስሙላ ሳይሆን እንዳይደገም በሚል ሐቀኛ ስሜት ነው ማስታወስ ያለባት። ሙዚየም የሚባለው ትክክል ነው። እኔ ይስማማኛል። ግን ለውጥም መምጣት አለበት። ዝም ብሎ ለይስሙላ ብቻ ሙዚየም አቁመህ መደለል እና ማታለል መሆን የለበትም።"

በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም በማዕከላዊ ምትክ "ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ የምርመራ ማዕከል" የተወካዮች ምክር ቤት ባፀደቀው የሰብአዊ መብት ድርጊት መርሃ ግብር መሰረት ተቋቁሞ በሌላ ሕንፃ ሥራ ጀምሯል ማለታቸውን የቢሯቸው ማኅበራዊ ድረ-ገፆች አስነብበዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ