1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የስደተኞቹ ነጋዴዎች ፈተና በደቡብ አፍሪካ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 29 2011

በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የውጭ አገራት ዜጎች እንደገና የጥቃት እና የዘረፋ ሰለባ ሆነዋል። ባለፈው እሁድ እንደ አዲስ ባገረሸው ጥቃት ተሽከርካሪዎች ጋይተዋል፤ የአልባሳት እና መሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጥ መሸጫ መደብሮች ተዘርፈዋል።

https://p.dw.com/p/3P0pA
Südafrika, Johannesburg: Ausschreitungen in Malvern
ምስል Getty Images/AFP/G. Sartorio

የስደተኛ ነጋዴዎች ፈተና በደቡብ አፍሪካ

ጁሐንስበርግ ዙሪያ የሚገኘው ጎልደን የገበያ አዳራሽ ከዕለተ-ሰኞ ጀምሮ በዘለቀ ዝርፊያ ውጥንቅጡ ወጥቷል። በአብዛኛው ልብስ የሚሸጥበት ግዙፍ አዳራሽ ውስጥ የሚገኙ መደብሮች መስተዋቶቻቸው ተሰብረዋል። ዘረፋ በበረታበት በዚያ የንግድ አዳራሽ ዙሪያ ኢትዮጵያውያን ተከራይተው የሚሰሩበት አካባቢ ነበር።

ላለፉት 20 ገደማ አመታት በደቡብ አፍሪካ የኖሩት አቶ ተከስተ ሹምዬ «የአሁኑ ዘረፋ ነው። በቀልም ይመስላል» ሲሉ ይናገራሉ። «ከሳምንት በፊት ፕሪቶሪያ ውስጥ የታክሲ ሹፌሮች አደንዛዥ ዕጽ የሚሸጡ ናይጄሪያውያንን እናባርራለን ብለው ይነሳሉ፤ በወቅቱ ከአንዱ ናይጄሪያዊ በተተኮሰ ሽጉጥ የታክሲ ሹፌር ይሞታል። በዚያ የተነሳ ሰላማዊ ሰልፍ ተጀመረ። ሰላማዊ ሰልፉ ወደ ኹከት ተቀየረ። በፕሪቶሪያ የተወሰኑ ቀኖች ለማረጋጋት ሞከሩ ከዚያ ወደ ጁሐንስበርግ ተላለፈ» የሚሉት አቶ ተከስተ «በተለይ የአበሾች ሱቆች ዛሬ [ነሐሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም.] ተዘርፈዋል። ጥያቄያቸው የሕዝቡ ጥያቄም አይደለም። አብዛኛው የአፍሪካ ስደተኛ ጥላቻ ያለበት ይመስላል። ምክንያቱም ቻይናዎች በዚህ ጉዳይ አልተጠቁም። ነጭ ስደተኞችም በዚህ ተጠቂዎች ሲሆኑ አታይም» ሲሉ መነሾውን ያብራራሉ።

የተሻለ ሥራ ፈልገው አሊያም በአገራቸው ይደርስብናል የሚሉትን ፖለቲካዊ አፈና ሸሽተው በደቡብ አፍሪካ ጁሐንስበርግ የከተሙ ኢትዮጵያውያን በብዛት ከሚሰሩባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው ጂፒ ስትሪት ላለፉት አራት ቀናት ተዘግቷል። በጁሐንስበርግ የሚኖሩት አቶ ፍቅር ሳቀታ «ትናንትና ጂፒ ስትሪት ሔደን ነበር። በአካል ያየሁት ነገር አንድ ሱቅ ተሰብሮ ዘርፈውት ሔደው ተገኝቷል። አንደኛውን ጀምረውት አባረዋቸዋል። እንደ አሌክሳንድሪያ ባሉ ሌሎች አካባቢዎች ግን የግሮሰሪ ዕቃዎች አቅርቦት የሚሰሩ ልጆች ተዘርፈው ተባረዋል። ሥራው ሙሉ በሙሉ ቆሟል» ብለዋል። 

በደቡብ አፍሪካ የውጭ ዜጎች በተለይም የሌሎች አፍሪካውያን ዜጎች ላይ ጥቃት እና ዘረፋ ሲፈጸም ይኸ የመጀመሪያው አይደለም። በጎርጎሮሳዊው 2008 ዓ.ም. በተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ኹከት ወደ 60 ገደማ ሰዎች ተገድለዋል። ከ50 ሺሕ በላይ ሰዎች ከሚኖሩበት እና ከሚሰሩበት አካባቢ ተፈናቅለዋል። ከአራት አመታት በፊት ይኸው ኩነት ሲደገም የሰባት ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።

በደቡብ አፍሪካ ቪትስ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ጥናት ተመራማሪዋ ዶክተር ታንያ ዛክ «ይኸ መጤ ጠል ኹከት የተቀጣጠለው ከአንድ ሳምንት በፊት የውጭ አገር ዜጎች ንብረት የሆኑ ሱቆችን ዒላማ ልናደርግ ይገባል በሚል በተካሔደ የማኅበራዊ ድረ-ገፆች ዘመቻ ነው» ሲሉ ጉዳዩ ቀድሞ የተወጠነ መሆኑን ይገልፃሉ። የፖሊሲ ጥናት ተመራማሪዋ «ከዚያ በፊት በነሐሴ መጀመሪያ በጁሐንስበርግ በሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች ንብረት የሆኑ በተለይ የኢትዮጵያውያን ሱቆች ላይ ፖሊስ ያካሔደው አሰሳ ነበር።  ይኸ አዲስ አይደለም። ባለፈው አስር አመት በዚያ አካባቢ ፖሊስ በርካታ አሰሳዎች አካሒዷል። ፖሊስ እና ሌሎች ኃይሎች በዚያ አሰሳ የሚያካሒዱት ተመሳስለው የተመረቱ ሸቀጦች በሕገ-ወጥ መንገድ ይሸጣሉ በሚል ሰበብ ነው። በእርግጥ ተመሳስለው የተመረቱ ሸቀጦች አሉ። ችግሩ አሰሳው በራሱ የሚካሔደው ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ነው» ሲሉ ጉዳዩ ተደራራቢ እየሆነ መምጣቱን ይገልፃሉ።

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ባለፈው ወር መጀመሪያ በጁሐንስበርግ ከተማ ሕገ-ወጥ ንግድ እና ተመሳስለው የተመረቱ ሸቀጦችን ለመቆጣጠር ያለመ ባለው ዘመቻ ወደ 600 ገደማ ሰዎች ታስረው ነበር። ዶክተር ታንያ የፖሊስ ዘመቻ ከሚጎድለው ሕጋዊነት ባሻገር ከስደተኛ ነጋዴዎች ተመሳስለው የተሰሩ ናቸው ብሎ የቀማቸውን ሸቀጦች መልሶ ይሸጣል ሲሉ ይወቅሳሉ። የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ዶክተር ታንያ በጠቀሱት ጥፋት የተጠረጠሩ አባላቱን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ባለፈው ወር አስታውቋል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች እና ዶክተር ታንያን የመሳሰሉ አጥኚዎች ግን ፖሊስ በሚያካሒደው አሰሳ የነጋዴዎችን ሕጋዊ ንብረቶች ጭምር ከመቀማት አይመለስም ሲሉ ይወቅሳሉ።

ባለፈው ወር ፖሊስ ባካሔደው አሰሳም ይሁን በሳምንቱ የደቡብ አፍሪካውያን የኹከት ዒላማ የሆነው የጁሐንስበርግ የመገበያያ አካባቢ ውስብስብ የስደት ሒደት አልፈው ደቡብ አፍሪካ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ቀዳሚ ማረፊያ ነው። አብዛኞቹ የቀደምቶቹን ፈለግ እየተከተሉ በንግድ ሥራ ይሰማራሉ። አቶ ፍቅር እንደሚሉት «ኢትዮጵያዊ በቀጥታ የሚገባው ወደ ንግድ ነው። ካልሲ ከማዞር ወይም ደግሞ ትንሽዬ ሱቅ ተከራይቶ የግሮሰሪ እቃዎች ሰፈር ውስጥ በመሸጥ ይጀምራል» አልፎ አልፎ ደግሞ አንዱ ከሌላው ጋ ይቀጠራል።  ለዚህ ደግሞ ጁሐንስበርግ እና እምብርቷ ላይ የሚገኘው ሲዲቢ መልካም ዕድል ሆነዋል።

ሲዲቢ «ጁሐንስበርግ መሐል እምብርቱ ላይ ነው ያለው። እንደ መርካቶ የንግድ አካባቢ ነው። የጅምላ እና የችርቻሮ ሸቀጥ የሚከፋፈለው እዚያ ነው። ጂፒ ተብሎ በተለምዶ በሚጠራው ጎዳና ላይ እና ስሞል ስትሬት ላይ የሚሸጠው ልብስ ነው። ከሞላ ጎደል ወደ አራት አምስት ስትሬት በአበሾች የተያዘ ነው። ሌሎች ጥቂት የዚምባብዌ እና የናይጄሪያ ዜጎች አሉ። ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ዕቃ በኮንቴነር ከቻይና ይጭናሉ። ከእንደገና ደግሞ እዚህም ያሉ ቻይናውያን ያቀርቡልናል። ሌላው ደግሞ ከዚህ ከከተማው አስር እና ሃያ ኪሎ ሜትር ወጣ ያሉ አካባቢዎች ላይ የግሮሰሪ እቃዎችን የሚያከፋፍሉ ኢትዮጵያውያን አሉ» ሲሉ አቶ ፍቅር ያስረዳሉ።

አቶ ተከስተ ደቡብ አፍሪካ ሲገቡ የንግድ ሥራን የተቀላቀሉት ከእርሳቸው ቀደመው የማከፋፈል ሥራ ከጀመሩ ኢትዮጵያውያን ሸቀጦች እየተረከቡ ነበር።  በታክሲ መቆሚያዎች እና መንገዶች ላይ ዕቃዎቻቸውን ይሸጡ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ተከስተ «ትርፉ ጥሩ ነበረ፤ እድገቱም ፈጣን ነበረ። እንዳሁኑ አልነበረም። ያኔ ውድድሩ ትንሽ ነበረ። በዚህ በሪቴይል ንግድ ላይ ከቻይና ቀጥሎ የገባው አበሻ ይመስለኛል እና አብዛኛው አበሻ እዚህ የደረሰበት ስኬት ላይ ለመድረስ አብቅቶታል ብዬ አስባለሁ» ሲሉ ሒደቱን ይገልጹታል።

Südafrika, Pretoria: Lagerhaus für Papierrecycling in Brand gesteckt
ምስል Getty Images/AFP/P. Magakoe

የፖሊሲ ጥናት ባለሙያዋ የዶክተር ታንያ ቢሮ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የሌሎች አገሮች ስደተኞች በንግድ ሥራ በተሰማሩበት የጁሐንስበርግ ከተማ ክፍል ይገኛል። ታንያ እንደሚሉት በቻይና የተመረቱ አልባሳት በገፍ በሚሸጡበት በዚሁ አካባቢ ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ የጎረቤት አገራት ሸማቾች ያዘውትሩታል።

«እነዚህን ሸቀጦች ለመግዛት ሰዎች ከዚምባብዌ፣ ዛምቢያ፣ ሞዛምቢክ፣ አንጎላ፣ ናሚቢያ፣ ስዋዚላንድ እና ከቦትስዋና በየቀኑ ከባቡር ጣቢያው አጠገብ ወደሚገኘው ወደዚህ ቦታ በአውቶቡስ ይመጣሉ። ቦታው የድንበር ተሻጋሪ ንግድ ልውውጥ ማዕከል ነው። እጅግ በጣም ብዙ የቻይና አልባሳት በዚያ ለግብይት ይቀርባሉ። የተወሰኑት ተመሳስለው የተሰሩ ናቸው። አብዛኛው ግን ተመሳስሎ የተሰራ አይደለም። ይኸ ግዙፍ ኤኮኖሚ በኢ-መደበኛ ነጋዴዎች ለድሆች አልባሳት ያቀርባል። በእኛ ግምት ከሌሎች አገሮች ወደዚያ ቦታ የሚመጡ ሰዎች ብቻ በአንድ አመት ከአስር ቢሊዮን ራንድ በላይ ወጪ ያደርጋሉ» ሲሉ የገበያውን ግዝፈት ያስረዳሉ።

«የተወሰኑ ተመሳስለው የተመረቱ ሸቀጦች የሚሸጡ ኢትዮጵያውያን» እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ተከስተ ያ ማለት ግን ሁሉም ሰው ለዚህ ሁሉ አመታት በእንዲህ አይነት ሕገ-ወጥ የንግድ ሥራ ተሰማርቷል ማለት አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ። ከሶማሊያ፣ ናይጄሪያ፤ ከዚምባብዌ እና ከኢትዮጵያ ድንበር አቆራርጠው በመደበኛም ይሁን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ደቡብ አፍሪካ የሚገቡ ስደተኞች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ለአገሪቱ ምጣኔ-ሐብት አስተዋፆ ቢያደርጉም «መደበኛ ወደሆነው የንግድ ሥራ  እንዳይገባ አብዛኛው ሰው የሰነድ ችግር አለበት። የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በሰነድ [አሰጣጥ] ደረጃ ብዙ ነገር ዘገምተኛ ነው። ለአብዛኞቹ የመኖሪያ ፈቃድ አልሰጣቸውም። ያ ፈቃድ ካልተሰጠ የባንክ አካውንት ለመክፈት ብርህን [በባንክ] ለመቆጠብ፤ በብርህ ወደ ተሻለው የንግድ ሥራ ለመሔድ ያኛው እንቅፋት ሆኗል» ብለዋል።

ዶክተር ታንያ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የፖለቲካ ተገን ጥያቄ ያቀረቡ ስደተኞች በመደበኛው ኤኮኖሚ የሥራ ዕድል የማግኘት ፈተና እንዳለባቸው ይናገራሉ። ባለሙያዋ «ገበያው የሚፈልገው ክኅሎት ስለሌላቸው ወይም ያ ክኅሎታቸው አነስተኛ የሆነ ስደተኞች በመሆናቸው በመደበኛው ኤኮኖሚ በቀላሉ ሥራ አግኝተው አይቀጠሩም። በደቡብ አፍሪካ ሕግ መደበኛ ሥራ ለማግኘት ለስደተኞች ሒደቱ እጅግ ውስብስብ ነው። ከዚህ በተጨማሪ  ተገን የሚያገኙ ቢሆን እንኳ ሒደቱ ብዙ አመታት የሚወስድ በመሆኑ የደቡብ አፍሪካ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ቢሮ (Department of Home Affairs) እንደሰጣቸው በየሶስት ወሩ፤ በየስድስት ወሩ ወይም በየአመቱ የሚታደስ የተገን ፈቃድ ይዘው ለመቆየት ይገደዳሉ» ይላሉ።

ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር ያላት ደቡብ አፍሪካ ዜጎች ግን ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ተጉዘው በከተሞቻቸው የሚነግዱ ስደተኞችን ዕድላችንን ነጥቀዋል ሲሉ ይከሷቸዋል። የደቡብ አፍሪካ ስታስቲክስ መስሪያ ቤት ባለፈው ወር ያወጣው ሪፖርት እንደሚለው ከአገሪቱ ዜጎች 29 በመቶው ወይም 6.7 ሚሊዮን የሚሆነው ሥራ የለውም።

Südafrika, Johannesburg: Ausschreitungen in Malvern
ምስል Getty Images/AFP/G. Sartorio

ዶክተር ታንያ ዛክ እንደሚሉት የደቡብ አፍሪካ ኢ-መደበኛ ኤኮኖሚ በአገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠን ያለው ድርሻ 5.2 በመቶ ገደማ ነው። ዘርፉ እንደሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጠንካራ ባይሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን እድገት እያሳየ ነው። በኢ-መደበኛው ኤኮኖሚ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው የጎዳና ንግድ ከተለያዩ አገሮች ወደ ደቡብ አፍሪካ ያመሩትን ስደተኞች ጨምሮ ለበርካታ የአገሪቱ ዜጎች ገቢ እና የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተመራማሪዋ አስረድተዋል። ይሁንና በበርካታ ከተሞች ይኸው የንግድ መስክ በሕግ የተከለከለ በመሆኑ ሕግ አስከባሪዎች እና መደበኛውን ኤኮኖሚ ጨምሮ በተደጋጋሚ የግጭት መነሾ ሲሆን ታይቷል።

ዶክተር ታንያ «ችግሩ ለኢ-መደበኛው ግብይት በደቡብ አፍሪካ ኤኮኖሚ እና ግብይቱ በሚካሔድባቸው አደባባዮች በቂ ቦታ አልተሰጠውም። በርካታ ሕግጋቶቻችን የጎዳና ላይ ንግድን ይከለክላሉ። ስለዚህ በከተሞቻችን፤ በመደበኛው እና መደበኛ ባልሆነው ኤኮኖሚ መካከል ባለ ፍጭት ሁልጊዜም ከጭንቀት ጋር የሚታገል ነው። አንዳንድ ከተሞች ይኸን ችግር በመፍታት ረገድ ከሌሎቹ አኳያ ተራማጅ ሆነው ዕድል ሰጥተውታል። በአሁኑ ወቅት ከተማዋ ለኢ-መደበኛው ግብይት ፖሊሲ እያዘጋጀች ነው። ፖሊሲው ምን ይዞ እንደሚመጣ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ነገር ግን በደቡብ አፍሪካ ለኢ-መደበኛ ግብይት እውቅና መስጠት አስፈላጊ ነው። በአገሪቱ ካለው የስራ አጥ ቁጥር አኳያ እውቅና የመስጠቱ አስፈላጊነት ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም ሰዎች የራሳቸውን ሥራ እንዲከውኑ ዕድሎቻቸውንም እንዲያሰፉ ያደርጋል» ሲሉ ለኢ-መደበኛው ግብይት እውቅና መስጠት ያለውን ፋይዳ ይገልፃሉ። 

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በውጭ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ትናንት በቴሌቪዥን ቀርበው በይፋ አውግዘዋል። በኬፕታውን ዛሬ በተከፈተው የዓለም ኢኮኖሚክ መድረክ የአፍሪቃ ስብሰባ ላይ የተገኙት ራማፎሳ በውጭ ዜጎች ላይ የሚደረገውን ጥቃት ለማስቆም ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ከስብሰባው ጎን በተዘጋጀ ስነ ስርዓት ላይ ለንግድ ሰዎች ንግግር ሲያደርጉም «ከሌሎች ሃገራት በመጡ ህዝቦች ላይ እርምጃ መውሰድ ተቀባይነት የለውም። በዚህች ውብ ሀገራችን ይህ በፍጹም ሊፈቀድ አይገባም» ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ