1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች ቀዉስና የአዉሮጳ ኅብረት ፈተና

ማክሰኞ፣ የካቲት 22 2008

ጦርነት፣ ችግር እና ጭቆናን በመሸሽ ወደ አዉሮጳ በገፍ የሚፈልሱ ስደተኞች ጉዳይ የአዉሮጳ ኅብረት አገሮችን የፖለቲካና የኤኮኖሚ ሁኔታ ከማጨናነቅ አልፎ የኅብረቱን ቋሚ ጥንካሪና ቀጣይነትም እየተፈታተነዉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1I4wS
Afghanische Flüchtlinge in Athen Griechenland
ምስል DW/R. Shirmohammadi

የስደተኞች ቀዉስና የአዉሮጳ ኅብረት ፈተና


በድንበር ቁጥጥር በስደተኞች አቀባበልና አያያዝ ላይ በአባል ሃገራት መካከል የተፈጠረዉ ልዩነትና አለመግባባት ራሱን የአዉሮጳ ኅብረት ወደ ቀዉስ እንዳይከተዉ ያሰጋል እየተባለ ነዉ። ባለፈዉ ዓመት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ወደ አዉሮጳ እንደገቡ የሚታወቅ ሲሆን ዘንድሮም ከጥር ወር ወዲህ ብቻ 100 ሺህ ስደተኞች ወደ ኅብረቱ አባል ሃገራት ገብተዋል። ይህንን ከሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የሕዝብ ፍልሰት ነዉ የሚባለዉን ክስተት አዉሮጳ በጋራ ለመቋቋምና በየሃገሮቹ ድንበሮች የሚታየዉን ሰብዓዊ ቀዉስ በማስወገድ ችግሩን ለመፍታት መሪዎች ሚኒስትሮችና ባለሞያዎች በየጊዜዉ እየተሰበሰቡ ዉሳኔዎችን እያሳለፉ ቢሆንም፤ ተግባራዊ የሆኑት ዉሳኔዎችና ድንጋጌዎች ግን ከቁጥር የሚገቡ አይደሉም። የተከሰተዉ የስደተኞች ቀዉስ በሁሉም የአዉሮጳ ኅብረት ሃገሮች ከፍተኛ ቀዉስ አስከትሎአል ቢባልም የስደተኞች መዳረሻ እንደሆኑት እንደ ግሪክና ጣልያን የመሳሰሉ ሃገሮች ያህል፤ በችግሩ የተመታ የለም። ይህን የጋራ ችግር በጋራና ወችን በመካፈል መወጣት ይገባል ቢባልም፤ የጀርመንና የስዊድንን ያህል ኃላፊነትን የወሰደ የለም። ችግሩን አዉሮጳዊ በሆነ የመፍትሄ ማዕቀፍ መፍታት አለበት ተብሎ ኮሚሽኑ የጋራ ስልትና እቅድ በመንደፍ የዳግም ሰፈራና የስደተኞች ምደባ ፕሮግራም ያቀረበ ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም። እንደ ቱርክና ሌሎች ስደተኞች በብዛት ከሚገኙባቸዉ ሃገሮች ጋር በጋራ በመሥራት የስደተኞችን አያያዝ የሚሻሻልበትን ስልት ማመቻቸት ያስፈልጋል፤ በሕገ ወጥ የሰዉ አዘዋዋሪዎች ላይ እርምጃ መዉሰድ ይገባል ቢባልም እስካሁን ግን የስደተኞች አያያዝም አልተሻሻለም፤ ወደ አዉሮጳ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥርም ቢበዛ እንጂ አልቀነሰም። በዚህ ረገድ አዉሮጳ መሰብሰቡን ዉሳኔ ማሳለፉን አልተወም። አሁንም ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሄ ብቻ ነዉ የሚያዋጣዉ በማለት በተለይ ጀርመንና ኅብረቱ አፅኖ ሰጥተዉ እያሳሰቡ ነዉ። ይሁንና አንዳንድ አባል ሃገሮች ከኅብረቱ ዉሳኔዎችና መርሆዎች ዉጭ የየራሳቸዉን ርምጃ በመዉሰድ ድንበራቸዉን መዝጋት ጀምረዋል፤ ስደተኞችንም አግደዋል። ኦስትርያ ይህን የድንበር ቁጥጥር ከባልካን ሃገሮች ጋር አጠናክራ ቀጥላለች። ሃጋሪ ደግሞ የድንበር አጥሩዋን ከማጠናከር አልፋ ኅብረቱ በወሰደዉ ኮታና ዳግም ሰፈራ ጉዳይ ሕዝበ ዉሳኔ የምታካሂድ መሆኑን አስታዉቃለች። በአዉሮጳ ኅብረት ስለተደቀነዉ የስደተኞች ቀዉስና ኅብረቱ ስለገጠመዉ ፈተና ዝርዝር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።


ገበያ ንጉሴ

Afghanische Flüchtlinge in Athen Griechenland
ምስል DW/R. Shirmohammadi


አርያም ተክሌ