1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች ቁጥር ማሻቃብ

ሐሙስ፣ ሰኔ 13 2011

ብዙ ሕዝብ በማሰደደ አምናም እንደ ሐቻምናዉ ሶሪያን የተስተካከለ ሐገር የለም።አፍቃኒስታን፣ደቡብ ሱዳን፣ ምያንማር እና ሶማሊያ ሶሪያን ይከተላሉ።ካጠቃላዩ ስደተኛ ሁለት-ሰወስተኛዉ የእነዚሕ አምስት ሐገራት ዜጋ ነዉ።ዘንድሮ ግን UNHCR እንደሚለዉ በስደተኛ ቁጥር ቬኑዙዋላ የመጀመሪያዉን ሥፍራ ይዛለች።

https://p.dw.com/p/3KipC
Venezuela Flüchtlinge an der Grenze zu Kolumbien bei Cucuta am Fluss Tachira
ምስል Getty Images/AFP/S. Mendoza

የስደተኞች ቁጥር መናር

የስደተኞች ቁጥር ከዓመት ዓመት እያሻቀበ መምጣቱ የዘመኑን ዓለም ስልጣኔ ጥያቄ ዉስጥ የሚጥል መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮምሽነር የUNHCR ኃላፊ አስታወቁ።ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ የስደተኞች ቁጥርን አስመልክተዉ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የስደተኞች ቁጥር ማሻቀብ ዓለም ሠላም ለማዉረድ አለመቻልዋን አመልካች ነዉ።ዓለም አቀፉ ድርጅት ይፋ ባደረገዉ ዓመታዉ ዘገባዉ እንዳስታወቀዉ የስደተኞች ቁጥር 71 ሚሊዮን ሊደርስ ጥቂት ነዉ የቀረዉ።ዲትሪሽ ካርል ማወር የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

 

በዓለም የተመዘገበ ታሪክ ሆኖ አያዉቅም።አምና ሆነ።71 ሚሊዮን ያሕል ሕዝብ ቤት፣ሐብት-ንብረት፣ሐገር-መንደር ሁሉም የለዉም።ካለዉም የምፅዋት ነዉ።በጎርጎሪያኑ አምና (2018) 3 ሚሊዮን ስደተኞች ወደየሐገሩ መመለሱ ተዘግቦ፣ለባለ ጉዳዮች ተስፋ ሰጪ መስሎ ነበር።የዓለም ሐቅ የመምሰሉ ተስፋ ቅጭት መሆኑ እንጂ ዚቁ።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) እንዳጠናዉ 3 ሚሊዮን ስደተኛ ወደየሐገር-ቀዬዉ በተመለሰበት ዓመት የአጠቃላዩ ስደተኛ ቁጥር በ2.3ሚሊዮን ጨመረ።ጥቅል ቁጥሩ 70.8 ሚሊዮን።ሰዎችን የሚያሰድዱ ዋና ዋና ምክንያቶች ያዉ እንደ ሁሌዉ ጦርነት፣ግጭት፣የገዢዎች ወይም የጉልበተኞች ጥቃት ናቸዉ።የUNHCR የበላይ ኃላፊ ፊሊፖ ግራንዲ የስደተኛዉን ቁጥር ማየል ዓለም ሰላም ለማዉረድ ያለመቻሉ ወይም ያለመፈለጉ ምልክት ያሉትም ለዚሕ ነዉ።

 «ይሕ ለስልጣኔያችን ምን ማለት እንደሆነ ከልብ ማጤን አለብን።የስደተኛ ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ ነዉ ማለት (ባለፉት አምስት ስድስት ዓመታት እየጨመረ ነዉ) ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰላም ለማዉረድ አልቻልንም ማለት ነዉ።»

ብዙ ሕዝብ በማሰደደ አምናም እንደ ሐቻምናዉ ሶሪያን የተስተካከለ ሐገር የለም።አፍቃኒስታን፣ደቡብ ሱዳን፣ ምያንማር እና ሶማሊያ ሶሪያን ይከተላሉ።ካጠቃላዩ ስደተኛ ሁለት-ሰወስተኛዉ የእነዚሕ አምስት ሐገራት ዜጋ ነዉ።ዘንድሮ ግን UNHCR እንደሚለዉ በስደተኛ ቁጥር ቬኑዙዋላ የመጀመሪያዉን ሥፍራ ይዛለች።የቬኑዙዌላ ፖለቲካዊ ቀዉስ 4 ሚሊዮን ሕዝብ አስድዷል።

Schweiz, Genf: UN-Beauftragte für Flüchtlinge Grandi und der UN-Koordinator für humanitäre Hilfe, Lowcock, nehmen an einer Pressekonferenz teil
ምስል Reuters/D. Balibouse

ከየአምስቱ ስደተኛ አራቱ የተጠለለዉ በየሐገሩ አጎራባች ሐገራት ነዉ።ብዙ ስደተኞች በመቀበል ቱርክ የመጀመሪያዉን ሥፍራ ስትይዝ፣ፓኪስታን ሁለተኛ ናት።ዩጋንዳ፣ሱዳን እና ጀርመን ከ3 እስከ 5 ያለዉን ስፍራ ይይዛሉ።

በሕዝብ ቁጥር ሲሰላ ደግሞ ትንሽ ሕዝብ ያላት ሊባኖስ ብዙ ስደተኛ በማስታገድ ቀዳሚዉን ሥፍራ ይዛለች።ከየስድስቱ የሊባኖስ ነዋሪ አንዱ ስደተኛ ነዉ።የሜድትራኒያንን ባሕር አቋርጦ ወደ አዉሮጳ የሚገባዉ ስደተኛ ቁጥር አምናና ዘንድሮ በጅጉ አሽቆልቁላል።በአማካይ በ45ሺሕ ቀንሷል።አሁንም ግን 140 ሺሕ ስደተኛ ኢጣሊያ፣ ስጳኝና ግሪክ ገብቷል።በዚሕም ምክንያት ይመስላል ግራንዲ አዉሮጶች ጫናዉን ለመጋራት ወይም ስደተኞችን ለመከፋፈል ባለመፍቀዳቸዉ ይወቅሳሉ።

                                       

«ለአዉሮጳ ብቸኛዉ አማራጭ ጫናዉን መጋራት ነዉ።ይሕ በጣም ትልቅ ፖለቲካዊ ዉዝግብ እንደሚያስከትል እናዉቃለን።ይሕን ያሕል ፖለቲካዊ ርዕሥ በመሆኑ አዝናለሁ።ምክንያቱም ጉዳዩ ፖለቲካዊ መሆኑ ጫናዉን ለመጋራት በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋልና።በምርጫ እሸነፋለሁ በማለት ስደተኞችን ለመቀበል የሚፈልግ መንግስት የለም።ይሁንና በጣም ሐብታም፣ሠላማዊ በሆነችዉ አሐጉር ስደተኞቹን ተከፋፍሎ መርዳት በጣም ቀላል በሆነ ነበረ።»

Kenia Flüchtlinge aus dem Südsudan | Flüchtlingszentrum in Kakuma
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba

ግራንዲ ድፍን አዉሮጳን የመዉቀሳቸዉን ያክል ጀርመንን አመስግነዋል።«ጀርመን ባለፉት 3 እና 4 ዓመታት ያደረገችዉ ክፍተኛ ድጋፍ እየታወቀ፤ከዚሕ በላይ እንድታደርግ መጠየቅ አስቸጋሪ ነዉ።»

UNHCR እንደሚለዉ ጀርመን አንድ ሚሊዮን ስደተኛ ታስተናግዳለች።ግማሹ የሶሪያ ዜጋ ነዉ።ጀርመን ዉስጥ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ2017 ጥገኝነት  የጠየቀዉ ስደተኛ ቁጥር 200 መቶ ሺሕ ነበር።አምና ግን ወደ 162ሺሕ ዝቅ ብሏል።

ነጋሽ መሐመድ

ተስፋለም ወልደየስ