1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች እልቂትና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 12 2007

የኦባማዋ አዲሲቱ ሊቢያ ታጣቂዎች በየቀበሌዉ የነገሱባት፤ ትጥቅ አልባዉ የሚገደል፤ የሚደፈር፤የሚገረፍባት ሐገር ናት።ከሊቢያዎች አልፎ ግብፆች እና ኢትዮጵያዉያን የሚታረዱባት፤ ስደተኛ አሸጋጋሪዎች የፈሉባት፤ ስደተኞች የሚሰቃዩ-ወደ አዉሮጳ በገፍ የሚሰደዱባት ሐገር ናት

https://p.dw.com/p/1FBMB
ምስል Opielok Offshore Carriers/dpa

«እንደኛዉ ሰዎች ናቸዉ። የተራቡ፤የተበደሉ፤የቆሰሉ፤ የተመዘበሩ፤ የጦርነት ሠለቦች» አሉ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሳሲስ።ዓላማቸዉ «የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነበር።» ግን አሩቅ አስበዉ፤ ብዙ ተመኝተዉ ባጭር ቀሩ።ሲበዛ-ዘጠኝ መቶ ሐምሳ፤ ሲያንስ 700 ስደተኞች ቅዳሜ-ለዕሁድ አጥቢያ ባሕር ላይ አለቁ።

ከዓመት ከመንፈቅ በፊት (ጥቅምት 2013-ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ላምፔዱዛ ደሴት መዳረሻ 360 ኤርትራዉያን ስደተኞች ማለቃቸዉ ለሰዉ ሕይወት አዛኞችን ልብ ሠብሮ፤ የመብት ተሟጋቾችን ጩኸት አንሮ፤ ሌሎችን አነጋግሮ-የአፍሪቃና የአዉሮጳ ፖለቲከኞችን ጭካኔ አጋልጦ-ጉድ አሰኝቶ ነበር።በቀደም በእጥፍ ተደገመ።ጭካኔዉ በዛ-ወይስ ጉዱን ጉድ ዘለቀዉ እንበል? ላፍታ አብረን አንጠይቅ።

ከአድማሱ ማዶ ብልጭ፤ ድርግም የሚለዉ መብራት ርዳታ አድራጊዎች መቃረባቸዉን ጠቋሚ መሆኑን ስደተኞቹ አላጡም።በርግጥም ነበር።ወደ ሊቢያ ትጓዝ የነበረችዉ የፖርቱጋል ዕቃ ጫኝ መርከብ ካፒቴን የድረሱልኝ ጥሪዉን እንደሰሙ የመርከባቸዉን አቅጣጫ ቀይረዉ ዉሐ ላይ ዥዋ-ዥዌ ወደምትጫወተዉ ጀልባ-ቀዘፉ።

ከሩቅ ብልጭ-ድርግም ይል የነበረዉ መብራት ድቅድቁን ጨለማ-ቦግ-ተግ፤-ደመቅ- ሲል ወትሮም ተስፋ ላለማጣት ከሚያደርጉት ተስፋ-በስተቀር ተስፋ የሌላላቸዉ ስደተኞች ልብ በመኖር ተስፋ ሳይሞላ አልቀረም።ለመኖር ግን እነሱም መፍጨርጭር አለባቸዉ።ሁሉም-እኩል ያሰቡ ይመስል መብራቱን ባዩበት አቅጣጫ ወደሚገኘዉ የጀልባቸዉ ጥግ-ለመድረስ ይራኮቱ ገቡ።አሳ ማጥመጃይቱ ጀልባ ከያ-ሜትር አትበልጥም።እንደነገሩ የተወታተፈች ነች።በዚያ ላይ በሕዝበ-ሰደተኛ ታጭቃለች።የኢጣሊያዉ ጠረፍ ጠበቂ ጦር ቃል አቀባይ ፊሊፕኖ ማሪኒ እንዳሉት፤ ስደተኛዉ እየተሻማ-አንድ ጥጓ ሲሰገሰግባት-ጀልባይቱ ድፍት አለች-ወደ ዉሐዉ።

Flüchtlingsboot am Frachtschiff OOC Cougar
ምስል picture-alliance/dpa/Opielok Offshore Carriers

«እስካሁን ድረስ የምናዉቀዉ ጀልባዋ መገልበጧን ነዉ።ስደተኞቹ በሙሉ እርዳታ የሚያደርጉት ወገኖች ወደሚመጡበት አቅጣጫ በሚገኘዉ የጀልባዋ ጥግ በመስፈራቸዉ ሳትገለበጥ አልቀረችም።»«አዲዮስ»------ብለዉ ይሆናል የፖርቱጋሉ ዕቃ ጫኝ መርከብ አዛዥ-ከስፍራዉ ሲደርሱ።ወይም «ቻዉ»።አሉም-አላሉ ሲያንስ የሰባት መቶ-ሲበዛ የዘጠኝ መቶዎቹ ባብዛኛዉ ወጣት ስደተኞች ያጭር ዕድሜ ረጅም-የጉስቁልና ጉዞ-ተጠናቀቀ።አለቁ።

እኒያ ጎስቋሎች ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሊሰናበቱት አስበዉት የነበረዉ ባሕር አስከሬን፤ ልብስ፤ ጨርቃቸዉ ይዋኝበት ገባ።ድንበር የለሽ ሐኪሞች የተሰኘዉ ዓለም አቀፍ ግብረ-ሥናይ ድርጅት ሐላፊ ሎሪስ ደ ፊሊፒ እንዳሉት የተዘረረዉ እስከሬን ብዛት ባሕሩን «የጦር ቀጠና አስመስሎታል።»

የዕልቂቱ ዜና ትናት ሮም ሲደርስ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ እንዳሉት ሟቾቹ በየሐገራቸዉ የሚደርስባቸዉን በደል፤መገፋት፤ ጭቆና፤ ሥቃይና ጦርነትን ለማምልጥ ያለሙ፤የተሻለ ኑሮ የሚመኙና የሚገባቸዉ-ወጣቶች ነበሩ።«ልክ እንደኛዉ ሰዎች ነበሩ።ወንዶችና ሴቶች።ወንድምና እሕቶቻችን።የተራቡ፤ የተሰቃዩ፤ የቆሰሉ፤የተጨቆኑ እና የጦርነት ሰለቦች ነበሩ።የተሻለ ኑሮ እና ደስታ ይፈልጉ ነበር።»

ፍራንሲስ እንደ ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ከቫቲካን ዉጪ የመጀመሪያዉን ጉዞ ያደረጉት ወደ ላምፔዱዛ ደሴት ነበር።ጥቅምት 2013፤ ከ360 በላይ በአብዛኛዉ ኤርትራዉያን ስደተኞች ያለቁበትን አካባቢ ለመጎብኘት።አብዛኞቹ የመብት ተሟጋቾች-በየጊዜዉ የሚሉትን ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳቱ ያኔ ብለዉት ነበር።ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ስደተኞቹን ያን ከመሰለዉ አደጋ እንዲያድን ተማፅነዉ ነበር።

ዓለም አቀፍ በሚል ቅፅል የሚጠሩት ሐብታም ሐያል ምዕራባዉያን መንግሥታት አንድ ዜጋቸዉ ሌላ ሥፍራ ቢገደል ደሙን ለበቀል፤ ቢታገት ለማስለቀቅ፤ ቢዛትባቸዉ ለመቅጣት ያየር-የባሕር፤ የምድር ጦር ለማዝመት ዕለታት አይፈጅባቸዉ ይሆናል። ሚሊዮነ-ሚሊዮናት ዶላር ለማዉጣት አያመነቱ ይሆናል።

Verstorbene Flüchtlinge im Hafen von Lampedusa
ምስል Reuters/Vista via Reuters TV

የአፍሪቃና የመካከለኛዉ ምሥራቅ አምባገነኖች ለገፉት፤ ምዕራባዉያን ራሳቸዉ ያቀጣጠሉት ጦርነት መድረሻ ላሳጣዉ -ምናልባት የነሱን እጅ ለመከጀል የሚጓዘዉን ስደተኛ ሕይወት ለማዳን የሚጨነቁበት ፖለቲካዊ ምክንያት ግን የለም።

የሜድትራኒያንን ባሕር የሚቆጣጠሩት የአዉሮጳ ሕብረት አባል መንግሥታት የስደተኞችን ሕይወት እንዲያድኑ የመብት ተሟጋችና ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች በተደጋጋሚ በሚያሳሰቡት ወቅት-አምና የአዉሮጳ ሕብረት ማር ኖስትሮም ያለዉን ዘመቻ አቋረጠ።ኢጣሊያ መራሹ ዘመቻ አነሰም በዛ በተለይ የሜድትራኒያን ባሕርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ለአደጋ የሚጋለጡ ስደተኞችን ለማዳን ያለመ ነበር።

ሕብረቱ ለኢጣሊያ አስፈላጊዉን ድጋፍ በመስጠት ፋንታ ዘመቻዉን ማቋረጡ ብዙዎችን እንዳሳዘነ፤ እንዳስተዛዘበ፤ የመብት ተማጋችን ጩኸት እንደጠናከረ አምና ዘንድሮ ሆነ ።የአዉሮጳ ሕብረት የተነሳበትን ወቀሳ ለማቀዝቀዝ ፍሮንቴክስ ብሎ የሰየመዉ ድርጅት እንዲጠናከር መወሰኑን አስታወቀ።ይሁንና ገንዘብ፤ የሰዉ ሐይልና መዋቅር አልባዉ ድርጅት ሕብረቱ የሚሰነዘርበትን ወቀሳና ትችት ለማድበስበስ መሳሪያ ከመሆን ባለፍ ስደተኞችን ለማዳን የተከረዉ የለም።

የአዉሮጳ ሕብረትን ሥራ ብቻዋን የተሸከመችዉ የኢጣሊያ ጠረፍ ጠባቂ ባሕር ሐይል አራተኛ ወሩን ባጋመሰዉ የጎሮጎሮሳዉያኑ 2015 ብቻ 11 ሺሕ ስደተኞችን አድኗል።በኢጣሊያ ጦር ድጋፍም፤ በአጋጣሚም ብለዉ ሰላሳ አምስት ሺሕ ስደተኞች አዉሮጳ መድረስ ችለዋል።ሺዎች ግን ባሕር ዉስጥ ቀርተዋል።

በጀርመን የተባበሩት መንግሥት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR- በምሕፃሩ) ተወካይ ሜሊሳ ፍሌሚንግ እንደሚሉት ድርጅታቸዉ ከጥር እስካለፈዉ ቅዳሜ ድረስ ብቻ የሜድትራኒያንን ባሕር ለማቋረጥ ሲሞክሩ 1600 ስደተኞች መሞታቸዉን መዝግቧል።«ባለፉት ሰወስት ወራት ዉስጥ ብቻ በትንሹ አንድ ሺሕ ስድት መቶ ስደተኞች መሞታቸዉን ቆጥረናል።እስካሁን በተለመደዉ መሠረት ብዙ ስደተኞች የሚመጡት ከግንቦት በኋላ ባለዉ ጊዜ ነበር።ስደተኞችን ለማዳን ፈጣን እርምጃ ካልተወሰደ ሁኔታዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱ አይቀርም።»

Luxbemburg EU Außenminister Krisentreffen Flüchtlinge Mittelmeer
ምስል picture-alliance/dpa/J. Warnand

ድርጅቱ ያልመዘገባቸዉን ሟቾች ቁጥር የሚያዉቅ የለም።የቅዳሜዉ ተደገመ።ጥሪ፤ ተማፅኖ፤ ፀሎት ምሕላዉም እንደ አመታዊ ግብር ቀጠለ።«ይሕን በመሰለዉ አደጋ ላሞቱት ሰዎች ጥብቅ ሐዘኔን እገልፃለሁ።ሁሌም በፀሎቴ እንደማረሳቸዉ ያሉበት ላልታወቁት፤ ለሟች ቤተሰቦችና ዘመድ ወዳጆች ቃል እገባለሁ።እንዲሕ አይነቱ ዘግናኝ እልቂት እንዳይደገም ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ባስቸኳይ፤ በቁረጠኝነትና በሐላፊነት መንፈስ እንዲጥር በድጋሚ አጠይቃለሁ።»

ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ።የቅዳሜዉ እልቂት ከተሰማ በሕዋላ የአዉሮጳ ሕብረት አባል መንግሥታት ባለሥልጣናት በየፊናቸዉ ለስደተኞቹ ሞት ሰዎችን የሚያስኮበልሉ አሸጋጋሪዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።የሞልታዉ ጠቅላይ ሚንስትር ጆሴፍ ሙስካት ከዚሕም አልፈዉ ስደተኞችን የሚያሻግሩ ሰዎችን «አሸባሪ» በማለት ወንጀለዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድም የአዉሮጳ ሕብረት ሰዎችን የሚያሸግሩ ሰዎችን በጥብቅ መቆጣጠር እንዳለበት አሳስበዋል።ዛሬ ሉክሰምቡርግ ሥለ ሥደተኞች የተነጋገሩት የሕብረቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮችም ለመዉሰድ ካቀዱት እርምጃ አንዱ ሰዎችን ወደ አዉሮጳ የሚያሻግሩትን ወገኖች አድኖ መያዝና መቅጣት ነዉ።

የአዉሮጳ ፖለቲከኞች መግለጫ፤ አስተያየትና ዕቅድ አዉሮጶች ሰዎች አሸጋጋሪዎችን እንዲቆጣጠሩ ሺዎች ማለቅ ነበረባቸዉ? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም።የአዉሮጳ ሕብረት ያደጋ ማግሥት ሽር ጉድ ምንም ሆነ ምን የሊቢያዉ ትርምስ፤ የአፍሪቃ ሐገራት ምሥቅልቅል ችግር፤ የሶሪያ ጦርነት እስካልቆመ ወይም እስካልተቃለለ ድረስ ሜድትራኒያን አቋርጦ አዉሮጳ ለመግባት የሚመኘዉን ወጣት ብዙዎች እንደሚያምኑት መግታት አይቻልም።ሕፃናት አድን (ሴቭ ዘችልድረን) የተሰኘዉ ግብረ ሰናይ ድርጅት ባልደረባ ሳራሕ ቴይለርም ይሕን ያረጋግጣሉ።«ሴቭ ዘ ችልድረን እንደሚያምነዉ እየተባባሰ የመጣዉ የሊቢያ ቀዉስ፤ ከሠሐራ በስተደቡብ የሚገኙት የአፍሪቃ ሐገራት ሁኔታ ካልተሻሻለ፤ የሶሪያዉ ጦርነት ካልቆመ ሁኔታዉ እየከፋ መምጣቱ አይቀርም።ሥለዚሕ ዉጥረቱና እየባሰ፤ ጭቆናዉ እየከፋ ሲመጠ የስደተኛዉ ቁጥርም ይጨምራል።»

አስቸጋሪዉን ጉዞ አልፎ አዉሮጳ የገባዉ ጋምቢያዊዉ ወጣት እንደሚለዉ ከሐገሩ የተነሳዉ ከተሳካለት አዉሮጳ-መግባት ካልሆነም ሞትን ለመጋፈጥ ቆርጦ ነዉ።

«በጣም ፈርቼ ነበር።ፈርቼ ነበር።አዉሮጳ ከመግባት እና ከመሞት አንዱን ለመቀበል ወስኜ ነዉ-የመጣሁት።» የሜድትራኒያን ባሕርን ለመቅዘፍ ሊቢያ ላይ ወረፋ የሚጠብቀዉ ኢትዮጵያዉ ስደተኛም የተለየ ዓላማ የለዉም። እስካሁን ካየሁት ስቃይ የሚብስ የለም ባይ ነዉ።የምዕራባዉያኑ መንግሥታት ያዘመቱት ጦርና የያኔዎቹy የሊቢያ አማፂያን የሐገሪቱን የረጅም ዘመን ገዢ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ሲገድሉ ሰሜን አፍሪቃዊቱ ሐገር የነፃነት፤ የዴሞክራሲ፤ የፍትሕ ምድር ሆነች ብለዉን ነበር።የሊቢያ ሕዝብ የሚሻዉን አስተዳዳሪ የሚሾም-የማይፈልገዉን የሚሽርባት፤ የሐገሩን ሐብት በእኩልነት የሚጠቀምባት ሥርዓት እንደሚመሰርት ተስፋ ተሰጥቶ ነበር።

Papst hält Messe zum 100. Jahrestag des Massenmords an Armeniern
ምስል Solaro/AFP/Getty Images

«ዛሬ ሙዓመር ቃዛፊ መሞታቸዉን የሊቢያ መንግሥት አስታዉቋል።ይሕ ለሊቢያ ሕዝብ ረጅሙ የሥቃይና የመከራ ዘመን ማብቃቱን የሚያበስር ነዉ።ከእንግዲሕ በአዲሲቱና በዴሞክራሲያዊቱ ሊቢያ ሕዝቧ የራሱን መፃኤ ዕድል ነፃነት አላቸዉ።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ ጥቅምት 20 2011።የኦባማዋ አዲሲቱ ሊቢያ ታጣቂዎች በየቀበሌዉ የነገሱባት፤ ትጥቅ አልባዉ የሚገደል፤ የሚደፈር፤የሚገረፍባት ሐገር ናት።ከሊቢያዎች አልፎ ግብፆች እና ኢትዮጵያዉያን የሚታረዱባት፤ ስደተኛ አሸጋጋሪዎች የፈሉባት፤ ስደተኞች የሚሰቃዩ-ወደ አዉሮጳ በገፍ የሚሰደዱባት ሐገር ናት።

አሜሪካ መራሹ ጦር በ2003 ኢራቅን ሲወር የወራሪዉ ጦር አዝማቾች የኢራቅን ሕዝብ ልክ እንደ ሊቢያዉ ሁሉ የልማት እድገት፤የዲሞክራሲ ተስፋ «እንቁልልጭ» ብለዉት ነበር።ሊቢያ ዳግማዊት ኢራቅነቷን አስመስክራለች። ከስሕተቱ የሚማር የለም፤ ለነገሩ ከስሕተት ለመማር መጀመሪያ ስሕተትን የማመን ጀግንነት ወይም ብልሕነትን ይጠይቃል።ሐያላኑ ፖለቲከኞች ግን አይሳሳቱም እና አይማሩም።ሶሪያ፤የመን፤ዩክሬን ማን ያሰልስ ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ