1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች የባልካን የጉዞ መስመር

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 26 2007

ከግሪክ ተነስተው በባልካን አገራት አቆራርጠው ጀርመን የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ከቀን ወቀን እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው ። በዚህ መንገድ የተጓዙ ወደ 200 የሚጠጉ ስደተኞች በዛሬው ዕለት ደቡባዊ ጀርመን ሽቱትጋርትና ምዕራባዊ ጀርመን ፍራንክፈርት ገብተዋል ።ከስደተኞቹ አብዛኛዎቹ የሶሪያ ና የአፍጋኒስታን ዜጎች ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/1GPkJ
Ungarn Flüchtlinge am Grenzzaun zu Serbien
ምስል Getty Images/M. Cardy

[No title]

የቀድሞዋ ዩጎዝላቭያ ግዛት መቄዶንያ በስተሰሜን ምዕራብ ከኮሶቮ፤ በስተሰሜን ከሰርቢያ፤ በስተምሥራቅ ከቡልጋሪያ፤ በስተደቡብ ከግሪክ እንዲሁም በስተምዕራብ ከአልባንያ ጋር የምትዋሰን ትንሽ ሃገር ናት ።በጎርጎሮሳዊው 1991 ከዩጎዝላቭያ ተገንጥላ ነፃ መንግሥት የመሠረተችዉ መቄዶንያ የአውሮፓ ህብረትና የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት NATO አባል ለመሆን በእጩነት የምትጠባበቅ ሐገር ናት። መቄዶንያ በአሁኑ ጊዜ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስባለች ። ከቅርብ ወራት ወዲህ በርካታ ስደተኞች ሜቄዶንያን ወደ ሰሜን አውሮፓ በተለይም ወደ ጀርመን መሸጋገሪያ አድርገዋታል። ከሜቄዲንያ ተነስተው በሌሎች የባልካን አገራት በኩል ወደ ሰሜን አውሮፓ ከሚሄዱ ስደተኞች ጋር የተጓዘችው የዶቼቬለዋ ኔማንያ ሩየቪክ እንደዘገበችው ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ በዚህ መስመር ወደ ሰሜን አውሮፓ ሃገራት ያቀኑ ስደተኞች ቁጥር 100 ሺህ እንደሚደርስ ይገመታል ።ግቭጌልያ ከግሪክ የምትዋሰን የመቄዶንያ የድንበር ከተማ ናት ። በዚህች ከተማ በሚገኘው የባቡር ጣቢያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ተኮልኩለዋል ። አንዳንዶቹ ሜዳ ላይ ተኝተዋል ። የአካባቢው ነጋዴዎች አጋጣሚውን በመጠቀም በባቡር ጣቢያው ዙሪያ የፕላስቲክ ጠረጴዛዎችን ዘርግተው ይነግዳሉ ። በአንድ ዩሮ ሁለት ሙዝ ፣ ወይም የታሸገ ፈንድሻ አለያም ውሐ ይሸጣሉ ። መንገደኞች በአነስተኛ ክፍያ የተንቀሳቃሽ ስልካቸውን ባትሪ ይሞላሉ(ቻርጅ )ያደርጋሉ ።
እዚያ ከሚገኙት ስደተኞች አንዱ የ25 ዓመቱ ሙሀመድ ነው ። ፓኪስታናዊው ሙሃመድ ከሌሎች የሃገሩ ሰዎች ጋር በባቡር ሃዲዱ ጫፍ ላይ ተቀምጧል ።በመቄዶንያዋ ግቭጌሊያ ፣መኝታም ሆነ መታጠቢያ እንደ ቅንጦት ነው የሚቆጠረው ።ሙሀመድ የተሰደደው ህይወቱ ለአደጋ በመጋለጡ መሆኑን ይናገራል ።
«የኛን የፓኪስታን ቴሌቪዥን ትከታተላላችሁ? ከ2 ወራት በፊት ታሊባን ትምሕርት ቤት ውስጥ ባደረሰው ጥቃት በርካታ ሕጻናትን ገድሏል ። የተገደሉት አበሳ የሌለባቸው ፍፁም ንፁህ የሆኑ የ8 ና የ6 ዓመት ህፃናት ናቸው ። ብዙ ሰዎች ወደ አውሮፓ ይሰደዳሉ። እኔም ከእነርሱን ጋር እየተጓዝኩ ነው ጀርመን እገባለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ።»
እድለኛ ከሆነኩ ጀርመን እሄዳለሁ ፤ እዚያም ጥሩ ሥራ አግኝቼ አስተማማኝ ህይወት እመራለሁ ብሎ ተስፋ የሚያደርገው ሙሀመድ ጀርመን ለመድረስ ብዙ ይቀረዋል ። በመጀመሪያ በደረሰበት በመቄዶንያ ውስጥ ለ3 ቀናት መቆየት የሚያስችለው ፈቃድ ለማግኘት ማመልከት ይኖርበታል ። የመቄዶንያ የድንበር ፖሊስ የሚሰጠውን ይህንኑ የፈቃድ ወረቀት ለማግኘት ብዙዎች ለቀናት እየጠበቁ ነው ። ወረቁቱን ለማግኘት ረዥም ሰልፍ ያስጠብቃል ።ጉልበት ያለው ወይም ስለት የያዘ ሰልፉ ሊያጥርለት ይችላል ። 3 ሚሊዮን እንኳን የማይደርስ ህዝብ ያላትን መቄዶንያ መተላለፊያ ያደረጓት በርካታ ስደተኞች ከአቅሟ በላይ ሆነዋል ።በየቀኑ 2ሺህ የሚገመቱ ስደተኞች ናቸው መቄዶንያ የሚገቡት ።የስደተኞች መነኻሪያ የሆነችው የግቭጌልያ ከንቲባ ግሪክ ችግሩን ወደ ኛ እያስተላለፈች ነው ይላሉ ። ከንቲባው ለስደተኞች ሃዘኔታ ቢኖራቸውም በነርሱ ምክንያት ግን ዜጎች መሰቃየት የለባቸውም ባይ ናቸው ።
«የስደተኞች ቀውስ በመቄዶንያ ሰብዓዊ ቀውስ ማስከተል አለበት ? በባቡር ጣቢያው ዙሪያ የሚኖሩ ዜጎችን አነጋግሬ ነበር ። ምን እንደሚያስቡ እነርሱን ለምን አትጠይቋቸውም ? የአካባቢው ሰዎች እና ልጆቻቸው ከቤታቸው ለመውጣት ይፈራሉ ። የስደተኞቹ ሁኔታ ይሰማኛል ። ሆኖም በነርሱ ምክንያት ሃገራችን ችግር ውስጥ መውደቅ የለባትም ።»
መንግስት መቄዶንያን የስደተኞች መተላለፊያ ኮሪደር በማድረግ ዜጎችእንዳይሰቃዩ ለማድረግ ሞክራለች ።ስደተኞቹ ወደ ሰርቢያ የሚወስዳቸውን የሰሜኑን መስመር እንዲሁም በሃንጋሪ በኩል ወደ ደንበር አልባዎቹ የሸንገን ስምምነት አባል ሃገራት የሚወስዳቸውን መንገድ ታመላክታለች ። ሙሃመድም ይህንን መስመር መከተል ይፈልጋል ።ሆኖም ወደ ሰሜን የሚያመሩት ባቡሮች በቀን ሶስት ወይም አራት ጊዜ ብቻ ስለሚመጡ ምናልባት በታክሲ መሄድ ሳይኖርበት አይቀርም ።ፖሊስ አንዳንድ ስደተኞች ባቡር እንዲሳፈሩ ይረዳል እንጂ ሁሉንም አያግዝም ።
«ፖሊሶች ልጆች የያዙ ቤተሰቦችን ነው የሚረዱት እኔ እዚህ ምንም እድል የለኝም ።»
በባቡር ይሁን በታክሲ አለያም በአውቶብስ ከመቄዶንያዋ ግቭጌልያ የሚነሱ ስደተኞች በሙሉ የሚሄዱት ሜቄዶንያን ከሰርብያ ወደ ምታዋስነውታባኖቭke ወደተባለችው መንደር ነው ።የዚህች መንደር ነዋሪ ነዋሪ ቶኒ ስደተኞቹ ከዚያ በኋላ ወዴት እንደሚሄዱ ሲናገር
«ወደ እርሻዎች ገብተው ድንች ወይም ሌሎች ምግቦች ይሰርቃሉ ። ተርበዋል ።ነዋሪዎችን ግን አይተናኮሉም ።»
ቶኒ መፍትሄ የሚለውንም ተናግሯል ።
«አሜሪካኖች ሊወስዱዋቸው ይገባል ። ጀርመንና ፈረንሳይም ስደተኞቹን በአውሮፕላን ሰብበው ወደዚያ መላክ አለባቸው ። በመሠረቱ ሶሪያ ና ኢራቅ በሁሉም ስፍራ ጦርነት የጀመሩት አሜሪካውያን ናቸው ። »
ድምፅ
በታባኖቭክ ባቡር ጣቢያ አጠገብ UNHCR አነስተኛ የስደተኞች መጠለያ ሰርቷል ። ጥቂት የመጠለያ ድንኳኖች አሉ ። ሆኖም ብዙዎች እዚያ መቆየት አይፈልጉም ።ወደ ሰርቢያ ለመሻገር ወደዚያ iየሚወስደውን የባቡር ሃዲድ እየተከተሉ ያዘግማሉ ። ሰርቢያ በ500 ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚትገኘው ከሞሮኮ የመጣው ዛማን ውሃ ጠምቶታል ።ዛማን አቴንስ ግሪክ ነበር ።ግሪክ ውስጥ ለ4 ዓመታት ያለ ምንም ፈቃድ ቆይቷል ።አሁን ተስፋ የሚያደርገው ጀርመን ለመግባት ነው ።
« ግሪኮች በጣም ጥሩ ህዝቦች ናቸው ።ፖሊሶቻቸው ግን ዘረኞች ናቸው ። ጀርመን የምፈልገውን እንደማገን ተስፋ አለን ።ብዙም አልጠይቅም ።ጥሩ ሥራ ና የተረጋጋ ህይወት ነው የምፈልገው ።ይህን ነው ።ድንበሩን ለማቋረጥ በጥንቃቄ መንቀሳቀስ አለብኝ ።እንግዲህ እናያለን ።»
አሁን ሰደተኞቹ ሰርቢያ ድንበር ደርሰዋል ። ፖሊሶች የሰርቢያን ድንበር ይጠብቃሉ ። ስደተኞቹን ካገኙም አያሳልፉም ።ከጥቂት ዎይታ በኋላ ፖሊስ አካባቢው ለቆ ሲሄድ በየጥሳሻው የተደበቁ የአፍጋን ስደተኞች ከያሉበት በመውጣት ጉዞ ጀመሩ ።ፖሊስና ስደተኞች እንደ አይጥና ድመት ነው የሚጠባበቁት ።የሰርቢያ ዋና ከተማ ቤልግሬድ የአውቶብስና የባቡር ጣቢያዎች ተጨናንቀዋል ። እዚህም እዚያም ድንኳኖች ይታያሉ ። ሁሉም ከሃንጋሪ በጥቂት ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ወደምትገነው ወደ ሰሜን ሰርቢያዋ ሱቢቲካ የሚወስዳቸውን ባቡር ትኬት ለመግዛት የሚጠባበቁ ናቸው ።የ17 ዓመቱ አህመድ ከጓደኞቹ ጋር ከኢራቅ ነው የመጣው ። በሃገሩ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው በአረብኛ ዳይሽ የሚለው ቡድን የሚፈፅመውን ግፍ ያብራራል ።
« ዳኢሽ ካገኑህ አንገትህን ይቆርጡታል ። ለዚህ ነው ከኢራቅ የተሰደድነው ። ጀርመን ነው የምንሄደው እዚያ ዘና ብለን መኖር እንችላለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን ።»አህመድ የመጣው በቡልጋሪያ አድርጎ ነው ።እርሱ እንደሚለው እዚያ ፖሊሶች ደብድበው ገንዘቡንም ቀምተውታል ።
ቤልጌርድ የሚገቡ ስደተኞች አብዛኛው ህዝብ ይረዳቸዋል ።የስደትን ምንነትን በቅጡ የሚያውቁት ሰርቦች የሚበላ የሚጠጣ ያቀርቡላቸዋል ።ሁሉም ግን ያዝንላቸዋል ማለት አይደለም ።የትራፊክ ፖሊሶች ወደ ሰሜን የሚያመሩ ስደተኞችን የያዙ መኪናዎችን በማስቆም ከስደተኞቹ ገንዘብ እንደሚቀሙ ያዩ ይናገራሉ ።ፓሊስ እዚያ ለመቆየት ሳይሆን በሰርቢያ ለማለፍ የሚሞክሩ ስደተኞች ላይ መጨከኑ ብዙዎች ሊረዱት አልቻሉም ።ግን ስደተኞቹ ቀጥለው የሚገቡባት ሃንጋሪ እነርስune በማንገላታት ተወዳዳሪ ያልተገኘላት ሃገር ሆናለች ። ሃንጋሪ ስደተኞች እንዳይገቡባት 6 ሜትር ርዝመት ያለው አጥር ድንበር ላይ እየገነባች ነው ። ከድንበሩ በስተደቡብ ምዕራብ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አጥሩን ዘለው ለመግባት የሚጠባበቁ ሰዎች በአንድ አሮጌ የሸክላ ፋብሪካ ተሰባስበዋል ። ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተማረው ፓኪስታናዊው ሚላድ ከወላጆቹ ጋር እዚያ ይገኛል ። ።1500 ዩሮ ተክፍሎት ጀርመን የሚያደርስ ደላላ ስልክ እየጠበቀ ነው። ሚላድ እንዳለው ሰውዬው ገንዘቡን ለሚያሳልፋቸው የድንበር ፖሊስ ነው የሚሰጠው ።ስደተኞቹ የፕሮቴስታንት ቄስ የሚያመጡላቸውን ምግብ ከቀመሱ በኋላ ነው የሽቦውን አጥር ለመዝለል የሚሞክሩት ።ቄስ ቲቦር ቫርጋ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ስደተኞች አጥር ሊገድባቸው አይችልም ይላሉ ። ጋዜጠኛ ኒማንያ መቄዶንያ ያገኘችውን የሶሪያ ስደተኛ ሃንጋሪ አጥር እየገነባች ነውና አንተ ሃንጋሪ ድንበር እስከምትደርስ ተሰርቶ ቢያልቅ ምን ታደርጋለህ ስትል ጠይቃው ነበር ።
«ድንበር ለማቋረጥ ስል ፤ለመዝለል ፣ለመቁረጥ ፣ማንኛውንም ነገር ለማድረግ እሞክራለሁ ። »
ነበር መልሱ ።እስካሁን ትላለች ጋዜጠኛ ኒማንያ የሽቦ አጥር፣ አጋዘኖች ካሉበት እንዳይወጡ ለማድረግ ጠቃሚ መሆኑ ብቻ ነው የተረጋገጠው ። አሁን በሰርቢያዋ ሱቦታካ የሚገኙ ሱቆች ለአጥሩ መላ አግኝተውለታል ። በዚያ የአጥር መቁረጫ እንደ ጉድ እየተቸበቸበ ነው ።

Mazedonien - Flüchtlinge
ምስል Reuters
Mazedonien Flüchtlinge sterben in Unfall an Bahngeleisen nahe Veles
ምስል Reuters/O. Teofilovski
Ungarn errichtet Zaun an der Grenze zu Serbien
ምስል Reuters/L. Balogh
Mazedonien Migrant Chaos
ምስል picture-alliance/AP Photo/D. Vojinovic

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ