1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የስፖርት ሳይንሳዊ ስልጠና

ረቡዕ፣ መጋቢት 25 2011

ስፖርተኞች በሳይንሳዊ ስልጠና ታግዘው በክለቦችና በብሄራዊ ቡድኖች ለመሳተፍ ብቁ እንዲሆኑ የማሰልጠኛ ማዕከላት ወሳኝ ናቸው። በኢትዮጵያም መሰል ስልጠና የሚሰጡ በጣት የሚቆጠሩ ማዕከላት ወጣቶችን ለማፍራት እየሰሩ ነው።

https://p.dw.com/p/3GBbx
Äthiopien Addis Abeba Jugendsport Akademie
ምስል Alamrew Mamo

ሳይንሳዊ ስልጠና ስፖርተኛው ረጅም ጊዜ በስፖርቱ እንዲቆይ ያግዛል

ማሰልጠኛ ተቋማት፤ እንዲሁም የታዳጊ ወጣቶች የስፖርት ፕሮጀክቶች፣ ስፖርቱን ለማሳደግ ወሳኝ ናቸው።  ችሎታ ያላቸው ታዳጊ ወጣቶች በሳይንሳዊ ስልጠና ከታገዙ ክለቦችንና ብሄራዊ ቡድንን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።የታዳጊ እና የወጣት ፕሮጀክቶች ፣በዓለም አቀፍ ደረጃ  በተለይ  የታላላቅ የእግር ኳስ ክለቦች ስኬት መሰረት ናቸው። ለብሄራዊ ቡድኖች እና ለክለቦች ተተኪ የሚሆኑ ስፖርተኞችን ለማፍራት በታዳጊ ደረጃ ሳይንሳዊ ስልጠና መስጠት ውጤታማ እንደሚያደርግ ይታወቃል። በኢትዮጵያም መሰል ስልጠና የሚሰጡ በጣት የሚቆጠሩ ማዕከላት ወጣቶችን ለማፍራት እየሰሩ ነው። ሳይንሳዊ ስፖርት በኢትዮጵያ መተግበር የጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሆኑ ይነገራል። የስፖርት ባለሙያዎች ግን በሀገሪቱ ሳይንሳዊ ስፖርት በበበቂ ሁኔታ እየተተገበረ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ለመሆኑ ሳይንሳዊ ስፖርት ሲባል ምን ማለት ነው? በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስፖርት ሳይንስ ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዘሩ በቀለ ያብራሩልናል። «በተፈጥሮው የተሰጠውን ብቃት አውጥቶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የማድረስ ሂደት ነው። በተመጠነ መልኩ የሚሰጡ የስልጠና ግብዓት አሉ። እያንዳንዱ ልጅ በየትኛው ዕድሜ ክልል ለየትኛው ስፖርት በየትኛው የሰውነት አቋም በሚል የአሰራር ስርዓት ይኖሩታል ። ለአትሌቱ መጥኖና አስተካክሎ በስነ ምግብ ባለሙያ፣ በአሰልጣኞች፣ በአካል ብቃት ባለሙያዎች፣ በስነ ልቦና ባለሙያዎች ተመጥኖና እየተመዘገበ በስልጠና ወቅት እየታየ የጎደለውን በልምምድ እያሳተፈ የሚኬድበት ስርዓት ነው።» ሳይንሳዊ ስልጠና ስፖርተኛው ረጅም ጊዜ በስፖርቱ ውስጥ እንዲቆይ ያግዛል ይላሉ አቶ ሳሙኤል ስለሺ በአዲስ አበባ ዩኒበርስቲ የስፖርት ስነ ልቦና መምህር። «ስልጠናዎቹ እንደስፖርት ዓይነቱ ይለያያል። ሳይንስ ነው የሚያስብለው ይሄ ስፖርተኛ ፈጣን ነው፤ ወይም ደካማ ነው የሚለውን በአይን አይተን ከምንወስን ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በስልጠናው የተሻለ ውጤታማ ማድረግ ይሆናል።»  በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የአፍሪቃ እግርኳስ ፌደሬሽን በምህጻሩ ካፍ ኢንስትራክተር አለባቸው ተገኝ ደግሞ ሳይንሳዊው ስልጠና በተገቢው መንገድ እንዳይሰጥ እንቅፋቶች አሉ ይላሉ። «እኛ ሀገር አሰልጣኙ ነው እየሰጠ ያለው። የአሰልጣኞቹ ያላቸው ችሎታ ወይም የስልጠና ብቃት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው። ሳይንሳዊ ስልጠና በተገቢው መንገድ እንዳይሰጥ እንቅፋት ሆኗል ብዮ እገምታለሁ።» «የሀገራችን እግር ኳስ የይድረስ የድረስ ነው ክፍተትም አለው» የሚሉት ደግሞ አሰልጣኝ ስዩም አባተ ናቸው። ስዩም አባተ የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ናቸው።  «ሳይንሳዊ ስልጠና በተግባር ለመተርጎም ከልጅነት ጀምሮ የሚከናወን ነው። እግር ኳስ ቴክኒክ ፣ ታክቲክ ፣ የአካል ብቃት፣ ስነ ልቦና እነዚህ ስልጠናው የሚጀምረው ከወጣትነት ጀምሮ ነው። ምን ያህል ተሰራ የሚለው ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም ስርዓቱን ተከትሎ እየሄደ ነው ለማለት አያስደፍረኝም።» አቶ ተሾመ ከበደ «በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል»ና በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ናቸው። በሁለቱ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት የሚሰጡትን ስልጠናዎች ሳይንሳዊ ለማድረግ እየተሞከረ እንደሆነ ነው የገልጹልን።  «በሁለቱ የማሰልጠኛ ማዕከላት የሚሰጠው የአትሌቲክስ ስልጠና በተቻለ መጠን በሀገራችን ከሚሰጠው የተሻለ ይዘት አለው ብዮ ነው የማስበው። ሳይንሳዊ መገለጫዎቹም በተቻለ መጠን ተግባራዊ ለማድረግ እየጣረ ነው። መሳሪያዎች ይጎሉናል። ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እናደርጋለን ማለት ሳይሆን እየተሞከረ ነው።» በስፖርቱ አገርን የሚወክሉ ተተኪ ወጣቶችን ማፍራት ሁሉም የሚስማማበት ጉዳይ ነው። ታዳጊዎች ላይ መስራት ከስፖርቱ የሚገኘውን ገቢ ይጨምራል፡፡ ሳይንሳዊ ስልጠናንም ለመተግበር የስፖርት መሰረተ ልማቶች እና የማሰልጠኛ ቁሳቁሶችን ማሟላት ይጠበቃል እንደባለሙያዎች አተያይ፡፡ ከዚህ ሌላ የስፖርት ማሰልጠኛ ተቋማት አካዳሚዎች የታዳጊና ወጣት ፕሮጀክቶች በቅንጅት መንቀሳቀሳቸውም አስፈላጊ ይሆናል፡፡

ነጃት ኢብራሂም

ኂሩት መለሰ