1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ፤ ሐምሌ 6 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

ሰኞ፣ ሐምሌ 6 2007

የሪያል ማድሪዱ ግብ ጠባቂ ኢከር ካሲያስ ከልጅነት ዘመኑ አንስቶ ይጫወትበት ከነበው ቡድን በእንባ ተውጦ ተሰናብቷል። የኢትዮጵያና የካሜሩን የሴቶች እግር ኳስ ቡድኖች ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተጋጥመው ያለ ግብ ተለያይተዋል። በማድሪዱ የዓለም አትሌቲክስ የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊው አብዲዋቅ ቱራ አሸንፏል።

https://p.dw.com/p/1Fy3h
Tour de France 2015 Samuel Sanchez mit Team
ምስል Getty Images/B. Lennon

የስፖርት ዘገባ፤ ሐምሌ 6 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች እግር ኳስ ተጫዋቾች በሚሳተፉበት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የሴቶች ውድድር ኢትዮጵያ እና ካሜሩን ያለምንም ግብ ተለያዩ። ሁለቱ ቡድኖች ትናንት ካሜሩን ያውንዴ ውስጥ ያከናወኑትን ጨዋታ ለመመልከት መግቢያ በነፃ እንደነበር ተጠቅሷል። ሆኖም የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌፌሬሽን እንደገለጠው ከሆነ ከቡድኑ ጋር አብረው ከተጓዙ የፌዴሬሽኑ ሠራተኞች በስተቀር አንድም ደጋፊ በስቴዲየሙ ውስጥ አልተገኘም። መሰል ጨዋታዎች ሲከናወኑ ኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ ደጋፊዎች ወደ ስቴዲየሞች ቢመጡ ለቡድኑ የበለጠ ብርታት ሊሰጠው ይችላል። በኢትዮጵያ እና ካሜሩን እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል የመልስ ጨዋታው የፊታችን ዓርብ ሣምንት ኢትዮጵያ ውስጥ ይከናወናል።

ስፔን ማድሪድ ውስጥ ቅዳሜ ዕለት በተከናወነ የ3000 ሜትር የሩጫ ሽቅድምድም ኢትዮጵያዊው አብዲዋቅ ቱራ በአንደኛነት ማጠናቀቁ ተዘግቧል። አብዲዋቅ ውድድሩን ለመፈጸም የፈጀበት ጊዜ 7:52:04 ነበር። በሀገሩ ምድር የሮጠው ስፔናዊው አዴል ሜሻል በ12 ማይክሮ ሠከንድ ተቀድሞ ሁለተኛ ሆኗል። የዩናይትድ ስቴትሱ ኪዬል ሜርበር በ7:52:95 ሦስተኛ ገብቷል።

Tour de France 2011 Getty
ምስል Getty Images

በማድሪዱ ውድድር በ100 ሜትር የአጭር ርቀት ሩጫ የዩናይትድ ስቴትሱ ማይክ ሮጀርስ በ9 ሠከንድ ከ88 ማይክሮ ሠከንድ አንደኛ ወጥቷል። የጃማይካው አንድሪው ፊሸር በ9 ሠከን ከ94 ማይክሮ ሠከንድ ሁለተኛደረጃ አግኝቷል። ሌላኛው የዩናይትድ ስቴትስ ሯጭ በ10 ሠከንድ ከ04 ማይክሮ ሠከንድ ሦስተኛ ሆኖ አጠናቋል።

ብስክሌት

በቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም 9ኛ ደረጃ ውድድር ትናንት የ BMC ቡድንን ወክሎ ይጋልብ የነበረው የነበረው የዩናይትድ ስቴትሱ ቴጃይ ቫን ጋርደርን በአንደኛነት አጠናቋል። ቴጃይ 28 ኪሎ ሜትሩን በብስክሌት ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 32 ደቂቃ፣ ከ15 ሠከንድ ነው። የብሪታንያው ብስክሌተኛ ክሪስቶፈር ፎሮሜ በአንድ ሰከንድ ተቀድሞ ሁለተኛ ወጥቷል። እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር በ2013 በተኪያሄደው የብስክሌት ሽቅድምድም አጠቃላይ ድምር ውጤት አሸናፊ የነበረው ክሪስ «ስካይ» ቡድንን ወክሎ ነው የተሰለፈው።

በቱር ደ ፍሯንስ ብስክሌት ሽቅድምድም ከአጠቃላዩ 9 ደረጃዎች በተሰበሰቡ ነጥቦች የሚመራው ክሪስቶፈር ፎሮሜ ነው። ክሪስቶፈር የተወለደው ምሥራቅ አፍሪቃ ኬንያ ውስጥ ነው። እንደ ረዥም እና ማራቶን ሩጫ ወደፊት የምሥራቅ አፍሪቃ ብስክሌተኞች በዓለም መድረክ ወደፊት ወርቃማ ዕድል አላቸው ሲል ተናግሯል። የኤርትራ ብስክሌተኞች ዳንኤል ተክለሃይማኖት እና መርሐዊ ቅዱስ በቱር ደ ፍሯንስ ውድድር የደቡብ አፍሪቃውን MTN Qhubeka ወክለው በመሣተፍ ላይ ይገኛሉ። በአጠቃላይ የ9ኝ ደረጃ ውጤት ከ185 ብስክሌተኞች ኤርትራዊው ዳንኤል ተክለሃይማኖት 109ኛ ላይ ይገኛል። ሌኛው ኤርትራዊ መርሐዊ ቅዱስ አጠቃላይ ውጤቱ ተደምሮለት እስካሁን የሚገኝበት ደረጃ 165ኛ ነው።

በእርግጥም የምሥራቅ አፍሪቃ ብስክሌተኞች በዓለም አቀፍ መድረክ እንደ መካከለኛ እና የረዥም ርቀት የሩጫ ውድድር ሁሉ ብርታታቸውን እያሳዩ ነው። በቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም አቀበት በመውጣት ብርታት ዳንኤል ተክለሃይማኖት ከተፎካካሪዎቹ በልጦ 4 ነጥብ አስመዝግቧል። ዘንድሮ በአፍሪቃ በተኪያሄደው የብስክሌት ሽቅድምድም ደግሞ ኢትዮጵያ በግል ወርቅ ማግኘቷን ብስክሌት ፌዴሬሽን ገልጧል።

Frankreich Tour de France 2015 8. Etappe
ምስል Getty Images/D. Pensinger

በኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን የውድድር እና የተሳትፎ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሞላ ተፈራ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በብስክሌ ሽቅድምድም ዘንድሮ በአፍሪቃ ጠንካራ ተወዳዳሪ እንደነበች ተናግረዋል። ከዚያም ባሻገር ለቱር ደ ፍሯንስ ውድድር ባይሰለፍም በደቡብ አፍሪቃው MTN Qhubeka ቡድን ውስጥ ኢትዮጵያዊው ብስክሌተኛ ጥጋቡ ገ/ማርያም ይገኝበታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በብስክሌት ውድድር ከአፍሪቃ ባሻገር ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ብቅ ማለት ያልቻለችው በቅሳቁስ አቅርቦት ችግር እንደሆነ አቶ ሞላ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን የጽ/ ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አበበ ድረስ በበኩላቸው ከቁሳቁስ ባሻገር ለፌዴሬሽኑ የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆኑም ተወዳዳሪዎች በዓለም አቀፍ መድረክ ብቅ እንዳይሉ ተግዳሮት መፍጠሩን ተናግረዋል። አንድ ብስክሌት ለመግዛት ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ እንደሚፈጅባቸው የጠቀሱት ኃላፊው የሚመደብላቸው በጀት በቂ እንዳልሆነ ገልጠዋል።

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን በ1942 ዓም እንደተመሠረተ እና በአሁኑ ወቅት 14 ቡድኖችን እንዳቀፈ የፌዴሬሽኑ የውድድር እና የተሳትፎ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሞላ ተፈራ ተናግረዋል።

የሜዳ ቴኒስ

በሜዳ ቴኒስ ውድድር ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች ትናንት ለሦስተኛ ጊዜ የዊምብልደን ዋንጫ ባለድል ሆነ። ኖቫክ ከዚህ ቀደም እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር በ2011 እና በ2014 የዌምብልደን ውድድር አሸናፊ ነበር። ትናንት ለሦስተኛ ጊዜ 6:4 እና 6:3 በሆነ ውጤት ያሸነፈው የስዊዘርላንዱን ጠንካራ ተፎካካሪ ሮጀር ፌዴረርን በመርታት ነው። ሮጀር በዓለም ደረጃ ለስምንተኛ ጊዜ አሸናፊ ለመሆን ትናንት ይዞት ወደ ሜዳ የገባው ተስፋ በኖቫክ ባክኖ ቀርቷል።

England Tennis Wimbledon Novak Djokovic
ምስል Getty Images/C. Brunskill

በሴቶች የዌምብልደን የሜዳ ቴኒስ ጨዋታ ደግሞ አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስ ለስድስተኛ ጊዜ ትናንት በማሸነፍ ጠንካራ ስፖርተኛነቷን አስመስክራለች። ከዌምብልደኑ ድል ባሻገር ሴሬና በሜዳ ቴኒስ የውድድር ዘመኗ ለ21 ጊዜያት አሸንፋለች። ቅዳሜ ዕለት ሁለቱንም ዙር 6:4 በሆነ ውጤት ያሸነፈችው የስፔኗ ጋርቢነ ሙኩሩዛን ነው።

ቡጢ

የጀርመኑ ቡጢኛ ፍራንቼስኮ ፒያኔታ ጀርመን ለ83 ዓመታት ስጠብቀው የነበረውን የከባድ ሚዛን ቡጢ ፍልሚያ ድል ማሳካት ሳይችል ቀረ። ጀርመን በከባድ ሚዛን ቡጢ ቀበቶ ያገኘችው እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር በ1932 ነበር። ከዛሬ 10 ዓመት በፊት በ99 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ቡጢኛ ማክስ ሽሜሊንግ ነበር የዛሬ 83 ዓመት ለጀርመን የከባድ ሚዛን ቀበቶ ድል አስገኝቶ የነበረው። ከጣሊያን ስደተኛ ወላጆች ጀርመን ውስጥ የተወለደው ፍራንቼስኮ ከትናንት በስትያ ከ37 ዓመቱ የኡዝቤክስታኑ ቡጢኛ ሩስላን ሻጋዬቭ ጋር ጀርመን ውስጥ ባደረገው ፍልሚያ በመጀመሪያው ዙር በዝረራ ተሸነፏል። ጀርመን ሐምቡርግ ውስጥ ነዋሪ የሆነው የኡዝቤክስታኑ የከባድ ሚዛን ቡጢ ተፋላሚ ሩስላን ሻጋዬቭ «ነጩ ታይሰን» በሚል ቅጽል ነው የሚጠራው። የሩስያው እጅግ ግዙፍ ቡጢኛ ኒኮላይ ቫሉቬን እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር በ2007 ዓም በነጥብ በማሸነፍ የዓለም ከባድ ሚዛን ቀበቶን በእጁ ያስገባው ሩስላን ሻጋዬቭ በ2009 ለመጀመሪያ ጊዜ የተረታው በክሊችኮ ነበር። በ2011 ደግሞ በአሌክሳንደር ፖቬትኪን ከመሸነፉ ውጪ «ነጩ ታይሰን» በስድስት ተከታታይ ፍልሚያዎች የሚረታ አልተገኘም።

Deutschland Fußballer Bastian Schweinsteiger
ምስል picture-alliance/dpa/M. Müller

የእግር ኳስ ተጨዋቾች የዝውውር ዜና

የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙይንሽን አማካይ ባስቲያን ሽቫይንሽታይገር ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ያደረገው ዝውውር ተጠናቆ ዛሬ ለሦስት ዓመታት ውል መፈረሙ ታውቋል። ከጀርመን ብሔራዊ ቡድን አንበሉ የ30 ዓመቱ ባስቲያን ባሻገር ማንቸስተር ዩናይትድ የሳውዝ ሐምፕተኑ አማካይ ሞርጋን ሽናይደርሊን በ34,8 ሚሊዮን ዶላር እንዳስፈረመ ተዘግቧል። አማካዩ ሞርጋን የፈረንሣይ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ አዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የሆላንዱ አጥቂ ቫን ፔርሲ ከኦልትራፎርድ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ቱርኩ ፌኔርባኅ ለማቅናት ተሰናድቷል ተብሏል። ቫን ፔርሲ ነገ ለቱርኩ ፌኔርባኅ ይፈርማል ተብሏል።

የሪያል ማድሪዱ ግብ ጠባቂ ኢከር ካሲያስ ከልጅነት ዘመኑ አንስቶ ይጫወትበት ከነበው ቡድን በእንባ ተውጦ ተሰናብቷል። የ34 ዓመቱ ግብ ጠባቂ ከቡድኑ እንዲወጣ የሪያል ማድሪድ ፕሬዚዳንት ግፊት አድርገዋል መባሉን ዛሬ አስተባብለዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ