1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 17 2008

ማንቸስተር ሲቲ ከባድ ሽንፈት ገጥሞታል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከታች ባደገ ቡድን ነጥብ ጥሏል። በስፔን ላሊጋ ቪላሪያል ኃያላኑ ሪያል ማድሪድና ባርሴሎናን ቀድሞ በደረጃ ሠንጠረዡ ከላይ ጉብ ብሏል። በጃፓኑ የመኪና ሽቅድምድም ልዊስ ሐሚልተን አሸንፏል። የፊፋው ሴፕ ብላተር ላይ ጫናው አይሏል፤ የሙስና ቅሌቱ በሚሼል ፕላቲኒ ላይም እያንዣበበ ነው።

https://p.dw.com/p/1Geuc
Fußballspieler Pierre-Emerick Aubameyang
ምስል Reuters/I. Fassbender

የስፖርት ዘገባ፥ መስከረም 17 ቀን 2008 ዓ.ም.

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዘንድሮ አጀማመሩ ላይ ካሳየው ግስጋሴ ገታ ያለ ይመስላል። የቀድሞው አሠልጣኝ ዬርገን ክሎፐን በተኳቸው ቶማስ ቱሽል የሚመራው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በዚህ የውድድር ዘመን ከሦስት ግብ ባነሰ ልዩነት ላለማሸነፍ ቆርጦ የተነሳ ይመስል ነበር። ይህ ቁርጠኝነት ግን እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ ብቻ ነው የዘለቀው። ዘንድሮ ደካማ ሆኖ በደረጃ ሠንጠረዡ ከታች ከሚገኘው ሆፈንሀይም ጋር ባለፈው ሳምንት አንድ እኩል አቻ ተለያይቷል።

በእርግጥ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአዲሱ አሠልጣኝ ቶማስ ቱሽል አመራር እስካሁን ባደረጋቸው 13 ግጥሚያዎች አንድም ጊዜ አልተሸነፈም። ከታች ወደ ቡንደስሊጋው ካደገው ዳርምሽታድት ጋር ትናንት ባደረገው ጨዋታ ሁለት እኩል በመለያየት ነጥብ ተጋርቷል። የቱርክ ዝርያ ያለው የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አማካኝ ኢካይ ጉዊንዶዋን ዳርምሽታድት ጠንካራ ተፎካካሪ እንደነበር ገልጧል።

«ለእኛ እጅግ ሲበዛ መራራ ሽንፈት ነው፤ ምክንያቱም በሁለተኛው አጋማሽ በጣም እልህ አስጨራሽ ጨዋታ ነበር። ዳርምሽታድቶችም ቢሆኑ እጅግ በቆራጥነት እየተጫወቱ በጥንካሬ ተከላክለዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም ማድረግ ባንችልም በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ለመጫወት ሞክረናል። ግን በመጨረሻው ሰአት እጅግ በሚያናድድ መልኩ ስጦታ ነው ያበረከትንላቸው። ድል ነው ከእጃችን ያመለጠው።»

ዶርትሙንድ አቻ ሲለያይ ይህ ሁለተኛው ሆኖ ተመዝግቦበታል። ከታች ያደገው ዳርምሽታድት እስካሁን እጅ የሰጠው ለባየርን ሙይንሽን ብቻ ነው።

የቦሩስያ ዶርትሙንድ ቶማስ ቱሸል
የቦሩስያ ዶርትሙንድ ቶማስ ቱሸልምስል Getty Images/Bongarts/A. Grimm

ባየር ሙይንሽን ከትናንት በስትያ ባየር ሌቨርኩዘን፤ ቬርደር ብሬመንን ባሸነፈበት የግብ መጠን ማይንትዝን ሦስት ለምንም በመሸኘት የደረጃ ሠንጠረዡን ተቆጣጥሮታል። ለሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታውን ከክሮሺያው ዲናሞ ዛግሬብ ጋር ማክሰኞ በሜዳው የሚያካሂደዉ ባየር ሙይንሽን 21 ነጥብ በመሰብሰብ በቡንደስ ሊጋው አንደኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። ባለፈው ሳምንት በግብ ልዩነት ብቻ ከሥሩ አድርጎት የነበረው ቦሩስያ ዶርትሙንድን አሁን በሦስት ነጥብ በልጦታል። የሁለቱ ቡድኖች የሚቀጥለው እሁድ ፍልሚያ በብዙዎች ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። ጨዋታው በባየር ሙይንሽን አሊያንስ አሬና ስታዲየም ይካሄዳል።

ሐምቡርግን በአንድ ብቸኛ ግብ ያሸነፈው ሻልከ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 16 ነጥብ አለው። ሆፈንሀይም አውስቡርግን እንዲሁም ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ሽቱትጋርትን 3 ለ1 አሸንፈዋል። ቅዳሜ ዕለት ሐኖቨር ከቮልፍስቡርግ እንዲሁም ትናንት ሔርታ ቤርሊን ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር አንድ እኩል በመለያየት ነጥብ ተጋርተዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታ፦ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያ ሽንፈቱን የቀመሰው ማንቸስተር ሲቲ የውድድር ዘመኑ ከተጀመረ ለሁለተኛ ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል። የማንቸስተር ሲቲ የቅዳሜው ዳግም ሽንፈት ለደጋፊዎቹ መሪር የሚባል ነው። በቶትንሐም ሆትስፐር 4 ለ1 በሆነ ሰፊ ልዩነት የተረታው ማንቸስተር ሲቲ ለስድስት ሣምንታት ተቆጣጥሮት የነበረውን የደረጃ ሠንጠረዥ ገስግሶ ለመጣው ጎረቤቱ ማንቸስተር ዩናይትድ አስረክቧል።

በቅዳሜው ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ በደረሰበት ከባድ ሽንፈት ሲሸማቀቅ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ሰንደርላንድን 3 ለ0 በሆነ የሰፋ ልዩነት ድል በመንሳት ተኮፍሷል። ለማንቸስተር ዩናይትድ የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ ሰአት አልቆ በተጨመረው 4ኛው ደቂቃ ላይ ሜምፊስ ዴፔይ የመጀመሪያዋን ግብ አስቆጥሯል። ዋይኔ ሩኒ በ46ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ከመረብ አሳርፏል። ሦስተኛዋን የማሳረጊያ ግብ በ90ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጁዋን ማታ ነው።

ሊቨርፑል በጄምስ ሚልነር እና በዳንኤል ስቱሪጅ ሁለት ግቦች አስቶን ቪላን 3 ለ 2 በመርታት ብዙም አለመራቁን አሳይቷል። በፕሬሚየር ሊጉ የሣምንቱ ማሳረጊያ ጨዋታዎች እንደ አርሰናል በግብ የተንበሸበሸ ቡድን የለም።

ሌስተር ሲቲን 5 ለ2 በማሸነፍ የግብ ጎተራ አድርጎታል። ሌስተር ሲቲ በጃሚ ቫርድሊ ግብ መሪነቱን ይዞ ነበር። ሆኖም የመጀመሪያዋ ግብ ከተቆጠረች ከ5 ደቂቃ በኋላ አርሰናልን አቻ የምታደርገዋን ግብ በ18ኛው ደቂቃ ቴዎ ዋልኮት ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። አሌክሲስ ሳንቼዝ በ33ኛው፣ 57ኛው እና 81ኛው ደቂቃዎች ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሔትሪክ ሠርቷል። ኦሊቨር ጂሮች መደበኛ ጨዋታው ተጠናቆ በባከነው 3ኛ ደቂቃ ላይ 5ኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል። ለሌስተር ሲቲ ሁለተኛዋንም ግብ በ89ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ጃሚ ቫርድሊ ነው።

የጆዜ ሞሪኒሆ ቸልሲ ግን በነጥብ ከማንቸስተር ዩናይትድ በእጥፍ አሽቆልቁሏል። ቅዳሜ ዕለት ከኒውካስል ጋር ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። ሳውዝሐምፕተን ስዋንሲ ሲቲን 3 ለ1 ማሸነፍ ችሏል። ቦርንመስ በስቶክ ሲቲ 2 ለ1 ተሸንፏል። ዌስትሐም ዩናይትድ እና ኖርዊች ሲቲ ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል። ትናንት ክሪስታል ፓላስ ዋትፎርድን 1 ለባዶ ረትቷል።

በዚህም መሠረት የደረጃ ሰንጠረዡን ማንቸስተር ዩናይትድ በ16 ነጥብ ይመራል። ማንቸስተር ሲቲ በ15 ይከተላል። አርሰናል 13 ነጥብ አለው ግን በዌስትሐም ዩናይትድ በግብ ክፍያ ተበልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ ነው። ሊቨርፑል በ11 ነጥብ ስምንተኛ፣ ቸልሲ በስምንት ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ናቸው። በቸልሲ በ6 ነጥብ የሚበለጠው ሰንደርላንድ የደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ 20ኛ ላይ ይገኛል። ዛሬ ከሊቨርፑል በአንድ ደረጃ ዝቅ የሚለው ኤቨርተን ከቸልሲ በአንድ ደረጃ ከፍ ከሚለው ዌስት ብሮሚች አልቢኖ ጋር ይጋጠማል።

በስፔን ላሊጋ ቅዳሜ እለት ባርሴሎና ላፓልማን 2 ለ1 አሸንፏል። ሪያል ማድሪድ ከማላገ ጋር ያለምንም ግብ ነጥብ ተጋርቷል። ትናንት ዴፖርቲቮ ላኮሩና ኤስፓኞላን እንዲሁም ጌታፌ ሌቫንቴን በተመሳሳይ 3 ለምንም ድል አድርገዋል። የደረጃ ሠንጠረዡን ቪላሪያል በ16 ነጥብ ይመራል። ባርሴሎና 15 ነጥብ አለው፤ ሁለተኛ ነው። ሪያል ማድሪድ በ14 ነጥብ ይሰልሳል። የባርሴሎናው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ ግራ ጉልበቱ ላይ በደረሰበት አደጋ ለሚቀጥሉት 7 እና 8 ሣምንታት እንደማይሰለፍ ተገልጧል።


የመኪና ሽቅድምድም
በጃፓኑ የፎርሙላ አንድ መኪና ሽቅድምድም ትናንት የብሪታንያው ልዊስ ሐሚልተን በመርሴዲስ አሸናፊ ሆኗል። የፌራሪ አሽከርካሪው ጀርመናዊ ኒኮ ሮዝበርግ ሁለተኛ ሲሆን፤ ሌላኛው የፌራሪ አሽከርካሪ ፊንላንዳዊ ኪም ራይኮነን ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።

የሜዳ ቴኒስ
በሜዳ ቴኒስ የውሃኑ የሴቶች ፉክክር ሠርቢያይቱ የሌና ያንኮቪች የብሪታንያዋ ሔተር ዋትሰንን 6 ለ3፣ 2 ለ6 እና 6 ለ3 አሸንፋታለች። በወንዶች የዓለም የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ሠርቢያዊው ኖቫክ ጅኮቪች በነጥብ እየመራ ነው። የስዊትዘርላንዱ ሮጀር ፌዴሬር ይከተለዋል። የብሪታንያው አንዲ ሙራይ ሦስተኛ ነው።

የቦሩስያ ዶርትሙንዱ ጋቦናዊው ፒዬር ኤመሪክ አውባሜንያንግ በ7 የቡንደስ ሊጋ ተከታታይ ጨዋታዎች በሁሉም ግብ በማስቆጠር የቡንደስሊጋውን ክብር-ወሰን ሰብሯል። እስካሁን በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁሉም ግብ በማስቆጠር ክብርወሰን ይዘው የነበሩት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1994 ፍሬዲ ቦቢች እና በ2009 ሽቴፋን ኪስሊንግ ነበሩ። ቡንደስ ሊጋውን ግን በአሁኑ ወቅት በ10 ግቦች የሚመራው የባየር ሙይንሽኑ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ነው። ጋቦናዊው ፒየር በ9 ግቦች ይከተላል። ሌላኛው የባየር ሙይንሽኑ ቶማስ ሙይለር 6 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል።

ትናንት ጀርመን በርሊን ከተማ ውስጥ በተከናወነው 42ኛው የበርሊን ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኬንያውያን በወንድም በሴትም አሸናፊ ሆነዋል። ኢትዮጵያውያቱ አበሩ ከበደ እና መሠረት ኃይሉ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል። በወንዶች የበርሊን ማራቶን ሩጫ ሦስተኛ የወጣው ኢትዮጵያዊው ፈይሳ ሊሌሳ ነው።

የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን በእንግሊዘኛ ምኅጻሩ FIFA ፕሬዚዳንት የ79 ዓመቱ ሴፕ ብላተር ገቡበት የተባለው የሙስና ቅሌት በፍጥነት ከሥልጣናቸው ሊያስነሳቸው ሳያስገድዳቸው እንዳልቀረ ተገለጠ። ሴፕ ብላተር የካቲት ወር ላይ ሥልጣን እንደሚለቁ ቀደም ሲል ተገልጧል። የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ፈረንሣዊው ሚሼል ፕላቲኒም የዛሬ አራት ዓመት ግድም ከሴፕ ብላተር 2 ሚሊዮን ዶላር ተቀብሏል የሚል ቅሬታ ቀርቧል የፊፋው ፕሬዚዳንት ለሚሼል ፕላቲኒ የተሰጠው የሦስት ዓመት አገልግሎት ድጎማ እንጂ የሙስና ድርጊት አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል።

የ79 ዓመቱ ሴፕ ብላተር
የ79 ዓመቱ ሴፕ ብላተርምስል picture alliance/empics
በመርሴዲስ ተሽከርካሪው ያሸነፈው ሌዊስ ሐሚልተን
በመርሴዲስ ተሽከርካሪው ያሸነፈው ሌዊስ ሐሚልተንምስል Getty Images/Clive Mason
የቸልሲው አሠልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ
የቸልሲው አሠልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆምስል AP
የማንቸስተር ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒ
የማንቸስተር ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒምስል Reuters/C. Recine

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ