1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ፤ ነሐሴ 4 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

ሰኞ፣ ነሐሴ 4 2007

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሣምንት ጨዋታዎች አርሰናል እና ቸልሲ አልቀናቸውም። አንደኛው ነጥብ ሲጥል ሌላኛው ሽንፈትን ቀምሷል። ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ዩናይትድ ጅማሬያቸው ሰምሯል። በለንደን ማራቶን የሦስተኛ ደረጃን አግኝታ የነበረችው ኢትዮጵያዊት አትሌት ከዓመታት በኋላ አንደኛነቱ እንደሚገባት ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/1GCy4
ምስል Reuters

[No title]

ሩስያዊቷ የወርቅ ሜዳሊያውንም የተሸለመችውንም ገንዘብ ሽልማቱ ለሚገባት ኢትዮጵያዊቷ ሯጭ እንድትመልስ ተወስኗል። አትሌቷን ደውለን አነጋግረናታል። በአትሌቲክስ ዙሪያ ትንታኔ የሚሰጥ የስፖርት ጋዜጠኛም የሚለን ይኖረናል።

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሰለፈች መርጊያ ከአምስት ዓመት በፊት በተኪያሄደው የለንደን ማራቶን አሸናፊ መኾኗ ሰሞኑን ተዘግቧል። በወቅቱ አሸናፊ የነበረችው ሩስያዊቷ አትሌት ሊሊያ ሾባኮቫ አንደኛ የወጣችው ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ አበረታች መድሃኒት ተጠቅማ ነው ተብሏል። ከዓመታት በኋላም ቢሆን የአንደኛነት ማእረጉ የሚገባው ለኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሰለፈች መርጊያ ነው ተብሏል።

Symbolbild Leichtathletik Laufen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

ነገሩ የተከሰተው የዛሬ አምስት ዓመት ለንደን ማራቶን ላይ ነው። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2010 የለንደን ማራቶን አትሌት አሰለፈች መርጊያ ከባድ ፉክክር አድርጋ ነበር። በወቅቱ ሩስያውያቱ ተፎካካሪዎች ኃያል ሆነው የአንደኛነቱን እና የሁለተኛነቱን ደረጃ ተቆጣጠሩት። ሁለተኛ የወጣችው አትሌት ውጤት የተሰረዘው በዓመቱ ነበር።አንደኛ ወጥታ የነበረችው ሊሊያ ሾባኮቫ ደግሞ ከዚህ ቀደም ያሸነፈቻቸው ውጤቶቿ ተቀምቶ ለተለያዩ አትሌቶች እንደሚሰጥ ሰሞኑን ተዘግቧል። ጋዜጠኛ ብዙአየሁ ዋጋው ለሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ አውታሮች በተለይ በአትሌቲክስ ስፖርት ዙሪያ ይዘግባል። ሊሊያ ሾባኮቫ በቺካጎና ለንደን በተከታታይ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶቿ ተነጥቆ ለሌሎች አትሌቶች መሰጠቱ አይቀርም ብሏል።

በለንደኑ ማራቶን ሁለተኛ ወጥታ የነበረችው ሩስያዊት ኢንጋ አቢቶቫ አበረታች መድሃኒት ተጠቅመሻል ተብላ የሁለተኛነቱን ደረጃ የተነጠቀችው ውድድሩ በተከናወነ በዓመቱ ነበር። አሰለፈች መርጊያ ያኔ ከሦስተኛ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችላ ነበር። አትሌት አሰለፈች መርጊያ የዛሬ አምስት ዓመት የሆነውን መለስ ብላ ታስታውሳለች።

Symbolbild Doping
ምስል AP

የጸረ- አበረታች መድሐኒት ድርጅት ከሰሞኑ በርካታ አትሌቶች ኃይል ሰጪ መድሐኒት ተጠቅመው ባገኙት ብርታት ነው ሊያሸንፉ የቻሉት ሲል ዘገባ አውጥቷል። በዚህም መሠረት በለንደኑ ማራቶን አንደኛ ወጥታ የወርቁን ሜዳሊያ አጥልቃ የነበረችው ሌላኛዋ ሩስያዊት ሊሊያ ሾባኮቫ በወቅቱ እሷም አንደ ሀገሯ ልጅ አበረታች ንጥር ተጠቅማለች በሚል የአንደኝነት ማዕረጓ ሊነጠቅ እንደሆነ ተዘግቧል። አትሌት አሰለፈች መርጊያ በለንደኑ ማራቶን ይገባት የነበረውን የአንደኛነት ደረጃ በሩስያውያኑ አትሌቶች ማጭበርበር በመነጠቋ በርካታ ዕድሎችን ነው ያጣችው።

ጋዜጠኛ ብዙአየሁ ዋጋው ሩስያዊቷ አትሌት የማይገባትን የአንደኛነት ማዕረግ በሕገ-ወጥ መንገድ ብትወስድም ገንዘቡን ለማስመለስ ግን ብዙ ውጣ ውረድ እንደሚኖረው ጠቅሷል። አትሌት አሰለፈች መርጊያ ይኽን ዜና ከሰማችበት ቅጽበት አንስቶ ምንም ያደረገችው ነገር እንደሌለ ገልጣለች።

London Marathon 2013 Sicherheitsmaßnahmen
ምስል DW/K. McKinnon

በዚህ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የሜዳሊያ ክብሩንም የሚገባትን የገንዘብ ሽልማትም እንድታገኝ የበኩላቸውን ጥረት ሊያደርጉ ይገባል እንላለን። ከሰሞኑ የወጣው መረጃ የተከለከሉ አበረታች መድሃኒቶችን ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን ጨምሮ አፍሪቃውያን አትሌቶችም ሳይጠቀሙ እንዳልቀሩ አትቷል። ከዚህ ቀደም ቁጥራቸው አምስት የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አበረታች መድሃኒት ተጠቅማችኋል በሚል የተላለፈባቸውን ቅጣት እንደጨረሱ ጋዜጠኛ ብዙአየሁ ዋጋው አክሎ ጠቅሷል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የትናንትና ውጤት መሰረት ሊቨርፑል አጀማመሩን በማሳመር ስቶክ ሲቲን አንድ ለባዶ አሸንፏል። ማንቸስተር ዩናይትድ ከሊቨርፑል አንድ ቀን ቀደም ብሎ በተመሳሳይ ውጤት ቶንትንሐምን አንድ ለባዶ በመርታት በድል ጎዳና መጓዝ ጀምሯል። ሌላኛው ኃያል ቸልሲ ስዋንሲን ማሸነፍ አልቻለም ሁለት እኩል በመለያየት ነጥብ ለመጋራት ተገዷል። ኒውካስል እና ሳውዝሐምፕተንም ትናንት ሁለት እኩል ነው የተለያዩት። አርሰናል ከዌስትሐም ጋር ባደረገው ግጥሚያ የግብ ጠባቂው ቼክ ጊዜ አስልቶ በመውጣት የመጀመሪያዋን ግብ አለማዳኑ አስተችቶታል። ሁለተኛውም ግብ ቢሆን ከፔተር ቼክ ብቃት አንፃር የማይጠበቅ ስህተት ነው ተብሏል። የአርሰናል ተከላካዮችም ለተቆጠሩት ግቦች ከተጠያቂነት አልዳኑም። በኳስ ይዞታ ልቆ የነበረው አርሰናል ከ22 ኳሶች ወደ ግብ ዓልሞ መምታት የቻለው ስድስት ኳሶችን ብቻ ነበር።

Hertha BSC Berlin Spielerbus Teambus
ምስል Imago

ጀርመን ቢሌፌልድ ውስጥ የሔርታ ቤርሊን ተጨዋቾችን ከባቡር ጣቢያ ለማምጣት ሲጓዝ የነበረ የቡድኑ አውቶቢስ ላይ ማንነቱ ያልታወቀ ሞተረኛ ትናንት ጥይት መተኮሱ ተሰማ። በአውቶቡሱ ውስጥ የነበረው አሽከርካሪ ጉዳት እንዳልደረሰበት፤ ሆኖም ጥይቱ በአሽከርካሪው አቅጣጫ የፊት ለፊቱ መስተዋትን መምታቱን ፖሊስ አስታውቋል።ሞተረኛው ማንነቱ አልታወቀም። አሽከርካሪው ወዲያውኑ ለፖሊስ በመወደል ወደ ባቡር ጣቢያ አቅንቶ ተጨዋቾቹን ወደ ሆቴላቸው ማምጣት ችሏል። ፖሊስ አውቶቡሱን በማጀብ ጥበቃ ያደረገ ሲሆን፤ በዛሬው ጨዋታም ቁጥጥሩ ጥብቅ መሆኑ ተነግሯል። ሔርታ ቤርሊን ለጀርመን እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ ከአርሚኒያ ቢሌፌልድ ጋር ይጋጠማል።

የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ደግሞ የፊታችን ዓርብ ይጀምራል። የ18 ቡድኖች አሠልጣኞች በተደረገላቸው ቃለ መጠይቅ አስራ ስድስቱ ዓርብ በሚጀምረው ቡንደስሊጋ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ገምተዋል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የቦሩስያ ዶርትሙንድ አሠልጣኝ የነበሩት ዬርገን ክሎፕ ምናልባትም ወደ ፈረንሳዩ ኦሎምፒያ ማርሴ ቡድን ሊያቀኑ እንደሚችሉ ጭምጭምታዎች እየተሰሙ ነው። አሠልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ባለፈው የጀርመን ቡንደስ ሊጋ የውድድር ዘመን ከፍተኛ ሽንፈት ከገጠማቸው በኋላ ከቡድኑ አሠልጣኝነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መሰናበታው ይታወቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ