1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 30 2004

ያለፈው ሰንበት በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ ከመደበኛው ሻምፒዮና ባሻገር በርካታ አስደናቂ የፌደሬሺን ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎችም የታዩበት ነበር።

https://p.dw.com/p/13ge7
ላየነል ሜሲምስል dapd



በአትሌቲክስ ደግሞ ኢትዮጵያዊው የአምሥትና የአሥር ሺህ ሜትር የኦሎምፒክ ባለድል ቀነኒሣ በቀለ በስኮትላንድ የኤዲንበርግ አገር አቋራጭ ሩጫ መሪር ሽንፈት ደርሶበታል።

በእግር ኳስ እንጀምርና ከአማተር እስከ ቀደምቱ ፕሮፌሺናል ክለቦች ሁሉም በአንድ ላይ የሚሳተፉበት የአውሮፓ ብሄራዊ ፌደሬሺኖች ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ውድድር ብዙ ጊዜ ትናንሾቹ ክለቦች ታላላቆቹን የሚፈታተኑበት ብቻ ሣይሆን በአጭር የሚያስቀሩበት ጭምር እንደሆነም የሚታወቅ ነው። ባለፈው ሰንበትም ታዲያ ይሄው ሃቅ በእንግሊዝና በፈረንሣይ የእግር ኳስ መድረክ ላይ ራሱን መድገሙ አልቀረም። በአንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዊጋን አትሌቲክ በአራተኛው ዲቪዚዮን ክለብ በስዊንደን-ታውን 2-1 ተሸንፎ ሲወጣ በፈረንሣይም ሰንበቱ ቀደምቱን ክለቦች እጅግ የፈተነ ነበር። እርግጥ በእንግሊዝ ፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ሶሥተኛ ዙር በተለይም የሁለቱ ቀደምት ክለቦች የማንቼስተር ዩናይትድና የማንቼስተር ሢቲይ ግጥሚያ ነው ብዙ ትኩረትን የሳበው።

በዚሁ እንደተጠበቀው ጠንካራ በነበረው ግጥሚያ ማንቼስተር ዩናይትድ ሢቲይን 3-2 በመርታት ከውድድሩ አስወጥቷል። ያለፈው ዋንጫ ባለቤት ማንቼስተር ሢቲይ ተጫዋቹ ቪንሤንት ኮምፓኒይ ከሜዳ ወጥቶበት አብዛኛውን ጊዜ በጎዶሎ ሲጫወት ማኒዩ እስከ እረፍት ድረስ ሶሥት-ለባዶ መምራቱ ብዙም አልከበደውም ነበር። ሆኖም የሢቲይ መልሶ ማየል ጨዋታውን ይበልጥ የደመቀ ሲያድገው ታይቷል። ለማኒዩ ሁለቱን ጎሎች በስነ ምግባር ጉድለት ሲተች የሰነበተው አጥቂ ዌይን ሩኒይ ሲያስቆጥር ሶሥተኛዋን ያከለው ደግሞ ምን ጊዜም የማይዳከመው የ 35 ዓመቱ ስኮልስ ነበር። ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ሶሥት ጊዜ ለዋንጫ ባለቤትነት በቅቶ የነበረው ቼልሢይ ደግሞ ፖርትማውዝን 4-0 በመርታት በቀላሉ ወደ ተከታዩ ዙር ተሻግሯል።

ሁለት የፕሬሚየር ሊጉ ክለቦች ቦልተን ወንደረርስና ኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስ ደግሞ ከዝቅተኛ ክለቦች ባደረጉት ግጥሚያ በእኩል-ለእኩል ውጤት ብቻ ነበር የተወሰኑት። እናም ወደፊት ለመዝለቅ ገና ብርቱ ትግል ይጠብቃቸዋል። በተረፈ የቀጣዩ አራተኛ ዙር የኤፍ.ኤ.ግጥሚያዎች ዕጣ ከወዲሁ ሲወጣ ከሁሉም በላይ አስደናቂው ማንቼስተር ዩናይትድ ከሊቨርፑል የሚገናኝ መሆኑ ነው። የኤስተን ቪላ ተጋጣሚ ምናልባት ኤቨርተን እንደሚሆን ሲጠበቅ ኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስም ቼልሢይ ሊደርሰው ይችላል። በነገራችን ላይ እነዚህ የአራተኛው ዙር ግጥሚያዎች የሚካሄዱት በፊታችን ጥር 19 እና 20 ነው።

በፈረንሣይ የፌደሬሺን ዋንጫ ውድድርም ቀደምቱ ፓሪስ ሣንት ዠርማን ከአምሥተኛ ዲቪዚዮኑ ክለብ ከሎክሚን ጋር ባደረገው ግጥሚያ በመጨረሻዋ ደቂቃ በመከራ ባስቆጠራት ጎል 2-1 በማሸነፍ ለጥቂት ነው ከውርደት የተረፈው። አዲሱ አሠልጣኝ ኢጣሊያዊው ካርሎ አንሄሎቲ በመጀመሪያ ግጥሚያቸው ከከፋ ሽንፈት ላተረፋቸው ጎል አግቢ ለዲየጎ ሉጋኖ ምስጋና ሊሰነዝሩ ይገባል። የፓሪሱ ክለብ እንዲህ በዕድል ለጥቂት ሲያመልጥ ሌላው ቱሉዝ ግን በሶሥተኛ ዲቪዚዮን ተጋጣሚው በአያቺዮ ተረትቶ ከወዲሁ ስንብት ማድረጉ ግድ ነው የሆነበት። ከፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ክለቦች መካከል ከቱሉዝ ሌላ ኬን፣ ሶሾ፣ ሎሪየንትናብሬስትም እንዲሁ ከውድድሩ ወጥተዋል። በአንጻሩ ማርሤይን፣ ኦላምፒክ ሊዮንን፣ ሊልንና፣ ዢሮንዲን ቦርዶን የመሳሰሉት ክለቦች በውድድሩ ይቀጥላሉ።

በቀደምቱ የአውሮፓ ሊጋዎች መደበኛ ሻምፒዮና የጀርመን ቡንደስሊጋ ከክረምት እረፍቱ ለመመለስ በበጨረሻ ዝግጅት ላይ ሲሆን በሌላ በኩል ከስፓኝ እስከ ኢጣሊያ ውድድሩ ቀጥሏል። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሬያል ማድሪድ ግራናዳን 5-1 በመቅጣት ባለፈው ዓመት በጀመረው የጎል ፌስታ ሲቀጥል የሁለተኛው የባርሤሎና ደከም ማለትም የነጥብ ልዩነትን እንዲያሰፋ በጅቶታል። ጎሎቹን ካሪን ቤንዜማ፣ ሤርጆ ራሞስ፣ ጎንዛሎ ሂጉዌይንና ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሲያስቆጥሩ ሶሥቱን ያመቻቸው የጀርመኑ ሜሱት ኡዚልም በአጨዋወቱ በስፓኝ ፕሬስ እ’ጅጉን ነው የተወደሰው። ባርሣ በበኩሉ ከከተማ ተፎካካሪው ከኤስፓኞል ጋር ባደረገው ግጥሚያ 1-1 በሆነ ውጤት ተወስኗል። ይህ ደግሞ የሬያል ማድሪድ አመራር በአምሥት ነጥቦች ልዩነት ከፍ እንዲል ነው ያደረገው።

በሌሎቹ የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ የሰንበት ግጥሚያዎች ቬሊካኖ ሤቪያን 2-1፤ ሬያል ቤቲስ ስፖርቲንግ ጊዮንን 2-0፤ እንዲሁም ሣንታንዴር ሣራጎሣን 1-0 ሲያሸንፍ እንደ ጌታፌና ቢልባዎ ደግሞ ሶሥት ግጥሚያች ያላንዳች ጎል ባዶ-ለባዶ ተፈጽመዋል። በጥቅሉ ሬያል ከ 17 ግጥሚያዎች በኋላ በ 43 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ባርሣ በ 38 ሁለተኛ እንዲሁም ቫሌንሢያ በ 34 ነጥቦች ሶሥተኛ ነው። በጎል አግቢነት ክሪስቲያኖ ሮናልዶ 21 በማስቆጠር የሚመራ ሲሆን ከቅርብ ተፎካካሪው ከሊዮኔል ሜሢ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ አምሥት ከፍ አድርጓል።

የዓለም ድንቅ ተጫዋች እንደገና ሜሢ?

የስፓኝን ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ካነሣን ዘንድሮም የዓመቱ ድንቅ ተጫዋች ተብሎ የሚሰየመው ስፖርተኛ ከዚያው የሚመነጭ መሆኑ ከወዲሁ እርግጠኛ ነው። የዓለም አግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ ዛሬ ማምሻውን ስዊትዘርላንድ-ዙሪክ ላይ በሚያካሂደው ምሽት የ 2011 ዓ.ምን ድንቅ ተጫዋች ይመርጣል። በዚሁ ምርጫ ትልቅ ዕድል አላቸው ተብለው የታጩት ሊዮኔል ሜሢና ሻቪ ከባርሤሎና እንዲሁም የሬያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሲሆኑ አርጄንቲናዊው ሜሢ በተከታታይ ለሶሥተኛ ጊዜ አሸናፊ እንደሚሆን የብዙዎች ዕምነትና ግምት ነው። በሴቶች የብራዚሏ ማርታ፣ የዓለም ሻምፒዮኑ የጃፓን ብሄራዊ ቡድን ኮከብ ሆማሬ ሣዋና አሜሪካዊቱ ኤቢይ ዋምባህ በዕጩነት ቀርበዋል። ከዚሁ ተያይዞ የዓመቱ ግሩም አሠልጣኞችም በምሽቱ ይሰየማሉ።

ወደ መደበኛው የአውሮፓ ሊጋዎች እንመለስና በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኤሢ.ሚላንና ጁቬንቱስ በየበኩላቸው ግጥሚያ በማሸነፍ በእኩል ነጥቦች መምራታቸው ቀጥለዋል። ኤሢ.ሚላን አታላንታ በርጋሞን 2-0 ሲረታ ጁቬንቱስም ሌቼን 1-0 አሸንፏል። ኡዲኔዘ ደግሞ ቼሤናን 4-1 ሲረታ ሁለት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሶሥተኛ ነው። ላሢዮ አራተኛ፤ ኢንተር ሚላን አምሥተኛ! በጎል አግቢነት ሶሥት ተጫዋቾች እኩል 12 ጎሎችን አስቆጥረው በእኩልነት የሚመሩ ሲሆን እነዚሁም የኤሢ.ሚላኑ ዝላታን ኢብራሂሞቪች፣ የበርጋሞው ጄናን ዴኒስና የኡዲኔዘው አንቶኒዮ ዲ-ናታሌ ናቸው።

በፖርቱጋል ሻምፒዮና ቤንፊካ ሊዝበን ኡኒያዎ-ዴ-ሌይሪያን 4-1 በማሸነፍ የሊጋውን አመራር ከፖርቶ ሊነጥቅ በቅቷል። ፖርቶ በሁለት ነጥብ ተበልጦ ወደ ሁለተኛው ቦታ ያቆለቆለው ከስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር ባዶ-ለባዶ ከተለያየ በኋላ ነው። የሁለቱ ክለቦች ግጥሚያ ጎል ባይታይበትም እንተለመደው የደመቀ ሆኖ ነው ያለፈው። ቤንፊካ አሁን በ 36 ነጥቦች አንደኛ ሲሆን ፖርቶ በ 34 ሁለተኛ ነው፤ ስፖርቲንግ ደግሞ በ 28 ነጥቦች ሶሥተኛ ሆኖ ይከተላል። በግሪክ ሻምፒዮና ኦሊምፒያኮስ ፒሬውስ ምንም እንኳ በእኩል ለእኩል ውጤት ቢወሰንም አመራሩን እንደያዘ ነው። ሆኖም ፓናቴናኢኮስ አቴን እስከ አራት ነጥቦች ልዩነት ድረስ ተቃርቦታል። የአቴኑ ክለብ ሁለት ግጥሚያዎች የሚጎሉት ሲሆን ወደፊት አመራሩን የመንጠቅ ግሩም ዕድልም አለው።

አትሌቲክስ

ስኮትላንድ ውስጥ ትናንት በተካሄደው ታላቅ የኤዲንበርግ አገር-አቋራጭ ሩጫ ኬንያዊው የ 1,500 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን አስቤል ኪፕሮፕ አሸናፊ ሆኗል። ኪፕሮፕ ሶሥት ኪሎሜትሩን ያቋረጠው በዘጠኝ ደቂቃ ከሃያ ሤኮንድ ጊዜ ነበር። የብሪታኒያው ወጣት አትሌት ጆኒይ ሄይ ሁለተኛ ሲወጣ ኬንያዊው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል። የኦሎምፒኩ የአምሥትና የአሥር ሺህ ሜትር ሩጫ የወርቅ ሜዳይ ተሸላሚ ቀነኒሣ በቀለ በአንጻሩ በውድድሩ ግንባር ቀደም ቦታ መያዙ አልተሳካለትም።

በአካል ጉዳት የተነሣ ለረጅም ጊዜ ከውድድር ተቆጥቦ የቆየው ቀነኒሣ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሥር ሺህ ሜትር ሩጫውን አቋርጦ መውጣቱ የሚታወስ ነው። ድንቁ የኢትዮጵያ አትሌት ራሱ እንደገለጸው ተግቶ በመሰልጠን ላይ ሲሆን በቅርቡ ወደ ቀድሞ ልዕልናው በመመለስ ለለንደን ኦሎምፒክ እንደሚደርስ ተሥፋ እናደርጋለን። በስምንት ኪሎሜትሩ አገር-አቋራጭ ደግሞ የስፓኙ አያድ ላምዳሤም አሸንፏል።

በአውስትራሊያ የሢድኒይ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድር ዛሬ በመጀመሪያው ዙር ግጥሚያዎች የአገሪቱ ተወላጅ ማቲዩ ኤብደን የስፓኙን ማርሤል ግራኖለርስን 2-1 ሲረታ በተቀሩት ግጥሚያዎች የአሜሪካው ቦቢይ ሬይኖልድስ የኡክራኒያውን ሤርጊይ ስታሆቭስኪን፤ የፊንላንዱ ጃርኮ ኒሚነን የአውስትራሊያ ተጋጣሚውን ጀምስ ዳክወርዝን፤ ኡዝቤኩ ዴኒስ ኢስቶሚን የስፓኙን ፓብሎ አንጁሃርን፤ የአሜሪካው ራያን ስዊቲንግ የሉክሰምቡርጉን ጊልስ ሙለርን፤ እንዲሁም የፖላንዱ ሉካሽ ኩቦት የክሮኤሺያውን ኢቫን ዲግን አሸንፈዋል። በተረፈ በፊታችን ሰኞ ሜልበርን ላይ የሚከፈተው የዘንድሮው አውስትሬሊያን ኦፕን በቴኒስ አፍቃሪዎች ዘንድ በጉጉት እየተጠበቀ ነው።

መሥፍን መኮንን
ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ