1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 14 2004

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሺን በሥልጠና ጉዳይ በተፈጠረ አለመግባባት የተነሣ ቀነኒሣ በቀለንና ጥሩነሽ ዲባባን ጨምሮ 35 የአገሪቱ አትሌቶች በዓለምአቀፍ ውድድር እንዳይሳተፉ ላልተወሰነ ጊዜ አግዷል።

https://p.dw.com/p/13oaO
ምስል AP

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሺን የቴክኒክ ጉዳይ ሃላፊ ዱቤ ጂሎ ባደረግ’ንላቸው ቃለ-መጠይቅ የዕርምጃውን መንስዔ በመዘርዘር አትሌቶቹ ይቅርታ ከጠየቁ ሊመለሱ ይችላሉ ሲሉም ተናግረዋል። ዝርዝሩን ያድምጡ!

ኔዘርላንዳዊው የቀነኒሣ ማኔጀር ጆስ ሄርመንስ እንደገለጸው ደግሞ ባለፈው የዴጎ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቶች ውጤት ደካማ ሆኖ መገኘት በአገሪቱ የአትሌቲክስ ፌደሬሺንና በኦሎምፒክ ኮሚቴው ፊት ሁኔታውን የመለወጥ ጥድፊያን አስከትሏል። ግን በመመሪያው መሠረት ሥልጠና ካምፕ መግባቱ ብዙዎችን የሚከብድ ነው።

“ለምሳሌ ቀነኒሣ ከበደ ከሁለት ዓመታት የአካል ጉዳት በኋላ ነው የተመለሰው። እናም አሁን በኦሎምፒክ ኮሚቴው ስር በአንድ ትልቅ ቡድን ውስጥ መሰልጠኑ ይከብደዋል። ስለዚህም የራሱን ፕሮግራም ነው የሚያካሂደው። ይሄን ለነገሩ ሁሌም በስኬት ሲያደርገው የነበረ ነው። እናም ከፌደሬሺኑና ከኦሎምፒክ ኮሚቴው ጋር በጉዳዩ መነጋገር እንደምንችልና መፍትሄም እንደምናገኝ ተሥፋ አደርጋለሁ። ምናልባት ጠቅላላውን ፕሮግራም ያለሟሟላት ግዴታ ሥልጠናው ኳምፕ መግባት ይቻል ይሆናል። ለሁሉም በሚቀጥሉት ቀናትና ሣምንታት አንድ መፍትሄ ይገኛል የሚል ተሥፋ አለኝ”

ሄርማንስ እንደሚለው ኢትዮጵያ ውስጥ ተስማሚው የሥልጠና ቦታ አለመኖሩ ያለ ነው። አትሌቶች በቀላሉ ይጎዳሉ፤ ይህ ደግሞ የቀነኒሣም ችግር ነበር።

“ትልቁ የኢትዮጵያ ችግር አዲስ አበባ ስታዲዮም ውስጥ ያለው ብቸኛው ሞንደል ባን፤ አርቲፊሻል መሮጫ ነው። በጣም ጠጣር መሆኑ ይታወቃል። እናም በሣምንት  ሁለት-ሶሥቴ በዚያ የሚለማመዱ አትሌቶች ከባድ ጉዳት ነው የሚገጥማቸው። እግር ላይ ከባድ-አሰቃቂ ጉዳት ነው የሚያደርሰው። የጥሩነሽና የቀነኒሣ ችግርም ታዲያ ይሄው ነው። ኢትዮጵያ እነዚህ ሁለት አትሌቶች በመቁሰላቸው በዴጉው የዓለም ሻምፒዮና አራት ሜዳሊያዎችን ነው ያጣችው። ምክንያቱም በአብዛኛው ይሄው መሮጫ ነበር”

ማኔጀሩ ጆስ ሄርመንስ ቀነኒሣ እገዳውን ከፌደሬሺኑ ሣይሆን ከቴሌቪዥን በመረዳቱ ብርቱ ቁጣ አድሮበት እንደነበርም ገልጾልናል። የኔዘርላንዱ ተወላጅ እንዳለው ድንቁ አትሌት ለሌላ አገር ብሮጥስ እስከማለትም ነበር የደረሰው።

“ባለፈው አርብ ከቀነኒሣ ጋር ተነጋግሬ ነበር። እና ዜናውን ከቴሌቪዥን በመስማቱ በጣም ነበር የተናደደው። እርግጥም ይሄ አክብሮት ይጎለዋል። ታዲያ በቁጣ ስሜት “ኢትዮጵያ ውስጥ የማይፈልጉኝ ከሆነ ለሌላ አገር ልሮጥ እችላለሁ” ነበር ያለው። ግን ይሄ ቀላል ነገር እንዳልሆነ እናውቃለን። ቀነኒሣ በመሠረቱ አገሩን የሚወድ ነው። ለኢትዮጵያ ለመሮጥም ነው የሚፈልገው። በሌላ በኩል አንድ አትሌት በኦሎምፒክ መሣተፍ እንደሚፈልግም መታሰብ አለበት። ለማንኛውም በመጨረሻ ሁሉም ነገር እየተረጋጋ እንደሚሄድና በንግግር መፍትሄ እንደምናገኝ አምናለሁ። ከኬንያ ብዙ መማር ይቻላል። ፌደሬሺኑ፣ ማኔጀሮችና አሠልጣኞች በሚያደርጉት ጥሩ ትብብር ግሩም ውጤት እያሳዩ ነው”

ቀነኒሣ በቀለን ለማነጋገር ቀኑን ሙሉ ያደረግነው ሙከራ ሊሳካልን ባለመቻሉ በጣሙን እናዝናለን። አትሌቶችም በራሳቸው ጉዳይ አስተየታቸውን በይፋ ቢገልጹ ችግሩን በመፍታቱ ረገድ ይበልጥ ጠቃሚ ሊሆን በቻለ ነበር።

እግር ኳስ

28ኛው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ባለፈው ቅዳሜ ጨዋታውን ከጋቡን ጋር አብራ በምታስተናግደው በኤኩዎሪያል ጊኒ ስኬት ተከፍቷል። ኤኩዋቶሪያል ጊኒ ባታ ላይ በምድብ-አንድ መክፈቻ ግጥሚያ ሊቢያን 1-0 ስትረታ በዚሁ ምድብ ዛምቢያ ደግሞ ሤኔጋልን 2-1 አሸንፋለች። በምድብ-ሁለት አይቮሪ ኮስት ትናንት ሱዳንን ዲዲየር ድሮግባ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል 1-0 ስታሸንፍ አንጎላም ቡርኪና ፋሶን 2-1 ረትታለች። ዛሬ ደግሞ በምድብ-ሶሥት ሌላዋ አስተናጋጅ ጋቡን ኒጀርን የምትገጥም ሲሆን በተለይም የሞሮኮና የቱኒዚያ ግጥሚያ ከበድ ያለው እንደሚሆን ይገመታል። ግብጽን፣ ናጄሪያንና ካሜሩንን የመሳሰሉት ጠንካራ ሃገራት በማጣሪያው ወድቀው በመቅረታቸው ዘንድሮ የአይቮሪ ኮስት፤ የሞሮኮ፣ የቱኒዚያ ወይም የጋና የዋንጫ ዕድል የላቀ መሆኑን ታዛቢዎች ይገምታሉ።  

መሥፍን መኮንን   
    



 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ