1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 23 2005

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውስጥ የሚካሄደው የእግር ኳስ ውድድር ሊጠቃለል እየተቃረበ ሳለ አመራሩን የያዙት ክለቦችም እንደተጠናከሩ ወደፊት ማምራታቸውን ቀጥለዋል።

https://p.dw.com/p/187kV
ምስል picture-alliance/dpa

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ቀደምቱ ባርሤሎና ከሤልታ ቪጎ 2-2 ቢለያይም በ 13 ነጥቦች ብልጫ መምራቱን እንደቀጠለ ነው። ሁለተኛው ሬያል ማድሪድም በበኩሉ ግጥሚያ ከሣራጎሣ 1-1 ሲለያይ ልዩነቱን ጥቂትም ቢሆን ለማጥበብ ያገኘውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።                        

ባርሣ ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ በ 75 ነጥቦች አንደኛ ሲሆን ኮከቡ ሊዮኔል ሜሢም በ 19ኛው ግጥሚያ በተከታታይ ጎል በማሰቆጠር የቡድኑ አለኝታ እንደሆነ መቀጠሉ ሊጠቀስ የሚገባው ጉዳይ ነው። አርጄንቲናዊው ድንቅ ተጫዋች በዚህ ከቀጠለ በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ የዓለም ድንቅ ተጫዋች ተብሎ በዓመቱ መጨረሻ እንደገና መሰየሙ የሚቀር አይመስልም። ሬያል ማድሪድም ሳይሸነፍ ሰንበቱን በማሳለፉ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረውን ክሪስቲያኖ ሮናልዶን ሊያመሰግን ይገባዋል።                                                             

እርግጥ ሁለቱ ክለቦች ኮከቦቻቸውን ለዚህ ሣምንት የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ቁልፍ ግጥሚያዎች ለማሳረፍ ተቀያሪ ተጫዋቾችን ማሰለፋቸው በእኩል ለእኩል ውጤቶች ለመወሰናቸው ምክንያት ሣይሆን አልቀረም። ያም ሆነ ይህ ባርሤሎና የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ውድድር ሊጠቃለል ዘጠኝ ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ከእንግዲህ ሻምፒዮንነቱን አሳልፎ መስጠቱ ጨርሶ የማይጠበቅ ነገር ነው።                                                                                                          

Lionel Messi
ምስል picture alliance / dpa

ከዚህ አንጻር ፈንጠር ብለው ለሚከተሉት የማድሪድ ክለቦች ለሬያልና ለአትሌቲኮ ዘንድሮ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ከማለፍ ባሻገር የሚገኝ ነገር አይኖርም። በነገራችን ላይ አትሌቲኮ ማድሪድ ትናንት ከቫሌንሢያ 1-1 ሲለያይ ቢያሸንፍ ኖሮ ሁለተኛውን ቦታ ሊይዝ በበቃ ነበር። ለማንኛውም ሁለቱ ክለቦች የሚከታተሉት በአንዲት ነጥብ ልዩነት ብቻ ነው። በተቀረ ሬያል ሶሢየዳድ የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ አራተኛ ሲሆን ማላጋ ደግሞ በአምሥተኝነት ይከተላል።    

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ሰንደርላንድን 1-0 ሲረታ ሊጋውን በ 15 ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። ውድድሩ ሊጠቃለል ስምንት ጨዋታዎች ቀርተው ሳለ ማኒዩ በክለቡ ታሪክ ለሃያኛው ዋንጫ የተቃረበ ነው የሚመስለው። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ማንቼስተር ሢቲይም ኒውካስልን 4-0 በመሸኘት ሁለተኝነቱን አጠናክሯል። ግን ማኒዩ ላይ ከእንግዲህ መድረሱ የማይታመን ነው።                                                                                               

ማንቼስተር ዩናይትድ በ 77 ነጥቦች አንደኛ ሲሆን ማንቼስተር ሢቲይ በ 62 ሁለተኛ ነው፤ ቶተንሃም ሆትስፐርም አምሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ በ 57 በሶሥተኝነት ይከተላል። ከዚሁ ሌላ ኤፍ ሲ ቼልሢይ በሳውዝሃምተን 2-1 ተሸንፎ ወደ አራተኛው ቦታ ሲያቆለቁል አርሰናል ደግሞ ሪዲንግን 4-1 በመርታት በአምሥተኝነቱ ቀጥሏል።

Fußball Bundesliga - FC Bayern München - Hamburger SV
ምስል picture-alliance/dpa

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሺን ሰባት ግጥሚያዎች ቀድሞ ሻምፒዮንነቱን ማረጋገጡ ባለፈው ሰንበት ሳይሣካ ቀርቶ ወደሚቀጥለው ሣምንት ተሸጋግሯል። ባየርን ምንም እንኳ በበኩሉ ግጥሚያ ሃምቡርግን 9-2 ቢቀጣም ሻምፒዮንነቱ ያልሰመረው ሽቱትጋርትን 2-1 የረታው ሁለተኛው ዶርትሙንድ ነጥብ ባለመጣሉ ነው። ባየርን ሙንሺን በሃያ ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ምናልባትም በፊታችን ሣምንት ድሉን የማክበር ትልቅ ዕድል አለው።                                                                          

ተከታዮቹ ክለቦች ከእንግዲህ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ ከመፎካከር ባሻገር ሌላ ዕድል አይኖራቸውም። የነጥብ ልዩነቱን ስፋት ለማመልከት ያህል ባየርን በ 72 ነጥቦች አንደኛ ሲሆን ዶርትሙንድ በ 52 ሁለተኛ፤ እንዲሁም ሌቨርኩዝን በ 48 ነጥቦች ሶሥተኛ ነው። ሻልከና ፍራንክፉርት ደግሞ በ42 ነጥቦች አራተኛና አምሥተኛ ሆነው ይከተላሉ።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጁቬንቱስ ቱሪን ዋና ተፎካካሪውን ኢንተር ሚላንን 2-1 በማሸነፍ ሻምፒዮንነቱን መልሶ ለማረጋገጥ ጠቃሚ ዕርምጃ አድረጓል። በዘጠኝ ነጥቦች ወረድ ብሎ በሁለተኝነት የሚከተለው ናፖሊ ነው። ናፖሊ በበኩሉ ግጥሚያ ቶሪኖን 5-3 ለማሸነፍ በቅቷል። ኤ ሲ ሚላንም ቺየቮን 1-0 አሸንፎ ሶሥተኛ ሲሆን ፊዮሬንቲና ደግሞ በአምሥተኝነቱ ቀጥሏል።

Fußball Lyon Michel Bastos
ምስል picture-alliance/dpa

በፈረንሣይ ሻምፒዮና ቀደምቱ ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ሞንትፔሊየርን 1-0 በመርታት ለዚህ ሣምንት የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚያው ራሱን ማማሟቁ ሰምሮለታል። የፓሪሱ ክለብ ፔ-ኤስ-ዤ አሁን ሊጋውን የሚመራው በሰባት ነጥቦች ልዩነት ነው። ለዚህም ምክንያት የሆነው ባለፉት አራት ግጥሚያዎቹ አንዴም ማሸነፍ የተሣነው ኦላምፒክ ሊዮን እንደገና በገዛ ሜዳው በሶሾው 2-1 መረታቱ ነው። ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ማርሤይ ፔ-ኤስ-ዤን ተከትሎ ሁለተኛ ሲሆን ሊዮን ሶሥተኛ፤ እንዲሁም ሣንት ኤቲየን አራተኛ ነው።

በኔዘርላንድ የክብር ዲቪዚዮን አያክስ አምስተርዳም ኒይሜኸንን 4-1 በማሸነፍ ውድድሩ ሊጠቃለል ስድሥት ጨዋታዎች ቀርተው ሳለ በሶሥት ነጥብ ልዩነት እየመራ ነው። አይንድሆፈን ከሮዳ-ኬርክራደ 2-2 ሲለያይ በ 57 ነጥቦች ሁለተኛ ነው፤ አርንሃይም ደግሞ ሶሥተኛውን ቦታ ከፋየኖርድ ነጥቋል። ሆኖም በኔዘርላንዱ ሻምፒዮና ገና ምኑም አልለየለትም። እንበል አራቱም ቀደምት ክለቦች አንደኛ የመሆን ዕድል አላቸው።

በፖርቱጋል ፕሪሜራ ሊጋ ቤንፊካ ሊዝበን ሪዮ አቬን 6-1 ሲያሸንፍ በአራት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። ለቤንፊካ ከስድሥት ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው ብራዚላዊው ሊማ ነበር። ሁለተኛው አካዴሚካን 3-0 ያሸነፈው ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ፖርቶ ነው። በፖርቱጋል ፕሪሜራ ሊጋም ውድድሩ ሊጠቃለል  ስድሥት ግጥሚያዎች ሲቀሩ የቤንፊካና የፖርቶ ፉክክር ምናልባትም እስከመጨረሻው የሚቀጥል ይሆናል።

Tennis Australian Open Andy Murray
ምስል Reuters

በትናንትናው ዕለት አሜሪካ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የማያሚ ቴኒስ ማስተርስ ፍጻሜ ግጥሚያ በወንዶች የብሪታኒያው ኤንዲይ መሪይ አሸናፊ ሆኗል። ይሄው ድል ኤንዲይ መሪይ በኤቲፒ የማዕረግ ተዋረድ ላይ ከአራት ዓመታት በኋላ ሁለተኛውን ቦታ መልሶ እንዲይዝ የሚያደርገው ነው። በማዕረግ ተዋረዱ ላይ ኖቫክ ጆኮቮች አንደኛ እንደሆነ ሲቀጥል ሮጀር ፌደረር ወደ ሶሥተኛው ቦታ ተንሸራቷል። የስኮትላንዱ ተወላጅ ለሁለተኝነቱ ክብር የበቃው የስፓኝ ተጋጣሚውን ዴቪድ ፌሬርን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 ካሸነፈ በኋላ ነው። ግጥሚያው ሶሥት ሰዓታት የፈጀ ትግል የታየበት ነበር።

በሴቶች ደግሞ በዓለም የቴኒስ ማሕበር የማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛና ሁለተኛ በሆኑት በአሜሪካዊቱ በሤሬና ዊሊያምስና በሩሢያዊቱ በማሪያ ሻራፖቫ መካከል በተካሄደው ፍጻሜ ግጥሚያ ሤሬና 2-1 አሸንፋለች። አሜሪካዊቱ በማያሚ ማስተርስ ስታሽንፍ ለስድሥተኛ ጊዜ ሲሆን ይህም ራሱን የቻለ ክብረ-ወሰን መሆኑ ነው። ሤሬና ዊሊያምስ  በአንድ ውድድር ስድሥት ጊዜ በማሸነፍ በዘመኑ ቴኒስ ከሽቴፊ ግራፍ፣ ከክሪስ ኤቨርትና ከማርቲና ናቭራቲሎቫ እኩል በመሰለፍ አራተኛዋ ሴት ለመሆን በቅታለች።

Flandern - Rundfahrt 2013 Fabian Cancellara
ምስል Reuters

በትናንትናው ዕለት ቤልጂግ ውስጥ ተካሂዶ የነበረው የፍላንደርስ ቱር የቢስክሌት እሽቅድድም አሸናፊ የስዊሱ ተወዳዳሪ የፋቢያን ካንቼላራ ሆኗል። ካንቼላራ ባለፈው ዓመት ኮረብታማና አድካሚ የሆነውን 256 ኪሎሜትር ማቋረጡ ሳይሳካለት ቀርቶ እንደነበር የሚታወስ ነው። የቀድሞው የኦሎምፒክ ሻምፒዮን በጊዜው በጠርሙስ ተደናቅፎ ከተሰናከለ በኋላ በደረሰበት የአካል ጉዳት 60 ኪሎሜትር ሲቀረው ውድድሩን ማቋረጥ ነበረበት። ስለዚህም የትናንቱ ደስታው ወሰን አልነበረውም።                                                                                           

የሶሥት ጊዜው አሸናፊ የቤልጂጉ ተወላጅ ቶም ቦነን በአንጻሩ ከ 19 ኪሎሜትር በኋላ በክንዱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ተሰናክሏል። በፍላንደሩ ቱር የስሎቫኪያው ፔተር ሣጋን ሁለተኛ ሲወጣ የቤልጂጉ ተወዳዳሪ ዩርገን ሮላንድስ ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል።

በአውሮፓ እግር ኳስ ሻምፒዮና ሊጋ ለማጠቃለል ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለመዝለቅ በሚደረገው ውድድር ነገና ከነገ በስቲያ ምሽት አራት የሩብ ፍጻሜ ዙር የመጀመሪያ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ባርሤሎናን የሚያስተናግድ ሲሆን የባየርን ሙንሺን ተጋጣሚ ደግሞ የኢጣሊያው ሻምፒዮን ጁቬንቱስ ቱሪን ነው። የፈረንሣዩ ሻምፒዮን ዘንድሮ ለሩብ ፍጻም ሲደርስ ከ 18 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ባርሤሎናን ማቆሙ የሚቀለው አይሆንም። በባየርንና በጁቬንቱስ መካከል የሚካሄደው ግጥሚያም ትግል የሰፈነበት እንደሚሆን ነው ከወዲሁ የሚጠበቀው።

ዘንድሮ ምንም እንኳ ቼልሢይን ወይም ማንቼስተር ዩናይትድን የመሰሉት የእንግሊዝ ክለቦች ከ 17 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሩብ ፍጻሜው ቢጎሉም ለንደን ላይ የሚካሄደው ፍጻሜ ግጥሚያ የሬክልና የባርሣ ክላሢኮ ወይም የባየርን ሙንሺንና የዶርትሙንድ የዋንጫ ትግል የሰፈነበት ሊሆን የሚችል ነው። ሂደቱ እርግጥ ሌላም ሊሆን ይችላል።

1. Bundesliga VfB Stuttgart gegen Borussia Dortmund
ምስል imago sportfotodienst

ለማንኛውም በፊታችን ረቡዕ ምሽት ደግሞ ማላጋ ከቦሩሢያ ዶርትሙንድና ሬያል ማድሪድ ከጋላታሣራይ ኢስታምቡል ቀሪዎቹ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ናቸው። የመልስ ግጥሚያዎቹ የሚካሄዱት በፊታችን ሚያዚያ አንድና ሁለት ቀን ነው። ከዚያ በኋላ የአራቱ ለግማሽ ፍጻሜው የሚያልፉት ክለቦች ማንነት ይለይለታል። በአውሮፓ ሊግ ውድድርም በፊታችን ሐሙስ አራት የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች የሚካሄዱ ሲሆን እነዚሁም ቼልሢይ ከሩሢያው ሩቢን ካዛን፤ ቶተንሃም ሆትስፐር ከቤልጂጉ ባዝል፤ ፌረንባቼ ኢስታምቡል ከሮማው ላሢዮ፤ እንዲሁም ቤንፊካ ሊዝበን ከኒውካስል ዩናይትድ ናቸው። የመልሱ ግጥሚያዎች ሚያዚያ 3 ቀን ይካሄዳሉ።

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ