1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 12 2005

የአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ከፊሉ ተጠናቆ የተቀረውም በመገባደድ ላይ ሲሆን እስከ መጨረሻው ብርቱ ፉክክር ሰፍኖበት የቆየው የፖርቱጋል ሻምፒዮናም ትናንት በአስደናቂ ሁኔታ ተፈጽሟል።

https://p.dw.com/p/18b5j
ምስል picture-alliance/empics

በጀርመን፣ በእንግሊዝ፣ በስፓኝና በኢጣሊያ ወይም በፈረንሣይ ሻምፒዮናው ቀድሞ ሲለይለት ፉክክሩ ያተኮረው ለመጪው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ ለመብቃትና ላለመከለስ በተያዘው ትግል ነበር።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል ትናንት በመጨረሻው የውድድር ቀን ኒውካስል ዩናይትድን 1-0 በመርታት ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ ማጣሪያ ዙር የሚያበቃውን አራተኛ ቦታ ለማረጋገጥ በቅቷል። በዚሁ ውድድር ከአርሰናል ሌላ ሻምፒዮኑ ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ሁለተኛው ማንቼስተር ሢቲይና ሶሥተኛው ቼልሢይም ይሳተፋሉ።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ውድድሩ ሊጠቃለል ገና ሁለት ጨዋታዎች ሲቀሩ ሻምፒዮኑ ባርሤሎና ትናንት ቫላዶሊድን 2-1 አሸንፎ 94 ነጥቦች ላይ ሲደርስ ባለፈው የውድድር ወቅት በሬያል ማድሪድ ተመዝግቦ የነበረውን የመቶ ጎሎች ክብረ-ወሰን ለማለፍ ጥሩ ዕድል አለው። ሬያልና አትሌቲኮ ማድሪድ በሻምፒዮናው ሊጋ ተሳትፎ ክልል ውስጥ ሲሆኑ ሬያል ሶሢየዳድም በአራተኝነት ተሥፋውን ሕያው አድርጎ እንደቀጠለ ነው። ከአምሥተኛው ከቫሌንሲያ ጋር እኩል ነጥብ አለው።

Fußball Spanien Pokal Copa del Rey Real Madrid Atletico Madrid
ምስል Denis Doyle/Getty Images

የማድሪዱን ክለቦች ካነሣን አትሌቲኮ ማድሪድ ባለፈው አርብ ምሽት በዝነኛው በርናቤው ስታዲዮም በተካሄደ የብሄራዊ ዋንቻ ፍጻሜ ግጥሚያ ሬያል ማድሪድን 2-1 በመርታት ለአሥረኛ ጊዜ የስፓኝ ኪንግስ ካፕ አሸናፊ ሆኗል። አትሌቲኮ የከተማ ተፎካካሪውን ሬያልን ሲያሸንፍ ከ 14 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አም ኤ ሲ ሚላን ተከላሹን ሢየናን 2-1 በማሸነፍ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ የሚያበቃውን ሶሥተኛ ቦታ ሊያረጋግጥ ችሏል። ሻምፒዮኑ ጁቬንቱስና ሁለተኛው ናፖሊ በቀጥታ የሻምፒዮናው ሊጋ ተሳታፊዎች ናቸው። እስከመጨረሻው የሁለት ክለቦች ፉክክር ሰፍኖ በቆየበት በፖርቱጋል ፕሪሜራ ሊጋ ደግሞ ፖርቶ ትናንት በአንዲት ነጥብ ብልጫ ለ 27ኛ ጊዜ ሻምፒዮን ሆኗል።

ፖርቶ ለረጅም ጊዜ በቤንፊካ ሲመራ ከቆየ በኋላ አንደኝነቱን ነጥቆ የያዘው ባለፈው ሣምንት የሊዝበኑን ክለብ በመርታት ነበር። ቤንፊካ ሊዝበን ከሣምንት በፊትም በአውሮፓ ሊግ ፍጻሜ በቼልሢይ ተሸንፎ ዋንጫ ሲያመልጠው ዘንድሮ ዕድል ጨርሶ ከድቶታል ለማለት ይቻላል።

Fußball Bundesliga 34. Spieltag SC Freiburg - FC Schalke 04
ምስል picture-alliance/dpa

የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድርም ባለፈው ቅዳሜ ሲጠናቀቅ ዕለቱ በተለይ ለሁለቱ እንግዳ ክለቦች በአንድ በኩል ለዱስልዶርፍ አስከፊና በሌላ በኩል ደግሞ ለአውግስቡርድ የደስታ ሆኖ ነው ያለፈው። ፎርቱና ዱስልዶርፍ ከአንድ የውድድር ወቅት ሳያልፍ ወደመጣበት ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ሲከለስ አውግስቡርግ በአንጻሩ በመጨረሻ ቀን ድል ከውድቀት ሊያመልጥ ችሏል።

እንደነዚህ ግጥሚያዎች ሁሉ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ ማጣሪያ ለሚያበቃው አራተኛ ቦታ ወሣኝ የነበረው በፍራይቡርግና በሻልከ መካከል የተደረገ ግጥሚያም ትኩረትን የሳበ ነበር። ሻልከ በዚሁ ግጥሚያ 2-1 በማሸነፍ በአራተኝነት ተሳትፎውን አረጋግጧል። በዕለቱ የፓሪስ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ ወደ ፍራይቡርግ ሻገር በማለት በስታዲዮም ጨዋታውን ስትከታተል ስለ ሂደቱ በስልክ አነጋግሬያት ነበር።

1500 Meter Finale Weltmeisterschaften Leichtathletik 2011 Flash-Galerie
ምስል dapd

ሻንግሃይ ላይ ባለፈው ቅዳሜ ተካሂዶ በነበረው የዳያመንድ ሊግ ውድድር በወንዶች 1,500 ሜትር ኬንያዊው አስቤል ኪፕሮፕ ሲያሸንፍ ከኢትዮጵያ ገብረመድህን ገብረማሪያም ሁለተኛ ወጥቷል። በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ድሉ በሙሉ የኬንያውያን ነበር። ከአንድ እስከ ስምንት ተከታትሎ በመግባት አሸንፈዋል። በሴቶች 5 ሺህ ሜትር ገንዘቤ ዲባባ ስታሸንፍ መሠረት ደፋር ደግሞ ሁለተኛ ሆናለች። እንደተለመደው በአጭር ርቀት ሩጫ የጃሜይካና የአሜሪካ አትሌቶች ጠንካሮቹ ነበሩ።

Australian Open Tennis Sloane Stephens siegt im Viertelfinale 23. Januar 2013
ምስል AP

በትናንትናው ዕለት ተካሂዶ በነበረው የሮማ የቴኒስ ፍጻሜ ውድድር የስፓኙ ራፋኤል ናዳል የስዊስ ተጋጣሚውን ሮጀር ፌደረድን በተለየ ልዕልና 6-1,6-3 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በሴቶችም አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስ የቤላሩሷን ቪክቶሪያ አዛሬንካን በተመሳሳይ ውጤት ረትታለች። ናዳልና ዊሊያምስ ትናንት ያሣዩት አጨዋወት ለመጨው የፍሬንች ኦፕን ተፎካካሪዎቻቸው ብርቱ ማስጠንቀቂያ የሚሆን ነው።

ፓሪስ ላይ በተካሄደ የጠረጴዛ ቴኒስ የዓለም ሻምፒዮና ደግሞ ቻይናውያን ልዕልናቸውን እንደገና አስመስክረዋል። በመካከላቸው በለየለት ውድድር በወንዶች ሻንግ ዋንግ ሹ ሢንን በማሸነፍ የዓለም ማዕረጉን ሲያስመልስ በሴቶችም ሊ ሺያዎሢያ ሊዩ ሺዌንን አሸንፋለች።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ