1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 4 2006

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከናይጀሪያ አቻው ጋር ያደረገው ግጥሚያ ዋነኛ ርዕሳችን ነው። ለኢትዮጵያ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው በኃይሉ አሠፋ፣ ምን ያህል ተሾመ እና ከእረፍት መልስ ተቀይሮ ከሜዳ የወጣው አዳነ ግርማ ካነጋገርናቸው ውስጥ ይገኙበታል።

https://p.dw.com/p/19zPR
ምስል Reuters

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታዋን ጥቅምት 3 ቀን፣ 2006 ዓም አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ ከናይጀሪያ ተፎካካሪው ጋር በማድረግ 2 ለ1 ቢሸነፍም ድንቅ የእግር ኳስ ጥበብ የታየበት እንቅስቃሴ ለማድረግ ችሏል። በተለይ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ የኢትዮጵያ ቡድን ጥንካሬ ለናይጀሪያውያን ፈተና ነበር የሆነባቸው።

ትናንት በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ የመስመር እና የመሀል ዳኛው ያላፀደቋት ሆኖም ከመስፈር አልፋ በናይጀሪያ ተከላካይ እንደምንም የወጣችው ኳስ ክስተት ለናይጀሪያውያኑ ከፈተናም በላይ ዱብ ዕዳ ነበር የሆነችው። ምናልባትም ያች ግብ ብትፀድቅ ኖሮ የጨዋታዋን አጠቃላይ ሂደትና ውጤት ልትቀይር ትችል ነበር ሲሉ የሚቆጩ ጥቂቶች አይደሉም። ለናይጀሪያውያን በ66ኛው እና 90ኛው ደቂቃ ላይ ሁለቱን ግቦች ያስቆጠረው ኢማኑኤል ኤሚኒኬን አዳነ ግርማ ከእረፍት መልስ ተቀይሮ እስኪወጣ ድረስ ቀጥ አድርጎ ይዞት ነበር የቆየው

የዓለም ዋንጫ የሚካሄድበት ስታዲየም፥ ብራዚል
የዓለም ዋንጫ የሚካሄድበት ስታዲየም፥ ብራዚልምስል imago/Fotoarena

የትናንቱን ጨዋታ ከተከታተሉ ተመልካቾች መካከል ደግሞ የሁለት ሰዎችን አስተያየት አካተናል። የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ እዮብ አንሳው ይባላል በሰዎች ለሰዎች ለጋሽ ድርጅት ውስጥ ሰራተኛ ነው። የትናንቱን ጨዋታ እንደበርካቶቹ ተመልካቾች በስሜት ተውጦ ነው የተከታተለው።

የዶቸ ቬለ የአድማጮች ክበብ መስራች እና ፕሬዚዳንት ዋቆ ወንድሙ በበኩሉ ከጨዋታው ባሻገር በትናንትናው ጨዋታ የድጋፍ አሰጣጥ ወቅት የታዘብኩት ነገር አለ ይላል።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ለማነጋገር ከጠዋት አንስቶ የእጅ ስልካቸው ላይ ብንሞክርም ምላሽ ባለማግኘታችን ሊሳካልን አልቻለም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ወሳኙን የመልስ ጨዋታ ቅዳሜ፣ ኅዳር 7 ቀን 2006 ዓም ናይጀሪያ ካላባር ውስጥ ያደርጋል። ቡድኑ መልካም ዕድል እንዲገጥመው ከወዲሁ እንመኛለን።

ሠባስቲያን ቬተል
ሠባስቲያን ቬተልምስል Alexander Klein/AFP/Getty Images

አሁን በቀሩን ጥቂት ደቂቃዎች አጠር ያሉ ዘገባዎችን እናሰማችሁ። ትናንት በተካሄደው የቺካጎ ማራቶን የሩጫ ውድድር ኬንያውያን በወንዶችም በሴቶችም ድል ቀንቷቸው አምሽተዋል። በወንዶች የሩጫ ውድድር ኬኒያዊው ዴኒስ ኪሜቶ በ2 ሠዓት ከ 3 ደቂቃ ከ45 ሠከንድ በማጠናቀቅ አንደኛ ወጥቷል። ዴኒስ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያዊው ፀጋዬ ከበደ ያስመዘገበውን የ2 ሠዓት ከ4 ደቂቃ ከ38 ሠከንድ ውጤት ለማሻሻልም ተሳክቶለታል። በቺካጎው ማራቶን ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶስተኛ ተከታትለው ለመግባት ችለዋል። በሴቶች የማራቶን ሩጫ ውድድርም እንዲሁ ኬንያዊቷ ሪታ ጄፕቶ 2 ሠዓት ከ19 ደቂቃ ከ57 ደቂቃ በማስመዝገብ አሸናፊ ሆናለች። አፀደ ባይሳ፣ ኢህቱ ኪሮስ እንዲሁም አበበች አፈወርቅ 5ኛ፣ 6ኛ እና 8ኛ ወጥተዋል። አድማጮች በኢትዮጵያ እግር ኳስ እና አትሌቲክስ ዙሪያ አስተያየት መስጠት ከፈለጋችሁ ስልክ ቁጥራችሁን ላኩልን፤ ደውለን እናናግራችኋለን።

ጀርመናዊው የመኪና ሽቅድምድም ተወዳዳሪ ሠባስቲያን ፌትል የፎርሙላ አንድ ውድድርን ለአራተኛ ጊዜ ለማሸነፍ ወደ ድል መስመር እየተጠጋ ነው። ፌትል በእዚሁ ከቀጠለ የፊታችን ጥቅምት 17 ለአራተኛ ጊዜ ባለድል ይሆናል ማለት ነው። ሰባስቲያን ፌትል እስካሁን ለአራት ተከታታይ ጊዜያት አሸናፊ ሲሆን፤ በ15 ውድድሮች ላይም 9ኙን በማሸነፍ ጥንካሬውን ያስመሰከረ ተወዳዳሪ ለመሆን በቅቷል።

ዝርዝር ዘገባዉን ለማድመጥ ከታች ያለውን ማጫወቻ ይጫኑ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ