1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 19 2006

የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ አጀማመሩ አላማረም። በተደጋጋሚ ነጥብ ለመጣል ተገዷል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባየር ሙንሽን የድል ጎዳናውን ተያይዞታል። በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ተጋጣሚውን ድል ነስቷል። ሞገደኛው ባላቶሊ ሴሪኣውን ተሰናብቶ ወደ ሊቨርፑል ሊያቀና ነው። ኢትዮጵያውያን ወጣት አትሌቶች በቻይና ኒናንጃንግ ድል ቀንቷቸዋል።

https://p.dw.com/p/1D0yp
የቻይና ናንጂንግ የወጣቶች ኦሎምፒክ መክፈቻ
ምስል Reuters

በመጀመሪያም አትሌቲክስ፦

ቻይና ናንጂንግ ውስጥ በሚካሄደው ሁለተኛው የወጣቶች የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ፉክክር ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የወርቅ፣ የብር እና የነሐስ ሜዳዮችን አግኝተዋል ። በወንዶች የ2000 ሜትር የመሰናከል ሩጫ ወገኔ ሠብስቤ እንዲሁም በ1500 ሜትር የሩጫ ፉክክር ኮከብ ተስፋዬ አንደኛ በመውጣት ዛሬ ተጨማሪ የወርቅ ሜዳዮችን አስገኝተዋል። ወገኔ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 5 ደቂቃ ከ38.42 ደቂቃ ሲሆን፤ የኬንያው አሞስ ኪሩዪ በ5.40.29 የሞሮኮው ቼምላል ሐቻም በ5.40.94 ተከታትለው በመግባት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሆነዋል። ዘውድነሽ ማሞ በ2000 ሜትር የመሠናክል ሩጫ ሁለተኛ በመውጣት ተጨማሪ ብር አግንታለች።

ኮከብ ተስፋዬ አንደኛ ሆና ያጠናቀቀችው በ4 ደቂቃ ከ15. 38 ሠከንድ በመግባት ነው። ኬንያዊቷ ዊንፍሬድ ምቤቲ በ4.17.91 ሁለተኛ ስትወጣ የባሕሬኗ ሯጭ ደሊላ ጎሣ በ4.18.36 ሦስተኛ ወጥታለች።

ትናንት በወንዶች የ3000 ሜትር የሩጫ ውድድር ዮሚፍ ቀጄልቻ ውድድሩን በ7.56.20 በአንደኛነት በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ወርቅ አስገኝቷል። ዮሚፍ የትናንትና ድሉ በተመሳሳይ ርቀት በተከታታይ ለሦስተኛ ጊዜ የተቀዳጀው ሆኖ ተመዝግቦለታል። በእዚህ ውድድር የብሩንዲው ቲዬሪ ንዲኩምዌናዬ በ8.06.05 ሁለተኛ፣ የኬንያው ሞሰስ ኮዬች ከቲዬሪ በ28 ማይክሮ ሠከንዶች ለጥቂት ተቀድሞ ሦስተኛ ሆኗል።

ትናንት በተካሄደው የ1500 ሜትር የሩጫ ፉክክር ሙሉጌታ አሠፋ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳይ ወስዷል። በሴቶች የ3000 ሜትር ውድድር ብርሐን ደሚሳ ሦስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳይ አጥልቃለች። የጃፓኗ ምዞሚ ታካማትሱ እና የጀርመኗ አሊና ሬህ አንደኛ እና ሁለተኛ ወጥተዋል።

በ800 ሜትር የትናንት በስትያ ፉክክር የጋናዋ ቢሳህ ማርታ በ2. 04. 90 አንደኛ ስትወጣ ሐዊ ዓለሙ በ2. 06. 01 በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የብር ሜዳይ ማስገኘቷ ይታወቃል። በእዚሁ ውድድር የጀርመኗ ማሪን ካሊስ ከሐዊ በ2 ማይክሮ ሠከንዶች ተቀድማ ሦስተኛ በመውጣት ለጀርመን የነሐስ ሜዳይ አስገኝታለች። ከነሐሴ 10 ቀን 2006 ዓም አንስቶ እስከ ነሐሴ 22 ድረስ ለሁለት ሣምንታት የሚካሄደው ሁለተኛው የወጣቶች የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ፉክክር እስከ ፊታችን ሐሙስ ይዘልቃል።

እግር ኳስ

የቻይና ናንጂንግ የወጣቶች ኦሎምፒክ መክፈቻ
የቻይና ናንጂንግ የወጣቶች ኦሎምፒክ መክፈቻምስል Reuters

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድ ለሁለተኛ ግጥሚያው ሰንደርላንድን ገጥሞ አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ለመጣል ተገዷል። ሁለቱ ሲቲዎች፤ ሁል እና ስቶክ ተገናኝተው በተመሳሳይ አንድ ለአንድ አቻ ተለያይተዋል። ቶትንሐም በትናንትናው ሁለተኛ ጨዋታው ዳግም ድል በመቀዳጀት ተጋጣሚውን ኪው ፒ አርን 4 ለባዶ ሸኝቶታል ።

የማንቸስተር ዩናይትዱ የቀድሞ አሠልጣኝ ዴቪድ ሞዬስ ከመሸኘታቸው ጥቂት ቀድም ብሎ ሆላንዳዊው የማንቸስተር የአሁኑ አሠልጣኝ ሉዊስ ቫን ጋል ቶትንሐምን ሊያሠለጥኑ ነው የሚል ጭምጭምታ ተሰምቶ ነበር። አሠልጣኝ ቫንጋል የሆላንድን ብሔራዊ ቡድን እየመሩ በዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ፍልሚያ የወርቁን ዋንጫ ከጨበጡ ብዙም አልራቀ። እናስ አሁን የቡድናቸው ማንቸስተር ደካማ አጀማመርን እና ቀደም ሲል ሊያሠለጥኑት ነበር የተባለው ቶትንሐም ኃያልነትን ሲያጤኑ ምን ይሰማቸው ይሆን? «አንድ ነጥብ ነው ያለን ያ ደግሞ ለማንቸስተር ዩናይትድ በቂ አይደለም» አሉ ሆላንዳዊው አሠልጣኝ ሉዊስ ቫንጋል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ። «ብዙ መስራት ይገባናል። ከጨዋታው በኋላ ተጨዋቾቹ በጣም ተናደው ነበር ምክንያቱም እናሸንፋለን ብለው ነበር ያሰቡት» ሲሉ አክለዋል። ለማንኛውም ሉዊስ ቫንጋል አርጀንቲኒያዊው የሪያል ማድሪዱ የክንፍ ተመላላሽ ኤንጀል ዲ ማሪያን ሊያስመጡ ከስምምነት መድረሳቸውን የእንግሊዝ መገናኛ ዘዴዎች ዛሬ በስፋት ዘግበዋል። ዲ ማሪያ ካለፉት አራት ዓመታት አንስቶ ለስፔኑ ኃያል ሪያል ማድሪድ ለመሰለፍ የቻለ ድንቅ ተጨዋች ነው።

ከትናንት በስትያ አስቶን ቪላ ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር ያለምንም ግብ በመለያየት ነጥብ ተጋርተዋል። ጠንካራው ቸልሲ ሁለተኛ ጨዋታውን ከሌስተር ሲቲ ጋር አከናውኖ 2 ለባዶ ለማሸነፍ ችሏል። ዌስት ሐም ዩናይትድ ክሪስታል ፓላስን 3 ለ 1 አሸንፏል። አርሰናል ከኤቨርተን ጋር ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ ጥሏል። የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያሸነፉት ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል ዛሬ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ይገናኛሉ። ሁለቱም ኃያላን ከመሆናቸው አንፃር በሁለተኛ ጨዋታቸው ነጥብ ላለመጣል የሚያደርጉት ፍልሚያ ግጥሚያውን የሚጠበቅ አድርጎታል።
ተናካሹ ሉዊስ ሱዋሬዝን በ94 ሚሊዮን ዩሮ ለስፔኑ ባርሴሎና የሸጡት ሊቨርፑሎች ካዝናቸው አሁንም የተሟጠጠ አይመስልም። የኤስ ሚላኑ አጥቂ ጣሊያናዊው ማሪዮ ባሎቴሊን በጠየቀው 16 ሚሊዮን ዩሮ የዝውውር ክፍያ በእጃቸው ሊያስገቡት እንደሆነ ተነግሯል። ባሎቴሊ የቀድሞው ቡድኑ ማንቸስተር ሲቲ ከሊቨርፑል ጋር በሚያደርገው ግጥሚያ መሰለፍ ባይችልም ስታዲየም ታድሞ ጨዋታውን ሊመለከት እንደሚችል ግን ተዘግቧል። ሊቨርፑሎች እስካሁን 8 አዳዲስ ተጨዋቾችን ለመግዛት ችለዋል።

በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ የትናንትና ግጥሚያ ፓዴርቦርን ከማይንስ ጋር ሁለት እኩል ተለያይቷል። ዘንድሮ በእድገት ወደ ቡንደስ ሊጋው ለገባው ፓዴርቦርን የትናንትናው ውጤት የድል ያህል ነው የተቆጠረው። ፓዴርቦርኖች በትናንቱ የመጀመሪያ የቡንደስሊጋ ጨዋታቸው አንድ ነጥብ ለማግኘት ችለዋል።

በትናንትናው ሌላኛው ግጥሚያ ሞንሼንግላድባህ ከሽቱትጋርት ጋር አቻ ተለያይቷል።የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ክሪስቶፍ ክራመር በ90ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ቡድኑ ሞንሼንግላድባህን ከመሸነፍ ባለቀ ሠዓት ታድጓል። ክሪስቶፍ ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ በሰጠው መግለጫ እንዲህ አቻ የምታደርገውን ግብ ባለቀ ሠዓት ማስቆጠሩ ተጋኖ ሊወራ እንደማይገባ ጠቅሷል።

«አዎ ዳግም ቦቦታው ላይ ነበርኩ። አቻ የምታደርገንን ግብ በማስቆጠሬ ደስተኛ ነኝ። ግን ያን ብዙም ማጋነን አይገባንም»

የሞንሽንግላድባህ አሠልጣኝ ሉሲየን ፋቭሬ ግን በክሪስቶፍ ክራመር ብቃት እጅግ መደነቃቸውን አልሸሸጉም። የ23 ዓመቱ ወጣት አማካይ፣ ክሪስቶፍ ክራመርን የዓለም ዋንጫ ድል የተቀዳጀ ባለድል ሲሉ አወድሰውታል።

«የዓለም ዋንጫ ባለድል ነው ያለን። ለ20 ደቂቃዎች ወደ ሜዳ ቢገባ አንድ ግብ አስቆጠረ። »

ክሪስቶፍ ክራመር የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ በመሆኑ ከዓለም ዋንጫ ድል በኋላ የብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች በተሰጣቸው ልዩ እረፍት ምክንያት እስከ ባለፈው ሦስት ሣምንት ድረስ እረፍት ላይ ነበር። ከቡድኑ ጋር ስልጠና ከጀመረ 20 ቀናት ያስቆጠረው ክሪስቶፍ በስልጠና ወቅት አንድ ግብ ሊያስቆጥር እንደሚችል ሲዝት እንደነበር አሠልጣኙ መስክረዋል።

ክሪስቶፍ ክራመር
ክሪስቶፍ ክራመርምስል Getty Images
ዲ ማሪያ ፍፁም ቅጣት ምት
ዲ ማሪያ ፍፁም ቅጣት ምትምስል picture-alliance/dpa

በስፔን ላሊጋ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያ ኃያሉ ባርሴሎና፣ ሴልታቪጎ እና ቪላሪያል ትናንትድ ድል ቀንቷቸዋል። ባርሳ ኤልቼን በሰፋ ልዩነት 3 ለባዶ አሸንፏል። ቪላሪያል ሌቫንቴን አስተማማን በሆነ መልኩ 2 ለባዶ ረትቷል። ሴልታቪጎ ጌታፌን 3 ለ አንድ ሸኝቷል። ከትናንት በስትያ ግራናዳ ዴፖርቲቮ ኮሩናን 2 ለ 1፣ ማላጋ አትሌቲክን 1 ለዜሮ አሸንፈዋል። ሴቪላ ከቫሌንሺያ እንዲሁም አልሜሪያ ከኤስፓኞላ አንድ እኩል አቻ ተለያይተዋል።

አጠር አጠር ያሉ የስፖርት ዜናዎች

የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን አጥቂ አልጄሪያ እግር ኳስ ሜዳ ውስጥ ከደጋፊ በተወረወረ ድንጋይ ጭንቅላቱን ተመትቶ ሕይወቱ ማለፉን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል። አልበርት ኤቦሴ የተሰኘው ካሜሩናዊ ትናንት በደረሰበት አደጋ ነው ሐኪም ቤት ውስጥ ማረፉ የተነገረው። ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑ ተዘግቧል። ለአልበርት ሕይወት መጥፋት ሰበብ የሆነው ድንጋይ የተወረወረው አልበርት የሚጫወትበት ቡድን ደጋፊዎች ከሚቀመጡበት አግጣጫ መሆኑም ታውቋል። አልበርት በድንጋይ ከመመታቱ በፊት ለቡድኑ ብቸኛዋን ግብ አስቆጥሮ ነበር። ሆኖም ቡድኑ ጄኤስ ካቢሌ 2 ለ1 መሸነፉ ያበሳጫቸው ደጋፊዎች በፈጠሩት ትርምስ ሌሎች ተጨዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል ሮጠው ማምለጥ ችለዋል። የ24 ዓመቱ ወጣት አጥቂ ግን ጥቃት ከደረሰበት ስታዲየም 500 ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ሐኪም ቤት ቢወሰድም ሊተርፍ አልቻለም። የአልጄሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥቃት አድራሹ ተይዞ ከባድ ቅጣት እንደሚፈፀምበት ያላቸውን ተስፋ ገልጠዋል።

የመኪና ሽቅድምድም

ካሜሩናዊው አጥቂ አልበር ኤቦሴ
ካሜሩናዊው አጥቂ አልበር ኤቦሴምስል Youtube.com

በትናንትናው የቤልጂየሙ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ዳኒኤል ሪካርዶ አሸናፊ ሆነ። አውስትራሊያዊው የሬድ ቡል መኪና አሽከርካሪ ዳናኤል የማርሴዲስ ተፎካካሪው ኒኮ ሮዘንበርግ ጥሶ ነው ያሸነፈው። ቫልተሪ ቦታስ ኒኮን ተከትሎ በዊሊያምስ ሦስተኛ ሆኗል። ኪሚ ራይኮነን በፌራሪ ተሽከርካሪው አራተኛ ሲወጣ፤ የሬድ ቡሉ ሠባስቲያን ቬትል በ5ኛነት ደረጃ ለማጠናቀቅ ተገዷል።

ቡጢ

ወንድማማቾቹ ቭላድሚር እና ቪታሊ ክሊችኮ
ወንድማማቾቹ ቭላድሚር እና ቪታሊ ክሊችኮምስል picture-alliance/dpa

የከባድ ሚዛን ቡጢ ባለድሉ ቭላድሚር ክሊችኮ ቀበቶውን ለማስጠበቅ ከቡልጋሪያዊው ኩርባርት ፓሌቭ ጋር ሊያደርገው የነበረው የቡጢ ግጥሚያ መሰረዙ ተነገረ። ቭላድሚር ኮብራው በሚል ቅፅል ከሚጠራው ኩባርት ጋር ከጥቂት ቀናት በኋላ ለመጋጠም ቀጠሮ ይዞ ነበር። ሆኖም በልምምድ ወቅት በደረሰበት የጡንቻ መሰንጠቅ ከኮብራው ጋር ሊያደርገው ቀጠሮ የተያዘለት ፍልሚያ መሰረዙን አሠልጣኙ ዛሬ አስታውቀዋል። ሰሞኑን በጀርመን ቴሌቪዥኖች ሁለቱም ተፋላሚዎች ቀርበው በጀርመንኛ ሲዛዛቱ ነበር። ኩርባርት ከፍጥነቴ የተነሳ እኔን ሰዎች ኮብራው እያሉ ነው የሚጠሩኝ ሲል ቭላድሚር ክሊችኮን ሊያስፈራራ ሲሞክር፤ ብላድሚር በበኩሉ ኮብራው በቅርቡ እንገናኛለን እያለ ሲዝትበት ነበር። ሆኖም ቭላድሚር በደረሰበት የጡንቻ መሰንጠቅ ውድድሩ መሰረዙ ተነግሯል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ