1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 28 2001

ባለፈው ሰንበት ከሮተርዳም እስከ ፓሪስ፤ ከፓሪስ እስከ በርሊን የማራቶን ሩጫ ውድድሮች ሲካሄዱ ሁሉም በተለይ የኬንያ አትሌቶች የበላይነት የታዩባቸው ነበሩ።

https://p.dw.com/p/HRLA
ቡንደስሊጋ፤ የቮልፍስቡርግ አጥቂ ግራፊትና የሣምንቱ አስደናቂ ጎል
ቡንደስሊጋ፤ የቮልፍስቡርግ አጥቂ ግራፊትና የሣምንቱ አስደናቂ ጎልምስል AP

አትሌቲክስ

ባለፈው ሰንበት ከሮተርዳም እስከ ፓሪስ፤ ከፓሪስ እስከ በርሊን የማራቶን ሩጫ ውድድሮች ሲካሄዱ ሁሉም በተለይ የኬንያ አትሌቶች የበላይነት የታዩባቸው ነበሩ።

አትሌቲክስ

በሮተርዳሙ ማራቶን ሶሥት ኬንያውያን ተከታትሎ በመግባት የተሟላ ድል ሲያስመዘግቡ ሩጫውን በአንደኝነት የፈጸመው ዱንካን ኪቤት ነው። ኪቤት ግሩም በሆነ 2 ሰዓት ከ 4 ደቂቃ ከ 27 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ጀምስ ኩዋምባይ በተመሳሳይ ጊዜ ሁለተኛ ሆኗል። ሶሥተኛው ኬንያዊ ደግሞ አቤል ኪሩዊ ነበር። ኪሩዊም ሩጫውን የፈጸመው ፈጣን በሆነ 2 ሰዓት ከ 5 ደቂቃ ከ 04 ሤኮንድ ነው። ኪቤት አሸናፊ የሆነበት ሰዓት በሮተርዳም ማራቶን ታሪክ እስካሁን ፈጣኑም ነበር። በሴቶች ደግሞ ሩሢያዊቱ ናይሊያ ዩላማኖቫ አሸናፊ ሆናለች።

በፓሪስ ማራቶን ምንም እንኳ የወንዶች አሸናፊ ኬንያዊው ቪንሤንት ኪፕሩቶ ለመሆን ቢበቃም የኢትዮጵያ አትሌቶችም ብርቱ ጥንካሬ አሳይተዋል። ኪፕሩቶ በ 2 ሰዓት ከ 5 ደቂቃ ከ 47 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሽንፍ ይህም በማራቶን ታሪክ ውስጥ ዘጠነኛው ፈጣን ጊዜ መሆኑ ነው። ኢትዮጵያዊው በዙ ወርቁ በግማሽ ሤኮንድ ያህል በመቀደም ሁለተኛ ሲወጣ ሌላው ኬንያዊ ዴቪድ ኪዬንግ ሶሥተኛ ሆኗል። ከሁለት ሰዓት አራት ደቂቃ በታች የሆነው ብችኛ የዓለም የማራቶን ክብረ-ወሰን ካለፈው ዓመት የበርሊን ማራቶን ወዲህ በሃይሌ ገ/ሥላሴ ዕጅ መሆኑ ይታወቃል። በተቀረ የፓሪሱ ማራቶን የኢትዮጵያ ሴቶች የበላይነት የሰመረበት ነበር። አጸደ ባይሣ ፈጣን በሆነ ጊዜ ስታሽንፍ አሰለፈች መርጊያ ደግሞ ሁለተኛ ለመሆን በቅታለች። ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመችው ፈረንሣዊቱ ክሪስቴል ዳውኒይ ነበረች።

ትናንት በዚህ በጀርመን ተካሂዶ የነበረው 29ኛው የበርሊን ግማሽ-ማራቶን ሩጫ ውድድርም ኬንያውያን አይለው የታዩበት ሆኖ ነው ያለፈው። ጠንካራ ፉክክር በታየበት ሩጫ በርናርድ ኪፕዬጎ በ 59 ደቂቃ ከ 34 ሤኮንድ ሲያሽንፍ ሣሚይ ኮስጋይ በሁለት መቶኛ ሤኮንድ ብቻ በመቀደም ሁለተኛ ሆኗል። ሶሥተኛው ኬንያዊ ዊልሰን ኪፕሮቲችም ሩጫውን የፈጸመው ኮስጋይን በቅርብ በመከተል ነው። በሴቶች ጀርመናዊቱ ዛብሪና ሞከንሃውት ሩጫውን በአንደኝነት ስትፈጽም ኬንያውያኑ አትሌቶች ሄለን ኪሙታይና ሊዲያ እንጄሪ ሁለተኛና ሶሥተኛ ወጥተዋል።
በተረፈ ዓለምአቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የሴቶች ቡጢ ከመጪው የ 2012 ዓ.ም. የለንደን ኦሎምፒክ ጀምሮ ለውድድር ይብቃ አይብቃ በፊታችን ነሐሴ ወር እንደሚወስን ከስዊትዘርላንድ መቀመጫው ከሉዛን ተገልጿል። ቡጡ ከ 26ቱ የኦሎምፒክ ስፖርት ዓይነቶች አንዱ ሲሆን ብቸኛው ሴቶች የማይካፈሉበት ዲሢፕሊን ነው። ለኦሎምፒኩ ኮሚቴ ሃሣቡን ያቀረበው ዓለምአቀፉ የአማተር ቡጡ ማሕበር ነው።

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውስጥ ውድድሩ ቀስ በቀስ ወደ መጠናቂቂያው መቃረብ በያዘበት ወቅት ሣምንቱ ለአብዛኞቹ መሪ ቡድኖች የሰመረ ነበር። ሰንበቱን በሽንፈት ብቻ ሣይሆን በውርደት ጭምር ያሳለፈው የጀርመኑ የብዙ ጊዜ ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን ብቻ ነው። በዚሁ ለመጀመር ዘንድሮ የጠበበ የሻምፒዮንነት ፉክክር ሰፍኖ የቀጠለበት ቡንደስሊጋ ከሰንበቱ ውጤቶች ወዲህ አዲስ መሪ አግኝቷል። ይሄውም ሃያሉን ባየርን ሙንሺንን 5-1 በመቅጣት እንዳልነበር አድርጎ ከሜዳ ያስወጣው ቮልፍስቡርግ ነው። ቡድኑ ግሩም ጨዋታ ሲያሳይ በተለይም ብራዚላዊ አጥቂው ግራፊት የባየርንን ተከላካዮች ተራ በተራ ካታለለ በኋላ በተረከዙ ለኮፍ አድርጎ ያስገባት ጎል ግሩም ነበረች። የባየርን ሙንሺንን ተጫዋቾች ቅስም ከሁሉብ በላይ የሰበረችው ይህቺው ጎል ናት። የአጠቃላዩ ጨዋታ ትውስት ለባየርን አሁንም ቁስል እንደሆነ ነው። አሠልጣኙ ዩርገን ክሊንስማን!

“ጨዋታው ሲያበቃ የተሰማን ብርቱ ውርደት ነበር። ከሶሥት ዓመታት በፊት ደርሶ የነበረው እንዳይደገም ቡድኑን አስጠንቅቄያለሁ። ያኔ ከፌሊክስ ማጋት፤ ከአሁኑ የቮልፍስቡርግ አሠልጣኝ ጋር መሆኑ ነው፤ ቡድኑ ድርብ ሻምፒዮን ከሆነ በኋላ ድንገት ወደ አራተኛ ቦታ በማቆልቆል በዩኤፋ ዋንጫ ውድድር ደረጃ መወሰኑ አይዘነጋም። ፌሊክስም በዚሁ ይሰናበታል። እርግጥ ገና የጀርመን ሻምፒዮን መሆን እንችላለን። ግን ይህ እንዲሆን መልሰን ጠቃሚ በሆነው ነገር ላይ ማተኮር ይኖርብናል። ቡንደስሊጋ እንዲህ ነው”
በእርግጥም ድሉ የቮልፍስቡርግ ብቻ አልነበረም። ባየርን ሙንሺን አንዴ ላባረረው ለቡድኑ አሠልጣኝ ለፌሊክስ ማጋትም የተለየ የመንፈስ እርካታን መስጥቱ አልቀረም። በሌላ በኩል የሊጋውን አመራር ለሁለት ሣምንታት ያህል ይዞ የነበረው በርሊን በገዛ ሜዳው በዶርትሙንድ 3-1 ተሸንፎ ወደ ታች ሲንሸራተት ሃምቡርግ በፊናው ሆፈንሃይምን 1-0 በመርታት ሁለተኛነቱን ይዟል። በአጠቃላይ ቮልፍስቡርግና ሃምቡርግ 51 እኩል ነጥቦች አሏቸው፤ ቮልፍስቡርግ የሚመራው በጎል ልዩነት ነው። በርሊን በ 49 ነጥቦች ሶሥተኛ፤ ባየርን በ 48 አራተኛ! ሊፈጸም ስምንት ግጥሚያዎች ብቻ የቀሩት የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ፉክክሩ የጠነከረበት እንደሆነ ይቀጥላል።

ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እንሻገርና ሶሥቱም ቀደምት ቡድኖች ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ሊቨርፑልና ቼልሢይ ለሻምፒዮንነት በሚያደርጉት ትግል ሣምንቱን በድል ነው ያሳለፉት። ማንቼስተር ዩናይትድ ትናንት ኤስተን ቪላን በመጨረሻዋ ደቂቃ 3-2 ሲረታ አመራሩን መልሶ ሊይዝ በቅቷል። ወሣኟን የመጨረሻ ግብ ያስቆጠረው ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰለፈው ወጣት ተጫዋች ፌደሪኮ ማቼዳ ነበር። ሊቨርፑል ፉልሃምን 1-0 ሲያሽንፍ በአንዲት ነጥብ ልዩነት ሁለተኛ ነው። ቼልሢይ ደግሞ ኒውካስል ዩናይትድን 2-0 ሲረታ በሶሥተኝነት ይከተላል። ሆኖም ከአንደኛው ቦታ የሚለዩት አራት ነጥቦች ብቻ ናቸው። ሻምፒዮናው ከሣምንት ሣምንት በሶሥቱ መካከል የሚለይለት እየመሰለ በመሄድ ላይ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኢንተር ሚላን ለተከታይ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን በያዘው ጥረት እንደገና የተሳካ ዕርምጃ አድርጓል። ኢንተር ኡዲኔሰን 1-0 ሲረታ አሁን በዘጠኝ ነጥቦች ልዩነት ይመራል። ሁለተኛው ጁቬንቱስ ከቬሮና 3-3 ሲለያይ ኤ.ሢ.ሚላን ደግሞ ሌቼን 2-0 በማሸነፍ በሶሥተኝነቱ እንደቀጠለ ነው። ሆኖም ከኢንተር ጋር ያለው የ 14 ነጥብ ልዩነት ሲታሰብ የሻምፒዮና ሕልሙ አልቆለታል። ዘንድሮ ለሚቀጥለው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ተሳትፎ የሚያበቃውን ሶሥተኛ ቦታ ከጠበቀ ትልቅ ነገር ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮንም ሁኔታው ከሞላ-ጎደል ከኢጣሊያው ሊጋ ይመሳሰላል። ቀደምቱ ክለቦች ባርሤሎናና ሬያል ማድሪድ ሁለቱም የውጭ ግጥሚያቸውን 1-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፉ ባርሣ በስድሥት ነጥቦች መምራቱን ቀጥሏል። ሆኖም የሊጋው ውድድር ሊጠናቀቅ ገና ዘጠኝ ግጥሚያዎች ስለሚቀሩ ሬያል አመራሩን ለመያዝ ገና ዕድል አለው። እርግጥ ባርሤሎና ደጋግሞ ከተሽነፈ ማለት ነው። በተቀረ ሤቪያ ሶሥተኛ፤ ቪላርሬያል አራተኛ፤ እንዲሁም ቫሌንሢያ አምሥተኛ ነው።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ኦላምፒክ ሊዮን በአንዲት ነጥብ ልዩነት እየመራ ሲሆን ማርሤይ ይከተለዋል፤ በአጠቃላይ ስድሥት ክለቦች ሻምፒዮን የመሆን ዕድል አላቸው። በኔዘርላንድ በአንጻሩ አልክማር አመራሩን ወደ 11 ነጥቦች ከፍ ሲያደርግ ከእንግዲህ የሚደርስበት መኖሩ ሲበዛ ያጠራጥራል። በፓርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ ፖርቶ ስፖርቲንግ ሊዝበንን በአራት ነጥብ ብልጫ እንዳስከተለ ነው፤ ቤንፊካ ሶሥተኛ!

በተቀረ ነገና ከነገ በስቲያ የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ የሩብ ፍጻሜ ዙር የመጀመሪያ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በውድድሩ ሂደት ተጣርተው ከቀሩት ስምንት ቡድኖች አራቱ የእንግሊዝ ክለቦች ሲሆኑ በነገው ምሽት አርሰናል ከቪላርሬያል፤ ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ ከፖርቶ ይጋጠማሉ። በማግሥቱ ረቡዕ በሁለቱ የእንግሊዝ ቡድኖች በሊቨርፑልና በቼልሢያ መካከል የሚካሄደው ግጥሚያ እርግጥ ጠንካራው የሚሆን ነው የሚመስለው። ያሳዝናል ሩብ ፍጻሜው ለአንዱ መሰናበቻው መሆኑ።

ሌላው የረቡዕ ግጥሚያ በባርሤሎናና በቫየርን ሙንሺን መካከል የሚካሄደው ሲሆን በቡንደስሊጋ የሰንበት ጨዋታው 5-1 ተቀጥቶ ከሜዳ የወጣው የባየርን ተጫዋቾች ለዚህ ከባድ ፈተና አስፈላጊውን በራስ መተማመን መልሰው ማስፈናቸው ጥቂትም ቢሆን የሚያጠያይቅ ነው። የስፓኝ ጋዜጦች በበኩላቸው አሠልጣኙ ዩርገን ክሊንስማን ይህን ለማግኘት የአዕምሮ ሣይንስ መጻሕፍት ማገላበጥ ሳይኖርበት አይቀርም ሲሉ ነው የተቹት። ያም ሆነ ይህ የባርሣ ተጫዋቾች በንቀት መንፈስ ሜዳ መግባታቸው ያጠራጥራል። ምክንያቱም ቀደም ያሉ ግጥሚያዎች ያሳዩት ባየርን ለስፓኝ ክለቦች ቀላል ተጋጣሚ አለመሆኑን ነው።

ቴኒስ

ማያሚ-ፍሎሪዳ ላይ ትናንት በተካሄደው ዓለምአቀፍ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያ የብሪታኒያው ኤንዲይ መሪይ የሰርቢያ ተጋጣሚውን ኖቫክ ጆኮቪችን በሁለት ምድብ ጨዋታ በማሸነፍ ለዓመቱ ሶሥተኛ የኤ.ቲ.ፒ.-ማስተርስ ድሉ በቅቷል። መሪይ በመጀመሪያው ምድብ በከፊል ደከም ከማለቱ በስተቀር በአጠቃላዩ ጨዋታ በአዕምሮ ንቃት፣ አጨዋወትን በመለዋወጥ ስልትና በተለመደ ጠንካራ የመከላከል ችሎታው የላቀው ነበር። በሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ የቤላሩሷ ወጣት ተጫዋች ቪክቶሪያ አዛሬንካ በዓለም የማዕርግ ተዋረድ ላይ አንደኛ የሆነችውን አሜሪካዊት ሤሬና ዊሊያምስን ረትታለች። አዛሬንካ 6-3, 6-1 በሆነ በለየለት ውጤት ስታሽንፍ እርግጥ ሤሬና በአካል ጉዳት የተነሣ በሙሉ አቅሟ ልትጫወት አልቻለችም።

ፎርሙላ አንድ

ለማጠቃለል ትናንት ማሌዚያ ውስጥ በተካሄደ የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም የብሪታኒያው አሽከርካሪ ጄንሰን ባተን አሸናፊ ሆኗል። እሽቅድድሙ በአዲሱ የውድድር ዓመት ሁለተኛው ሲሆን ባለፈው ሣምንት ሜልበርን ላይ ተካሂዶ በነበረው በመጀመሪያውም ያሸነፈው ባተን እንደነበር አይዘነጋም። የጀርመን ተወዳዳሪዎች ኒክ ሃይደፌልድና ቲሞ ግሎክ ደግሞ ሁለተኛና ሶሥተኛ ሆነዋል።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ