1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 13 2001

ያለፈው ሣምንት በአውሮፓ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ አስከፊ የሆነው በእንግሊዝ የሼፊልድ ሂልስቦሮህ ስታዲዮም የደረሰው አደጋ ሃያኛ ዓመት የታሰበበት ነበር። በሣምንቱ አጋማሽ ላይ የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋና የዩኤፋ ማጣሪያ ግጥሚያዎች፤ የሰንበቱ የሊጋ ውድድሮችም የተካሄዱት ይሄው አሳዛኝ ትውስት ጋርዷቸው ነው።

https://p.dw.com/p/HagC
ቡንደስሊጋ፤ የቮልፍስቡርግ ፌስታ ቀጥሏል
ቡንደስሊጋ፤ የቮልፍስቡርግ ፌስታ ቀጥሏልምስል picture-alliance / Pressefoto ULMER / Lukas Coch

የሂልስቦሮህ ስታዲዮም አደጋ በአውሮፓ ውስጥ እስከዛሬ ከሚታወቀው የኳስ ሜዳ ቀውስ ሁሉ የከፋው ነው። እ.ጎ.አ. ሚያዚያ 15 ቀን 1989 ዓ.ም.! ባለፈው ረቡዕ ሃያ ዓመት የሞላው ያ ዕለት እንደ ብዙዎች የእንግሊዝ እግር ኳስ አፍቃሪዎች ቢሆን ግሩም ሆኖ ባለፈ ነበር። በኖቲንግሃም ፎረስትና በሊቨርፑል መካከል የእንግሊዝ ፈደሬሺን ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ዙር ግጥሚያ ከተጀመረ አሥር ደቂቃ እንኳ ሳይሞላው ያልታሰበው ቀውስ ይደርሳል። የብሪታኒያ ራዲዮ ቢ.ቢ.ሲ. በጊዜው እንዲህ ነበር የዘገበው።

“በሂልስቦሮህ ስታዲዮም ምዕራባዊ ትሪቡን አንዳንድ የመቆሚያ ቦታዎች ገና ከወዲሁ ጢም ብለር ሞልተው ነበር። ሆኖም ግን ተጨማሪ የሊቨርፑል ደጋፊዎች ከበስተጀርባ እየገቡ ፊት ያሉትን ተመልካቾች ከመከላከያው አጥር ጋር ያጣብቃሉ። እነዚሁ አጥሩን ዘለው ሜዳ በመግባታት ራሳቸውን ለማዳን መሞከራቸው አልቀረም። ግን ፖሊስ ያግዳቸዋል”

መጨረሻው አስከፊና አሰቃቂ ነበር። ከተመልካቾቹ 96 ይሞታሉ፤ 730 የሚሆኑም ይቆስላሉ። ከአደጋው ሰለቦች አብዛኞቹ ዕድሜያቸው ከሃያ በታች የሆነ ወጣቶች ነበሩ። በጉዳዩ የተካሄደ ምርመራ ውጤት ወደ ስታዲዮም የሚጎርፈውን ተመልካች በጊዜው ቦታ እንዲይዝ አላደረጉም በሚል ለቀውሱ ተጠያቂ ያደረገው ፖሊስን ነው። ከዚያ አራት ዓመታት ቀደም ሲል በብራስልስ-ሃይዘል ስታዲዮም በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ግጥሚያ ፖሊሶች ማምለጫ ደጃፎችን ዘግይተው በመክፈታቸው ተመሳሳይ ቀውስ መድረሱ የሚዘነጋ አይደለም። ተወቃሾቹ ሁለቱንም ጊዜ ሥነ ሥርዓእት አስከባሪዎቹ ነበሩ። ለማንኛውም በነዚህ ሁለት አደጋዎች የተነሣ በስታዲዮም ደህንነት ረገድ ጠቃሚ ትምሕርት ነው የተገኘው።

ወደ አውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የሰንበት ግጥሚያዎች እንመለስና በየቦታው ወደ መጨረሻው እየተቃረበ በላው ውድድር በኔዘርላንድ ሻምፒዮናው ከወዲሁ ለይቶለታል። ውድድሩ ሊያበቃ ሶሥት ግጥሚያዎች ቀርተውት ሳለ ለዚሁ ክብር የበቃው የዘንድሮው አስደናቂ ከለብ አልክማር ነው። አልክማር በቅዳሜ ግጥሚያው ምንም እንኳ በአርንሃይም 2-1 ቢሽነፍም አያክስ አምስተርዳም በአይንድሆፈን 6-2 መረታቱ ነው ሻምፒዮንነቱን ከወዲሁ ማክበር እንዲችል ያበቃው። ክለቡ ለዚህ ድል ሲበቃ ከ 28 ዓመታት ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ይሆናል። 11 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛው ኤንሼዴ ሲሆን አያክስ አምስተርዳም በሶሥተኝነት በቅርብ ይከተለዋል። ያለፉት ዓመታት ግንባር ቀደም ክለብ አይንድሆፈን በአንጻሩ ለመጪው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር መድረሱ ራሱ ያጠራጥራል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰንበቱን ይበልጥ ያደመቁት የፌደሬሺኑ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ነበሩ። በዝነኛው ዌምብሌይ ስታዲዮም ባለፈው ቅዳሜ በአርሰናልና በቼልሢይ መካከል በተካሄደው ግጥሚያ ቼልሢይ 2-1 በማሽነፍ ወደ ፍጻሜው አልፏል። ሁለተኛዋን የድል ጎል ዘግየት ባለ ሰዓት ያስቆጠው የአይቮሪ ኮስቱ ኮከብ ዲዲየር ድሮግባ ነበር። ትናንት ደግሞ በዚያው በዌምብሌይ የተካሄደው የሁለተኛው ግጥሚያ ውጤት የተጠበቀ አልነበረም። በዚሁ ግጥሚያ ኤቨርተንና ማንቼስተር ዩናይትድ በመደበኛና በተጨማሪ ጊዜ ባዶ-ለባዶ ሲለያዩ ኤቨርተን በፍጹም ቅጣት ምት 4-2 ለማሸነፍ በቅቷል።

ሁለት ፍጹም ቅጣት ምቶችን በማክሸፍ ለኤቨርተን ድል ዋስትና የሆነው የቀድሞው የዩናስትድ በረኛ ቲም ሃዋርድ ነበር። ኤቨርተን ከ 14 ዓመታት በኋላ ለፍጻሜ መድረሱ ሲሆን ከቼልሢይ ጋር ለዋንጫ የሚገናኘው በፊታችን ግንቦት 22 ቀን ነው። በተረፈ ከዚሁ ግን ለጎን በተካሄዱ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ቶተንሃም ሆትስፐር ኒውካስል ዩናይትድን 1-0 ሲረታ ማንቼስተር ሢቲይ ደግሞ ብሮንዊች አልቢዮንን 4-2 አሸንፏል። ፔሚየር ሊጉን በቀደምትነት የሚመራው ማንቼስተር ዩናይትድ ሲሆን ሊቨርፑልና ቼልሢይ በቅርብ ይከተሉታል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ በአንጻሩ ኢንተር ሚላን ከጁቬንቱስ 1-1 ቢለያይም የሊጋው ውድድር ስድሥት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተውት ሳለ በአሥር ነጥብ ልዩነት ተዝናንቶ መምራቱን ቀጥሏል። ኤ.ሢ.ሚላን ቶሪኖን 5-1 ሲረታ የሰንበቱ ዋነኛ ተጠቃሚ ነው። ከጁቬንቱስ ጋር እኩል ነጥብ ሲኖረው በጎል ብልጫ ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ብሏል፤ አራተኛ ጌኖዋ፤ አምሥተኛ ፊዮሬንቲና ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮንም ሰባት ግጥሚያዎች ቀርተው ባርሤሎና በስድሥት ነጥቦች ይመራል። ባርሣ አርጄንቲናዊ ኮከቡ ሊዮኔል ሜሢ ባስቆጠራት ብችኛ ግብ አማካይነት ጌታፌን 1-0 ሲረታ ሬያል ማድሪድም ሁዌልቫን በተመሳሳይ ውጤት በማሸነፍ በሁለተኝነት እየተከተለው ነው። ሤቪያ በቫሌንሢያ 3-1 ቢረታም ሶሥተኘቱን እንደያዘ ቀጥሏል፤ ቫሌንሢያም አራተኛ ነው።

የሻምፒዮናው ፉክክር እንደጠበበ በቀጠለበት በጀርመን ቡንደስሊጋ የማይበገር ሆኖ የተገኘው ቮልፍስቡርግ ሌቨርኩዝንን 2-1 በማሽነፍ በሶሥት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። ባየርን ሙንሺን ቢለፌልድን 1-0 ሲረታ ሁለተኛ ነው፤ ሃኖቨርን 2-1 ያሸነፈው ሃምቡርግ ደግሞ በተመሳሳይ ነጥብ ሶሥተኛ ሆኖ ይከተለዋል። ሄርታ በርሊን በተከታታይ ሶሥት ጨዋታዎችን በመሸነፍ ካቆለቆለ በኋላ ትናንት ብሬመንን 2-1 በመርታት አራተኛ ቦታውን ለማስከበር ችሏል። አምሥተኛው ኮሎኝን 3-0 የሽኘው ሽቱትጋርት ነው።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ባለፈው ሣምንት አመራሩን ከኦላምፒክ ሊዮን የነጠቀው ማርሤይ ሎሪየንትን 2-1 ሲያሸንፍ በሁለት ነጥቦች ልዩነት ቁንጮ ሆኖ ቀጥሏል። ለኦላምፒክ ሊዮን ይህም ሣምንት የቀና አልነበረም። በዢሮንዲን ቦርዶው ተሸንፎ ከሁለተኛ ወደ ሶሥተኛ ቦታ ማቆልቆሉ ግድ ነው የሆነበት። በተቀረ በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶ የሰንበት ግጥሚያውን በማሸነፍ ሊጋውን በአራት ነጥቦች ልዩነት እንደመራ ነው።

በትናንትናው ዕለት ጃፓን-ናጋኖ ላይ ተካሂዶ በነበረ የማራቶን ሩጫ ኬንያዊው አይዛክ ማቻሪያ ሲያሸንፍ ግርማ ቶላ ከኢትዮጵያ ሁለተኛ ሆኗል። ሶሥተኛ ሣይመን ዋንጋይ ከኬንያ፤ አራተኛ ግደይ አምሃ ከኢትዮጵያ! በሴቶች ደግሞ ሩሢያዊቱ ኢሪና ቲሞፌቫ ስታሸንፍ ኢሬነ ሊምካ ከኬንያ ሁለተኛ፤ አኬሚ ኦዛኪ ከጃፓን ሶሥተኛ፤ እንዲሁም ደራርቱ ቱሉ አረተኛ ሆናለች።

በቪየና ማራቶንም ጎልተው የታዩት የኬንያና የኢትዮጵያ አትሌቶች ነበሩ። ጂልበርት ኪርዋ አንደኛ ሲወጣ ደረጀ ቱሉ ሁለተኛ ሆኗል። ሩጫውን ሶሥተኛ በመሆን የፈጸመው ደግሞ ኬንያዊው ጆዜፍ ማሬጉ ነበር። በቤልግሬድ ማራቶንም እንዲሁ ግንባር ቀደም የሆኑት የኬንያ አትሌቶች ናቸው። በወንዶች ከአንድ እስከ ሶሥት ተከታትለው ሲገቡ በሴቶችም ድሉን አላስቀመሱም። የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ፉክክር ዛሬ ማምሻውን በቦስተንና በፊታችን ሰንበትም በለንደን ማራቶን ይቀጥላል።

በሞንቴ-ካርሎ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያ በዓለም የማዕርግ ተዋረድ ላይ ቀደምቱ የሆነው የስፓኝ ኮከብ ራፋዔል ናዳል የሰርቢያ ተጋጣሚውን ኖቫክ ጆኮቪችን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 በማሽነፍ ባለድል ሆኗል። ናዳል የሞንቴ-ካርሎን ማስተርስ ሲያሸንፍ በተከታታይ ለአምሥተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በባርሤሎና የዓለም ቴኒስ ማሕበር ፍጻሜ የሴቶች ግጥሚያ ኢጣሊያዊቱ ሮቤርታ ቪንቺ ሩሢያዊቱን ማሪያ ኪሪሌንኮን በአስተማማኝ ሁኔታ ረትታለች።
የቪንቺ ድል ከቦጎታ ወዲህ ሁለተኛው ይሆናል። በደቡብ ካሮላይና-ቻርልስተን ደግሞ ጀርመናዊቱ ዛቢነ ሊዚኪ የዴንማርክ ተጋጣሚዋን ካሮሊን ቮዝኒያችኪን በማሽነፍ ለመጀመሪያ የፍጻሜ ድሏ በቅታለች። ሌላው አዲስ የቴኒስ ዜና ሩሢያዊቱ ዲናራ ሣፊና በዓለም የማዕርግ ተዋረድ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ አንደኛውን ቦታ መያዟ ነው።

በተቀረ ትናንት ሻንግሃይ ላይ በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ የአውቶሞቢል እሽድድም ጀርመናዊው የሚሻዔል ሹማኸር አልጋ-ወራሽ ዜባስቲያን ፌትል በአስደናቂ ሁኔታ አሸናፊ ሆኗል። የ 21 ዓመቱ ወጣት ከሞንሣ ወዲህ ለድል ሲበቃ ሁለተኛ ጊዜው ነው። ቬትል በትናንት ድሉ በአጠቃላይ ነጥብ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ሊል ችሏል።

መሥፍን መኮንን, DW, RTR, AFP

ሸዋዬ ለገሠ