1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 17 2001

የአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ሻምፒዮና በአብዛኛው ሲለይለት ድሉን ለማወጅ እስከሚቀጥለው ሣምንት የመጨረሻ ግጥሚያ ድረስ መጠበቅ ግድ የሆነበት የፈረንሣዩ ክለብ ዢሮንዲን ቦርዶው ብቻ ነው።

https://p.dw.com/p/Hx9r
ምስል picture-alliance/ dpa

የጀርመን ቡንደስሊጋ የ 2008/2009 ውድድር በዓለምአቀፍ ደረጃ ብዙም ባልታወቀው ክለብ በ VfL Wolfsburg ሻምፖዮንነት ባለፈው ቅዳሜ ተፈጽሟል። ክለቡ በታሪኩ የመጀመሪያው ለሆነው ድል የበቃው ቨርደር ብሬመንን ግሩም በሆነ ጨዋታ 5-1 በማሸነፍና ቁንጮነቱም የአጋጣሚ እንዳልሆነ በማስመስከር ነው። አሠልጣኙ ፌሊክስ ማጋትም ድሉ የተገኘው በጨዋታ ብቃት እንደሆነ ነበር የሊጋው የመጀመረሻው ግጥሚያ እንዳበቃ ያረጋገጠው።

“አንድ ሕልም ዕውን ሆነ ለማለት ይቻላል። በጠቅላላው በውድድሩ ሂደት ጠንካራ ጨዋታ ነው ያሳየነው። ስለዚህም ሻምፒዮን መሆናቸውን ተገቢ ነው ለማለት እችላለሁ”

ቮልፍስቡርግ በተለይ በቡንደስሊጋው ውድድር ሁለተኛ ዙር ያሳየው የአጨዋወት ጥንካሬና ስክነት ማንም የጠበቀው አልነበረም። ሁለቱ ድንቅ አጥቂዎቹ ብራዚላዊው ግራፊችና የቦስናው ተወላጅ ኤዲን ጄኮ ብቻቸውን 54 ጎሎችን በማስቆጠር ክለቡ በሊጋው ውስጥ የነበረውን ጥንካሬ በሚገባ አስመስክረዋል። የክለቡ የመጀመሪያ ድል የፎልክስዋገን ኩባንያ መናኸሪያ በሆነችው ከተማ በቮልፍስቡርግ ከዚህ ቀደም ያልታወቀ የአደባባይ ፌስታ እንዲታይ ነው ያደረገው።
የብዙ ጊዜው ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን በአንጻሩ ምንም እንኳ አቻ ተፎካካሪውን ሽቱትጋርትን በዕለቱ ግጥሚያ 2-1 ቢረታም ያለፉት ሁለት ዓመታት ድሉን ሊደግመው አልቻለም። በሁለተኝነት መወሰኑ ግድ ሆኖበታል። ሽቱትጋርትም በሶሥተኝነት ለመጪው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ማጣሪያ የሚያበቃ ዕድሉን አረጋግጧል። በርሊንና ሃምቡርግ ደግሞ በዩኤፋ ምትክ አዲስ ለሚጀመረው የአውሮፓ ሊጋ ውድድር ተሳትፎ በቅተዋል።

ዘንድሮ በጅምሩ ብዙ ቢጠበቅባቸውም ክስረት የደረሰባቸው ክለቦች ሻልከ፣ ሌቨርኩዝንና ብሬመን ነበሩ። ውድድሩን ስምንተኛ፣ ዘጠነኛና አሥረኛ በመሆን ነው የፈጸሙት። እርግጥ ብሬመንና ሌቨርኩዝን በቅርቡ በጀርመን ፌደሬሺን ዋንጫ ፍጻሜ የሚገናኙ ሲሆን የዚሁ ግጥሚያ አሸናፊ ቢቀር መጽናኛ ይኖረዋል። በጎል አግቢነት 28 በማስቆጠር የበላይነቱን የያዘው የቡንደስሊጋው ሻምፒዮን የቮልፍስቡርግ ኮከብ ግራፊች ነው። በተቀረ ቢለፌልድና ካርልስሩኸ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን አቆልቁለዋል።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ዢሮንዲን-ቦርዶው ከአሥር ዓመት በኋላ እንደገና ሻምፒዮን ለመሆን እየተቃረበ ነው። ቡድኑ ባለፈው ቅዳሜ ሞናኮን 1-0 ሲረታ ከኦላምፒክ ማርሤይ ጋር ያለውን የሶሥት ነጥቦች ልዩነት እንደጠበቀ ሊቀጥል በቅቷል። ቦርዶው ሻምፒዮን ለመሆን በሚቀጥለው ሣምንት የመጨረሻ ግጥሚያ እኩል-ለእኩል ውጤት ይበቃዋል። ናንሢይን 2-1 ያሸነፈው ሁለተኛው ማርሤይ በበኩሉ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያበቃውን ሁለተኛ ቦታ ከወዲሁ ሲያረጋግጥ ኦላምፒክ ሊዮንም በሶሥተኝነቱ ረግቷል። ማርሤይ ቦርዶው ተሸንፎ የበኩሉን ግጥሚያ በሁለት ጎሎች ብልጫ በስኬት ከተወጣ በመጨረሻዋ ዕለት ሻምፒዮንነቱን የመንጠቅ ዕድልም አለው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና ሻምፒዮንነቱን፤ ሬያል ማድሪድም ሁለተኝነቱን ከወዲሁ አረጋግጠው ሳለ ሤቪያ ደግሞ ውድድሩን በሶሥተኝነት ለመፈጸም ተቃርቧል። ሤቪያ ይህን ግቡን ዕውን ለማድረግ ሣምንት አቻ ለአቻ ውጤት ይበቃዋል። በጎል አግቢነት የባርሤሎናውን ኮከብ ሣሙዔል ኤቶን አልፎ በሁለት ጎሎች ብልጫ በ 31 የሚመራው የአትሌቲኮ ማድሪዱ ዲየጎ ፎርታን ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የማንቼስተር ዩናይትድ ሻምፒዮንነት፤ የሊቨርፑልና የቼልሢይ ተከታይነትም ቀድሞ የለየለት ጉዳይ ሲሆን በውድድሩ የመጨረሻ ሰንበት ይበልጥ ትኩረት ስቦ ያለፈው የኒውካስል ዩናይትድና የሚድልስቦሮህ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን መከለስ ነበር። በውድድሩ መጀመሪያ ይህ ይሆናል ብሎ ያሰበ ብዙ አልነበረም። ውድድሩን በቀደምት ጎል አግቢነት የፈጸመው የቼልሢው ኒኮላስ አኔልካ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ከኢንተር ሚላን ሻምፒዮንነት በኋላ የሚጠበቀው የትኞቹ ሁለት ክለቦች ሁለተኛና ሶሥተኛ ሆነው ለአውሮፓ ሻምሚዮና ሊጋ እንደሚያልፉ ነው። ሁለተኛው ጁቬንቱስና ኤ.ሢ.ሚላን እኩል 71 ነጥብ ሲኖራቸው ፊዮሬንቲና በሶሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ ይከተላል። ሚላንና ፊዮሬንቲና ሣምንት በመጨረሻው ግጥሚያ የሚገናኙ ሲሆን ይሄው ግጥሚያ ለሻምፒዮናው ሊጋ ተሳትፎ ወሣኝነት አለው። ሌቼና ሬጂና ደግሞ ከወዲሁ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን አቆልቁለዋል።

በተረፈ ግላስጎው-ሬንጀርስ ትናንት ዳንዲይ-ዩናይትድን 3-0 በመርታት የስኮትላንድ ፕሬሚየር ሊግ ሻምፒዮን ሊሆን በቅቷል። በቤልጂግ ሻምፒዮና ደግሞ ተመሳሳይ ድል የተጎናጸፈው አንደርሌህትን 1-0 ያሸነፈው ስታንዳርድ ሊግ ነው። አውስትሪያ ውስጥ አውስትሪያ-ቪየና አድሚራን በተጨማሪ ሰዓት 3-1 በመርታት የፌደሬሺኑ ዋንጫ አሸናፊ ሲሆን በእሥራኤል ሊጋ ደግሞ ማካቢ-ሃይፋ ለ 11ኛ ሻምፒዮንነቱ በቅቷል።

ወደ አፍሪቃ፤ በትክክል ወደ ሰሜናዊው አፍሪቃ ሻገር እንበልና ዝነኛው የግብጽ ክለብ አል-አህሊ ለተከታታይ አምሥተኛ ጊዜ የአገሪቱ ሻምፒዮን ሆኗል። አል-አህሊ ለዚህ ክብር የበቃው ትናንት ካይሮ ላይ ኢስማኢሊን 1-0 ከረታ በኋላ ነው። ቱኒዚያ ውስጥ CS Sfaxien ደግሞ ትናንት ሞናስቲርን በማሸነፍ የብሄራዊ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል። ለስፋክሢየን ይሄው አራተኛው ዋንጫ ሲሆን ቡድኑ ለትናንቱ ድል የበቃው በተጨማሪ ሰዓት ላይ ባስቆጠራት ብችኛ ፍጹም ቅጣት ምት ነበር።

አትሌቲክስ

ካናዳ-ኦታዋ ላይ ትናንት ተካሂዶ በነበረ የማራቶን ሩጫ ውድድር ኬንያዊው ዴቪድ ቼሩዮት አሸናፊ ሆኗል። ከኢትዮጵያ ዋጋየሁ ግርማ ስድሥት ሤኮንዶች ያህል በመዘግየት ሁለተኛ ሲወጣ ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመው የሞሮኮው አትሌት አሕመድ ባዳይ ነበር። በሴቶች ሞሮካዊቱ አስሜ ሌግዛዊ ስታሸንፍ ካናዳዊቱ ሉድሚላ ኮቻጊና ሁለተኛ፤ እንዲሁም ኬንያዊቱ ኢሬነ ኮስጋይ ሶሥተኛ ወጥታለች።

በብራዚል የአትሌቲክስ ግራንድ-ፕሪ ደግሞ በአጭር ርቀት ሩጫ አሜሪካና ጃማይካ የበላይነት ሲያሳዩ በአሥር ሺህ ሜትር ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል አሸንፈዋል። የአስተናጋጇ አገር አትሌቶች በ 800 ሜትር ሩጫ አንደኛና ሁለተኛ ሲወጡ በተቀረ በውድድሩ የተመዘገበ አዲስ ክብረ-ወሰን አልነበረም። በሌላ የአትኬቲክስ ዜና ትናንት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በተካሄደው ዓመታዊ የኮምሬድስ-ማራቶን ውድድር የዚምባብዌው ተወላጅ ስቴፈን ሙዚንጊ አሸናፊ ሆኗል።
አዘውትሮ ባልተለመደውና ሩሢያውያን ሃያል በሆኑበት የ 89 ኪሎሜትር ማራቶን 13 ሺህ ሰዎች ሲሳተፉ ሙዚንጊ ደርባን ውስጥ ከግቡ የደረሰው በ 5 ሰዓት ከ 23 ደቂቃ ከ 27 ሤኮንድ ጊዜ ነው። ያለፈው ዓመት ሻምፒዮን ሩሢያዊው ሌዎኒድ ሽቬትሶቭ ሁለተኛ ሲወጣ የደቡብ አፍሪቃው ተወዳዳሪ ሉካስ ኖንያና ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል።

ፎርሙላ-አንድ/ቡጢ

ባለፈው ሰንበት ሞናኮ ላይ በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም የብሪታኒያው ዘዋሪ ጄንሰን ባተን አሸናፊ ሆኗል። ለጄንሰን የትናንቱ ድል በስድሥት ውድድሮች አምሥተኛው መሆኑ ነበር። ብራዚላዊው ሩበንስ ባሪኬሎ ሁለተኛ ሲወጣ ውድድሩን በሶሥተኝነት የፈጸመው የፊንላንዱ ኪሚ ራይኮነን ነው። ባተን ሞናኮ ላይ ሲያሸንፍ ከ 36 ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው የብሪታኒያ ዜጋ ሲሆን በወቅቱ ውድድር ገና 11 እሽቅድድሞች ቀርተው ሳለ በአጠቃላይ ውጤት በ 16 ነጥቦች ይመራል።

በታላቁ ዢሮ-ዴ-ኢታሊያ የቢስክሌት እሽቅድድም ከፎርሊ እስከ ፌኤንዛ በዘለቀው 15ኛው ደረጃ የ 16 ኪሎሜትር እሽቅድድም ኢጣሊያዊው ሌዎናርዶ ቤርታኞሊ አሸናፊ ሆኗል። ሁለተኛ ሤርዥ ፓውቫይስ ከቤልጂግ፤ ማርኮ ፔኖቲ ከኢጣሊያ ሶሥተኛ! በአጠቃላይ ውጤት የሚመራው የሩሢያው ዴኒስ ሜንቾቭ ነው።

ሜክሊኮ ውስጥ በተካሄደ የቡጢ ግጥሚያ ደግሞ ጃፓናዊው ቶሺያኪ ኒሺዮካ የዓለም የቦቅስ ካውንስል የ WBC ሻምፒዮንነቱን በፍጹም ልዕልና ሊያስከብር በቅቷል። ተጋጣሚው የሜክሢኮው የቀድሞ ሻምፒዮን ጆኒ ጎንዛሌስ በመጀመሪያው ዙር አይሎ ቢታይም በሶሥተኛው ዙር ላይ መዘረሩ ግድ ሆኖበታል። ኒሺዮካ ባለፈው ጥር የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን የሆነው ሌላውን ሜክሢካዊ ጄናሮ ጋርሢያን በ 12 ዙር በማሽነፍ ነበር። ጃፓናዊው የቡጢ ሻምፒዮን እስካሁን ባካሄዳችው ግጥሚያዎች 34 ጊዜ ሲያሸንፍ ከነዚሁ 21ዱንም በመዘረር ነበር። በተቀረ አራቴ ብቻ ሲሸነፍ ሶሥቴ ደግሞ ግጥሚያውን የፈጸመው በእኩልነት ነው።

በእግር ኳስ የጀመርነውን ዘገባ በእግር ኳስ ለማጠቃለል በፊታችን ረቡዕ በክለቦች ደረጃ በዓለም ላይ ታላቁ የሆነው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ ግጥሚያ ሮማ ላይ ይካሄዳል። ተጋጣሚዎቹ የስፓኙ ባርሤሎናና የእንግሊዙ ማንቼስተር ዩናይትድ ሁለቱም በአገራቸው የሊጋ ሻምፒዮንነታቸውን ሲያረጋግጡ ወደ ግጥሚያው የሚያመሩት በረጋ ስሜት ነው። የረቡው ፍጻሜ ግጥሚያ የአሸናፊዎች አሸናፊ የሚውጣጣበት ውድድር ከተጀመረ ወዲህ 54ኛው ሲሆን ሁለቱም ክለቦች በየጊዜው ገናና ታሪክ ያስመዘገቡ ናቸው።
የአሸናፊዎች ዋንጫ ሲሰኝ የቆየው ውድድር የሻምፒዮና ሊጋነት ስያሜ የተሰጠው ከ 16 ዓመታት በፊት ነበር። ለማንኛውም ባርሤሎና የአሸናፊዎቹን ዋንጫ አራት ጊዜ ሲወስድ ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ ከኤ.ሢ.ሚላን የ 1989/90 የሻምፒዮና ሊጋ ተከታታይ ድል በኋላ ያለፈውን ዓመት ድሉን የመድገም ዕድል አለው። በዓለም ዙሪያ ጨዋታውን በቴሌቪዥን አማካይነት የሚከታተሉ አያሌ ኳስ አፍቃሪዎች ዓይን በተለይ በሁለቱ ክለቦች ከዋክብት በሊዮኔል ሜሢና በክሪስቲያኖ ሮናልዶ ላይ የሚያርፍ ለመሆኑ አንድ ሁለት የለውም።
የሮማ ባለሥልጣናት በበኩላቸው የእግር ኳሱ ፌስታ ያላንዳች ኹከት በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ አስፈላጊውን ሁሉ የጸጥታ ጥበቃ ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው። ሮማ ፍጻሜውን ስታስተናግድ መጪው አራተኛው ሲሆን ፊፋ ከጸጥታ አስተማማኝነት አንጻር ትክክለኛውን ቦታ እንደመረጠ ተሥፋ እናደርጋለን። በነገራችን ላይ እስካሁን አብዛኛው የአውሮፓ ሻምፒዮና ፍጻሜ ውድድር የተካሄደው በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲዮም ነው።

DW/RTR/AFP

መሥፍን መኮንን ፣

ተክሌ የኋላ፣