1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 9 2001

ባለፈው አርብ ምሽት ኦስሎ ላይ የተካሄደው ሁለተኛው ዙር የአትሌቲክስ ጎልደን-ሊግ ውድድር በተለይ በመካከለኛ ርቀት ሩጫ የኢትዮጵያ አትሌቶችም ድንቅ ውጤት ያስመዘገቡበት ሆኖ አልፏል።

https://p.dw.com/p/IiBR
ሯጮች በኢትዮጵያምስል DW / Alexander Göbel

በስድሥት ደረጃ በተከፈለው የአትሌቲክስ ጎልደን-ሊግ ውድድር ከበርሊን የቀጠለው ሁለተኛው ዙር ባለፈው አርብ ምሽት በኦስሎ ቢስሌት ስታዲዮም ተካሂዷል። በውድድሩ በአጠቃላይ ድንቅ ውጤቶች ሲመዘገቡ የኢትዮጵያ አትሌቶች ውጤትም የሚያኮራና ከጥቂት ሣምንታት በኋላ በርሊን ላይ ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሥፋን የሚያዳብር ሆኖ ነው ያለፈው። በሴቶች አምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ መሠረት ደፋር ከሁለት ዓመታት በፊት አስደናቂ የዓለም ክብረ-ወሰን አስመዝግባበት በነበረው ስታዲዮም እንደገና ግሩም ለሆነ ድል በቅታለች።
እርግጥ ዋነኛ ተፎካካሪዋ ጥሩነሽ ዲባባ ቀለል ባለ የአካል ጉዳት የተነሣ አልተሳተፈችም። ቢሆንም መሠረት ደፋር ኬንያዊቱን ቪቪያን ቼሩዮትን የመሰለች ጠንካራ አትሌት በመቅደም ነው ያሸነፈችው። በዚሁ የአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ኢትዮጵያ ወደፊትም ጠንካራ ሆና እንደምትቀጥል ሶሥት አትሌቶቿ ከአንድ እስከ አምሥት ያለውን ቦታ መያዛቸው ያመለክታል። መሰለች መልካሙ ሶሥተኛ ስትወጣ ውዴ አያሌው ደግሞ አምሥተኛ ሆናለች። የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ሩጫም ግሩም ሆነው ታይተዋል። ኬንያዊቱ ሩት ኒያንጋው ሩጫውን በአንደኝነት ስትፈጽም ሶፊያ አሰፋና መቅደስ በቀለ ሁለተኛና ሶሥተኛ ሆነዋል። በአጠቃላይ እጅግ የሚያስደስትና የሚያኮራ ውጤት ነው።

ቀነኒሣ በቀለም በአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ የካታሩን ጀምስ ኩዋላንና ኬንያዊውን ቪንሤንት ቼፕኮፕን በማስከተል በጎልደን-ሊጉ ውድድር ለሁለተኛ ድሉ በቅቷል። ድሉ ቀነኒሣን በውድድሩ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ላይ አተኮሮ እንዲቀጥል የሚያደርገው ነው። የተቀሩት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ስለሺ ስሂኔና በካና ዳባም አራተኛና አምሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። በመካከለኛው ርቀት ሩጫ የኢትዮጵያ አትሌቶች ድል በዚህ ብቻ አላበቃም። በአንድ ማይል ሩጫም ደረሰ መኮንን ከምሽቱ አሸናፊ ከዋክብት መካከል አንዱ ነበር። ኬንያውያኑ ዊሊያም ቢዎትና አጉስቲን ቾጌ ሁለተኛና ሶስተኛ ሲወጡ መኮንን ገ/መድህን ደግሞ አራተኛ ሆኗል።

በተቀረ በወንዶች ሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶሥት ተከታትለው ሲገቡ በ 1,500 ሜትርም የበላይ ነቱን የያዙት የኬንያ አትሌቶች ነበሩ። በሶሥት ሺህ ሜትር ሪቻርድ ባርታሌ፤ በ 1,500 ሜትር ደግሞ ኮሊንስ ቼቦይ አሸናፊ ሆነዋል። በእር ርቀት ሩጫ ጃማይካዊው አሣፋ ፓውል በ 10,07 ሤኮንድ ሲያሸንፍ የትሪኒዳዱ ሬኒይ ኩዎው በአራት መቶ፤ እንዲሁም የሩሢያው ዩሪ ቦርዛኮቭስኪ በስምንት መቶ ሜትር ሩጫ ባለድሎቹ ነበሩ። በሴቶች አራት መቶ ሜትር ሩጫ አሜሪካዊቱ ሣኒያ ሪቻርድስ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ለሁለተኛ የጎልደን ሊግ ድሏ በቅታለች። ሩሢያዊቱ የምርኩዝ ዝላይ የዓለም ሻምፒዮን የለና ኢዚምባዬቫም እንዲሁ በጎልደን ሊጉ ሽልማት አቅጣጫ ማምራጧን እንደቀጠለች ነው።

ከኦስሎው ውድድር ውጤት በኋላ ስድሥት አትሌቶች የአንድ ሚሊዮኑን ዶላር ሽልማት የማግኘት ዕድል አላቸው። እነዚሁም በወንዶች ቀነኒሣ በቀለና የፊንላንዱ ጦር ወርዋሪ ቴሮ ፒትካማኪ፤ ከሴቶች ደግሞ የጃማይካዋ የመቶ ሜትር አሸናፊ ኬረን ስቱዋርት፣ አሜሪካዊቱ የመቶ ሜትር መሰናክል ባለድል ዳሙ ቼሪይ፤ እንዲሁም ሣኒያ ሪቻርድስና የለና እዚምባዬቫ ናቸው። በነገራችን ላይ የጎልደን-ሊጉን ሙሉ ሽልማት መውሰድ የሚችለው በስድሥቱን ጎልደን-ሊግ ውድድሮች የሚያሸንፈው አትሌት ነው። የሚቀጥለውና ሶሥተኛው የጎልደን-ሊግ ውድድር በፊታችን አርብ ሮማ ላይ የሚደረግ ሲሆን ከሣምንት በኋላ በፓሪስ፤ ከዚያም በነሐሴ ወር በዙሪክና በብራስልስ ይካሄዳል።
በአካል ጉዳት ምክንያት በኦስሎው ውድድር ያልተሳተፈችው ጥሩነሽ ዲባባ እስከዚያው በሚገባ አገግማ በርሊን ላይ በሚከተለው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በስኬት እንደምትካፈል ተሥፋ እናደርጋለን።

MM/AFP