1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 4 2002

አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቴኒስና የአውቶሞቢል እሽቅድድም

https://p.dw.com/p/Jeug
ደቡብ አፍሪቃይቱ አትሌት ካስተር ሤሜንያ
ደቡብ አፍሪቃይቱ አትሌት ካስተር ሤሜንያምስል AP

በአትሌቲክስ እንጀምርና ከቅርቡ የዓለም ሻምፒዮናና ጎልደን-ሊግ ውድድር ወዲህ ምናልባትም ከአውሮፓው ክረምት በፊት የመጨረሻው የሆነው ከባድ ውድድር ሰንበቱን ግሪክ-ሣሎኒኪ ላይ ተካሂዷል። ውድድሩ በተለይም የኢትዮጵያ አትሌቶች ከመካከለኛና ረጅም ርቀት ብርቱ የኬንያ ተፎካካሪዎቻቸው አየል ብለው የታዩበትም ነበር። የኢትዮጵያ አትሌቶች በሶሥትና በአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ በወንዶች ብቻ ሣይሆን በሴቶችም ሙሉ ድል ለመጎናጸፍ በቅተዋል።

በሴቶች ሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ባለፈው ወር የበርሊን የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ያልቀናት መሠረት ደፋር በአስተማማኝ ሁኔታ ኬንያዊ ተፎካካሪዋን ቪቪያን ቼሩዮትን ቀድማ አሽንፋለች። ከተቀሩት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ውዴ አያሌው ሶሥተኛ ስትወጣ ቃልኪዳን ገዛኸኝ ደግሞ አምሥተኛ ሆናለች። የመሠረት ደፋር ድል በዚህ ብቻ አላበቃም። ወደተለመደ ጥንካሬዋ መመለስ የያዘችው አትሌት በአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫም አሸንፋለች። ጥሩነሽ ዲባባም ሩጫውን በሁለተኝነት በመፈጸም ድሉን ድርብ ስታደርገው ኬንያዊቱ ቪቪያን ቼሩዮት በአንጻሩ በሶሥተኝት መወሰኑ ግድ ሆኖባታል።

በወንዶች አምሥት ሺህ ሜትር ምንም እንኳ የኢትዮጵያ የድል ዋስትና ቀነኒሣ በቀለ ባይሳተፍም ኬንያ ያሰለፈቻቸው እስከ ሰባት የሚደርሱ ፈጣን ሯጮች የመብዛታቸውን ያህል ዕድሉን ተጠቅመው ግንባር-ቀደም ሊሆኑ አልቻሉም። ብርቱ ፉክክር በታየበት በዚህ ሩጫ አሸናፊ የሆነው በብራስልሱ የቅርብ የጎልደን ሊግ የመጨረሻ ውድድር ቀነኒሣን ተከትሎ በሁለተኝነት የፈጸመው ኢማነ መርጋ ነበር። በተቀረ ከሁለተኛ እስከ ስምንተኛ ቦታ ተከታትለው የገቡት የኬንያ አትሌቶች ናቸው።
የኬንያ አትሌቶች በሌላ በኩል በ 1,500 ሜትርና ሃያል በሆኑበት የሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ሩጫ አሸናፊ ሆነዋል። በሁለቱ ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቶች ደረሰ መኮንን ስምንተኛ፤ እንዲሁም ጋሪ ሮባ አራተኛ በመሆን ያስመዘገቡት ግሩም ውጤትም ለወደፊት የተሥፋ ምንጭ የሚሆን ነው። በነገራችን ላይ የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ቀነኒሣ በቀለም በተወዳደረበት የሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ በርናርድ ላጋትን በመቅደም አሸንፏል።
በአጭር ርቀት የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ጃማይካዊ ዩሤይን ቦልት ምንም እንኳ በአንድ መቶ ሜትር ሩጫ ባይወዳደርም በሁለት መቶ ሜትር አስደናቂ በሆነ 19,68 ሤኮንድ ጊዜ አሸንፏል። በመቶ ሜትሩ ለድል ,የበቃው አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ ነበር። ሌላው አስደናቂ ውጤት አሜሪካዊቱ ካርሜሊታ ጄተር በዚሁ ርቀት ያስመዘገበችው ውጤት ነው። ጄተር መቶ ሜትሩን በዓለም ላይ እስካሁን ሶሥተኛው በሆነው ፈጣን ጊዜ በ 10,67 ሤኮንድ ለመፈጸም በቅታለች።

የሣሎኒኪው ውድድር ገጽታ ከሞላ-ጎደል ይህን የመሰለ ሲሆን በአትሌቲክሱ መድረክ ላይ ያለፈው ሣምንት ትልቅ አነጋጋሪ ጉዳይ የደቡብ አፍሪቃይቱ የስምንት መቶ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን የካስተር ሤሜንያ የጾታ ጉዳይ ነበር። ዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር IAAF በአትሌቷ ላይ እንዲካሄድ ያደረገው ምርመራ የሁለት የጾታ፤ ማለት የወንድም የሴትም ባሕርያት እንዳላት አረጋግጧል ሲል የአውስትራሊያው Daily Telegraph ጋዜጣ ያሰራጨው ዘገባ በተለይ የደቡብ አፍሪቃን ባለሥልጣናት ክፉኛ ነው ያስቆጣው። የአገሪቱ የስፖርት ሚኒስትር ሚኒማኬንኬሢ ስቶፊሌ የ 18 ዓመቷ ወጣት አትሌት ሤሜንያ ከውድድር ከታገደች “ሶሥተኛ የዓለም ጦርነት” ይከተላል ሲሉ ነው ባለፈው አርብ ዛቻ ያሰሙት።

“ዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ሤሜንያን ከውድድር ካስወጣ ወይም ካገለለ፤ ወይም ሜዳሊያዋን ካስመለሰ ምንድነው የምናደርገው? የሚከተለው ሶሥተኛ የዓለም ጦርነት ነው። ይህን መሰሉን አግባብ የለሽና ፍትሃዊ ያልሆነ ውሣኔ በከፍተኛው ደረጃ እንሞግታለን ብዬ አስባለሁ”

ዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር በጉዳዩ ውሣኔ የሚያስተላልፈው በፊታችን ሕዳር ወር ነው። እስከዚያው ሽኩቻው እየተካረረ መሄዱ የሚቀር አይመስልም። በነገራችን ላይ ሴት አትሌቶች በጾታ ባሕርያቸው ሲጠረጠሩና ክርክርን ሲያስነሱ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ከብዙ በጥቂቱ አንዳንድ ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ያህል እ.ጎ.አ. የ 1932 ዓ.ም. የኦሎምፒክ መቶ ሜትር አሸናፊ ፖላንዳዊቱ ስቴላ ዋልሽ ከነዚሁ አንዷና የመጀመሪያዋ ነበረች።
አትሌቷ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየች በኋላ ነበር በ 1980 ዓ.ም. አሜሪካ ውስጥ የተካሄደ የአስከሬን ምርመራ የወንድ ብልትና ድርብ የጾታ ባሕርያት እንደነበሯት ያረጋገጠው። በ 2006 ተራው የሕንዷ የእሢያ ጨዋታ የ 800 ሜትር ሩጫ ተወዳዳሪ የሣንቲ ሶንዳራጃን ነበር። አትሌቷ ወንዳ-ወንድ ባሕርይ እንዳላት በምርመራ ተደርሶበታል በሚል የብር ሜዳሊያን እንድትመልስ ትደረጋለች። በተረፈ በቀድሞይቱ ሶቪየት ሕብረትና የምሥራቅ አውሮፓ ሶሻሊስት አገሮች የወንድነት ባሕርይ የሚታይባቸው ሴት አትሌቶች በየጊዜው መከሰት ያከራከረበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። ብሄራዊ ፌደሬሺኖች ይህን መሰሉ አጣራጣሪ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ስፖርተኞቻቸውን ከወዲሁ ቀድመው በመመርመር ጉዳዩን ቢያጣሩ እንደ ሤሜንያ ላሉት አውቆ አጥፊ ላልሆኑ አትሌቶች ምንኛ በበጀ ነበር።

እግር ኳስ

የያዝነው ሣምንት አጋማሽ በአውሮፓ የክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር የመጀመሪያ ዙር የምድብ ግጥሚያዎች የሚካሄዱበት ነው። ታዲያ ባርሤሎናን፣ ማንቼስተር ዩናይትድን፣ ሬያል ማድሪድንና ቼልሢይን የመሳሰሉት ቀደምት ክለቦች ሰንበቱን በየሊጋቸው ባካሄዱት ግጥሚያ ለመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ራሳቸውን ማሟሟቃቸው አልቀረም።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን የብሄራዊና የአውሮፓው ሻምፒዮና ሊጋ ድርብ ድል ባለቤት ባርሤሎና ሁለተኛ ግጥሚያውንም በማሽነፍ በጎል ብልጫ ቀደምቱን ቦታ ይዟል። ክሪስቲያኖ ሮናልዶንና ካካን በመሳሰሉ ከዋክብት ያሽበረቀው ሬያል ማድሪድ፣ ቫሌንሢያና አትሌቲኮ ቢልባኦም በተመሳሳይ ነጥብ ይከተላሉ። የስፓኙ ውድድር ገና በለጋ ደረጃው ላይ ሲሆን በሌላ በኩል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አምሥተኛው ጨዋታ ሰንበቱን ተካሂዷል።
ኤፍ.ሢ.ቼልሢይ ስቶክ ሢቲይን 2-1 በማሽነፍ በ 15 ነጥቦች አመራሩን ሲያጠናክር ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ማንቼተር ሢቲይና ቶተንሃም ሆትስፐር ደግሞ እያንዳንዳቸው 12 ነጥቦች ይዘው ይከተላሉ። ማንቼስተር ዩናይትድ ሆትስፐርን 3-1 ሲረታ፤ ማንቼስተር ሢቲይ አርሰናልን 4-2 ሸኝቷል። ከቀደምቱ የእንግሊዝ ክለቦች አንዱ የሆነውን አርሰናልን የሰንበቱ ሽንፈት ወደ ዘጠነኛ ቦታ እንዲያቆለቁል ነው ያደረገው። ሊቨርፑል ደግሞ ምንም እንኳ በርንሊይን 4-0 ቢረታም በዘጠኝ ነጥቦች አምሥተኛ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጄኖዋ፣ ጁቬንቱስና ሳምፕዶሪያ ዘንድሮ በጥሩ አጀማመራቸው በመግፋት ሶሥተኛ ግጥሚያቸውንም በማሸነፍ ተወጥተዋል። ሶሥቱም እኩል ዘጠኝ ነጥብ አላቸው፤ ጌኖዋ በጎል ብልጫ ብቻ ይመራል። ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ኢንተር ሚላን ለጊዜው በሰባት ነጥቦች ከታች ወደ ላይ ተመልካች ነው። የከተማ ተፎካካሪው ኤ.ሢ.ሚላን ደግሞ አሥረኛ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ሃምቡርግና ሌቨርኩዝን የሰንበት ግጥሚያቸውን በማሸነፍ አመራሩን እንደያዙ ቀጥለዋል። ሶሥተኛው ብሬመን ትናንት በሜዳው ከሃኖቨር ባዶ ለባዶ በመለያየቱ ቦታውን ኮሎኝን 2-1 ላሽነፈው ለሻልከ አስረክቧል። የሣምንቱን ታላቅ እመርታ ያሳየው ግን ዶርትሙንድን ለዚያውም 1-0 ከተመራ በኋላ 5-1 አከናንቦ የተመለሰው ባየርን ሙንሺን ነው። ሆኖም ሆላንዳዊ አሠልጣኙ ሉዊስ-ፋን-ኸል ጥቂትም ቢሆን በቡድናቸው ላይ ድክመት ማየታቸው አልቀረም።

“እንደማስበው አጀማመራችን ጥሩ አልነበረም። ግን ሪቤሪይ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ጨዋታውን ለመቆጣጠር በቅተናል። በሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተጫዋቾቼ የግል ችሎታ ነው ወሣኝ የሆነው።
በቡንደስሊጋው ውድድር ጅማሮ ደከም ብሎ የነበረው የብዙ ጊዜው የጀርመን ሻምፒዮን ባየርን በዚሁ ወደ እምሥተኛው ቦታ ከፍ ሊል በቅቷል።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ሶሥቱም የሣምንቱ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ተሳታፊዎች ዢሮንዲን ቦርዶ፣ ሊዮንና ኦላምፒክ ማርሤይ የሰንበት ግጥሚያዎቸቸውን ሲያሸንፉ አመራሩን የያዙት ቦርዶና ሊዮን እኩል 13 ነጥቦች አሏቸው። ማርሤይ በ 11 ነጥብ አራተኛ ነው። በፖርቱጋል ሊጋ ከአራት ግጥሚያዎች በኋላ ብራጋ በ 12 ነጥቦች ቀደምቱ ነው፤ ቤንፊካ ሁለተኛ፤ ፖርቶ ሶሥተኛ!
የሻምፒዮና ሊጋውን ውድድር ካነሣን ከሣምንቱ አጋማሽ የመጀመሪያ የምድብ ግጥሚያዎች አንዳንዶቹ ከወዲሁ የሚማርኩ ናቸው። በነገው ምሽት ከሚደረጉት ግጥሚያዎች መካከል ምናልባትም ጠንካሮቹ ጁቬንቱስ ከቦርዶ፤ ማርሤይ ከኤ.ሢ.ሚላን፤ ቼልሢይ ከፖርቶ ሊሆኑ ይችላሉ። በማግሥቱ ረቡዕ ምሽት ግን በኢንተር ሚላንና በባርሤሎና መካከል የሚካሄደው ግጥሚያ ታላቁ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም።

ቴኒስ

የዘንድሮው ዩ.ኤስ-ኦፕን ፍጻሜ የሴቶች አሸናፊ በወሊድ ምክንያት ሁለት ዓመታት ያህል ካረፈች በኋላ ከጥቂት ሣምንታት በፊት የተመለሰችው የቤልጂጓ ተወላጅ ኪም ክላይስተርስ ሆናለች። ክላይስተርስ የዴንማርክ ተጋጣሚዋን ካሮሊን ቮዝኒያችኪን 7-5, 6-3 በሆነ ውጤት ስታሸንፍ ይሄው ከአራት ዓመታት በኋላ ሁለተኛው ታላቅ ዓለምአቀፍ ድሏ መሆኑ ነው። ክላይስተርስ ወደ ፍጻሜው ያለፈችው በግማሽ ፍጻሜው አሜሪካዊቱን ሤሬና ዊሊያምስን በማሸነፍ ነበር። ሤሬና ራሷን መቆጣጠር ተስኗት በመስመር ዳኛ ላይ ባነሳችው ኸከት የውድድሩ ባለሥልጣናት የ 10,500 ዶላር መቀጮ ጥለውባታል። በስዊሱ ሮጀር ፌደረርና በአርጀንቲናው ሁዋን-ማርቲን-ዴል-ፖንቶ መካከል የወንዶቹ ፍጻሜ የሚካሄደው በአየር ጠባይ ሳቢያ በውድድሩ ሂደት ባጋጠመ ሽግሽግ የተነሣ ገና በዛሬው ምሽት ነው።

አውቶሞቢል

ዘገባችንን በአውቶሞቢል ስፖርት ለማጠቃለል ትናንት ኢጣሊያ-ሞንሣ ላይ የተካሄደው የፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም አሸናፊ የብራውን-ጂፒ ቡድን ዘዋሪ ብራዚላዊው ሩበርን ባሪቼሎ ሆኗል። እሽቅድድሙን በሁለተኝነት የፈጸመውም የዚሁ ቡድን ባልደረባ ጄሰን ባተን ነበር። እስካሁን ዘንድሮ ከሚካሄዱት 17 ውድድሮች 13ቱ በዚሁ ሲጠናቀቁ በጠቅላላ ነጥብ የብሪታኒያው ጄሰን ባተን መምራቱን ቀጥሏል። ባተን 80 ነጥቦች ሲኖሩት ሩበንስ ባሪቼሎ በ 66 ሁለተኛ ነው። በሌላ በኩል የትናንቱን ውድድር በስምንተኝነት የፈጸመው የጀርመኑ ወጣት ኮከብ ዜባስቲያን ፌትል በ 54 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን የዓለም ሻምፒዮን የመሆን ዕድሉ የመነመነ ነው የሚመስለው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ