1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 11 2002

“ተመልካቹ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ግሩም ነበር። ለጀርመን ሕዝብ በተለይም ለበርሊናውያን ታላቅ ምስጋናዬን ልገልጽ እወዳለሁ። ትልቅ ሥራ ነው ያከናወኑት” ሃይሌ ገ/ሥላሴ!

https://p.dw.com/p/JleH
ኃይሌ ገ/ሥላሴ
ኃይሌ ገ/ሥላሴምስል picture-alliance/ dpa

አትሌቲክስ

የትናንቱ ሰንበት በዚህ በጀርመን ለኢትዮጵያ አትሌቶች እጅግ የቀና ሆኖ ነው ያለፈው። በ 36ኛው የበርሊን ማራቶን ሃይሌ ገ/ሥላሴና አጸደ ሃብታሙ በየፊናቸው አሸናፊ በመሆን የኢትዮጵያን ድል እጥፍ ድርብ አድርገውታል። ሃይሌ በበርሊን ማራቶን እጅግ በሚወደውና በሚያደንቀው ተመልካች ፊት ሲያሸንፍ በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን ለ 21 ዓመቷ ወጣት አትሌት ለአጸደ በአንጻሩ የመጀመሪያው ታላቅ ዓለምአቀፍ ድል ነበር። ይህም የወደፊት ተሥፋን የሚያዳብር አስደሳች ውጤት ነው። ሃይሌ ባለፈው ዓመት በዚያው ያስመዘገበውን የዓለም ክብረ-ወሰን ማሻሻሉ በሞቃት አየር ሳቢያ ባይሳካለትም ሩጫውን በፍጹም ልዕልና ማሽነፉ ግን አላዳገተውም።
ኬንያዊው ፍራንሲስ ኪፕሮፕ ሁለተኛ ሲወጣ ነጋሪ ተርፋ ደግሞ ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽሟል። በሴቶችም ከአጸደና ከሩሢያ ተፎካካሪዋ ቀጥላ ሶሥተኛ የሆነችው ኢትዮጵያዊቱ ማሚቱ ዳስካ ነበረች። አርባ ሺህ ያህል ሰዎች የተሳተፉበት የበርሊን ከተማ ማራቶን በዓለም ላይ ታላላቅ ከሚባሉት አንዱ ነው። ይህም የተገኘውን ድርብ ድል የተለየ ክብደት ይሰጠዋል። የበርሊን ወኪላችን ይልማ ሃ/ሚካዔል ከውድድሩ በኋላ ባለድሎቹን ሃይሌንና አጸደን አነጋግሮ ነበር! ያድምጡ!

እግር ኳስ

በሰንበቱ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች እንጀምርና ኤፍ,ሢ.ቼልሢይ በዘንድሮው ውድድር በያዘው ጥሩ ጅማሮ እንደቀጠለ ነው። ቼልሢይ ትናንት ቶተንሃም-ሆትስፐርን 3-0 ሲረታ ሊጋውን በሶሥት ነጥቦች ልዩነት ይመራል። ለቀደምቱ ክለብ የትናንቱ ድል በስድሥት ግጥሚያዎች ስድሥተኛው መሆኑ ነው። እስካሁን አንዴም አልተሽነፈም፤ 18 ነጥቦች አሉት። ዋነኛ ተፎካካሪሪው ማንቼስተር ዩናይትድ በገዛ ሜዳው ከማንቼስተር-ሢቲይ ባካሄደው ግጥሚያ ማይክል ኦወን በመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ጎል 4-3 ለማሸነፍ በቅቷል። ዩናይትድ በዌይን ሩኒይ አማካይነት ሶሥት ጊዜ ቢመራም ማንቼስተር ሢቲይ እስከ ዘጠናኛዋ ደቂቃ ድረስ ምላሹን በመስጠት እስከመጨረሻው ነበር የታገለው።

ማንቼስተር ዩናይትድ ከዚሁ በዕድል ካገኘው ድል በኋላ በ 15 ነጥቦች ሁለተኛ ነው። በተቀረ ሊቨርፑል ዌስት-ሃምን 3-2፤ አርሰናልም ዊጋን-አትሌቲክን 4-0 በማሸነፍ በ 12 ነጥቦች ወደተለመደው ከአንድ እስከ አራት አመራር ስፍራ ለመመለስ በቅተዋል። ማንቼስተር-ሢቲይ፣ ኤስተን-ቪላና ቶተንሃም-ሆትስፐርም በነጥብ እኩል ሆነው ይከተላሉ።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን አራተኛ ሣምንቱን በያዘው ውድድር ሰንበቱ በተለይ የሬያል-ማድሪድ ነበር። ሬያል ማድሪድ በዝነኛው በርናቤው ስታዲዮሙ ክሤሬስን 5-0 ሲረታ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው ቀደምት ኮከቡ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነበር። ባርሤሎና አትሌቲኮ-ማድሪድን 5-2 ሲሸኝ አትሌቲክ ቢልባዎ ደግሞ ቪላርሬያልን 3-2 አሸንፏል። በተረፈ ቫሌንሢያና ስፖርቲንግ-ጊዮን 2-2 ሲለያዩ ሤቪያ ኦሣሱናን 2-0ረትቷል። ከሰንበቱ የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ሶሥተኛ ግጥሚያዎች በኋላ ሶሥት ክለቦች እኩል ዘጠኝ ነጥብ ሲኖራቸው በጎል ብልጫ የሚመራው ሬያል ማድሪድ ነው። ባርሤሎና ሁለተኛ፤ ቢልባዎ ሶሥተኛ!

በጀርመን ቡንደስሊጋ በእኩል ነጥብ ቀደምትነቱን እንደያዙ የቀጠሉት ሃምቡግና ሌቨርኩዝን ትናንት የየበኩላቸውን ግጥሚያ በማሸነፍ አመራራቸውን ለማጠናከር ዕድላቸውን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ሃምቡርግ ከፍራንክፈርት አቻ-ለአቻ 1-1 ሲወጣ፤ ሌቨርኩዝንም ከብሬመን ጋር ባዶ-ለባዶ ከሆነ ተመሳሳይ ውጤት ማለፍ አልቻለም። የሁለቱ ቡድኖች አለማሸነፍ የጠቀመው ከአጀማመር ድክመት በኋላ ቀስ በቀስ ከፍ እያለ ለመጣው ለባየርን-ሙንሺን ነው። የጀርመኑ የብዙ ጊዜ ሻምፒዮን ከጥቂት ዕድል ጋርም ቢሆን ኑርንበርግን 2-1 ሲያሸንፍ አመራሩን በሶሥት ነጥቦች ለመቃረብ በቅቷል። በተመሳሳይ ነጥብ ሆፈንሃይምና ማይንስም አራተኛና አምሥተኛ ናቸው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ሣምፕዶሪያና ጁቬንቱስ በሊጋው አራተኛ ግጥሚያም በድል በመቀጠል ሙሉ ነጥብ ይዘው ይመራሉ። ጁቬ ሊቫርኖን 2-0 ሲረታ ሣምፕዶሪያ ደግሞ ሢየናን 4-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ሁለቱም ክለቦች እኩል ነጥብ አላቸው። ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ኢንተር-ሚላን በበኩሉ ካልጋሪን 2-1 ሲያሸንፍ ኤ.ሢ.ሚላን ደግሞ ቦሎኛን 1-0 ረትቷል። ለኢንተር ከእረፍት በኋላ ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው ዲየጎ ሚሊቶ ነበር። ከሰንበቱ ግጥሚያዎች ወዲህ ሣምፕዶሪያና ጁቬንቱስ በ 12 እኩል ነጥብ ቀደምቱ ሲሆኑ ኢንተር በአሥር ነጥብ ሶሥተኛ ነው። ኤ.ሢ.ሚላን የትናንት ግጥሚያውን ቢያሽንፍም በአማካይ ስምንተኛ ቦታ ላይ እንዳለ ቀጥሏል።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዢዮን የኦላምፒክ ሊዮን ከፓሪስ-ሣን-ዣርማን 1-1 መለያየት ለዢሮንዲን-ቦርዶ የብቻ አመራር መንገድ ከፍቷል። ቦርዶ በበኩሉ ግጥሚያ ቦሎኝ-ሱር-ሜርን 2-0 ሲረታ 16 ነጥቦች አሉት። ኦላምፒክ ሊዮንና ሞንትፔልዬን 4-2 ያሽነፈው ኦላምፒክ ማርሤይ ደግሞ በእኩል 14 ነጥቦች፤ ሆኖም በጎል ልዩነት ሁለተኛና ሶሥተኛ ናቸው። በኔዘርላንድ ሻምፒዮና ከቀደምቱ አራት ክለቦች ሶሥቱ ሲቀናችው ሰንበቱን በሽንፈት ያሳለፈው ፋየኖርድ ብቻ ነበር።
ኤንሼዴ ከሄረንፌን 2-0 ፤ እንዲሁም አይንድሆፈን ከፋየኖርድ 3-1 ሲለያዩ አያክስ-አምስተርድ ደግሞ ፌንሎን 4-0 አሰናብቷል። አይንድሆፈን በጎል ብልጫ አንደኝነቱን ሲይዝ ኤንሼዴ በተመሳሳይ ነጥብ ሁለተኛ ነው፤ አያክስ ደግሞ አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ በሶሥተኝነት ይከተላል። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን አልክማር በገዛ ሜዳው በኒሜኸን 1-0 ሲሸነፍ ወደ ስድሥተኛው ቦታ አቆልቁሏል። በፖርቱጋል አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ብራጋ በአመራሩ ሲቀጥል ቤንፊካ ፖርቶን 1-0 በማሸነፍ ሁለተኛ ነው።

ዘገባችንን በቢስክሌት ስፖርት ለማጠቃለል ትናንት በተጠናቀቀው በ 21 ደረጃ የተካሄደ የስፓኝ አገር አቋራጭ ውድድር በአጠቃላይ ነጥብ የአገሪቱ ተወዳዳሪ አሌሃንድሮ ባልቬርዴ አሸናፊ ሆኗል። ሌላው የስፓኝ ተወዳዳሪ ሳሙዔል ሳንቼዝም ሁለተኛ ሲወጣ ሶሥተኛ የሆነው የአውስትራሊያው ካዴል ኤቫንስ ነው። ቫልቬርድ ከትናንት ድሉ በኋላ በመጪው ዓመት ዢሮ-ዴ-ኢታሊያና ቱር-ደ-ፍራንስ ታላላቅ ውድድሮች ላይ ለማሸነፍ እንደሚዘጋጅ አስታውቋል።

MMDW/RTR/AFP

SL