1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 18 2002

እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቡጢ፣ ቴኒስና የአውቶሞቢል እሽቅድድም!

https://p.dw.com/p/JsEv
ሃምቡርግ ባየርን 1-0
ሃምቡርግ ባየርን 1-0ምስል AP

እግር ኳስ

ግብጽ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው ከሃያ ዓመት በታች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር የአራት ጊዜ ሻምፒዮኗ ብራዚል ትናንት ኮስታ ሪካን 5-0 በማሸነፍ ለቀጣይ አምሥተኛ ድል ተሥፋን የሚያጠናክር ግሩም ጅማሮ አድርጋለች። ለብራዚል ከአምሥት ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው ካርዴስ ነበር። በዚሁ ምድብ አምሥት ውስጥ ቼክ-ሬፑብሊክ ደግሞ አውስትራሊያን 2-1 ረትታለች። በሌሎች የምድብ ግጥሚያዎች ጀርመን ዩ.ኤስ.አሜሪካን በቀላሉ 3-0 ስትረታ ካሜሩን ደግሞ ደቡብ ኮሪያን 2-0 አሸንፋለች።
ምድብ ስድሥት ውስጥ የተባበሩት አረብ ኤሚሮችና ደቡብ አፍሪቃ 2-2 ተለያይተዋል። ያለፈው ጊዜ ሻምፒዮን አርጄንቲና ገና በማጣሪያው ተሰናክላ በመቅረቷ ታዛቢዎች ለዋንጫ ባለቤትነት የላቀ ዕድል የሚሰጡት ለብራዚል ወጣት ቡድን ነው። ሆኖም አስተናጋጇን አገር ግብጽን ጨምሮ ሶሥት የአፍሪቃ አገሮች ካሜሩን፣ ጋናና ናይጄሪያ፤ እንዲሁም አውሮፓውያኑ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ኢጣሊያና ስፓኝ ብርቱ ተፎካካሪዎች መሆናቸው አይቀርም። በስድሥት ምድቦች ተከፍሎ በሚካሄደው ውድድር 24 አገሮች እየተሳተፉ ነው።

ወደ አውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች እንመለስና ሰንበቱ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የቼልሢይ የድል ጉዞ በያዝነው የጨዋታ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገታበት ነበር። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ውስጥ ደግሞ ሬያል ማድሪድና ባርሤሎና አመራሩን እንደተጋሩ ሲቀጥሉ በኢጣሊያ ሤሪያ-አ በአንጻሩ ጁቬንቱስ ግንባር ቀደም ለመሆን የነበረውን ዕድል አልተጠቀመበትም። በጀርመን ቡንደስሊጋ ስኬት አልባ ከሆነ ጅማሮ በኋላ እንደገና የተነሣው የብዙ ጊዜው ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን በዚህ ሰንበት እንደገና መልሶ ማቆልቆሉ ግድ ሆኖበታል።

በዝርዝሩ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የኤፍ-ሢ.ቼልሢይ መቶ በመቶ የድል ጉዞ ባለፈው ቅዳሜ ሰባተኛ ግጥሚያ ላይ ለጊዜውም ቢሆን ተሰናክሏል። ክለቡ በዊጋን አትሌቲክ 3-1 ሲሽነፍ ይህም ወደ ሁለተኛው ቦታ ዝቅ እንዲል ነው ያደረገው። ዋነኛ ተፎካካሪው ማንቼስተር ዩናይትድ በአንጻሩ ስቶክ ሢቲይን 2-0 በመርታት በጎል ብልጫ ብቻም ቢሆን አመራሩን ለመረከብ ችሏል። ሁለቱ ክለቦች እያንዳንዳቸው 18 ነጥቦች አሏቸው። ከዚሁ ሌላ ሊቨርፑል ሃል ሢቲይን 6-1 በሆነ ውጤት ሲሸኝ ሶሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሶሥተኛ ነው። ለሊቨርፑል ሶሥቱን ጎሎች በማስቆጠር የዕለቱ ኮከብ የሆነው የስፓኙ ግሩም አጥቂ ፌርናንዶ ቶሬስ ነበር። በርንሊይን 5-0 የረታው ቶተንሃም ሆትስፐር ደግሞ እኩል 15 ነጥብ ይዞ በአራተኝነት ይከተለዋል።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ሃያላኑ ክለቦች ሬያል ማድሪድና ባርሤሎና አምሥተኛ ግጥሚያቸውንም በድል በመወጣት አመራሩን እንደተጋሩ ነው። ሬያል ማድሪድ ቴነሪፋን 3-0 ሲረታ ባርሤሎናም ማላጋን 2-0 አሸንፏል። በነገራችን ላይ ለባርሣ ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው የፈረንሣዩ ኮከብ ካሪም ቤንዜማ ነበር። ሁለቱም ቡድኖች እኩል 15 ነጥብ ሲኖራቸው ሬያል የሚመራው በአንዲት ጎል ብልጫ ነው። ሤቪያ በፊናው አትሌቲክ ቢልባዎን 4-0 በመሸኘት በ 12 ነጥቦች ሶሥተኝነቱን ይዟል። ማዮርካ፣ ቢልባዎና ቫሌንሢያ ቀረብ ብለው ይከተላሉ።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ዘንድሮ ማንም ያልጠበቀው ሣምፕዶሪያ ጎኔዋ ሊጋውን በ 15 ነጥቦች በበላይነት መምራቱን እንደቀጠለ ነው። ቡድኑ ያለፉትን ዓመታት ሻምፒዮን ኢንተር ሚላንን 1-0 ሲረታ ጥንካሬው ያጋጣሚ እንዳልሆነ ቢቀር በዚህ ግጥሚያ አሳይቷል። አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ በሁለተኝነት የሚከተለው ጁቬንቱስ ከቦሎኛ 1-1 አቻ-ላቻ ብቻ በመለያየቱ አንደኝነቱን ለመያዝ የነበረውን ዕድል ሊጠቀምበት አልቻለም። ኢንተር ከሰንበቱ ሽንፈት በኋላ በ 13 ነጥቦች ሶሥተኛ ነው። ጌኖዋ አመራሩን ይዞ ይቀጥል ወይም ኢንተር ሚላን እንደተለመደው ግንባር ቀደም ቦታውን ይያዝ ምናልባት የሚቀጥሉት ጥቂት ሣምንታት ይወስናሉ። በሌላ በኩል የዘንድሮው ጅማሮ ብዙም ያልተዋጣለት ኤ.ሢ.ሚላን ከባሪ ጋር ባዶ-ለባዶ በመለያየት ወደ 11ኛው ቦታ አቆልቁሏል።

በዚህ በጀርመን ቡንደስሊጋ በሣምንቱ ታላቅ ዕርምጃ ያደረገው ክለብ ሆፈንሃይም ነበር። ሆፈንሃይም ትናንት ሄርታ በርሊንን ግሩም በሆነ ጨዋታ 5-1 ሲሸኝ ከመሃል ተነስቶ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ሊል በቅቷል። ከአምሥት ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው ግሩም ተጫዋቹ የቦስናው ተወላጅ ቬዳድ ኢቢዜቪች ነበር። ለበርሊን በአንጻሩ ሽንፈቱ መሪር ነው የሆነው። ባለፈው የውድድር ወቅት ለሻምፒዮንነት ይፎካከሩ ከነበሩት ቀደምት ክለቦች መካከል አንዱ የነበረው ሄርታ በስድሥት ጨዋታዎች በተከታታይ በመሽነፍ የቡንደስሊጋው መጨረሻ ነው። ከዚህ ክስረት በኋላ አሠልጣኙ ሉሢየን ፋብር የሚባረሩበት ቀን ሩቅ የሚሆን አይመስልም።

“በዚህ ሁኔታ ማንም ረክቶ ሊቀጥል አይችልም። ግን ከዚህ ጨዋታ በኋላ ምንም ለማለት የምፈልገው ነገር የለም”

ሉሢየን ፋብር ባልጠበቁት ዱብ-ዕዳ የትችት ዒላማ ሲሆኑ ከክለቡ ጋር ለመክረም ከቻሉ እንኳ ቀላል ሣምንታት አይጠብቋቸውም። በሌላ በኩል ሃምቡርግና ሌቨርኩዝን በእኩል 17 ነጥቦች የቡንደስ ሊጋውን አመራር እንደያዙ ለመቀጠል ችለዋል። ሃምቡርግ ሌቨርኩዝንን የሚቀድመው በአንዲት ጎል ብልጫ ብቻ ነው። ባየርን ሙንሺን በአንጻሩ በሃምቡርግ 1-0 በመሽነፉ ከሶሥተኛው ወደ ሰባተኛው ቦታ ማቆልቆሉ ግድ ሆኖበታል። በተቀረ ሌቨርኩዝን ኮሎኝን በተመሳሳይ ውጤት 1-0 ሲረታ ሻልከ ዶርትሙንድ 1-0፤ ሽቱትጋርት ፍራንክፈርት 3-0፤ ብሬመን ማይንስም እንዲሁ 3-0፤ ቮፍስቡርግ ሃኖበር 4-2፤ ፍራይቡርግ መንሸን ግላድባህ 3-0 ተለያይተዋል። ሻልከና ብሬመን አራተኛና አምሥተኛ ናቸው።

በተረፈ በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ዢሮንዲን ቦርዶ፣ በኔዘርላንድ ሊጋ አይንድሆፈን፤ እንዲሁም በፖርቱጋል ሻምፒዮና ብራጋ በየፊናቸው እየመሩ ነው። ከዚሁ ሌላ ነገና ከነገ በስቲያ የአውሮፓ ሻምፒናዮና ሊጋ ውድድር ሁለተኛ የምድብ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ከነዚሁ ዋና ዋናዎቹም ነገ በፊዮሬንቲናና በሊቨርፑል፤ በባርሤሎናና በዲናሞ ኪየቭ፤ በሩሢያው ሻምፒዮን በሩቢን ካዛንና በኢንተር ሚላን፤ እንዲሁም ከነገ በስቲያ በባየር ሙንሺንና በጁቬንቱስ፤ በሬያል ማድሪድና በኦላምፒክ ማርሤይ መካከል የሚካሄዱት ናቸው።

አትሌቲክስ

ባለፈው ሣምንት ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ውስጥ የአትሌቲክ ውድድሮች ተካሂደው ነበር። በሣምንት አጋማሽ ጃፓን-ካዋዛኪ ላይ በተካሄደው ውድድር በወንዶች አንድ መቶ ሜትር ሩጫ አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ በ 10,13 ሤኮንድ አንደኛ ወጥቷል። በ 110 ሜትር መሰናክል ጃማይካዊው ድዋይት ቶማስ ሲያሸንፍ የባሃማስ ዶናልድ ቶማስ ደግሞ በከፍታ ዝላይ ባለድል ሆኗል። በሴቶች መቶ ሜትር አሜሪካዊቱ አሊይሰን ፌሊክስ ቀዳሚ ስትሆን በርዝመት ዝላይ ሩሢያዊቱ ታቲያና ሌቤዴቫ አሸንፋለች።
አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ ደቡብ ኮሪያ-ዴጉ ላይም የመቶ ሜትር ድሉን ሲደግመው አሣፋ ፓውልና ኔስቶር ካርተር፤ ሁለቱም ከጃማይካ ተከትለውት ገብተዋል። የባህሬይኑ ዩሱፍ ካሜል በ 800 ሜትር ሲያሸንፍ ጠንካራ ዓለምአቀፍ ተፎካካሪዎች በሌሉበት በአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል ገብተዋል። ኬንያውያን በሴቶች 1,500 ሜትር ሩጫም ሲያሸንፉ ሩሢያዊቱ የምርኩዝ ዝላይ ኮከብ የለና ኢዚምባየቫም በተለመደ ልዕልናዋ ለድል በቅታለች። በተቀረ ዓለምአቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ከለንደን ቀጥሎ የ 2016 ዓ.ም. የኦሎምፒክ ጨዋታን የምታዘጋጀዋን ከተማ በፊታችን አርብ ይመርጣል። ለውድድር የቀረቡት ከተሞች ቺካጎ፣ ቶኪዮ፣ ሪዮ-ዴ-ጃኔይሮና ማድሪድ ናቸው።

ቡጢ

የኡክራኒያው ተወላጅ ቪታሊይ ክሊችኮ ሜክሢካዊ-አሜሪካዊ ተጋጣሚውን ክሪስቶባል አሬዎላን ያለ ብዙ ድካም በማሸነፍ የዓለም ቡጢ ካውንስል WBC የከባድ ሚዛን ማዕረጉን አስከበረ። ክሊችኮ ያሽነፈው በአሥረኛው ዙር መጨረሻ በቃኝ በማሰኘት ነው። የሎስ አንጀለሱ ተወላጅ አሬዎላ ክፉኛ ሲደበደብ ሜክሢካዊ ምንጭ ያለው የመጀመሪያው የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ለመሆን የነበረው ሕልምም ዕውን ሳይሆንለት ቀርቷል። በሌላ መለስተኛ የከባድ ሚዛን ግጥሚያም ካናዳዊው ዣን ፓስካል የኢጣሊያ ተጋጣሚውን ሢልቪዮ ብራንኮን እንዲሁ በአሥረኛው ዙር ላይ በበቃኝ አሸንፏል።

ዘገባችንን በአውቶሞቢል ስፖርት ለማጠቃለል ትናንት ሢንጋፑር ላይ ተካሂዶ የነበረው የፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም አሸናፊ የብሪታኒያው ዘዋሪ ሉዊስ ሃሚልተን ሆኗል። ያለፈው ዓመት አሸናፊ የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ሶሥተናኛ ሲወጣ የብሪታኒያው ጄሰን ባተንም ውድድሩን በአምሥተኝነት ፈጽሟል። ባተን በዚህ ውጤቱ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን በሚያደርገው ትግል ጠቃሚ ነጥቦችን ነው የሰበሰበው። የዓለም ሻምፒዮናው ሊጠናቀቅ ሶሥት እሽቅድድሞች ቀርተው ሳለ በአጠቃላይ ነጥብ ይመራል። ጄሰን 84 ነጥቦች ሲኖሩት 69 ይዞ በሁለተኝነት የሚከተለው ብራዚላዊው ሩበንስ ባሪቼሎ ነው።

MM/AA/DW/AFP/RTR