1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 25 2002

“አሸናፊዋ፤ ሪዮ-ዴ-ጃኔይሮ ናት”-የዓለምአቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚደንት ዣክ ሮግ! ብራዚል በሣምንቱ መጨረሻ ኮፐንሃገን ላይ በተካሄደው የኦሎምፒኩ ኮሚቴ ጠቅላይ ጉባዔ የ 2016 ዓ.ም.ን የኦሎምፒክ ጨዋታ እንድታስተናግድ ተመርጣለች።

https://p.dw.com/p/Jy7G
ሪዮ-ዴ-ጃኔይሮ
ሪዮ-ዴ-ጃኔይሮምስል AP

ሪዮ ውስጥ በዝነኛው ኮፓ-ካቫና የባሕር ዳርቻ ውሣኔውን ተከትሎ የታየው የሕዝብ ፈንጠዝያ ወሰን አልነበረውም። ሪዮ-ዴ-ጃኔይሮ የ 2016 ዓ.ም.ን የኦሎምፒክ ጨዋታ እንድታስተናግድ መመረጧ ያስደሰተውና ያስፈነደቀው ብራዚልን ብቻ አይደለም። እስካሁን ይህን ታላቅ ትዕይንት ማዘጋጀቱ ተነፍጎት የቆየውን መላውን ደቡብ አሜሪካ ጭምር ነው። አንዴ የኤኮኖሚ ብቃት፤ ሌላም ጊዜ ይህ ወይም ያ ምክንያት እየተሰጠ ክፍለ-ዓለሚቱ ለአያሌ ዓመታት በተመልካችነት ሚና ተወስና ቆይታለች። በኮፐንሃገኑ የዓለምአቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጉባዔ ላይ ከዝነኛው የዓለም እግር ኳስ ጠበብ ከፔሌ ጋር በአካል ተገኝተው ከተማቸውን ያስተዋወቁት የብራዚሉ ፕሬዚደንት ሉዊስ-ኢናሢዮ-ዳ-ሢልቫ የአገራቸውን የይገባኛል ጥያቄ ገና ከጅምሩ ጠንከር አድርገው ነበር ያቀረቡት።

“በዓለም ላይ በኤኮኖሚ ጥንካሬ ታላላቅ ከሆኑት አሥር ሃገራት መካከል እስካሁን የኦሎምፒኩን ጨዋታ ለማዘጋጀት ዕድል ያላገኘችው ብራዚል ብቻ ናት። አሁንም ቢሆን እዚህ ለከተሞቻቸው ለመወዳደር ከቀረቡት ከአራቱ አገሮች መካከል የኦሎምፒክን ወይም የፓራሊምፒክስን ጨዋታ ብራዚል አንዴም አስተናግዳ አታውቅም። በመሆኑም ቢሣካ ለኛና ለመላው ደቡብ አሜሪካ ልዩ ዕድል በሆነ ነበር”

የፕሬዚደንት ሉላ ምኞትና የይገባናል ጥሪ ታዲያ በመጨረሻ ሰሚ ጆሮ ማግኘቱ አልቀረም። የዓለምአቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዓባላት የብራዚልንና የደቡብ አሜሪካን ሕዝብ ፍላጎት በማያሻማ ሁኔታ ነው የተከተሉት። እርግጥ የብራዚል ተጠሪዎችና ሕዝብ ያሳዩት ጠንካራ ፍላጎትም ለሪዮ መመረጥ ወሣኝ አስተዋጽኦ አድርጓል። የዝንባሌ መለኪያ መጠይቅ ውጤቶች እንዳመለከቱት ለታላቁ የስፖርት ትዕይንት አስተናጋጅነት የሪዮን ያህል የሕዝብ ፍላጎት የታየበት ተወዳዳሪ ከተማ አልነበረም። 85 በመቶው ነዋሪ ቆሞለታል። በአንጻሩ በቺካጎ ለምሳሌ 67 በመቶ ብቻ ነበር። ታዲያ ከተማይቱ ምንም እንኳ ቀደም ሲል ብርቱ ተፎካካሪ ሆና ብትቆጠርም በመጀመሪያው ዙር ቀድማ መውጣቷ ከዚህ አንጻር ብዙም አያስደንቅም። ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ሳይቀር በሥፍራው መገኘታቸውም ለቺካጎ አልበጀም።

በተቀረ ቶኪዮ በሁለተኛው ዙር ድምጽ አሰጣጥ ስትወሰን ለሪዮ-ዴ-ጃኔይሮ እስከመጨረሻው ተሻሚ ሆና የቀጠለችው የስፓኝ ርዕሰ-ከተማ ማድሪድ ነበረች። ግን አስደሳች ነው፤ ሪዮ ከፉክክሩ ገናና ሆና ወጥታለች። በዚሁ ልባቸው የተነካው የብራዚል ፕሬዚደንት ምኞታቸው ዕውን በመሆኑ እርግጥ የደስታ እንባ ሳይተናነቃቸው አልቀረም።

“በመጀመሪያ በአቀራረቡ ወቅት ወኔ አልነበረኝም። አሁን ግን አልቅሻለሁ” ሉላ-ዳ-ሢልቫ!
መለስ ብሎ ላስተዋለ የኦሎምፒኩ ጨዋታ አብዛኛውን በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ መካከል ሲፈራረቅ ነው የቆየው። እስካሁን ከተካሄዱት 26 ጨዋታዎች 15ቱ ለምሳሌ በአውሮፓ ነበሩ። እናም አሁን ጨዋታው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ደቡብ አሜሪካ መሸጋገሩ ጀርመናዊው የዓለምአቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ምክትል ፕሬዚደንት ቶማስ ባህም እንዳሉት የውድድሩን ዓለምአቀፍ ገጽታ ይበልጡን የሚያድስ ነው የሚሆነው።

“ምርጫው ለዓለምአቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴና ለኦሎምፒኩ ጨዋታም ግሩም የሆነ ምርጫ ነው። ምክንያቱም በዚህ ምርጫ ከጨዋታው ዓለምአቀፋዊነት አንጻር ታላቅ የወደፊት ዕርምጃ አድርገናል። ጥቃሚ የዓለምአቀፋዊነት ምልክት ነው የታየው። የስፖርቱ ዓለም እዚህ ከበፊቱ ይበልጥ ተቀራርቧል”

እርግጥ ጀርመን ከማድሪድ ይልቅ ሪዮን ለመደገፍ ሌላም ምክንያት አላት። በብራዚሏ ከተማ መመረጥ ጀርመን በ 2018 የክረምቱን ኦሎምፒክ ጨዋታ ለማስተናገድ ያላት ዕድል ከፍ ያለ ነው የሚሆነው። ለማንኛውም የብራዚል ታላቅ ከተማ ሪዮ-ዴ-ጃኔይሮ የአሎምፒክ መንደርና የፕሬስ ማዕከል፣ የሌላ ስፖርት ዓይነቶች አዳራሾችና የአትሌቲክስ ስታዲዮም ለኦሎምፒኩ ጨዋታ ለማነጽ፤ ለማደስ ታቅዳለች። መክፈቻውና መዝጊያው ትዕይንት የሚደረገው እርግጥ በእግር ኳስ ታላቅ ዝናን ባተረፈው በነፔሌና በበነጋሪንቻ የአንዴ የተውኔት መድረክ በሪዮ ማራካና ስታዲዮም ነው።

የብራዚል መንግሥት በጠቅላላው ትራንስፖርትን፣ መዋቅራዊ ተሃድሶንና ጸጥታ ጥበቃን ጨምሮ ለኦሎምፒኩ ዝግጅት 15 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚጠጋ በጀት ለመመደብ ያቅዳል። ሉዊስ-ኢናሢዮ-ዳ-ሢልቫ ብራዚል በአገርም ሆነ በዓለምአቀፍ ደረጃ እስከዚያው አቻ ያልታየለት መስተንግዶ እንደምታደርግ ነው የተናገሩት። ብራዚል ከ 2014 ጀምሮ በሁለት ዓመት ልዩነት ውስጥ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫና የኦሎምፒክ ጨዋታ ማዕከል ስትሆን ዝግጅቱ ለአገሪቱ ስፖርት ብቻ ሣይሆን ለኤኮኖሚ ዕርምጃም ታላቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አንድና ሁለት የለውም። ታላላቆቹን የስፖርት ትዕይንቶች በቅርብ ለማየት በሕይወት ዘመን ምናልባት አንዴ ብቻ ለሚገኘው ዕድል መብቃትም ለብራዚል ሕዝብ መታደል ነው።

በተቀረ ትናንት በዚህ በጀርመን ተካሂዶ የነበረው 13ኛ የኮሎኝ ከተማ ማራቶን ከሞላ ጎደል የኬንያ አትሌቶች ልዕልና የታየበት ሆኖ አልፏል። በወንዶች ኤቫንስ ኪፕኮስጋይና ሣምሶን ቡንጋኢ ቀዳሚዎች ሲሆኑ በሴቶች ጀርመናዊቱ ዛብሪና ሞከንሃውፕት አሸናፊ ሆናለች። የኬንያ ሴቶች ደግሞ ሁለተኛና ሶሥተኛ ወጥተዋል።

እግር ኳስ

ግብጽ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው ከሃያ ዓመት በታች ወጣቶች የዓለም ዋንጫ ውድድር የመጀመሪያው የምድብ ዙር በሣምንቱ መጨረሻ ላይ ተጠናቋል። ወደ ሩብ ፍጻሜው ለማለፍ የሚደረጉት ግጥሚያዎች ዛሬ የሚጀምሩ ሲሆን የዕለቱ ተጋጣሚዎች ስፓኝ ከኢጣሊያና፤ ፓራጉዋይ ከደቡብ ኮሪያ ናቸው። በነገው ዕለት ደግሞ ጋና ከደቡብ አፍሪቃ፤ አስተናጋጇ ግብጽ ከኮስታ ሪካ፤ እንዲሁም ሁንጋሪያ ከቼክ ሬፑብሊክ ይጋጠማሉ። በማግሥቱ ረቡዕ ተራው ብራዚል ከኡሩጉዋይ፤ ቬኔዙዌላ ከተባበሩት አረብ ኤሞሮች፤ እንዲሁም ጀርመን ከናይጄሪያ ነው።
የፍጻሜው ግጥሚያ ግማሽ ፍጻሜውን ተከትሎ በመጪው ጥቅምት 6 የሚካሄድ ሲሆን የብራዚልን የዋንጫ ዕድል ከፍ አድርገው የሚመለከቱት ታዛቢዎች ብዙዎች ናቸው። በዚያው በአፍሪቃ ትናንት ደግሞ የክለቦች ሻምምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ ዙር የመጀመሪያ ግጥሚያዎች ተካሂደው ነበር። የሱዳኑ አል-ሂላል በዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ ተጋጣሚው በማዜምቤ በገዛ ሜዳው 2-5 ሲረታ በሁለት የናይጄሪያ ክለቦች መካከል በተካሄደው ሌላ ግጥሚያ ደግሞ ኸርትላንድ ኤፍ.ሢ. ካኖ ፒላርስን 4-0 አሸንፏል።

በዚህ በአውሮፓ ሰንበቱ በቀደምቱ ሊጋዎች ውድድር በየቦታው የአመራር ለውጥ የታየባቸው ነበሩ። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ የሬያል ማድሪድ የዘንድሮ ግሩም ጅማሮ በሤቪያ በደረሰበት 2-1 ሽንፈት ለጊዜውም ቢሆን ተገትቷል። የቡድኑ ኮከብ የክሪስቲያኖ ሮናልዶ በአካል ጉዳት የተነሣ አለመሰለፍ ሬያልን በጣሙን ነው ያጎደለው። ባርሤሎና በሌላ በኩል አልሜይራን 1-0 በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶሥት ነጥቦች ልዩነት ለመምራት በቅቷል። ዝቅ ብለው የሚከተሉት ሬያል ማድሪድና ሤቪያ በ 15 ነጥቦች እኩል ናቸው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ባለፈው ሣምንት በዊጋን አትሌቲክ ደርሶበት ከነበረው አስደንጋጭ ሽንፈት ያገገመው ቼልሢይ ሊቨርፑልን ያህል ሃያል ተፎካካሪ 2-0 በማሸነፍ እንደገና ወደ አመራሩ ተመልሷል። ቼልሢይ ከስምንት ሰባት ግጥሚያዎቹን በድል በመወጣት ሊጋውን በ 21 ነጥቦች ይመራል። ከሰንደርላንድ ጋር አቻ-ላቻ፤ 2-2 የተለያየው ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ በ 19 ነጥቦች በሁለተኝነት ይከተላል፤ ሶሥተኛው ቶተንሃም ሆትስፐር ነው። ሊቨርፑል ወደ አምሥተኛው ቦታ አቆልቁሏል።

እንደ ሊቨርፑል የታላላቅ ክለቦች ማቆልቆልና መንገዳገድ ከተነሣ በዚህ በጀርመን ቡንደስሊጋም ይሄው የባየርን ሙንሺን መለያ እየሆነ ነው። በአዳዲስ ተጫዋቾች ላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያፈሰሰው ቀደምት ክለብ በገዛ ሜዳው ከኮሎኝ ጋር ባደረገው ግጥሚያ በድን ሆኖ ባዶ-ለባድ ተለያይቷል። ይህም ወደ ስምንተኛው ቦታ እንዲወርድ ነው ያደረገው። አሠልጣኙ ሉዊስ-ፋን-ሃል ራሳቸው የቡድናቸውን ድክመት ሊሸፋፍኑት አልሞከሩም።

“የአካል ቅልጥፍናና ጠንካራ ትግል ጎድሏል። በተጋጣሚያችን 16 ሜትር ክልል ውስጥ ብዙ ያለቀለት ዕድል ለመፍጠር አልቻልንም። እና በቂ አልነበረም”
በአንጻሩ ሌቨርኩዝንና ሃምቡርግ በድል ጉዟቸው በመቀጠል አመራራቸውን እያጠናከሩ ነው። ሻልከና ብሬመንም የሰንበት ግጥሚያቸውን በማሸነፍ ከቀደምቱ አራት ክለቦች መካከል ለመሆን ችለዋል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ሻምፒዮኑ ኢንተር ሚላን ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጋውን አመራር ሊይዝ በቅቷል። ዘንድሮ ከተጠበቀው በላይ ጠንክሮ የተገኘው ሣምፕዶሪያ ጄኖዋ በጎል ብቻ በመበለጥ ሁለተኛ ሲሆን ጁቬንቱስ በመሽነፉ አመራሩ አምልጦታል። ሁለት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሶሥተኛ ነው። በተረፈ በፈረንሣይ ሊጋ የቦርዶ የመጀመሪያ ሽንፈት ኦላምፒክ ሊዮን አመራሩን እንዲይዝ ሲበጅ በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮንም እንዲሁ አይንድሆፈን ቀደምቱን ቦታ ለኤንሼዴ መልሶ አስረክቧል። በፖርቱጋል ሻምፒዮና በአንጻሩ ዘንድሮ ማንም ያልጠበቀው ክለብ ብራጋ ግንባር-ቀደም ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ሊጋውን በአምሥት ነጥቦች ይመራል።

ዘገባችንን በአውቶሞቢል ስፖርት ለማጠቃለል ትናንት ጃፓን ውስጥ በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል አሸንፏል። በዚሁ በፌትልና በብሪታኒያው ቀደምት ዘዋሪ በጄሰን ባተን መካከል በአጠቃላይ ነጥብ ያለው ልዩነት ወደ 16 ሲያቆለቁል ድሉ የዘንድሮውን ሻምፒዮና ይበልጥ ማራኪ አድርጎታል። ሁለተኛ የኢጣሊያው ጃርኖ ትሩሊ ሰወጣ እሽቅድድሙን በሶሥተኝነት የፈጸመው የብሪታኒያው ሉዊስ ሃሚልተን ነው። የዘንድሮው ውድድር ሊያበቃ የቀሩት ሁለት እሽቅድድሞች ብቻ ናቸው። በአጠቃላይ ነጥብ አንደኛ ጄሰን ባተን፣ ሁለተኛ ብራዚላዊው ሩበንስ ባሪቼሎና ሶሥተኛ ዜባስቲያን ፌትል ሲሆኑ ሁሉም የዓለም ሻምፒዮን የመሆን ዕድል አላቸው።

መሥፍን መኮንን፣

ተክሌ የኋላ፣