1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 8 2002

ያለፈው ሣምንት በተለይም የኢትዮጵያ አትሌቶች በስቶክሆልም የአዳራሽ ውስጥ ውድድር ግሩም ውጤት ያስመዘገቡበት ነበር።

https://p.dw.com/p/M1q8
ዩሤይን ቦልትምስል AP

ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች

ባለፈው ሣምንት በዓለምአቀፍ ደረጃ ከተደረጉት የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል ዋነኛው በስዊድን ርዕሰ-ከተማ በስቶክሆልም የተካሄደው ነበር። በዚሁ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር በርከት ያሉ ቀደምት አትሌቶች ሲታሰፉ በተለይም መሠረት ደፋርና ቃልኪዳን ገዛኸኝ በተዋደሩበት ርቀት በማሽነፍ ታላቅ ጥንካሬ አሳይተዋል። መሠረት ደፋር በአምሥት ሺህ ሜትር ምንም እንኳ ባለፈው ዓመት በዚያው ስፍራ ያስመዘገበችውን የዓለም ክብረ-ወሰን ለማሻሻል ባትችልም ግሩም በሆነ አሯሯጥ ለድል በቅታለች። ክብረ-ወሰኑን ለማስተካከል ግማሽ ሤኮንድ ያህል ብጫ ነበር የጎደላት። ለማንኛውም በዚሁ ሩጫ ለቱርክ የተወዳደረችው አትሌት ዓለሚቱ በቀለ በአዲስ የአውሮፓ ክብረ-ወሰን ሁለተኛ ስትወጣ ስንታየሁ እጅጉ ሶሥተኛ ሆናለች። ድሉ የተሟላ የኢትዮጵያውያን ድል ነበር ለማለት ይቻላል።

ሌላዋ ድንቅ ኢትዮጵያዊት ቃልኪዳኝ ገዛኸኝ ደግሞ በ 1,500 ሜትር ሩጫ ሩሢያዊቱን አና አልሚኖቫንና ኬንያዊቱን ሢልቪያ ኪቤትን በማስከተል አሸናፊ ሆናለች። ቃልኪዳን ሩጫውን በአራት ደቂቃ ከ 3,28 ሤኮንድ ጊዜ ስትፈጽም ይህም አዲስ የአፍሪቃ ክብረ-ወሰን መሆኑ ነው። በወንዶች ሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ኬንያዊው አውጉስቲን ቾጌ ሲያሸንፍ ታሪኩ በቀለ ሌላውን ኬንያዊ ሣሚ ሙታሂን ከኋላው በማስቀረት ሁለተኛ ወጥቷል። የአራትና ስምንት መቶ ሜትር ሩጫው ደግሞ የሱዳን አትሌቶች ልዕልና የታየበት ነበር። ራባህ ዩሱፍና አቡባከር ካኪ በየፊናቸው አሽናፊ ለመሆን በቅተዋል።

በስልሣ ሜትር መሰናክል ሩጫ ኩባዊው የዓለም ሻምፒዮን ዴይሮን ሮብልስ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሩጫ በሴቶች ደግሞ አሜሪካዊቱ አንጄላ ዊሊያምስ ቀዳሚ ሆናለች። በከፍታ ዝላይ ክሮኤሺያዊቱ የዓለም ሻምፒዮን ብላንካ ቭላዚች ሁለት ሜትር ከአንድ ከፍታን በማቋረጥ ስታሽንፍ በርዝመት ዝላይ ደግሞ ሩሢያዊው ቪክቶር ኩዝኔትሶቭ 8 ሜትር ከ 09 በመዝለል ባለድል ሆኗል። በተቀረ በፊታችን ቅዳሜ በርሚንግሃም ላይ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር የሚካሄድ ሲሆን በታላቅ ጉጉት ከሚጠበቁት ቀደምት ዓለምአቀፍ አትሌቶች አንዱ ቀነኒሣ በቀለ ነው። ይሄው ውድድር ሣምንት የምናተኩርበት ይሆናል።

ወደ እሢያ ሻገር እንበልና እንደ ኢትዮጵያ ባለድል አትሌቶች ባልተለመዱባት ወይም ጨርሶ ብርቅዬ በሆኑባት ለምሳሌ በፓኪስታን የአገሪቱ ሴት አትሌት ናሢም ሃሚድ በደቡብ ኢሢያ ፌደሬሺን ጨዋታ አሸንፋ ባለፈው ሐሙስ ወደ አገሯ ስትመለስ የተደረገላት አቀባበል ጨርሶ የተለየ ነበር። የ 22 ዓመቷ ወጣት ናሢም በመቶ ሜትር ሩጫ በማሽነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ስትሽለም በአካባቢው የ 26 ዓመታት ውድድር ታሪክ ውስጥ ለድል የበቃችው የመጀመሪያዋ የፓኪስታን ሴት መሆኗ ነበር። በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ደጋፊዎችና ዘመድ-አዝማድ በካራቺ አየር ጣቢያ ተገኝተው በደመቀ ሁኔታ ሲቀበሏት የስፖርት ባለሥልጣናትና የከተማይቱ ከንቲባ ሳይቀር በገንዘብ ሽልማት በሽልማት አድርገዋታል። የአገሪቱ መማክርት እንዲያውም ከድሆች መኖሪያ ቀበሌ ለመነጨችው አትሌት የሙሉ ቀን ሥራና ቤት እንዲሰጥ እስከመጠየቅ ነው የደረሱት።

በተቀረ የጃማይካው ፈጣን መንኮራኩር ዩሤይን ቦልት ባለፈው ቅዳሜ በአገሩ ተካሂዶ በነበረ የአራት መቶ ሜትር ሩጫ በማሸነፍ ለያዝነው 2010 ዓ.ም. የውድድር ወቅት ተሥፋ ሰጭ የሆነ ግሩም ጅማሮ አድርጓል። የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ቦልት ሩጫውን ያሽነፈው ለስፍራው ፈጣን የሆነውን ጊዜ በመሮጥ ነው። ዩሤይን ቦልት በመቶና ሁለት መቶ ሜትር የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ሲሆን በአራት መቶ ሜትርም ቁንጮ ለመሆን መነሣቱ ይታወቃል። ለዚሁ ዕድል ከሚሰጡት አጋጣሚዎች ምናልባት አንዱ በፊታችን ጥቅምት ወር ሕንድ ውስጥ የሚካሄደው የኮመንዌልዝ አገሮች ጨዋታ ሊሆን ይችላል። እርግጥ የሚሳተፍ ከሆነ!

የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታ በቫንኩቨር

Äthiopien Robel Teklemariam
ሮቤል ተ/ማርያምምስል AP

21ኛው የቫንኩቨር-ካናዳ የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታ ባለፈው አርብ በደመቀ ትርዒት ሲከፈት 2,700 ገደማ የሚጠጉ የ 82 ሃገራት ስፖርተኞች እየተሳተፉበት ነው። እርግጥ በዋዜማው የጆርጂያው የቦብ ተወዳዳሪ የናዳር ኩማሪታሽቪሊ በልምምድ ላይ እንዳለ ተንሸራቶ በደረሰበት ከባድ ጉዳት መሞት በውድድሩ ላይ አሳዛኝ ጥላውን ሳያሳርፍ አልቀረም። የ 21 ዓመቱ ወጣት በሰዓት 145 ኪሎሜትር በሚሆን ፍጥነት በአግባብ ካልተሸፈነ የብረት ሞሶሶ ጋር ተላትሞ ሲሞት ይህ ዘግናኝ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ከስፖርተኞቹ አዕምሮ በቀላሉ መውጣቱ የሚያጠራጥር ነው። ሆኖም የኦሎምፒኩ መርሆ ነውና ጨዋታው መቀጠል ስላለበት ቀጥሏል። ይሄን ለጊዜው በዚሁ ተወት እንድርገውና በሌላ በኩል እንደ አትሌቲክሱ መድረክ በበረዶው የስፖርት ዓለም ገናና መሆን ቀርቶ ጨርሶ የማትታወቀው ኢትዮጵያም በነገራችን ላይ ዘንድሮ የቫንኩቨር ኦሎምፒክ ተሳታፊ ናት። አገሪቱን ለዚህ ያበቃት ብቸኛ ተወዳዳሪ ደግሞ ሮቤል ተ/ማርያም ይባላል። ሮቤል በመክፈቻው ስነ-ስርዓት ላይ ከብዙ ሃገራት ስፖርተኞች ጋር አብሮ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጎልቶ እንዲታይ አድርጓል። ለመሆኑ ሮቤል ወደዚህ የስፖርት ዓለም እንዴት ሊያተኩር ቻለ? መወዳደር የጀመረው መቼ ነው? ዘንድሮስ ምን ዝግጅት አድርጓል? የዋሺንግተን ዘጋቢያችን አበበ ፈለቀ እነዚህንና መሰል ጥያቄዎች በማንሣት አነጋግሮት ዘግቧል።

ዓለምአቀፍ ቴኒስ

በትናንትናው ዕለት ካሊፎርኒያ-ሣን ሆሴ ላይ በተካሄደ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያ የስፓኙ ፌርናንዶ ቫርዳስኮ ቀደምቱን አሜሪካዊ ኤንዲይ ሮዲክን በሶሥት ምድብ ጨዋታ ባልተጠበቀ ሁኔታ 2-1 በመርታት አሸንፏል። ቫርዳስኮ በትናንቱ ውጤት በአጠቃላይ ለአራተኛውና በአሜሪካ ምድር ላይም ለሁለተኛው የውድድር ድሉ መብቃቱ ነበር። ለንጽጽር ያህል ሮዲክ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ሰባተኛው ሲሆን ቫርዳስኮ 11ኛ ነው። በመሆኑም የአሜሪካ ተጋጣሚውን በማሽነፉ በጣሙን ነው የተደሰተው። በብራዚል-ኦፕን ደግሞ የቀድሞው የፍሬንች-ኦፕን ሻምፒዮንና የዓለም ግንባር ቀደም ተጫዋች ሁዋን-ካርሎስ-ፌሬሮ የፖላንድ ተጋጣሚውን ሉካሽ ኩቦትን በለየለት 6-1, 6-0 ውጤት እንዳልነበር አድርጎ ከሜዳ በማስወጣት ለ 13ኛ የውድድር ድሉ በቅቷል። የስፓኙ ኮከብ ባለፈው ወር አውስትሬሊያን-ኦፕን ውድድር ገና በመጀመሪያው ዙር ተሸንፎ መውጣቱ የሚታወስ ነው።

በፓሪስ የአዳራሽ ውስጥ የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ ሩሢያዊቱ ኤሌና ዴሜንቲቫ የቼክ ተጋጣሚዋን ሉሲ ሳፎሮቫን አሸንፋለች። ባለፈው ዓመት በዚያው ቦታ ከፍጻሜ ደርሳ በአሜሊ ማውሬስሞ የተረታችው ሩሢያዊት በፓሪሱ ውድድር ስታሸንፍ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። በታይላንድ የፓታያ-ኦፕን ፍጻሜም ሌላዋ የሩሢያ ኮከብ ቬራ ዝቮናሬቫ ታማሪን ታናሱጋምን በአገሯ በማሽነፍ ለተከታታይ ሁለተኛ የፓታያ ድሏ በቅታለች። ዝቮናሬቫ ያሸነፈችው 6-4, 6-4 በሆነ የበላይነት በታየበት ውጤት ነበር። ለታማሪን በአንጻሩ በአገሯ ምድር ሻምፒዮን ለመሆን የነበራት ተሥፋ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል። በተቀረ በትናንትናው ዕለት በዱባይና በሜንፊስ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ሻምፒዮና ውድድሮች ተጀምረው እየተካሄዱ ነው።

በእግር ኳስ ለማጠቃለል በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ማጣሪያውን ዙር አልፈው ለጥሎ ማለፍ ውድድር በደረሱት 16 ቡድኖች መካከል ነገና ከነገ በስቲያ የመጀመሪያዎቹ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ውድድሩን በዓለም ዙሪያ በቴሌቪዥን አማካይነት ለሚከታተሉት ኳስ አፍቃሪዎች ነገ ለምሳሌ ኦላምፒክ ሊዮን-ከሬያል ማድሪድ ወይም ኤ-ሢ,ሚላን-ከማንቼስተር ዩናይትድን የመሳሰሉት ማራኪ ግጥሚያዎች ይጠብቋቸዋል።

መስፍን መኮንን/AFP/RTR

አርያም ተክሌ