1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 4 2002

ሣምንቱ በአውሮፓ የእግር ኳስ መድረክ ላይ በሻምፒዮናው ሊጋና በብሄራዊው ክለቦች ውድድርም እጅግ አርኪ ግጥሚያዎች የታዩበት ሆኖ ነው ያለፈው።

https://p.dw.com/p/MuUN
ናኒምስል AP

የአውሮፓ የእግር ኳስ ሻምፒዮና

Fußball Bayern München Manchester United April 2010
አርየን ሮበንምስል AP

የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ሩብ ፍጻሜ ውድድር በሣምንቱ አጋማሽ ላይ ሲጠናቀቅ ከብዙ ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድም የእንግሊዝ ክለብ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ ሳይችል ቀርቷል። ባለፉት ሶሥት ዓመታት እንዲያውም ከአራት ሶሥቱ የግማሽ ፍጻሜ ተሳታፊዎች የእንግሊዝ ክለቦች ነበሩ። የፕሬሚየር ሊጉ ልዕልና እንግዲህ በአውሮፓ ደረጃ ዘንድሮ ምናልባት ለጊዜውም ቢሆን በዚሁ መገታቱ ነው።

በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ እስከ ግማሽ ፍጻሜው በመዝለቅ ደምበኛ ሆነው ከቆዩት ቀደምት የእንግሊዝ ክለቦች መካከል ሊቨርፑል ዘንድሮ ደካማው ሲሆን ቼልሢይም ባለፈው ወር ገና በመጀመሪያው ጥሎ ማለፍ ግጥሚያ በኢንተር ሚላን ተሸንፎ ቀድሞ መሰናበቱ አይዘነጋም። ቀሪዎቹ ማንቼስተር ዩናይትድና አርሰናል ደግሞ በሩብ ፍጻሜው መወሰኑ ግድ ነው የሆነባቸው።

በተለይ በጀርመኑ ባየርን ሙንሺን ተሽንፎ ለወጣው ለማንቼስተር ዩናይትድ ሣምንቱ ይበልጡን መሪር ነው። ማኒዩ በዚህ በሚዩኒክ በመጀመሪያው ግጥሚያ ቀድሞ ከመራ በኋላ ብዙ ዕድሉን ሳይጠቀም ቀርቶ 2-1 መሽነፉ አይዘነጋም። ባለፈው ረቡዕ ምሽት የመልስ ግጥሚያም ሶሥት ጎል ካስቆጠረ በኋላ ነው ሁለት ጎል ገብቶበት የተሰናከለው። እርግጥ የመልሱም ግጥሚያ ለማኒዩ ተሥፋ ሰጭ ሆኖ ነበር የጀመረው።

ከዕለቱ የማንቼስተር ዩናይትድ ድንቅ ተጫዋቾች አንዱ ቴረን ጊብሰን የመጀመሪያዋን ዕድሉን በመጠቀም ብዙ ሳይቆይ 1-0 ያስቆጥራል። ከዚያም ቫሌንሢያ ሁለቴ አታሎ ወደ ባየርን 16 ሜትር ክልል የላካትን ኳስ የፖርቱጋሉ ኮከብ ናኒ በተረከዙ በቄንጥ ወደ ጎል ይልካታል። 2-0! ጥበብ የተመላው ግሩም ምት ነበር። ሶሥተኛዋም ጎል በሁለቱ ድንቅ አጨዋወት የተገኘች ነበረች። ቫሌንሢያ ያቀብላል፤ ናኒ ያስፈጽማል፤ 3-0! ከዚህ በኋላ ማንቼስተር ዩናይትድ በቀላሉ ድሉን አሳልፎ ይሰጣል ብሎ ያለመ የባየርን ተጫዋች አልነበረም።

እርግጥም ማንቼስተር ብራዚላዊ ወጣት ተጫዋቹ ራፋኤል በ 50ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳ ሲወጣበት ይህ ለባየርን በጣሙን እንደበጀ አንድና ሁለት የለውም። ሆኖም የማንቼስተር ዩናይትድ ተጫዋቾች ራሳቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኟቸውን ብዙ ዕድሎች ተጠቅመውባቸው ቢሆን ኖሮ ለድል በበቁም ነበር። ግን አልሆነም። ስለዚህም መቆጨታቸው አልቀረም።

“ባየርን በመጀመሪያው ግጥሚያ ሻል ያለው ነበር። እርግጥ እኛ በመጀመሪያውም ግጥሚያ ብዙ ዕድላችንን ሳንጠቀምበት ቀርተናል። አራትም ልናስቆጥር እንችል ነበር። በዛሬው ምሽት ግን እኛ የተሻልነው እንደነበርን ጥርጥር የለውም። ተጫዋቻችን ከሜዳ እስከወጣብን ድረስ”

ያም ሆነ ይህ ባየርን ሙንሺን በክሮኤሺያው ተጫዋች በኢቪትሣ ኦሊች አማካይነት የመጀመሪያ ጎሉን በመጀመሪያው አጋማሽ ማብቂያ ላይ ሲያስቆጥር የኔዘርላንዱ አሪየን ሮበን ደግሞ በ 74ኛዋ ደቂቃ ላይ ወሣኟን ሁለተኛ ጎል ያስገባል። ባየርን 3-2 ቢሽነፍም በውጭ ባስቆጠረው ጎል ብልጫ በጠቅላላ ውጤት ለግማሽ ፍጻሜ በቅቷል። ለዚህም በተለይ የሮበን ድርሻ ከፍተኛ ነው።

በዚህ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የሩብ ፍጻሜ ሣምንት እርግጥ ከሁሉም በላይ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የኳስ አፍቃሪዎችን ቀልብ የሳበው የባርሤሎናው ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ነበር። ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን ባርሣ ከሌላው የእንግሊዝ ቀደምት ክለብ ከአርሰናል ጋር በመጀመሪያው የለንደን ግጥሚያ ሁለት ለባዶ መርቶ በመጨረሻ እኩል-ለእኩል ሲለያይ በአጭሩ እንዳይቀር የሰጉት ደጋፊዎቹ ጥቂቶች አልነበሩም። ሆኖም ባርሣ በቀላሉ አልተንበረከከም። በመልሱ ጨዋታ ምንም እንኳ ቀድሞ ቢመራም ሊያሸንፍ በቅቷል። አራቱንም ጎሎች ያስቆጠረው ደግሞ ያስደንቃል፤ የአውሮፓና የዓለም ድንቅ ተጫዋች በመባል መመረጡ የሚታወሰው ሜሢ ነው። ሊገታ የማይችል መሆኑን የአርሰናል ተጫዋቾች ጭምር አምነው የተቀበሉት ነገር ነው።

“እርግጥ በጅምሩ ብዙ ግፊት ለማድረግ ሞክረናል። ግን አልሆነልንም። ይህም የቡድናቸውን የተሻለ ጥንካሬ የሚያሣይ ነው። ዛሬ በጣም ግሩም ነበሩ። ጥሩ ተጫውተዋል፤ ቦታ አያያዛቸው ድንቅ ነው። በተለይ ደግሞ ሜሢ! አራቱንም ጎሎች ለማስቆጠር ችሏል”

የግማሽ ፍጻሜው የመጀመሪያ ግጥሚያዎች በመጪው ሣምንት አጋማሽ የሚካሄዱ ሲሆን ማክሰኞ ሞስኮን ያስወጣው የኢጣሊያው ሻምፒዮን ኢንተር ሚላን ከባርሤሎና፤ በማግሥቱ ረቡዕ ምሽትም ባየርን ሙንሺን ከፈረንሣዩ ኦላምፒክ ሊዮን ይጋጠማሉ። ከዚያም በሣምንቱ የመልሱ ግጥሚያዎች የሚካሄዱ ሲሆን ፍጻሜው የሚደረገው ግንቦት 14 ቀን ነው።

በመለስተኛው የዩኤፋ የአውሮፓ ሊጋ ውድድር ደግሞ ሁለቱ የእንግሊዝ ክለቦች ሊቨርፑልና ፉልሃም፤ እንዲሁም ሃምቡርግና አትሌቲኮ ማድሪድ ለግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል። የግማሽ ፍጻሜው ተጋጣሚዎችም ሊቨርፑል ከአትሌቲኮ ማድሪድና ሃምቡርግ ከፉልሃም ይሆናሉ።

Fußball Bundesliga Spieltag 30 Leverkusen München
ምስል AP

በዚሁ ወደ አውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር እንሻገርና በስፓኝ ላ-ሊጋ የሻምፒዮናው ሊጋ መንኮራኩር ባርሤሎና የቅርብ ተፎካካሪውን ሬያል ማድሪድን በገዛ ሜዳው በቤርናቤው ስታዲዮም 2-0 በማሸነፍ ሰባት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ አመራሩን በሶሥት ነጥቦች ሊያሰፋ በቅቷል። ጎሎቹን ሜሢና ፔድሮ ሲያስቆጥሩ የአርጄንቲናው ኮከብ ለዚህም ድል ወሣኝ ድርሻ ነበረው። ሁለቱንም ጎሎች በማዘጋጀት ክሣቪ ድንቅ አስተዋጽኦ ሲያደርግ ሊዮኔል ሜሢም 27ኛ ግቡን በማስቆጠር የጎል አግቢነት አመራሩን ከፍ ሊያደርግ ችሏል። ሊዮኔል ሜሢ በዚህ ማራኪ ተውኔቱ ከቀጠለ በቅርቡ የዓለም ዋንጫ ውድድር ኮከብ የመሆን ዕድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ኢንተር ሚላን ከፊዮሬንቲና 2-2 ብቻ ሲለያይ አታላንታ በርጋሞን 2-1 ያሸነፈው ሮማ ዕድሉን ተጠቅሞ ለመጀመሪያ ጊዜ አመራሩን ሊጨብጥ በቅቷል። ሮማ ከ 33 ግጥሚያዎች በኋላ በ 68 ነጥቦች ግንባር ቀደም ሲሆን እንተር አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው። ሶሥተኛው ኤ.ሢ.ሚላንም እንደ ኢንተር ሁሉ ከካታኛ 2-2 በመለያየቱ አመራሩን ለመቃረብ የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከሮማ አራት ነጥቦች ይለዩታል። ውድድሩ ሊጠቃለል አምሥት ግጥሚያዎች የሚቀሩ ሲሆን እርግጥ ሶሥቱም ክለቦች የሻምፒዮንነት ዕድል አላቸው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰንበቱ ለማንቼስተር ዩናይትድ ከሣምንቱ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ስንብት በኋላ እንደገና የክስረት ሆኖ ነው ያለፈው። ለተከታታይ አራተኛ ጊዜ የፕሬሚየር ሊጉን ድል ለመጨበጥ የሚታገለው ቀደምት ክለብ ከብላክበርን ሮቨርስ ባዶ-ለባዶ ሲለያይ አመራሩን ለጊዜውም ቢሆን ከቼልሢይ መንጠቁ ሳይሆንለት ቀርቷል። 73 ነጥቦች አሉት። ቼልሢይ በሰንበቱ የፌደሬሺን ዋንጫ ግጥሚያ የተነሣ አንድ ጨዋታ የሚጎለው ቢሆንም ሊጉን በአንዲት ነጥብ ብልጫ እየመራ ነው። ሶሥተኛው አርሰናልም አንድ ጨዋታ ጎሎት 71 ነጥቦች ሲኖሩት የሻምፒዮናው የቅርብ ተፎካካሪ እንደሆነ ይቀጥላል።

በሌላ በኩል በእንግሊዝ ፌደሬሺን ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ውድድር ቼልሢይ ኤስተን ቪላን 3-0 ሲያሽንፍ ካለፈው ቅዳሜ ወዲህ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን መውረዱ የተረጋገጠው ፖርትማውዝም ባልተጠበቀ ሁኔታ ቶተንሃምን በተጨማሪ ሰዓት 2-0 በመርታት ለፍጻሜ በቅቷል። ፍጻሜው ግጥሚያ በዝነኛው ዌምብሌይ ስታዲዮም የሚካሄደው በፊታችን ግንቦት ወር ነው።

በጀርመን ቡድነስሊጋ ቀደምቱ ባየርን ሙንሺን ከቅርብ ተፎካካሪው ከሌቨርኩዝን 1-1 ቢለያይም በሁለተኛው በሻልከ መሸነፍ የተነሣ አመራሩን ወደ ሁለት ነጥቦች ከፍ ሊያደርግ ችሏል። ባየርን 60፤ ሻልከ 58፤ ሌቨርኩዝን 54 ነጥቦች ሲኖሯቸው ሁሉም በቀሩት አራት ጨዋታዎች ሻምፒዮን የመሆን ዕድል አላቸው። እርግጥ በወቅቱ ከሶሥቱ ልበ-ሙሉ ሆኖ የሚገኘው ግን ከኋላ ተነስቶ ለቁንጮነት የበቃው ባየርን ሚንሺን ነው። ሆኖም ክለቡ ዘንድሮ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ፣ በቡንደስሊጋና በጀርመን የፌደሬሺን ዋንጫ ውድድሮች ሶሥት የድል ዕድል የሚጠብቀው ቢሆንም ፕሬዚደንቱ ኡሊ ሄነስ ያልተለመደ ቁጥብነት ማሳየቱን ነው የመረጠው።

“የትንቢት ሰው አይደለሁም፤ ለመሆንም አልፈልግም። ከጥቂት ሣምንታት በፊት ባየርን በጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለም ሲሉ የጻፉ አንዳንዶች ነበሩ። አሁን ደግሞ ሁሉም ነገር ግሩም ነው ባይ ናቸው። እኔ በበኩሌ እንደማስበው ደረጃ በደረጃ በያዝነው ጥረት መቀጠል ነው ያለብን። ከዚያ በኋላ የሚመጣውን እናያለን”

ማራቶን በፓሪስና በሮተርዳም

ትናንት በፈረንሣይ የተካሄደው 34ኛ የፓሪስ ማራቶን ሩጫ አሸናፊዎች በወንዶችና በሴቶችም ኢትዮጵያውያን ሆነዋል። የ 22 ዓመቱ ወጣት አትሌት ታደሰ ቶላ በሁለተኛ ዓለምአቀፍ የማራቶን ሩጫው ግሩም በሆነ የሁለት ሰዓት ከስድሥት ደቂቃ 41 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ኬንያውያን ከሁለት እስከ አምሥት በመከተል ውድድሩን ፈጽመዋል። በሴቶች ደግሞ አጸደ ባይሣ ስታሸንፍ ክሪስቴል ዳውናይ ከፈረንሣይ ሁለተኛ ወጥታለች።
በተቀረ የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ግንባር ቀደም ተፎካካሪ ሆነው ሲታዩ ትርፊ ጸጋዬ ሶሥተኛ፤ አዛለች ወ/ሥላሴ አራተኛ፤ እንዲሁም ወርቂቱ አያኑ አምሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። በሮተርዳም ማራቶንም የሴቶቹ ድል የኢትዮጵያ ነበር። አበሩ ከበደ አሸንፋለች። በወንዶች ኬንያዊው ፓትሪክ ማካው ቀዳሚ ሲሆን ሁለት የአገሩ ልጆች ተከትለውት ገብተዋል።

ቴኒስ

በዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድሮች ትናንት ሂዩስተን-ቴክሣስ ውስጥ በተካሄደ የኤቲፒ ፍጻሜ ግጥሚያ አርጄንቲናዊው ሁዋን-ኢግናሢዮ-ቼላ አሜሪካዊ ተጋጣሚውን ሣም ኩዌይሪን 2-1 አሸንፏል። በካዛብላንካ ኤቲፒ ፍጻሜ ደግሞ የስዊሱ ስታኒስላቭ ቫቭሪንካ የሩሜኒያውን ቪክቶር ሃኔስኩን በሁለት ምድብ ጨዋታ ሲረታ በፍሎሪዳ የሴቶች የዓለም ቴኒስ ማሕበር ፍጻሜ ግጥሚያም የዴንማርኳ ካሮሊን ቮዥኒያችኪ የቤላሩሷን ኦልጋ ጎቮሮትሶቫን በተመሳሳይ ሁለት-ለባዶ ውጤት አሸንፋለች።

MM/DW/RTR/AFP