1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 11 2002

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ ሊጠቃለል እየተቃረበ ባለው ውድድር ለሻምፒዮንነት የሚደረገው ፉክክሩ ይበልጥ ተጠናክሯል።

https://p.dw.com/p/N0M2
የባየርን ተጫዋቾች ሮበን፣ ኦሊችና ላምምስል AP

እግር ኳስ፤ የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በዚህ ሰንበት የቼልሢይ በቶተንሃም ሆትስፐር 2-1 መሸነፍ ለማንቼስተር ዩናይትድ በጣሙን በጅቷል። ማኒዩ ማንቼስተር-ሢቲይን ፓውል ስኮልስ በመጨረሻይቱ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ግብ 1-0 ሲያሸንፍ አሁን ከቼልሢይ የሚለየው በአንዲት ነጥብ ብቻ ነው። ቼልሢይ በ 77 ነጥቦች በአንደኝነት ይመራል፤ ማንቼስተር ዩናይትድ 76 ነጥቦች አሉት። ውድድሩ ሊጠናቀቅ ሶሥት ግጥሚያዎች ብቻ ሲቀሩት አርሰናል በአንጻሩ በዊጋን-አትሌቲክ 3-2 በመሸነፍ ከሻምፒዮናው ፉክክር ወደታች አቆልቁሏል። አርሰናል በተለይ 2-0 ከመራ በኋላ በአሥር ደቂቃዎች ውስጥ ሶሥት ጎሎች ገብተውበት 3-2 መሸኘቱ በዚህ ሰንበት የድክመቱ መለያ ነበር።
በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሺን ሃኖቨርን ሰባት ጎሎች አጠጥቶ ሲሸኝ ተጫዋቾቹ ከነገ በስቲያ ከኦላምፒክ ሊዮን ጋር ለሚካሂደው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ሰውነት በማሟሟቅ ላይ ያሉ መስለው ነበር የታዩት። ባየርን ሙንሺን በዚሁ ድሉ የሁለት ነጥብ የቡንደስሊጋ አመራሩን እንደጠበቀ ሊራመድ ችሏል። እንዳለፉት ሣምንታት ጥንካሬው ከሆነ ሙንሸን-ግላድባህን 3-1 ካሸነፈው ከቅርብ ተፎካካሪው ከሻልከ የላቀ የሻምፒዮንነት ዕድል ያለው ነው የሚመስለው። ምናልባት ከሰባት ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው ሆላንዳዊ አጥቂው የአርየን ሮበን ሚና ለዚህ ወሣኝ ሊሆን ይችላል።

“በጣም የሚያስደስት ነገር ነው። በውድድሩ ሂደት እስካሁን በመንፈስም ሆነ በአካል ይዞታ በግሩም ሁኔታ ላይ ነኝ። ለዚህም ነው ጠንካራ ጨዋታ የማሳየው። ይህ አርኪ ነገር ነው። ግን ዋናው ነገር ውድድሩን በመጨረሻ በአንደኝነት ማጠናቀቁ ይሆናል”

በአርግጥም ባየርን ገና ብቻውን አይደለም። ሻልከ ሁለት ነጥቦች ብቻ ዝቅ ብሎ በቅርብ የሚከተለው ሲሆን አሠልጣኙ ፌሊክስ ማጋት ቀሪዎቹን ሶሥት ግጥሚያዎች አሽንፈን ለሻምፒዮንነት እንበቃለን እያለ ነው።

ጨዋታችንን ሳይ፤ ግላድባህን ማሸነፋችንን ስመለከት ሻምፒዮን ለመሆን ጥሩ ዕድል እንዳለን እርግጠኛ ነኝ። በቀሩት ግጥሚያዎች ግባችን የሚሆነውም ይሄው ነው። ሶሥቱንም ቀሪ ግጥሚያዎች በማሸነፍ ሻምፒዮን የመሆን ዕድላችን ከፍተኛ ነው”

በሌላ በኩል አብዛኛውን ጊዜ ሊጋውን ሲመራ ቆይቶ በመጨረሻ መንገዳገድ የያዘው ሌቨርኩዝን በሽቱትጋርት 2-1 ሲሸነፍ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ የሚያበቃውን ሶሥተኛ ቦታ እንኳ ይዞ ለመቆየት አልቻለም። ይህንኑ ቦታውን ቮልፍስቡርግን 4-2 ላሸነፈው ለብሬመን ማስረከቡ ግድ ነው የሆነበት። በሌላ በኩል በመጨረሻ ቦታ ላይ የሚገኘው በርሊን ከፍራንክፉርት 2-2 ሲለያይ ወደ ሁለተኛው ዲቪዢዮን ከማቆልቆል መትረፉ ከዚህ ሰንበት ወዲህ ብዙ የሚያጠራጥር ነው።

በስፓኝ ላ-ሊጋ የሻምፒዮናው እሽቅድድም ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ እንደገና የጠበቀ ፉክክር የሰፈነበት ሊሆን በቅቷል። ለዚህም ምክንያት የሆነው ቀደምቱ ባርሤሎና ከከተማ ተፎካካሪው ከኤስፓኞል ባደ-ባዶ ሲለያይ ሬያል ማድሪድ ደግሞ በበኩሉ ግጥሚያ ሶሥተኛውን ቫሌንሢያን 2-0 አሸንፎ ከባርሣ የነበረውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ማጥበቡ ነው። በቤርናቤው ስታዲዮም ለሬያል ሁለቱን ጠቃሚ ጎሎች ያስቆጠሩት የአርጄንቲናው ጎንዛሉ ሂጉዌይንና የፖልቱጋሉ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነበሩ። ቫሌንሢያ ከሬያል 24 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሶሥተኛ ነው። በሻምፒዮንነቱ ላይ የሚዘይደው ነገር አይኖረውም።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኤ.ኤስ.ሮማ የከተማ ተፎካካሪውን ላሢዮን 2-1 በመርታት በአመራሩ ቀጥሏል። ለሮማ ሁለቱን ወርቃማ ጎሎች ያስቆጠረው ሚርኮ ቩቺኒች ነበር። ኢንተር-ሚላንም እንዲሁ ጁቬንቱስን 2-0 በመሸኘት በቅርብ እየተከተለ ነው። ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ሮማ 71፤ ኢንተር ደግሞ 70 ነጥቦች አሉት። በሌላ በኩል የሶሥተኛው የኤ.ሢ-ሚላን የሻምፒዮንነት ተሥፋ በሣምፕዶሪያ 2-1 ከተሸነፈ በኋላ በቀጭን ገመድ ላይ የመቆምን ያህል ነው የሆነው። ክለቡን በወቅቱ በስድሥት ነጥቦች ከሁለተኛው ቦታ ይለዩታል።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ኦላምፒክ-ማርሤይ ቦሎኝ-ሱር-ሜርን 2-1 ሲያሸንፍ ኦግዜርን በስድሥት ነጥብ አስከትሎ በ 68 ነጥቦች እየመራ ነው። ኦላምፒክ ሊዮንና ሞንትፔሊየር የየበኩላቸውን ግጥሚያዎች እኩል-ለእኩል በሆነ ውጤት ሲፈጽሙ ሶሥተኛና አራተኛ ናቸው። በኔዘርላንድ ትዌንቴ-እንሼዴ ለዘንድሮው ሻምፒዮንነት በጣሙን እየተቃረበ ነው።
ቡድኑ ፋየኖርድን ሁለት-ለባዶ ሲረታ የፊታችን ዕሑድ ሣምንት ብሬዳን ካሸነፈ ሻምፒዮንነቱን ሊያረጋግጥ ይችላል። በአንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ የሚከተለው አያክስ አምስተርዳምም እንዲሁ ዕድል አለው። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ቤንፊካ ሊዝበን ሶሥት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ሳለ ብራጋን ከኋላው እንዳስከተለ ነው። በስድሥት ነጥቦች ልዩነት የሚመራ ሲሆን ለሻምፒዮንነቱ በጣሙን የተቃረበ ይመስላል።

እግር ኳሱን በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ለማጠቃለል የዚሁ ግማሽ ፍጻሜ ዙር የመጀመሪያ ግጥሚያዎች ነገና ከነገ በስቲያ ምሽት ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት ያለፈው ሻምፒዮን ባርሤሎና የኢንተር-ሚላን እንግዳ ሲሆን በፊታችን ረቡዕ የሚጋጠሙት ደግሞ ባየርን ሙንሺንና ኦላምፒክ ሊዮን ናቸው። በነገራችን ላይ የአይስላንዱ እሣተ-ገሞራ ለኳስ ጠበብቱም አልራራም። የባርሣው ኮከብ ሊዮኔል ሜሢና መሰሎቹ በአየር በረራው መሰናከል የተነሣ ወደ ሚላን የሚጓዙት በአውቶቡስ ነው።
ይህ ደግሞ የ 985 ኪሎሜትር ጉዞ ሲሆን በመሠረቱ ቀላል ነገር አይደለም። ለማንኛውም ሁኔታው ለኢንተር ይጥቀም-አይጥቀም ከግጥሚያው በኋላ የሚታይ ይሆናል። የሁለተኛውን ግጥሚያ ሂደት መተንበዩም ቀላል ነገር አይሆንም። በሩብ ፍጻሜው ዙር ማንቼስተር ዩናይትድን ያሰናበተው ባየርን ሙንሺን በወቅቱ ጠንከር ያለ ቢመስልም በሌላ በኩል ኦላምፒክ ሊዮንም ከዚህ ቀደም ከአንዴም ሁለቴ እንደታየው ፈታኝ ሊሆን የሚችል ነው።

ቴኒስ

Australian Open Serena Williams Tennis
ምስል AP

የስፓኙ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ኮከብ ራፋኤል ናዳል በሞንቴካርሎ-ማስተርስ ፍጻሜ ትናንት የአገሩን ልጅ ፌርናንዶ ቫርዳስኮን እጅግ ጠንካራ በሆነ አጨዋወት 6-0, 6-1 በማሽነፍ ወደ ቀድሞ ልዕልናው በመመለስ ላይ መሆኑን አስመሰከሯል። ናዳል የሞንቴካርሎን ፍጻሜ ሲያሸንፍ በተከታታይ ለስድሥተኛ ጊዜ ሲሆን በዚሁም ደስታው ወሰን አልነበረውም። የአራት ጊዜው የፍሬንች-ኦፕን ሻምፒዮን ድል ከሃምሣ ሣምንታት በኋላ እንደገና ታሪክ ለመስራት መመለሱን ያበሰረ ነበር።

በደቡብ ካርላይና-ቻርልስተን ደግሞ ትናንት በተካሄደ የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያ የአውስትራሊያዋ ሣማንታ ስቶሰር ሩሢያዊቱን ኮከብ ቬራ ዝቮናሬቫን እንዳልነበረች 6-0, 6-3 በማሸነፍ ለሁለተኛ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ድሏ በቅታለች። በሌላ በኩል አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስ ዛሬ በወጣ የዓለም ቴኒስ ማሕበር የማዕረግ ተዋረድ መሠረት በአንደኝነቷ እንደጸናች ቀጥላለች። ሁለተኛ ካሮሊን ቮዥኒያችኪ ከዴንማርክ፤ ሶሥተኛ ዲናራ ሣፊና ከሩሢያ!

ሻንግሃይ፤ ፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም

Formel 1 China 2010 Rennen
ምስል AP

ትናንት ሻንግሃይ ላይ የተካሄደው የፍርሙላ-አንድ እሽቅድድም በማክላረን ዘዋሪዎች ድርብ ድል ተፈጽሟል። የብሪታኒያው ጄሰብ ባተን ዝናብ አስቸጋሪ ሁኔታን በፈጠረበት ሁኔታ ለዘንድሮው ሻምፒዮና ሁለተኛ ድሉ ሲበቃ ሉዊስ ሃሚልተንም ተከትሎት ገብቷል። ጄሰን በዚሁ በጠቅላላ ነጥብም አመራሩን ሊይዝ ችሏል።

“ይህ ድል የተለየ ድል ነው። ከባድ እሽቅድድም ነበር። ግን እኛ ሁሉንም ነገር ትክክል ነው ያደረግነው። በዚህ በዝናብ በተቃወሰ ሁኔታ ከሉዊስ አንዲት ሤኮንድ ቀድሜ መግባቴ የሚያሳየው ጥንካሬያችንን ነው። ለቡድኑ በጠቅላላ ታላቅ ስኬት ነበር”

ከጀርመን ተወዳዳሪዎች እሽቅድድሙን ከፖል-ፖዚሺን፤ ማለት ከመጀመሪያ ቦታ የጀመረው ዜባስቲያን ፌትል ስድሥተኛ፤ እንዲሁም ሚሻኤል ሹማኸር አሥረኛ ሲወጡ የሜርሤዲሱ ዘዋሪ ኒኮ ሮዝበርግ ብቻ ለሶሥተኝነት በቅቷል።

“ሶሥተኛ መውጣት በጣም ትልቅ ነገር ነው። በአራት ውድድሮች ውስጥ ሁለቴ ከመጀመሪያዎቹ ሶሥት መካከል መሆን ቀላል ነገር አይደለም”

ሮዝበርግ አሁን በጠቅላላ ነጥብ ሁለተኛ ሲሆን በሶሥት ሣምንት ጊዜ ውስጥ ባርሤሎና ላይ በሚካሄደው ቀጣይ እሽቅድድም ባተንን አልፎ ለመሄድ ነው የሚጥረው።

አትሌቲክስ

ጃፓን-ናጋኖ ላይ በተካሄደ የማራቶን ሩጫ ውድድር በወንዶች ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል የተሟላ ድል ለማስመዝገብ በቅተዋል። አሸናፊው የ 27ዓመቱ ኒኮላስ ቼሊሞ ሲሆን ሩጫውን የፈጸመው በሁለት ሰዓት ከአሥር ደቂቃ 24 ሤኮንድ ጊዜ ነበር። በሴቶች የአውስትራሊያ ሊዛ ዋይትማን አሸናፊ ሆናለች። በቪየና ማራቶን ደግሞ ኬንያውያን በወንዶች ሄንሪይ ሱጉት፤ በሴቶችም ሄለን ኪሙታይ በየፊናቸው ለአሸናፊነት በቅተዋል። በተረፈ የቦስተን ማራቶን ዛሬ ማምሻውን ብርቱ ፉክክር በሰፈነበት ሁኔታ ይካሄዳል።

መስፍን መኮንን/አርያም ተክሌ

መስፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

DW/RTR/AFP/dpa