1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 18 2002

ኬንያውያን በተከታታይ ለስድሥት ዓመታት አሸናፊ ሆነው የቆዩበት የለንደን ማራቶን ውድድር ትናንት በጸጋዬ ከበደ ድል ተፈጽሟል።

https://p.dw.com/p/N70g
ምስል AP

በእግር ኳሱ ዓለም በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውስጥ መዝጊያው የተቃረበው ውድድር በፍጻሜ ሂደቱ ጠንካራ ፉክክር የሰፈነበት እንደሆነ ነው። ዘንድሮ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ ግጥሚያ ማን ከማን እንደሚገናኝም ነገና ከነገ በስቲያ በሚካሄዱት ሁለት የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ይለይለታል። የአንዴው የዓለምአቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የረጅም ጊዜ ፕሬዚደንት የሁዋን-አንቶኒዮ-ሣማራንዥ ከዚህ ዓለም በሞት መለየትም የሣምንቱ አሳዛኝ ጉዳይ ነው።

ጸጋዬ ከበደ የለንደን ማራቶን አሸናፊ

የለንደን ማራቶን ድል ትናንት ከስድሥት ዓመታት ተከታታይ ድል በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኬንያ አትሌቶች እጅ ሊወጣ በቅቷል። የኬንያን አትሌቶች ተሥፋ ፍጹም ልዕልና በታየበት ሩጫ ከንቱ ያደረገው ደግሞ የኢትዮጵያው የኦሎምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የናስ ሜዳይ ተሸላሚ ጸጋዬ ከበደ ነው። ጸጋዬ ሩጫውን ግሩም በሆነ ሁለት ሰዓት ከአምሥት ደቂቃ ከ 19 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም በተለይም በመጨረሻዎቹ አሥር ኪሎሜትሮች ሂደት ከቅርብ ተፎካካሪዎቹ የጠነከረው እንደነበር አስመስክሯል።
የኬንያው ኤማኑዌል ሙታይ ሁለተኛ ሲወጣ ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመው ደግሞ የሞሮኮው ጃዋድ ጋሪብ ነው። ኤርትራውያኑ ዘረሰናይ ታደሰና ዮናስ ክፍሌም ሰባተኛና ዘጠነኛ በመሆን ግሩም ውጤት አስመዝግበዋል። ያለፈው ዓመት አሸናፊ የቤይጂንጉ ኦሎምፒክ የወርቅ ተሸላሚ ኬንያዊ ሣሚይ ዋንጂሩ በአንጻሩ ጉልበቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት የተነሣ ሩጫውን በ 25ኛው ደቂቃ ላይ አቋርጦ ቀርቷል። ጸጋዬ ከበደ ዝናብ ባያውከው ኖሮ ምናልባትም ዋንጂሩ ባለፈው የለንደን ማራቶን ያስመዘገበውን ጊዜ ሊያሻሽልም በቻለ ነበር።
ኢትዮጵያዊው አትሌት ባለፈው ዓመት ሁለተኛ ከሆነ በኋላ ዘንድሮ አንደኛ መውጣቱ ግሩም ውጤት እንደሆነ በማመልከት በሚቀጥለው ዓመት ያለዝናብ ምናልባት ሁለት ሰዓት ከአራት ደቂቃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል ተሥፋውን ገልጿል። በሴቶች ድሉ የሩሢያ ሲሆን የኢትዮጵያ አትሌቶችም ግሩም ውጤት ነው ያስመዘገቡት። ያለፈው ጥቅምት የቺካጎ ማራቶን ባለድል ሊሊያ ሾቡኮቫ በዓመቱ ፈጣን ጊዜ ሁለት ሰዓት ከ 22 ደቂቃ አንደኛ ስትወጣ ሌላዋ ሩሢያዊት ኢንጋ አቢቶቫ ደግሞ በ 19 ሤኮንዶች ዘግይታ በሁለተኝነት ገብታለች።
ቀጣዩን ቦታዎች የያዙት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ነበሩ። አሰለፈች መርጊያ ሶሥተኛ፣ ብዙነሽ በቀለ አራተኛ፤ እንዲሁም አስካለ መገርሣ አምሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። ያለፈው ዓመት አሸናፊ ጀርመናዊቱ ኢሪና ሚኪቴንኮ በሕመም ምክንያት ሩጫውን ከ 18 ኪሎሜትር በኋላ ማቋረጥ ተገዳለች። ቻይናዊቱ የዓለም ሻምፒዮን ባይ ሹዌም ከሰባተኝነት በላይ ወደፊት ማለፉ አልሆነላትም። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ውጤት ሊደነቅ የሚገባው ነው።
በለንደኑ ማራቶን ለታሪክ ማሕደር የሚሆን የሚደነቅ ነገር መታየቱም አልቀረም። ይሄውም ልዕልት ቤአትሪስ በለንደን ማራቶን በመሳተፍ የመጀመሪያዋ የብሪታኒያ ንጉሣዊ ቤተሰብ ዓባል መሆኗ ነው። ቤአትሪስ 42ቱን ኪሎሜትር በአምሥት ሰዓት ከ 15 ደቂቃ ከ 57 ሤኮንድ በማቋረጥም ከግብ ደርሳለች። የሚደነቅ ነው! የለንደኑን ያህል በታላቅነት የሚታወቅ ባይሆንም በዚህ በጀርመን በሃምቡርግም ሰንበቱን የከተማ ማራቶን ሩጫ ተካሂዶ ነበር።
በወንዶች ኬንያዊው ዊልፍሬድ ኪገን ሲያሸንፍ የኖርዌዩ ኡሪገ ቡታ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ኤርትራዊው በየነ በራክ ሶሥተኛ ሆነዋል። በሴቶችም ቼሮፕ ሻሮን ከኬንያ ቀዳሚ ስትሆን ብሩክታይት ደገፋ ከኢትዮጵያ ሁለተኛ ወጥታለች፤ ቤአታ ናይጋምቦ ከናሚቢያ ሶሥተኛ! ዓለሚቱ በቀለ ደግሞ ሩጫውን በሰባተኝነት ፈጽማለች።

የሁዋን-አንቶኒዮ-ሣማራንዥ ዕረፍት

Flagge IOC Halbmast Samaranch
ምስል AP

በአትሌቲክሱና በአጠቃላይም በስፖርቱ ዓለም ሣምንቱ ያለፈው የዓለምአቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የረጅም ጊዜ ፕሬዚደንት የሁዋን-አንቶኒዮ-ሣማራንዥ ሞት ባስከተለው ሃዘንም ታጅቦ ነው። የስፓኙ ተወላጅ በ 89 ዓመት አንጋፋ ዕድሜ ከዚህች ዓለም ሲለዩ በአመራር ብቃታቸው የተወደሱ ሆኖም ግን በቀድሞ ታሪካቸው ደግሞ አከራካሪ ነበሩ። የባርሤሎናው ተወላጅ ሁዋን-አንቶኒዮ-ሣማራንዥ እ.ጎ.አ. በ 1980 የኦሎምፒኩ ንቅናቄ መሪ ሆኖ በመመረጥ ድርጅቱን ለ 21 ዓመታት አስተዳድረዋል። ሣማራንዥ ድርጅቱን ከቴሌቪዥንና ሌሎች የገበያ ጥቅሞች በማስተሳሰር በአመራር ዘመናቸው በዚህ ብቻ እንኳ 11 ሚሊያርድ ዶላር ገቢ እ’ንዲያገኝ አብቅተዋል። የቀድሞው የጀርመን ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚደንት ቫልተር ትሩገር መለስ ብለው እንደሚያስታውሱት የስፖርቱ ዓለም በሣማራንዥ በጣም ነው ተጠቃሚ የሆነው።

“የኦሎምፒኩ ኮሚቴ IOC አጽናፋዊ እንዲሆን አድርጓል። ማለት ያኔ በአብዛኛው በአውሮፓውያንና በሰሜን አሜሪካውያን ይመራ በነበረው የኦሎምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ብዙሃኑ እንዲያውም የሌሎች ክፍለ-ዓለማት ዓባላት ይሆናሉ። ስፖርቱ የሁሉም እንዲሆን አድርጓል። ይህም ማለት የስፖርት እንቅስቃሴ በዚህች ዓለም ላይ የእያንዳንዱ ሰው ሰብዓዊ መብት መሆኑን ማረጋገጥ ማለት ነው”

በሣማራንዥ የአመራር ዘመን እርግጥ የኦሎምፒኩን ኮሚቴ ዝና የተፈታተኑ የሙስና ድርጊቶች መነሳታቸው ባይቀርም በሟቹ ታሪክ ላይ ከሁሉም በላይ ጉድፍ ሆኖ የሚኖረው ምናልባት የስፓኙ አምባገነን ገዢ የፍራንኮ ደጋፊ መሆናቸው ነው። የኋላ ኋላም ጸጸት አላደረጉም። እንዲያውም ያለፈውን ታሪኬን እኮራበታለሁ ነበር ያሉት። ...

እግር ኳስ፤ የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች

Fußball Bundesliga - Borussia Mönchengladbach gegen Bayern München
ቡንደስሊጋ ባየርንምስል AP

የአውሮፓ ቀደምት ክለቦች ውድድር በመጠቃለያ ደረጃው ላይ ቢሆንም የሻምፒዮናው ፉክክር ግን በየቦታው ጠባብ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቼልሢይ ስቶክ-ሢቲይን 7-0 ሲሸኝ ብችኛ ተፎካካሪው ማንቼስተር-ዩናይትድም ቶተንሃም-ሆትስፐርን 3-1 አሸንፏል። በቼልሢይ የጎል ፌስታ ለክለቡ ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው ድንቁ ተጫዋች የአይቮሪ ኮስቱ ሶሎሞን ካሉ ነበር። አሁን ውድድሩ ሊጠናቀቅ ሁለት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ሳለ ቼልሢይ በአንዲት ነጥብ ልዩነት መምራቱን ይቀጥላል። ሶሥተኛው አርሰናል ከማንቼስተር-ሢቲይ ባዶ-ለባዶ ሲለያይ ሻምፒዮን የመሆን ዕድሉም በዚሁ ውጤት ለመጨረሻ ጊዜ ነው ያከተመው።

በስፓኝ ላ-ሊጋም ሁኔታው ከእንግሊዙ የሚመሳሰል ነው። ባርሤሎና ዴፖርቲቮ-ላ-ኮሩኛን 3-1 ሲረታ ሬያል-ማድሪድም በበኩሉ ግጥሚያ ሣራጎሣን 2-1 አሸንፏል። ባርሣ በአንዲት ነጥብ ብልጫ ይመራል፤ ሬያል በቅርብ ይከተላል። ሰንበቱ የሬያሉ ብራዚላዊ ኮከብ የካካ ነበርም ለማለት ይቻላል። በአካል ጉዳት ሳቢያ ስድሥት ሣምንታት አርፎ የተመለሰው ብራዚላዊ ጨዋታው ሊያበቃ ሩብ ሰዓት ሲቀር ገብቶ ያስቆጠራት ጎል ለሬያል ድል ወሣኝ ነበረች። የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ውድድር ሊጠቃለል ገና አራት ግጥሚያዎች ይቀራሉ።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ሮማ ከሣምንት በፊት ነጥቆት የነበረውን አመራር ለኢንተር-ሚላን መልሶ አስረክቧል። ሮማ ትናንት ከተከታታይ ስድሥት ድሎች በኋላ በጌኖዋ 2-1 ሲረታ አሁን የውድድሩ ወቅት ሊጠናቀቅ ሶሥት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ሳለ ኢንተር በሁለት ነጥቦች ልዩነት እየመራ ነው። ሚላን በበኩሉ ግጥሚያ አታላንታን 3-1 አሸንፏል። ኤ.ሢ.ሚላን በፓሌርሞ ሲሸነፍ ከእንግዲህ ከሻምፒዮንነቱ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም። ሶሥተኝነቱን ከጠበቀም ትልቅ ነገር ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋም የሻምፒዮናው ፉክክር የሚካሄደው በሁለት ክለቦች መካከል ሲሆን ባየርን ሙንሺን የሁለት ነጥብ አመራሩን ሊያስከብር ሳይችል ቀርቷል። ከግላድባህ ጋር 1-1 በሆነ ውጤት ሲወሰን የሰንበቱ ተጠቃሚ በዕድል በመጨረሻ ደቂቃ ጎል በርሊንን 1-0 ያሸነፈው ሻልከ ነው። ሁለት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ባየርንም ሻልከም እኩል 64 ነጥብ አላቸው። በዚህ በጠበቀ ፉክክር ባየርን ምንም እንኳ ሰፊ የጎል ብልጫ ቢኖረውም ሆላንዳዊ ተጫዋቹ አርየን ሮበን እንዳለው አስተማማኙ ነገር ምናልባትም የሚቀጥሉትን ሁለት ግጥሚያዎች ማሸነፉ ሳይሆን አይቀርም። እኩል-ለእኩሉ ውጤት የሚቆረቁር ቢሆንም!

“እግር ኳስ እንዲህ ነው። ምናልባትም ቡንደስሊጋን አስደናቂ የሚያደርገው ይሄው ነው። ሆኖም አሁን በጣም መረጋጋት ያስፈልጋል። ዛሬ ሶሥት ነጥቦችን የመውሰድ ግባችን ተሳክቶ ቢሆን ግሩም ነበር። ግን አልሆነም። እናም የሚቀረው ግዴታ ሁለቴ ማሸነፍና ሻምፒዮን መሆን ነው”

ከዚሁ ሌላ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ተሳትፎ የሚያበቃውን ሶሥተኛ ቦታ ለመያዝ የሚደረገው የቡንደስሊጋ ፉክክርም እንደጦፈ ቀጥሏል። ሶሥቱም የቡንደስሊጋ ክለቦች ብሬመን፣ ዶርትሙንድና ሌቨርኩዝን የየበኩላቸውን ግጥሚያ ሲያሽንፉ ሣምንትም ጠባብ በሆነው ፉክክራቸው ይቀጥላሉ።

በፈረንሣይ ሊጋ ማርሤይ በአምሥት ነጥብ ልዩነት መምራቱን ሲቀጥል በፖርቱጋል ሻምፒዮና ቤንፊካ-ሊዝበን ሻምፒዮን ለመሆን ከእንግዲህ በሚቀጥሉት ሁለት ግጥሚያዎች አንዲት ነጥብ ትበቃዋለች። በግሪክ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ባለፈው ሣምንት ሻምፒዮን የሆነው ፓናቴናኢኮስ-አቴን ትናንት ደግሞ ሣሎኒካን 1-0 በማሸነፍ የፌደሬሺኑን ዋንጫም ከስምንት ዓመታት በኋላ ለመደረብ ችሏል። በኔዘርላንድ ሊጋ ደግሞ አያክስ-አምስተርዳም ለዳች ዋንጫ ባለቤትነት እየተቃረበ ነው። ክለቡ ዘንድሮ በደርሶ መልስ በሚካሄደው የዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ትናንት በመጀመሪያው ጨዋታ ፋየኖርድን 2-0 አሸንፏል።

በተቀረ የአውሮፓው ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት ኦላምፒክ ሊዮን ባየርን ሙንሺንን የሚያስተናግድ ሲሆን ባለፈው ሣምንት ሚዩኒክ ላይ ከደረሰበት 1-0 ሽንፈት ለማገገም ብርቱ ትግል ነው የሚጠብቀው። ባርሤሎናም በማግሥቱ ረቡዕ ከኢንተር-ሚላን የሚጋጠም ሲሆን ሁኔታው ቀላል አይሆንም። ባርሣ በሚላን 3-1 ተሸንፎ መመለሱ አይዘነጋም።

ዘገባችንን በቴኒስ ለማጠቃለል ኢጣሊያ በፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ዘንድሮም እንደገና ለፍጻሜ ለመድረስ በቅታለች። የፍጻሜ ተጋጣሚዋ በሁለተኛው ግማሽ ፍጻሜ ከሩሢያና ከአሜሪካ የሚያሸንፈው ይሆናል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ