1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ረቡዕ፣ ግንቦት 11 2002

አዲሱ የዓለም አትሌቲክስ የዲያመንድ-ሊግ ተከታታይ ውድድር ካታር-ዶሃ ላይ ሲጀመር ሰንበቱ በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥም ሚላን፣ ቼልሢይና ባየርን የውድድሩን ወቅት በድርብ ድል ያጠናቀቁበት ነበር።

https://p.dw.com/p/NQ7S
ምስል picture-alliance/dpa/DW

አትሌቲክስ

Usain Bolt aus Jamaika gewinnt Goldmedaille 100 Meter
ዩሤይን ቦልትምስል AP

በስድሥት ተከታታይ ደረጃ ይካሄድ የነበረው የዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ጎልደን-ሊግ ውድድር በዲያመንግ-ሊግ እንዲተካ መደረጉ የሚታወቅ ነው። የዚሁ ውድድር የመጀመሪያ ክፍልም ባለፈው አርብ ምሽት ካታር-ዶሃ ላይ ተካሂዷል። የዓለምና የኦሎምፒክ የመቶ፣ ሁለት መቶና አራት ጊዜ መቶ ሜትር የዱላ ቅብብል የክብረ-ወሰን ባለቤት የሆነው ዩሤይን ቦልት በውድድሩ ባይሳተፍም በመቶ ሜትር የአገሩ ልጆች ያየሉበት ሆኖ አልፏል። አሳፋ ፓውል በ 9,81 ሤኮንድ ሲያሸንፍ ሩጫውን እንዲሁ ከአሥር ሤኮንድ ባነሰ ጊዜ በሁለተኝነት የፈጸመውም ሌላው ጃማይካዊ ኔስታ ካርተር ነበር። አሜሪካዊው ትራቪስ ፓድጌት ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል።

በመካከለኛ ርቀት ይበልጡን ጥንካሬያሳዩት ኬንያውያን ናቸው። በ 800 ሜትር ዴቪድ ሩዲሻና አስቤል ኪፕሮፕ አንደኛና ሁለተኛ ሲሆኑ የሞሮኮው አሚኔ ላሉ ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽሟል። በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል ሩጫውን የፈጸሙት በሙሉ ኬንያውያን ነበሩ። ኤዜኪል ኬምቦይ አንደኛ ሲሆን ፓውል ኮችና ፓትሪክ ላንጋት ተከትለውት ገብተዋል። በአምሥት ሺህ ሜትርም ቢሆን ኬንያ ለድርብ ድል ስትበቃ ኤሊዩድ ኪፕቾጌ አንደኛ፤ እንዲሁም ቪንሤንት ኪፕሮፕ ሁለተኛ ወጥተዋል። ኢትዮጵያዊው ኢማኔ መርጋ በሶሥተኝነት መወሰኑ ግድ ነው የሆነበት።

በሴቶች የአጭር ርቀት ሩጫ ጃማይካና ዩ.ኤስ.አሜሪካ የተለየ ጥንካሬያቸውን ሲያስመሰክሩ በመቶ ሜትር ጃማይካዊቱ ኬረን ስቱዋርት የአገሯን ልጅ ሼረን ሲምሰንን በማስከተል አሸናፊ ሆናለች። በሁለት መቶ ሜትር ደግሞ ድሉ የአሜሪካዊቱ አትሌት የአሊሰን ፌሊክስ ነበር። አሜሪካ በሎሎ ጆንስ አማካይነት ደግሞ የመቶ ሜትር መሰናክል አሸናፊም ሆናለች። በተረፈ ክሮኤሺያዊቱ የዓለም ሻምፒዮን ብላንካ ቭላዚች ደግሞ የከፍታ ዝላይ ባለድሏ ነበረች።
በአጠቃላይ 6,6 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ በተመደበለት በ 14 ደረጃ በሚካሄደው ውድድር በዲያመንድ-ሉጉ የመጀመሪያ ዙር በርካታ ቀደምት አትሌቶች ሳይሳተፉበት ቀርተዋል። ከነዚሁ በጥቂቱ ለመጥቀስ ቀነኒሣ በቀለና አሜሪካዊቱ የአራት መቶ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ሣኒያ ሪቻርድስ በአካል ጉዳት ሳቢያ ሲቀሩ የምርኩዝ ዝላይ የኦሎምፒክ ወርቅ ተሸላሚዋ ሩሢያዊት የለና ኢዚንባየቫ ደግሞ ከስፖርት ዕረፍት በማድረግ ላይ ናት። ብዙዎቹ በውድድሩ ሂደት እንደሚመለሱ ተሥፋ ይደረጋል።

በተረፈ ትናንት እንግሊዝ ውስጥ የተካሄደው የታላቁ የማንቼስተር ሩጫ ድል ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያውያን ሆኗል። በወንዶች ሃይሌ ገ/ሥላሴ ሩጫውን ለሶሥተኛ ጊዜ ሲያሽንፍ የስፓኙ አያድ ላምዴሴም ሁለተኛ፤ እንዲሁም የኡክሪኒያው የስምንት ጊዜ የአውሮፓ የአገር-አቋራጭ ሻምፒዮን ሤርጌይ ሌቢድ ሶሥተኛ ሆኗል። የ 37 ዓመቱ ሃይሌ ምንም እንኳ አሥር ኪሎሜትሩን ከዓለም ክብረ-ወሰን ሰዓት አንድ ደቂቃ ያህል በዘገየ ጊዜ ቢፈጽምም ውጤቱ የሚደነቅ ነው። በሴቶች ደግሞ የ 2003 ዓ.ም. የዓለም የአሥር ሺህ ሜትር የብር ሜዳይ ተሸላሚ ወርቅነሽ ኪዳኔ አሸናፊ ሆናለች።

ደቡብ አፍሪቃ በዓለም ዋንጫ ዋዜማ

Bundesliga letzter Spieltag MEISTER BAYERN MÜNCHEN
ምስል AP

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊጀመር 24 ቀናት ቀሩት። ደቡብ አፍሪቃ ስታዲዮሞቿን፣ ሆቴሎችና መገናኛ መንገዶችን በጊዜው ገንብታ ትጨርስ ይሆን? ጸጥታን ማስከበሩስ? ወዘተ. እነዚህ በተለይ በዚህ በአውሮፓ ያለማቋረጥ ሲነሱ የቆዩ ጥያቄዎች ናቸው። ሆኖም ደቡብ አፍሪቃ እንደማንኛውም አዳጊ አገር ሁሉ ይህ ወይም ያ ማሕበራዊ ችግር ባያጣትም መስተንግዶዋን ለማሳመር መጣሯ አልቀረም። ክፋቱ ማሳካቷ አጠያያቂ መሆኑ ላይ እንጂ!

የአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር

በዚህ በአውሮፓ የየአገሩ የአግር ኳስ ሻምፒዮና ከሞላ-ጎደል ሲጠናቀቅ ኢንተር ሚላን፣ ቼልሢይና ባየርን ድላቸውን ሰንበቱን ድርብ ለማድረግም በቅተዋል። በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኢንተር ቀደም ብሎ የፌደሬሺኑን ዋንጫ ማሸነፉ ሲታወቅ በዚህ ሰንበትም በውድድሩ መጨረሻ ዕለት ሢየናን 1-0 በመርታት በተከታታይ ለአምሥተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ሊሆን ችሏል። ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው አርጄንቲናዊው አጥቂ ዲየጎ ሚሊቶ ነበር። ሮማ በበኩሉ ግጥሚያ ቺየቮን 2-0 ቢያሽንፍም በሁለት ነጥብ ልዩነት በሁለተኝነት መወሰኑ ግድ ሆኖበታል።

Formel 1 GP Monaco - Mark Webber
ምስል AP

በጀርመን ቡንደስሊጋም ቅደም-ተከተሉ ከመለያየቱ በስተቀር ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር። ባየርን ቀደም ሲል የሊጋ ሻምፒዮንነቱን ካረጋገጠ በኋላ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ደግሞ በፌደሬሺኑ ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ብሬመንን 4-0 በመቅጣት ድሉን ድርብ አድርጓል። በጎል ፌስታ የክለቡን ድል ያረጋገጡት ሮበን፣ ኦሎች፣ ሪቤሪይና ሽቫይንሽታይገር ነበሩ። የኢጣሊያው ሻምፒዮን ኢንተር ሚላንና ባየርን ሙንሺን በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ ግጥሚያ በፊታችን ቅዳሜ በማድሪዱ ቤርናቤዉ ስታዲዮም የሚገናኙ ሲሆን የሁለቱም ፍላጎት የውድድሩን ወቅት በሶሥተኛ ታላቅ ድል ለመዝጋት ነው።

በሌላ በኩል ያለፈው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ባለድል ባርሤሎና ዘንድሮ ቀደም ብሎ ቢሰናበትም በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ግን የበላይነቱን መልሶ አረጋግጧል። ባርሣ 99 ነጥቦች በማግኘት በአዲስ ክብረ-ወሰን ሻምፒዮን ሲሆን ተፎካካሪው ሆኖ የቆየው ሬያል ማድሪድ በመጨረሻ በሶሥት ነጥቦች ተበልጦ ሁለተኛ ሆኗል። የባርሣው ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ 34 በማስቆጠር በጎል አግቢነት በስፓኝ ሊጋ ውስጥ ቀደምቱ ሲሆን የአውሮፓን የወርቅ ጫማም ተሸልሟል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም የዘንድሮው የሊጋ ሻምፒዮን ቼልሢይ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የወረደውን ፖርትማውዝን ባለፈው ቅዳሜ 1-0 በማሸነፍ የፌደሬሺኑን ዋንጫም ሊጠቀልል በቅቷል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውስጥ የዘንድሮ የውድድር ወቅት ገደ ቢስ ሆኖ ያለፈው በተወሰነ ደረጃ ለሁለተኛው ለማንቼስተር ዩናይትድና በተለይም ለሊቨርፑል ነው። በተቀረ ፖርቶ በተከታታይ ለሁለተኛ ዓመት የፖርቱጋል ፌደሬሺን ዋንጫ አሸናፊ ሲሆን ቱርክ ውስጥ ደግሞ የአገሪቱ ሻምፒዮን ቤሺክታሽ ኢስታምቡል በመጨረሻዋ ቀን ድሉን በቡርዛስፖር ተነጥቋል።
በቼክ ሬፑብሊክም ሻምፒዮናው በመጨረሻው ዕለት ሲለይለት ስፓርታ ፕራግ ለ 35ኛ የሊጋ ድሉ በቅቷል። የዘንድሮው የፖላንድ ሻምፒዮን ደግሞ ሌኽ ፖዝናን ነው። ቀደም ሲል ከብዙ በጥቂቱ በፖርቱጋል ቤንፊካ ሊዝበን፣ በክሮኤሺያ ዲናሞ ዛግሬብና በፈረንሣይም ኦላምፒክ ማርሤይ ሻምፒዮን መሆናቸው ይታወቃል።

ዘገባችንን በፎርሙላ-አንድ የአውቶሞቢል እሽቅድድም ለማጠቃለል ትናንት ሞናኮ ላይ የተካሄደው ስድሥተኛ ውድድር አሸናፊ የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር ሲሆን ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል ሁለተኛ ወጥቷል። የቀድሞው የሰባት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ሚሻኤል ሹማኸር ግን አሁንም ከድል እንደራቀ ነው። በትናንቱ እሽቅድድም እንዲያውም ደምብን በመጣስ ከስድሥት ወደ 12ኛው ቦታ ወርዷል።

ከ 19 ስድሥቱ እሽቅድድም ተደርጎ በአጠቃላይ ነጥብ ማርክ ዌበርና ዜባስቲያን ፌትል በእኩል 78 ነጥቦች የሚመሩ ሲሆን የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ በ 75 ሶሥተኛ፤ እንዲሁም ያለፈው ሻምፒዮን ጄሰን ባተን በሰባ ነጥቦች አራተኛ ነው።

MM/RTR/AFP

Negash Mohammed