1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 30 2002

በአፍሪቃ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው 19ኛው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊጀመር እየተቃረበ ሲሆን በፊታችን አርብ በደመቀ ስነ-ስርዓት ይከፈታል።

https://p.dw.com/p/Nk7k
ምስል AP

19ኛው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በፊታችን አርብ ደቡብ አፍሪቃና ሜክሢኮ ጆሃንስበርግ ላይ በሚያካሂዱት ግጥሚያ ይከፈታል። ከ 32ቱ ተሳታፊ ሃገራት ቡድኖች አብዛኞቹ ደቡብ አፍሪቃ ሲገቡ የየበኩላቸውን የመጨረሻ ዝግጅት ቀስ በቀስ እያጠናቀቁ ነው። ሃያላን ከሚባሉት አገሮ መካከል የብራዚልና የአርጄንቲና ቡድኖች ቀደም ብለው ወደ ደቡብ አፍሪቃ ሲጓዙ የጀርመን ብሄራዊ ቡድንም ዛሬ ማለዳ ላይ ጆሃንስበርግ ገብቷል። ቡድኑ አየሩን ለመላመድ አሁን በቅርቡ የመጀመሪያ ልምምዱን እንደሚያካሂድ ነው የሚጠበቀው።

ደቡብ አፍሪቃ ዓለምን ለአንድ ወር ጊዜ ለማስተናገድ ዝግጁ ሆና እየጠበቀች ሲሆን እርግጥ ትናንት ጆሃንስበርግ ውስጥ በናይጄሪያና በሰሜን ኮሪያ መካከል በተካሄደ የአቅም ፍተሻ ግጥሚያ አኳያ ደጋፊዎች የተዘጋ የስታዲዮም መግቢያን ሰብረው ለመግባት ሲሞክሩ ቢያንስ 16 ሰዎች ተረጋግጠው መቁሰላቸው የደህንነት ጥበቃ በሚገባ መረጋገጡን እንደገና አጠያያቂ ማድረጉ አልቀረም። የደቡብ አፍሪቃ የፖሊስ አፈ-ቀላጤ እምቬሊ ላፖ እንደገለጹት ከሆነ የወዳጅነቱ ግጥሚያ ያን ያህል ብዙ ደጋፊዎችን ይስባል ብሎ ያሰበ የነበረ አይመስልም።

“ጨዋታውን ለመመልከት የሚፈልጉት ደጋፊዎች መብዛት ያልተጠበቀ ችግርን ፈጥሮ ነበር። እና መግቢያው ላይ ከአዘጋጆቹ በኩል ተገቢው ቁጥጥር አለመደረጉ የሚያሳዝን ነው”

ወደ ውድድሩ መለስ እንበልና በ 80 ዓመታት ዘመኑ እስካሁን የዋንጫ ባለቤት ለመሆን የበቁት ሰባት ሃገራት በሙሉ የአፍሪቃው የእግር ኳስ ፌስታ ተሳታፊዎች ናቸው። የዓለም ዋንጫን በታሪኩ ብራዚል አምሥት ጊዜ፣ ኢጣሊያ አራት ጊዜ ጀርመን ሶሥት ጊዜ፣ አርጄንቲናና ኡሩጉዋይ እያንዳንዳቸው ሁለቴ ሲያገኙ እንግሊዝና ፈረንሣይም አንድ አንድ ዕድል ደርሷቸዋል።

ዘንድሮስ ተራው የማን ይሆን? ዛሬ በኢጣሊያ እንደሚኖረው እንደቀድሞው የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ኮከብ እንደ ሉቺያኖ ቫሳሎ ከሆነ አፍሪቃም በአጨዋወት ዕድገት ለዚሁ ክብር ከሚያበቃ ደረጃ ደርሳለች። ካመነችበት ሊሣካ ይችላል። ከሶሥተኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ባለቤት፣ ከስድሥተኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋችና ምን ጊዜም በኩራት ከሚታወሰው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አምበል ከሉቺያኖ ቫሳሎ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ አድምጡ!

መሥፍን መኮንን