1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 7 2002

19ኛው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ባለፈው አርብ በደመቀ ትርዒት ተከፍቷል።

https://p.dw.com/p/NqYm
ምስል AP

ደቡብ አፍሪቃ ለዓለም ዋንጫው ውድድር ስታዲዮሞቿን በጊዜው አንጻ ትጨርስ ይሆን? ሆቴል፣ ትራንስፖርቱ፣ ጸጥታውስ ወዘተ. በጥርጣሬ ያልተባለ ነገር አልነበረም። ግን ይሁ ሁሉ ካለፈው አርብ ወዲህ አክትሞለታል። ደቡብ አፍሪቃ በጆሃንስበርጉ ሶከር-ሢቲዮ ስታዲዮም ውድድሩን በደመቀ ስነ-ስርዓት ስትከፍት ከደርባን እስከ ኬፕታውን የተለያዩት ስታዲዮሞቿ ውበትም ብዙዎችን እያስደነቀ ነው።

ወደ ጨዋታው ሻገር ልበልና አስተናጋጇ አገር ስነ-ስርዓቱን ተከትሎ ባካሄደችው የመክፈቻ ግጥሚያ ከሜክሢኮ ጋር 1-1 ስትለያይ ማዕዘን ባያግዳት ኖሮ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ለድል በበቃችም ነበር። ይህም ሆኖ ውጤቱ ለተከታዮቹ ግጥሚያዎች ተሥፋን የሚያዳብር ነው። የባፋና-ባፋናን፤ የደቡብ አፍሪቃ ተጫዋቾች መጠሪያ ነው፤ የቡድኑን ግሩም ጎል በ 55ኛዋ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ሢፊዌ ሻባላላ ነበር።
“ይህች ግብ ስለተሳካችልኝ በጣሙን ነው ደስ ያለኝ። በብሄራዊው ቡድን ውስጥ 50ኛዬ በመሆኗም ለኔ ታላቅ ትርጉም አላት። ሁሉም ነገር የሰመረ ነበር። እናም የሚቀጥለውን ጨዋታ በጉጉት ነው የምጠብቀው”

ደቡብ አፍሪቃ በሌላ በኩል በተለይም የመጀመሪያው አጋማሽ ሲታሰብ ልትሽነፍ በበቃችም ነበር። እስካሁን ከተቀሩት የአፍሪቃ አገሮች ጋና፣ ናይጄሪያና አልጄሪያም የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን ሲያካሂዱ ናይጄሪያ በአርጄንቲና መሸነፏ ብዙም ባያስደንቅም በስሎቬኒያ 1-0 የተረታው የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ግን ትልቅ ድክመት ታይቶበታል። ግጥሚያዋን በድል የተወጣችው ሰርቢያን 1-0 ያሽነፈችው ጋና ብቻ ናት። የዶቼ ቬለ የስፖርት ክፍል ባልደረባ ቮልፍጋንግ ፋን-ካን እንደሚለው ከሆነ ግን የአፍሪቃ ቡድኖች በዚህ የዓለም ዋንጫ ውድድር ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ የሚያጠራጥር ጉዳይ ነው።

“በደቡብ አፍሪቃ ብዙም አልተማመንም። ገና በመጀመሪያው አጋማሽ በሜክሢኮ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ሊመሩም በቻሉ ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሶሥት፣ አራት ወይም አምሥት በገባባቸው ነበር። የሜክሢኮ ቡድን የተሻለው ሲሆን ብዙም ዕድል ነበረው። እናም ወደፊት መዝለቃቸውን እጠራጠራለሁ። አልጄሪያም እስካሁን ባሳየችው አጨዋወት ይሳካላታል ብዬ አላስብም። ጋናን ደግሞ ጠብቆ ማየት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ጨዋታዋ ከመጨረሻዎቹ ለድል ካበቋት ሃያ ደቂቃዎች በስተቀር ያን ያህል አልነበረም። ለማንኛውም አንድ ሁለት ጨዋታ ጠብቆ መመልከቱ ግድ ነው። በጥቅሉ ግን የአፍሪቃ ቡድኖች ትልቅ፣ በጣም ትልቅ ስኬት ያገኛሉ ብዬ አልጠብቅም”

የሆነው ሆኖ ቩቩዜላ በተሰኘ ጥሩምባቸው ተጋጣሚን የሚያሸብሩት የደቡብ አፍሪቃ ብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች ባፋናዎች ወደፊት እንደሚገፉ ጨርሶ አይጠራጠሩም። እንደ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ከሆነ እንዲያውም መፈክሩ “የገባ አይወጣም” ነው። የዓለም ዋንጫ ወደ አፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ስትዘልቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን የምትቀረው እዚያው ነው ብለዋል ዙማ! ይህ የብዙዎች አፍሪቃውያን ሕልምና ምኞትም ነው።

WM100613 Ghana Serbien Weltmeisterschaft Südafrika
ምስል AP

ወደ ጨዋታው ልመለስና በመክፈቻው ዕለት ሁለተኛ ግጥሚያ ኡሩጉዋይና ፈረንሣይ ብዙም ባልደመቀ ግጥሚያ ባዶ-ለባዶ ሲለያዩ በማግሥቱ ቅዳሜ ደቡብ ኮሪያ ግሪክን 2-0፤ አርጄንቲናም ናይጄሪያን 1-0 አሸንፈዋል። በምሽቱ ያልተጠበቀው የእንግሊዝና የአሜሪካ 1-1 ውጤት ነበር። የዕለቱ አሳዛኝ ፍጡር በተለይም በስህተት ጎል የገባበት የእንግሊዝ በረኛ ሮበርት ግሪን ነበር። ፋን-ካን እንደሚለው ግን ለእንግሊዝ ድክመት ምክንያቱ የበረኛው ስህተት ብቻ አይደለም። አርጄንቲናም ቢሆን ታሸንፍ እንጂ ብዙ የጎል ዕድሏን አለመጠቀሟ ውሎ አድሮ ሊጎዳት ይችል ይሆናል።

“በእንግሊዞች እንጀምርና ቀድሞ የተጠበቀባቸውን ሁሉ አላሣዩም። እርግጥ በበረኛቸው ትልቅ ስህተት ነው ጎል የገባባቸው። ሆኖም ግን እኩል ለእኩል ለመውጣታቸው ወሣኙ ይህ ብቻ አልነበረም። ከዚያ በኋላም የ 55 ደቂቃዎች ጊዜ ሲቀራቸው ተጨማሪ ጎል ሊያስገቡ ይችሉ ነበር። ግን አልሆነም። ትልቅ ድክመት ነው ያሳዩት።
በአንጻሩ የአርጄንቲና ቡድን የተለየ ነበር። ግሩም ነው የተጫወቱት። ሆኖም እነርሱም ቢሆን ብዙ የጎል ዕድላቸውን አልተጠቀሙም። በመጨረሻ 1-0 ብቻ ነው ያሸነፉት። ይሄ ደግሞ ከሌሎች ጠንከር ካሉ ቡድኖች ጋር ከተደገመ ሊጎዳቸው ይችላል። እናም በጣም ጥሩ መጫወት፤ ነገር ግን ጥቂት ጎሎች ብቻ ማስቆጠር ሁሌ የሚበቃ አይሆንም”

ለአርጄንቲና ጋብሪዬል ሃይንሰ ብቸኛዋን ጎል ገና በስድሥተኛዋ ደቂቃ ላይ ሲያስቆጥር ጋውቾዎች የሳቱት ጎል እርግጥ ቁጥር ስፍር አልነበረውም። ከሜሢ እስከ ሂጉዌንና ሚሊቶ በዓለምአቀፍ ከዋክብት የተሞላው ቡድን አጨዋወት ግን ልብን የሚማርክ ነው። አሠልጣኙ የአንዴው የዓለም ኮከብ አርማንዶ ዲየጎ ማራዶናም ከሜዳ ዳር ያሳየው ደስታና ፈንጠዝያም ራሱን የቻለ ውበት ያለው ተውኔት ነበር። ማራዶና እንደ ተጫዋች የጨበጣትን የዓለም ዋንጫ እንደ አሠልጣኝም ሊጌጥባት የቆረጠ ነው የመሰለው። ጥበቡን ለተጫዋቾቹ አውርሶ ከሆነ እርግጥ የሚገደውም አይሆንም። የአርጄንቲና ብሄራዊ ቡድን በመሠረቱ በብዙዎች ግምት የዋንጫ ባለቤት ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት ቀደምት አገሮች መካከል አንዱ ነው።

“እርግጥ እነርሱም ለዋንጫ ዕድል ካላቸው ቀደምት አገሮች መካከል ነው የሚቆጠሩት። ይህ ጨርሶ ጥያቄ የለውም። ግን ለዚህ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የተካሄደውን ማጣሪያ በመከራ ማለፋቸው ደግሞ መረሣት የሌለበት ነገር ነው። ከዚህ ሌላ ሜሢን አንስተሃል! ሜሢን በተመለከተ እስካሁን ድረስ ሁሌም ለክለቡ ሲጫወት ከብሄራዊ ቡድኑ ይልቅ የተሻለ ሆኖ ነው የታየው። ስለዚህም የአርጄንቲና ጨዋታ እንዴት እያለ እንደሚቀጥል ጠብቆ መታዘብ ያስፈልጋል። ተናጠል ተጫዋቾችን በተመለከተ ጠንካራ ለመሆናቸውና ለዋንጫም ዕድል እንዳላቸው ግን አንድና ሁለት የለውም”

Training deutsche Mannschaft WM Südafrika Flash-Galerie
ሚሮስላቭ ክሎዘምስል AP


እንደ አርጄንቲና፣ ብራዚል፣ ኢጣሊያ ወዘተ. ሁሉ ለዋንጫ ባለቤትነት ይበቃሉ ከሚባሉት ወይም ሃያል ሆነው ከቆዩት አገሮች መካከል ጀርመንም አንዷ ስትሆን ባለፈው ምሽት ደርባን ላይ ባካሄደችው የመጀመሪያ ግጥሚያዋ አውስትራሊያን 4-0 በማሸነፍ ተፎካካሪዎቿን አስደንግጣለች። የጀርመን ቡድን በአጨዋወቱ በአገሩ ብቻ ሣይሆን በሌሎች ተፎካካሪዎቹ ዘንድም አድናቆትን ነው ያተረፈው። መለያውም እንደ ጥንቱ ትግል ብቻ አልነበረም።

“የጀርመን ቡድን አጨዋወት በጣሙን አስተማማኝ ነበር። ከዚህ ቀደም እንደሚታወቀው በትግል ብቻ ሣይሆን በጨዋታም ግሩም ሆኖ ነው የታየኝ። በተለይም በመሃል ሜዳ ከፍተኛ የቴክኒክ ብቃት ነው የታየው ምንም እንኳ የአውስትራሊያ ቡድን ደከማና አንድ ደረጃ ዝቅ ያለ ሆኖ መገኘቱ ባይታበልም! ግን ከእንዲህ ዓይነት ቡድን ጋርም ቢሆን ብዙ ጎሎችን ለማስገባት በሚገባ መጫወት ያስፈልጋል”

በሌላ በኩል የአውስትራሊያ ቡድን አንድ ተጫዋቹ ከሜዳ ወጥቶበት ከግማሽ ሰዓት በላይ በጎዶሎ ሲጫወት እስካሁን በዓለም ዋንጫው ለተመዘገበው 4-0 ከፍተኛ ውጤት የአውስትራሊያ ድካም ይሁን በዕውነት የጀርመን ጥንካሬ መጪዎቹ ግጥሚያዎች ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ። ቮልፍጋንግ ፋን-ካን ግን ድሉ የአውስትራሊያ ደካማነት ውጤት አይደለም ባይ ነው።

“አይመስለኝም! የጀርመን ቡድን በከፍተኛ የድል ፍላጎት ነው ወደ ሜዳ የገባው። ቀደም ሲል ባላክን፣ አድለርን ወይም ሮልፈስን የመሳሰሉ ጠቃሚ ተጫዋቾች በመቁሰላቸው ችግር ገጥሞት እንደነበር ይታወቃል። እና ቡድኑ ይህን ፈተና መቋቋም መቻሉም ማጠያየቁ አልቀረም። ሆኖም ወጣቶቹ ተጫዋቾች በታላቅ የድል ፍላጎትና በራስ መተማመን መንፈስ ነው የተጫወቱት። ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በስተቀር ለአውስትራሊያ ቡድን አንድም ዕድል አልሰጡም”

ቡድኑ በዕውነት ጠንካራ ከሆነ እ’ስከ ምን ደረጃ ይዘልቃል ነው ጥያቄው። ከአራት ዓመት በፊት በአገሩ “የበጋ ተረት” የሚል ስያሜ በተሰጠው የእግር ኳስ ፌስታ ወቅት ከግማሽ ፍጻሜ ደርሶ ነበር። ዘንድሮስ የበጋው ተረት እየተጻፈ ይሆን”

“የበጋው ተረት ወይም ተዓምር አንድ ነገር ነው፤ ስኬት ደግሞ ሌላ! መረሳት የሌለበት ባለፈው የ 2006 የዓለም ዋንጫ ውድድር በዚህ በጀርመንም የዋንጫ ባለቤት አልሆንንም። ሶሥተኛ፤ እንበል ሶሥተኛ ብቻ ነው የወጣነው። እርግጥ የጀርመን ቡድን ከትናንቱ መክፈቻ ግጥሚያ በኋላ ወደፊት እንደሚራመድ እተማመናለሁ። ግን በግድ የዋንጫ ባለቤትነት ዕድል ከሚሰጣቸው መካከል ይሆናል ብዬ አልጠብቅም። እንበል’ እስከ ግማሽ ፍጻሜው የሚዘልቅ ይመስለኛል”

ለማንኛውም በዛሬው ዕለት ቀደም ሲል ኔዘርላንድና ዴንማርክ 2-0 ሲለያዩ በወቅቱ ጃፓንና ካሜሩን እየተጫወቱ ነው፤ ማምሻውን ደግሞ ኢጣሊያ ከፓራጉዋይ ትገናኛለች።

መሥፍን መኮንን