1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሐምሌ 26 2002

ስፓኝ ከተማ ባርሤሎና ላይ ሲካሄድ የሰነበተው የአውሮፓ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባለፈው ምሽት ተፈጽሟል።

https://p.dw.com/p/Oa9W
ምስል AP

ስፓኝ፤ ባርሤሎና ላይ ሲካሄድ የሰነበተው የአውሮፓ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናንት በስኬት ተጠናቋል። በታላላቅ ውድድሮች ላይ እንደተለመደው ሁሉ በዚህ የአውሮፓ ሻምፒዮናም አዲስ ኮከብ መከሰቱ እልቀረም። ይሄውም የሶሥት ወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነው የፈረንሣይ ወጣት አትሌት ክሪስቶፍ ሌሜትር ነው። እርግጥ ውድድሩ የአውሮፓ ክፍለ-ዓለም ቢሆንም ቢቀር በተዘዋዋሪ አፍሪቃዊ አሻራ ያረፈበትም ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። የሶማሊያ ተወላጅ የሆነው ሞ ፋራህ የስደት አገሩን ብሪታኒያን በመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫ ለድርብ ድል አብቅቷል። ለቱርክም ከሶሥት ወርቅ ሜዳሊያዎች ሁለቱን ያስገኙት የኢትዮጵያ ተወላጅ አትሌቶች ኤልቫን-አቤይ-ለገሰና ዓለሚቱ በቀለ ናቸው።

ወደ ፈረንሣዩ ወጣት አትሌት እንመለስና ክሪስቶፍ ሌሜትር በመቶ፣ ሁለት መቶና አራት ጊዜ አንድ መቶ ሜትር የዱላ ቅብብል ሩጫ በተርታ በማሸነፍ በአውሮፓው ሻምፒዮና ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ስፖርተኛ ሆኗል። በዚህ የአጭር ርቀት ሩጫ በመቶና ሁለት መቶ ሜትር የብሪታኒያ ተወዳዳሪዎች ሁለተኛ ሲወጡ ሶሥተኛ የሆነው ፈረንሣዊው ማርሻል እምባንጆክ ነው። በአራት መቶ ሜትር ሩጫ የቤልጂጉ ኬቪን ቦርሊ ሲያሸንፍ በ 800 ሜትር ደግሞ የፖላንዱ ማርሲን ሌቫንዶቭስኪ ቀዳሚ ሆኗል።

በ 1,500 ሜትር የአስተናጋጇ አገር የስፓኙ አትሌት አርቱሮ ካሣዶ የጀርመን ተፎካካሪውን ካርስተን ሽላንገንን አስከትሎ ሲያሸንፍ ሶሥተኛ የሆነውም የስፓኝ ተወዳዳሪ ማኑዌል ኦልሜዶ ነው። በወንዶች አምሥትና አሥር ሺህ ሜትር ሩጫዎች ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ሞ ፋራህ ሲያሸንፍ ሩጫውን ይበልጥ ታላቅ ያደረገው በአሥር ሺህ ሜትር ክሪስ ቶምሰንም በሁለተኝነት ተከትሎ ለብሪታኒያ ድርብ ድል መመዝገቡ ነው። በነገራችን ላይ አንድ አትሌት ለብሪታኒያ የአሥር ሺህ ሜትር ድል ሲያስመዘግብ ሞ ፋራህ የመጀመሪያው መሆኑ ነው።

በወንዶች ማራቶን የስዊሱ ቪክቶር ሮትሊን ሲያሸንፍ የስፓኙ ሆሴ-ማኑዌል-ማርቲኔዝ ሁለተኛ፤ እንዲሁም የሩሢያው ዲሚትሪይ ሣፍሮኖቭ ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። በሴቶች አጭር ርቀት ሩጫም የፈረንሣይና የብሪታኒያ አትሌቶች ጠንክረው ሲታዩ በአራት መቶና ስምንት መቶ ሜትር ድሉ የሩሢያውያኑ ተወዳዳሪዎች የታቲያና ፊሮቫና የማሪያ ሣቪሮቫ ነበር። በ 1,500 ሜትር አንደኛ ኑሪያ ፌርናንዴዝ ከስፓኝ፣ ሁለተኛ ሂንድ ዴሂባ ከፈረንሣይ፣ ሶሥተኛ ናታሊያ ሮድሪጌዝ ከስፓኝ!

በአምሥት ሺህ ሜትር በቀደምትነት በመከታተል ከኢትዮጵያ የመነጩት ዓለሚቱ በቀለና አቤይ-ለገሰ ቱርክን ታላቅ ድል አጎናጽፈዋል። አቤይ-ለገሰ ቀደም ሲል በአሥር ሺህ ሜትር አሸናፊ ስትሆን ድሏን በአምሥት ሺህ ለመድገም የነበራት ሕልም ዕውን አልሆነላትም። የፖርቱጋሏ ጄሢካ አውጉስቶ ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽማለች። በሴቶች ማራቶን ድሉ የሊቱዋኒያ ሲሆን የሩሢያና የኢጣሊያ አትሌቶችም ለብርና ለናስ ሜዳሊያ በቅተዋል። በተረፈ በከፍታ ዝላይ ክሮኤሺያዊቱ የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ብላንካ ቭላዚች 2,03 ሜትር ከፍታን በማቋረጥ የአውሮፓ ሻምፒዮንም ለመሆን በቅታለች።

Athletik EM in Barcelona 2010
ምስል AP

በአጠቃላይ ሩሢያ አሥር ወርቅ፣ ስድሥት ብርና ስምንት ናስ፤ በጠቅላላው 24 ሜዳሊያዎችን በማግኘት የዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮና አሸናፊ አገር ስትሆን ፈረንሣይ በስምንት ወርቅ ሁለተኛ፤ ብሪታኒያ በስድሥት ወርቅ ሶሥተኛ፤ ጀርመን በአራት ወርቅ አራተኛ፤ ቱርክ በሶሥት አምሥተኛ፤ እንዲሁም አስተናጋጇ አገር ስፓኝ በሁለት ወርቅ ስድሥተኛ ሆናለች። በነገራችን ላይ ቱርክ ያለ ኢትዮጵያ ድንቅ አትሌቶች አስተዋጽኦ ለአምሥተኝነት ባልበቃችም ነበር። በታሙን ልትረካ ይገባታል። በዚህ በጀርመንም የብሄራዊው አትሌቲክስ ፌደሬሺን ፕሬዚደንት ክሌመንስ ፕሮኮፕ በአገሪቱ ስፖርተኞች ውጤት መደሰታቸውን ነው የገለጹት።

“ውጤቱን ከጠበቅነው በላይ ሆኖ ተገኝተነዋል። ካለፈው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሲነጻጸር በስድሥት ተጨማሪ ሜዳሊያዎች ነው የተሻሻልነው። ከዚሁ ሌላም አንዳንድ በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚታዩ ውጤቶችን አስመዝግበናል። በጠቅላላው ውድድሩ በጣም ግሩም ነበር”

ይሄን በዚሁ ተወት እናድርግና የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ብቃት ማነሣቱ ካልቀረ ሰሞኑን ኬንያ ውስጥ ሲካሄድ በሰነበተው የአፍሪቃ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የአገሪቱ ኮከብ የደበዘዘ ሆኖ ነው ያለፈው። ውድድሩን ኬንያ በአሥር ወርቅ፣ በሰባት ብርና ስምንት ናስ ሜዳሊያዎች በበላይነት ስትፈጽም ኢትዮጵያ በአንዲት ወርቅ፣ በአራት ብርና አራት ናስ በመወሰን ዘጠነኛ ሆናለች። ናይጄሪያ በስምንት ወርቅ ሁለተኛ፣ ደቡብ አፍሪቃ በስድሥት ወርቅ ሶሥተኛ! ኬንያውያን በአጠቃላይ አይለው ሲታዩ የኢትዮጵያ ድል በጥሩነሽ ዲባባ የአምሥት ሺህ ሜትር አሸናፊነት ብቻ ተወስኖ ቀርቷል። የድክመቱ መንስዔ በውል ሊጤን የሚገባው ነው የሚመስለው።

እግር ኳስ

የአውሮፓ ቀደምት እግር ኳስ ክለቦች ከዕረፍት ተመልሰው በቅርቡ ለሚጀምረው ለመጪው የውድድር ወቅት እየተዘጋጁ ሲሆን ከወዲሁ ግን አንዳንድ ግጥሚያዎች እየተካሄዱ ነው። ሣምንቱ የመጀመሪያው ዙር የአውሮፓ ሊጋ ሶሥተኛ ማጣሪያ ግጥሚያዎች የተካሄዱበትም ነበር። በነዚሁ ግጥሚያዎች ከብዙ በጥቂቱ አልክማር ከጎተቡርግ 2-0፤ ጁቬንቱስ ቱሪን ከአየርላንዱ ሻምሮክ ሮቨርስ 2-0፤ ስፖርቲንግ ሊዝበን ከኖርድስየላንድ ዴንማርክ 1-0፤ ኦሎምፒያኮስ ፒሬውስ ከማካቢ ቴላቪቭ 2-1፤ ሮቦትኒችኪ ስኮፕዬ ማቄዶኒያ ከሊቨርፑል 0-2፤ እንዲሁም ዲናሞ ቡካሬስት ከሃይዱክ ስፕሊት ክሮኤሺያ 3-1 ተለያይተዋል።

በኔዘርላንድ የዳች ሱፐር-ካፕ ፍጻሜ ግጥሚያ የሊጋው ሻምፒዮን ትዌንቴ ኤንሼዴ አያክስ አምስተርዳምን 1-0 በመርታት የዘንድሮውን ዋንጫ ለመውሰድ በቅቷል። አያክስ የኡሩጉዋይ አጥቂው ሉዊስ ሱዋሬስ ከዕረፍት በፊት ቀይ ካርድ ተሰጥቶት ከሜዳ ሲወጣበት አብዛኛውን ጊዜ በጎዶሎ መጫወት ነበረበት። ለኔዘርላንዱ ሻምፒዮን ብችኛዋን የድል ጎል ያያስቆጠረው ዴ-ዮንግ ነበር።

በተረፈ ቀደምቱ የአውሮፓ ክለቦች አዳዲስ ተጫዋቾችን በመግዛት ለመጪው ውድድር ራሳቸውን ማጠናከር ሲቀጥሉ እዚህ በጀርመን በዚህ ረገድ ታላቁ የሣምንቱ ዜና የሬያል ማድሪድ የአያሌ ዓመታት መለያ አርማ ራውል ወደ ሻልከ መምጣቱና በሌላ በኩልም የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ሣሚ ኬዲራ ለሬያል መሸጥ ነው። ራውል ገና ከአሁኑ በሰንበቱ የሊጋ ዋንጫ ውድድር ፍጻሜ ግጥሚያ በባየርን ሙንሺን ላይ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ከሻልከ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ ሊገባ በቅቷል። በበኩሉ መጪውን የውድድር ጊዜ የሚመለከተውም በታላቅ ተሥፋ ነው።

“ኤፍ.ሢ.ሻልከ ለጣለብኝ ዕምነት በጣም አመሰግናለሁ። የሚጠብቀን ትልቅ ፈተና ነው። ሆኖም ደጋፊዎቻችን በቡድኑ ደስተኛ እንደሚሆኑና በዘንድሮው ውድድር ካሰብነው ግብ እንደምንደርስ ተሥፋ አደርጋለሁ”

የ 23 ዓመቱ ሣሚ ኬዲራ ድግሞ ሬያል ማድሪድን የመሰለ ታላቅ ክለብ ለመቀላቀል ያጋጠመውን ዕድል በታላቅ ደስታ ነው የተቀበለው። ሣሚ ኬዲራ በደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ባሳየው ድንቅ አጨዋወት ለዚህ ክብር ሲበቃ ወደፊት የሬያልን ጨዋታ ከመሃል ሜዳ የማቀናጀት ከባድ ሃላፊነት ነው የሚኖረው። የሚጠበቅበትን ማሟላት መቻሉ በቅርቡ የሚታይ ይሆናል። ለማንኛውም ታላቁን ክለብ ለመቀላቀል የተሰጠውን ዕድል በደስታ ከመቀበል ብዙ አላንገራገረም።

“ውሣኔዬን ያደረጉት ከአሠልጣኙ ከሆሴ ሞሬኖ ተገናኝቼ ከተነጋገርኩ በኋላ በተፋጠነ ሁኔታ ነው። ይህን መሰል አስተማማኝ አሠልጣኝና ታላቅ ክለብ እምቢ ለማለት አይቻልም”

በሌላ በኩል በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ውስጥ የሬያል ዋነኛ ተፎካካሪ የሆነው ባርሤሎና የሜክሢኮ ኮከቡን ራፋኤል ማርኬዝን ከሰባት ዓመታት በኋላ አሰናብቷል። የሜክሢኮው ብሄራዊ ቡድን አምበል እንደ አንዴው የባርሣ ፈረንሣዊ አጥቂ እንደ ቲየሪ ኦንሪ በአሜሪካ ለሬድ ቡልስ እንደሚጫወት ነው የሚጠበቀው። በሌላ በኩል የክለቡ የረጅም ጊዜ ተከላካይና አምበል ካርልስ ፑጆል ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት፤ ማለት እስከመጪው የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር ድረስ የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ሆኖ ለመቀጠል ወስኗል። በጎፈሬው የሚለየው ፑጆል ከደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ድል በኋላ አበቃለሁ ብሎ እንደነበር የሚታወስ ጉዳይ ነው።

የ 32 ዓመቱ ፑጆል ውሣኔውን ከብሄራዊው ቡድን አሠልጣኝ ከቪቼንቴ-ዴል-ቦስከ የመከረበት ነገር ሲሆን ለቡድኑ ጠቃሚ መሆኑ ምንጊዜም አያጠራጥርም። በሌላ በኩል የአርጄንቲናው አሠልጣኝ ዲየጎ ማራዶና በብሄራዊው ፌደሬሺን እንዲሰናበት መደረጉ እርሱን ብቻ ሣይሆን መላውን የአገሪቱን የኳስ አፍቃሪዎች አስቆጥቷል። ብዙዎች አድናቂዎቹ እንደሚሉት ድንቁ የእግር ኳስ ጠቢብ ለውለታው የክብር ስንብት በተገባው ነበር። ለማንኛውም ዲየጎ በአንድ ዓመት ተኩል የአሠልጣኝነት ጊዜው ብዙዎች እንደተመኙት ቡድኑን ለዓለም ዋንጫ ድል ባያበቃም እንደ ተጫዋች ግን በአርጄንቲና ብቻ ሣይሆን በመላው ዓለም ተደናቂ ሆኖ ለመቀጠሉ አንድና ሁለት የለውም።

በፎርሙላ-አንድ የአውቶሞቢል እሽቅድድም ለማጠቃለል ትናንት ሁንጋሪያ ውስጥ በተካሄደው ታላቅ ውድድር የሬድ-ቡሉ አውስትራሊያዊው ዘዋሪ ማርክ ዌበር አሸናፊ ሆኗል። የፌራሪው ዘዋሪ የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ሁለተኛ ሲወጣ የጀርመኑ ዜባስቲያን ፌትል አሁንም እንዳለፈው ጊዜ የመጀመሪያ ረድፍ ጀማሪነቱን ሳይጠቀምበት በሶሥተኝነት ተወስኖ ቀርቷል። በአጠቃላይ ነጥብ ዌበር በ 161 የሚመራ ሲሆን የብሪታኒያው ሉዊስ ሃሚልተን በ 157 ነጥቦች ሁለተኛ ነው፤ ዜባስቲያን ፌትል ደግሞ በ 151 ነጥቦች በሶሥተኝነት ይከተላል።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ