1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 22 2003

የትናንቱ ሰንበት በስፖርት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ማራቶን የተሮጠበት ወይም የማራቶን ታሪክ የተጀመረበት 2,500ኛ ዓመት በጥንታዊ ስፍራው በግሪክ በተደረገ ውድድር የታሰበበት ነበር።

https://p.dw.com/p/PvdY
ምስል AP

ከዚሁ ሌላ በፍራንክፈርት ከተማ በተለይም የኬንያና የኢትዮጵያ አትሌቶች ቀደምት የሆኑበት ግሩም የማራቶን ሩጫ ተካሂዷል። በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥም ፉክክሩ አስደናቂ እንደሆነ ሲቀጥል የያዝነው ሣምንት አጋማሽ ደግሞ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር የተወሰኑ ክለቦች ወደ ጥሎ ማለፉ ዙር ለማለፍ የሚችሉበት ነው።

ማራቶን ከግሪክ እስከ ጀርመን

ግሪክ ከአቴን ወጣ ብላ የምትገኘውን ስፍራ የማራቶንን ጦርነት 2,500ኛ ዓመት ትናንት በታሪካዊ ዝግጅት አስባለች። በስፖርት ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ማራቶን ከተሮጠ ከዚያን ወዲህ በሚካሄደው ውድድር በዘንድሮው 28ኛ የአቴን ጥንታዊ ሩጫ ኬንያዊው ሬይመንድ-ቤት-ኪሙታይ በስፍራው አዲስ ክብረ-ወሰን አሸናፊ ለመሆን በቅቷል። ከማራቶን እስከ አቴን የጥንቱን ፈለግ ተከትሎ በተደረገው ታሪካዊ ሩጫ ያሸነፈው ኪሙታይ አስቸጋሪውን መንገድ ያቋረጠው በ 2 ሰዓት ከ 12 ደቂቃ ከ 40 ሤኮንድ ጊዜ ነው።
የተቀሩት ኬንያውያን ጆናታን ኪፕኮሪርና ኤድዊን ኪሙታይ ደግሞ ሁለተኛና ሶሥተኛ ሆነዋል። በሴቶች አስቸጋሪ የሆነውን ዳገት የበዛበት መንገድ የሊቱዋኒያዋ ራዛ ድራዳውስካይተ በመጀመሪያነት አቋርጣለች። በሩጫው 12,500 ሰዎች ሲሳተፉ ይህም ከዚህ ቀደም ከተለመደው በሶሥት ዕጅ የጨመረ መሆኑ ነው። ታሪካዊው ሰንበት ከአቴን እስከ ፍራንክፈርት በጥቅሉ የኬንያውያን ልዕልና የታየበት ነበር ቢባል ብዙም ማጋነን አይሆንም። ጥቂት ቀደም ሲል ትናንት ከቀትር በፊት በዚህ በጀርመን በፍራንክፈርት ከተማ በተካሄደው የማራቶን ሩጫም ሌላው ኬንያዊ ዊልሰን ኪፕሣንግ እጅግ ፈጣን በሆነ ጊዜ በ 2 ሰዓት ከ 4 ደቂቃ ከ 57 ሤኮንድ ለድል በቅቷል።
ኪፕሣንግ የሃይሌ ገብረ-ሥላሴን የዓለም ክብረ-ወሰን በ 58 ሤኮንዶች ሲቃረብ ገና በሁለተኛ ሩጫው በማራቶኑ የግሩም ጊዜ ማዕረግ ተዋረድ ላይ ስምንተኛውን ቦታ ሊይዝ ችሏል። በፍራንክፈርቱ ማራቶን የ 23 ዓመቱ ወጣት ኢትዮጵያዊ ታደሰ ቶላም ምንም እንኳ በልደት ቀኑ መቅደሙ ባይሳካለትም ሁለተኛ በመሆን አኩሪ ውጤት ነእ ያስመዘገበው። ሶሥተኛ የወጣው ኬንያዊው ኤሊያስ ቼሊሞ ነበር። በሴቶችም እንዲሁ ሁለት የኬንያ አትሌቶች ድሬ ጡኔን በሁለተኝነት መሃላቸው ማስገባት ከመገደዳቸው በስተቀር ድላቸውን አላስነጠቁም። አንደኛና ሶሥተኛ ሆነዋል።
በሩጫው ካሮሊን ኪሌል ስታሸንፍ 42ቱን ኪሎሜትር ያቋረጠችው ፈጣን በሆነ የ 2 ሰዓት ከ 23 ደቂቃ ከ 25 ሤኮንድ ጊዜ ነው። ከዚሁ ሌላ ትናንት ኬንያ ውስጥ የናይሮቢ ዓለምአቀፍ ማራቶን ሩጫም ሲካሄድ በወንዶችና በሴቶች ከአንድ እስከ ሶሥት ተከታትሎ በመግባት ያሸነፉት በሙሉ የኬንያ አትሌቶች ነበሩ።

1. Bundesliga 10. Spieltag 1. FSV Mainz 05 - Borussia Dortmund
ምስል dapd

የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ሻምፒዮና

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ላይ እናተኩርና በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን የክሪስቲያኖ ሮናልዶ አጨዋወት ማበብ ለክለቡ ለሬያል ማድሪድም የልዕልና ዋስትና ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ሬያል ሄርኩለስን ከኋላ ተነስቶ 3-1 ሲያሸንፍ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረውም ሮናልዶ ነበር። ሮናልዶ ባለፉት አራት ግጥሚያዎች ብቻ አሥር ጎሎችን ሲያስቆጥር በወቅቱ ለሬያል ማድሪድ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ማሰቡ አያዳግትም።

ሬያል ማድሪድ ከዘጠኝ ግጥሚያዎች በኋላ ሊጋውን በ 23 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ሤቪያን 5-0 አከናንቦ የሽኘው ባርሤሎና አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ በሁለተኝነት ይከተለዋል። በሃያ ነጥቦች ሶሥተኛው ከስፖርቲንግ-ጊሆን 1-1 የተለያየው ቪላርሬያል ነው። በጎል አግቢነት በጠቅላላው 13 በማስቆጠር ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ይመራል። በሰባት ጎሎች ሁለተኛው የባርሣው ሊዮኔል ሜሢ ሲሆን ሶሥተኛው ደግሞ የቢልባኦው ፌርናንዶ ሎሬንቴ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቼልሢይ፣ አርሰናልና ማንቼስተር ዩናይትድ በየበኩላቸው ግጥሚያዎች በመርታት ቀደምት ቦታቸውን እንደያዙ ሲቀጥሉ ማንቼስተር-ሢቲይ ግን በተከታታይ በደረሰበት ሁለተኛ ሽንፈት ወደታች ሸርተት ብሏል። ቼልሢይ ብላክበርን-ሮቨርስን 2-1 በማሸነፍ በአምሥት ነጥብ ልዩነት መምራቱን እንደያዘ ሲቀጥል አርሰናልም ዌስት-ሃም-ዩናይትድን 1-0 ረትቶ ሁለተኛ ነው። ማንቼስተር-ዩናይትድ ደግሞ ቶተንሃም-ሆትስፐርን 2-0 ሲረታ ከአርሰናል ጋር እኩል ሃያ ነጥቦች አሉት። በጎል ልዩነት ሶሥተኛ ነው።

ባለፈው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የውድድር ሰንበት እርግጥ ይበልጡን አነጋጋሪ ሆኖ የተገኘው የማንቼስተር-ዩናይትድ ፖርቱጋላዊ ኮከብ ናኒ ከሆትስፐር በረኛ ዕጅ ሞጭልፎ በመጨረሻ ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ጎል ትክክል መሆን አለመሆን ጉዳይ ነበር። ያም ሆነ ይህ ዳኛው አልሻራትም፤ ተቆጥራለች። ያም ሆነ ይህ የሣምንቱ ተንሸራታች ቡድን እንደገና ለሽንፈት የበቃው ማንቼስተር-ሢቲይ ነበር። ቡድኑ በዎልቨርሃምፕተን-ወንደረርስ 2-1 ሲሽነፍ ይልቁንስ ሊቨርፑል ነፍስ በመዝራት ችሏል። ቡድኑ ቦልተን-ወንደረርስን 1-0 በማሸነፍ ለሁለተኛ ተከታታይ ድሉ ሲበቃ ይህም ከታች ወደ 12ኛው ቦታ ከፍ እንዲል ነው ያደረገው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ዶርትሙንድ ማይንስን 2-0 በመርታት ከሣምንት በፊት የተነጠቀውን አመራር መልሶ ለመያዝ ችሏል። ቡድኑ በእስካሁኑ ሂደት አምሥት የውጭ ግጥሚያዎቹን በተከታታይ በማሸነፍ የራሱን ክብረ-ወሰን ሲያስመዘግብ አመራሩን መያዙ የአጋጣሚ አይመስልም። እስካሁን እንደታየው ከሆነ ከተቀሩት የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ሰከን ያለው ቡድን ነው። ዶርትሙንድ አሁን ከአሥር ግጥሚያዎች በኋላ 25 ነጥቦችን ይዞ በአንዲት ነጥብ ብልጫ ማይንስን በሁለተኝነት በማስከተል ይመራል። እሠልጣኙ ዩርገን ክሎፕ ማይንስን ማሽነፍ ቀላል እንዳልነበረ ነው የገለጸው።
“ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር። እናም ስኬት ማግኘቱ በዚያው መጠን ግሩም ነው። ፉክክሩ ምን ያህል የጠበበ እንደነበረና የማይንስን ጥንካሬ ዛሬ ሁሉም የታዘበው ጉዳይ ይመስለኛል። ታዲያ ድሉን ጣፋጭ የሚያደርገውም ይሄው ነው። ጠንካራ ቡድንን ማሽነፍ ይበልጥ አስደሳች በመሆኑ!”

ሆፈንሃይም ሃኖቨርን 4-0 በማሸነፍ ሶሥተኛ ሲሆን ሌቨርኩዝንም ሻልከን 1-0 በመርታት አራተኛ ነው። ሻልከን ካነሣን ዘንድሮ የቡንደስሊጋው ውድድር አልሳካለት ያለው ቀደምት ክለብ አሁንም ከወደቀበት አዘቅት በቀላሉ ሊወጣ አልቻለም። ከሰንበቱ ሽንፈት በኋላ ከመጨረሻው ከግላድባህ በጎል ብቻ በመሻል 17ኛ ነው። ሌላው ቀደምት ክለብ ባየርን ሙንሺን ፍራይቡርግን 4-2 አሸንፎ ወደ ስምንተኛው ቦታ ከፍ በማለት የማገገም አዝማሚያ ሲያሳይ በአንጻሩ ብሬመን ለዚያውም በገዛ ሜዳው በኑርንበርግ 3-2 ተረትቶ እንደገና አቆልቁሏል። የባየርን ማገገም ቶማስ ሙለርን የመሳሰሉት ተጫዋቾቹ መልሰው በራስ መተማመንን እንዲያዳብሩ ሳያደርግ አልቀረም።

“ዛሬ ሶሥቱንም ነጥቦች በዕጃችን ለማስገባት በቅተናል። በመጀመሪያ ላይ በተወሰነ መጠንም ቢሆን የተወቀስነው ጎል ለማግባት ባለመቻላችን ነበር። ግን ዛሬ ይህን ለማድረግ ችለናል። እናም በዚሁ ደስተኛ ነን”

በቡንደስሊጋው ውድድር እስካሁን ዘጠኝ በማስቆጠር በጎል አግቢነት የሚመራው ግሪካዊው የፋርንክፈርት አጥቂ ቴኦፋኒስ ጌካስ ነው።

በተቀረ በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ላሢዮ ባልተጠበቀ ጥንካሬው በመቀጠል አመራሩን ወደ አራት ነጥቦች ልዩነት ከፍ ሲያደርግ ኤሢ.ሚላን በአንጻሩ በገዛ ሜዳው በጁቬንቱስ ተረትቷል። ሁለተኛው ጄኖዋን 1-0 የረታው ኢንተር ሚላን ነው። በፈረንሣይ ሻምፒዮና የማርሤይና የስታድ-ሬንስ ግጥሚያ በዝናብ ሳቢያ በመሸጋሸጉ ሣንት ኤቲየንን 2-0 ያሽነፈው ብሬስት ለጊዜው በሁለት ነጥቦች ልዩነት ከኋላኛው አመራሩን ወስዷል። በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን ኤንሼዴ አይንድሆፈንን 1-0 በማሽነፍ አመራሩን ሲነጥቅ በፖርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ ፖርቶ በሰባት ነጥቦች ልዩነት ፍጹም የበላይ እንደሆነ ነው።

Caroline Wozniacki Tennis Dänemark U.S. Open Flash-Galerie
ካሮሊን ቮዝኒያችኪምስል AP

የዶሃ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ፍጻሜ ግጥሚያ

የቤልጂጓ የቴኒስ ኮከብ ኪም ክላይስተርስ በካታር-የዶሃ ፍጻሜ ግጥሚያ በማሸነፍ ለሶሥተኛ ጊዜ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ሻምፒዮና ባለድል ሆነች። ክላይስተርስ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛ የሆነችውን የዴንማርክ ተጋጣሚዋን ካሮሊን ቮዝኒያችኪን በሶሥት ምድብ ጨዋታ ስታሽንፍ ለድሏም 1,5 ሚሊዮን ዶላር ተሸልማለች። የቤልጂጓ ተወላጅ ባለፈው ቅዳሜ ደርሶ ከነበረ የመኪና አደጋ አንዳች ጉዳት ሳይደርስባት ስታመልጥ ግጥሚያውን ያላንዳች መረበሽ ማጠናቀቋ ብዙዎችን ነው ያስደነቀው።
ክላይስተርስ በወቅቱ በዓለምአቀፉ ተዋረድ ላይ በአራተኛ ደረጃ የምትገኝ ሲሆን ከሰባት ዓመታት በፊት ለአጭር ጊዜም ቢሆን አንደኛ እንደነበረች የሚታወስ ነው። በሌሎች የሰንበቱ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያዎች በቫሌንሢያ-ኦፕን የአርጄንቲናው ሁዋን ሞናኮ የስፓኝ ተጋጣሚውን ሮቤርቶ ባውቲስታን 3-1 አሸንፏል። በሞንትፔሊዬር ፍጻሜ ደግሞ የፈረንሣዩ ጌል ሞንፊልስ የክሮኤሺያውን ኢቫን ሉቢቺችን በተመሳሳይ ውጤት ረትቷል። ከዚሁ ሌላ በሣንት-ፒተርስቡበርግ የኤ.ቲፒ. ፍጻሜም የሩሢያው ሚሃኢል ዩሽኒ የካዛክስታን ተጋጣሚውን አሸንፋል።

ሕዝባዊት ቻይና ጉዋንግሹ ላይ የምታስተናግደው የእሢያ ጨዋታ ሊከፈት 11 ቀናት ቀርቶት ሳለ ውድድሩ ግዙፍ መሆኑ ብቻ ሣይሆን የቻይና ልዕልና የሚንጸባረቅበት መሆኑም ከወዲሁ እየተነገረ ነው። ከ 42ቱ የስፖርት ዓይነቶች ከአንዱ በስተቀር በሁሉም የምትሳተፈው አስተናጋጅ አገር ለተከታታይ ስምንተኛ ጊዜ አብዛኛውን ሜዳሊያ ለመውሰድ እንደምታልም አስታውቃለች። ከአራት ዓመታት በፊት በዶሃው አሢያድ 165 የወርቅ ሜዳሊያ ማሽነፏ አይዘነጋም። ቻይና ውድድሩን ለመጪው የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታ መዘጋጃ ጭምር አድርጋም ነው የምትመለከተው።

ዘገባችንን በእግር ኳስ ለማጠቃለል በአፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ ውድድር የመጀመሪያ ግጥሚያ ትናንት የዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ ክለብ ማዜምቤ የቱኒዚያ ተጋጣሚውን ኤስፔራንስን 5-0 በማሸነፍ ለመልሱ ጨዋታ ጥሩ ሁኔታን አመቻችቷል። ኤስፔራንስ በዚህ መጠን ሊሸነፍ የበቃው በተለይም ተከላካዩ ሞሐመድ-ማንሱር ገና በመጀመሪያው አጋማሽ ከሜዳ እንዲወጣበት በመደረጉ ነው። ከዚህ ውጤት በኋላ ማዜምቤ በመልሱ ጨዋታ በማሸነፍ ያለፈውን ዓመት ድሉን እንደሚደግም ብዙም የሚጠራጠር የለም።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ