1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 6 2003

በፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ዜባስቲያን ፌትል ትናንት ሁለተኛው ጀርመናዊ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን በቅቷል።

https://p.dw.com/p/Q9Pl
ምስል AP

ዜባስቲያን ፌትል የፎርሙላ-አንድ ሻምፒዮን

ትናንት አቡ-ድሃቢ ላይ በተጠናቀቀው በዘንድሮው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን በቅቷል። የ 23 ዓመቱ ፌትል ከዝነኛው ሚሻኤል ሹማኸር ቀጥሎ ለዚህ ድል የበቃው ሁለተኛው ጀርመናዊ ሲሆን በዕድሜም እስካሁን ወጣቱ የፎርሙላ-አንድ ሻምፒዮን መሆኑ ነው። በትናንቱ 19ኛና የመጨረሻ እሽቅድድም የብሪታኒያ ዘዋሪዎች ሉዊስ ሃሚልተንና ጄሰን ባተን ደግሞ ሁለተኛና ሶሥተኛ ወጥተዋል።
በአጠቃላይ ነጥብ እስከ ትናንት ይመራ የነበረው የስፓኙ ዘዋሪ ፌርናንዶ አሎንሶ ለሻምፒዮንነት የሚያበቃውን አምሥተኛ ቦታ እንኳ ለመያዝ ሳይችል ቀርቷል። ወጣቱ ዜባስቲያን ፌትል እሽቅድድሙ እንዳበቃ ደስታውን የገለጸው እንባ እየተናነቀው ነበር። በአንጻሩ ወደ ውድድሩ እንደገና የተመለሰው የሰባት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ሚሻኤል ሹማሸር በአጠቃላይ ነጥብ በዘጠነኝነት ሲወሰን በጅምሩ ያሰበው ሁሉ አልሆነለትም። እናም መቀጠሉ ሲበዛ የሚያጠራጥር ነው።

Champions League FC Chelsea Spartak Moskau Flash-Galerie
ምስል AP

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እንጀምርና ለኤፍ.ሢ.ቼልሢይ ሰንበቱ ያለፈው በዘንድሮው የውድድር ወቅት በገዛ ሜዳው ለመጀመሪያ ጊዜ በደረሰበት ሽንፈት ነው። ቡድኑ በሰንደርላንድ 3-0 ሲቀጣ በሜዳው ባካሄዳቸው ባለፉት ስድሥት ግጥሚያዎች በሙሉ በማሽነፍ በጎልም አንድ እንኳ ሳይገባበት 17 ማስቆጠሩ ለፕሬሚየር ሊጉ አዲስ ክብረ-ወሰን ነበር። ማንቼስተር ዩናይትድ ከኤስተን ቪላ 2-2 በመለያየት ከሁለተኛው ቦታ ሲያቆለቁል አርሰናል በአንጻሩ ኤቨርተንን 2-1 በመርታት በቦታው ተተክቷል።
ከፕሬሚየር ሊጉ 13 ግጥሚያዎች በኋላ ቼልሢይ በ 28 ነጥቦች በአንደኝነት መምራቱን የቀጠለ ሲሆን አርሰናል በ 26 ሁለተኛ ነው፤ ማንቼስተር ዩናይትድ አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተላል። በጎል አግቢነት እያንዳንዳቸው ሰባት በማስቆጠር አራት ተጫዋቾች በእኩልነት የሚመሩ ሲሆን ከነዚሁ አንዱም የቼልሢው ፍሎሬንት ማሉዳ ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን እስካሁን አንዴም ያልተሸነፈው ሬያል ማድሪድ ዋነኛ ተፎካካሪውን ባርሤሎናን በአንዲት ነጥብ ብልጫ አስከትሎ መምራቱም ቀጥሏል። ሬያል አመራሩን ሊጠብቅ የቻለው ስፖርቲንግ ጊዮንን አርጄንቲናዊ አጥቂው ጎንዛሎ ሂጉዌይን ባስቆጠራት አንዲት ግብ በመርታት ነው። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ባርሤሎናም ቪላርሬያልን 3-1 በማሸነፍ የሣምንቱን ፈተናውን በስኬት ተወጥቷል። ከሶሥት ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው የቡድኑ ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ነበር።

ሬያል ማድሪድ ከ 11 ግጥሚያዎች በኋላ በ 29 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ባርሤሎና አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ በሁለተኝነት ይከተላል፤ ቪላርሬያል ደግሞ በ 23 ነጥቦች ሶሥተኛ ነው። በጎል አግቢነት የሬያል ማድሪዱ ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ 11 አስቆጥሮ ይመራል።

Bundesliga 12. Spieltag Bayern Nürnberg 2010
ምስል picture-alliance/dpa

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር የዘንድሮው ግሩም ቡድን ቦሩሢያ ዶርትሙንግ በሻምፒዮንነት አቅጣጫ የያዘው የብቻ ጉዞ በዚህ ሣምንትም አልተገታም። ሃምቡርግን 2-0 አሸንፏል። ቡድኑ በዚሁ አመራሩን ወደ ሰባት ነጥቦች ልዩነት ሲያሰፋ ለዚህም የጠቀመው እርግጥ ከድንቅ አጨዋወቱ ሌላ በተለይ በቅርብ የሚከተለው የማይንስ እንደገና መሸነፍ ነበር። ዶርትሙንድ ከ 12 ግጥሚያዎች አሥሩን በማሸነፍ ከባየርን ሙንሺን ክብረ-ወሰን ላይ ሲደርስ አሠልጣኙ ዩርገን ክሎፕ ሳይቀር በቡድኑ አጨዋወት በጣሙን የተማረከው።

“ቡድኑ ዛሬ ያሳየው ጨዋታ እጅግ ግሩም ነበር። ሃምቡርግን ከመሰለ በጨዋታ የጠነከረ ቡድን ጋር ይህን የመሰለ የኳስ ችሎታ ማሳየት አስገራሚ ነገር ነው። በጥቅሉ ምሽቱ ግሩም ነበር ለማለት እወዳለሁ”
ቡድኑ ከራስ ጥንካሬው ሌላ በሁለተኛው በማይንስ መሸነፍ መጠቀሙም አልቀረም። ማይንስ በሃኖቨር 1-0 በመረታት ወደ ሶሥተኛው ቦታ ሲያቆለቁል መጠናከር የያዘው ሌቨርኩዝን ደግሞ ሣንት ፓውሊን በተመሳሳይ ውጤት በማሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ብሏል። አሠልጣኙ ዩፕ ሃይንከስ በተለይም የቡድኑን የትግል መንፈስ ነው ከፍ አድርጎ ያወደሰው።

“በኔ አመለካከት በመጀመሪያው አጋማሽ ያሳየነው አጨዋወት በጣም አስደሳች ነበር። ይህን መሰሉን ግጥሚያ ማሸነፋችን እርግጥ በዘንድሮው የውድድር ወቅት ያልተለመደ ነገር አይደለም። ብዙ ግጥሚያዎችን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጎል በማስቆጠር አሸንፈናል። ቡድኑ ከልብ የሚታገልና የእግር ኳስ አጨዋወት ችሎታ ያለው ሲሆን ሞራሉም ከፍተኛ ነው”

የብዙ ጊዜው ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺንም ከአጀማመር ድክመቱ በመላቀቅ ቀስ በቀስ ቀደምቱን ክለቦች እየተቀላቀለ በመሄድ ላይ ነው። ባየርን ትናንት ኑርንበርግን 3-0ሲያሸንፍ ወደ ስድሥተኛው ቦታ ከፍ ሊል በቅቷል። የሣምንቱ አቆልቋይ ክለብ በተለይም በሙንሸን ግላድባህ በሜዳው 4-0 ተቀጥቶ ወደ መጨረሻው ቦታ የተንሸራተተው ኤፍ.ሢ.ኮሎኝ ነው። በጎል አግቢነት የፍራንክፉርቱ ቴኦፋኒስ ጌካስ 11 አስቆጥሮ ይመራል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኤ.ሢ.ሚላን የከተማ ተፎካካሪውን ኢንተርን 1-0 ሲረታ በአንዲት ነጥብ ብልጫ ቀደምቱ እንደሆነ ነው። የብዙ ጊዜው ሻምፒዮን ኢንተር ሚላን በአንጻሩ በትናንት ሽንፈቱ ወደ አምሥተኛው ቦታ ማቆልቆሉ ግድ ሆኖበታል። መንገዳገድ በያዘው ሻምፒዮን ክለብ በኢንተር ላይ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ዝላታን ኢብራሂሞቪች ነበር። የስዊድኑ ኮከብ ቀድሞ ለኢንተር መጫወቱ ይታወቃል። ኤ.ሢ.ሚላን በወቅቱ አካሄዱ ከቀጠለ ኢንተርን ከአምሥት ዓመታት በኋላ ከዙፋኑ የሚፈነቅል እየመሰለ ነው። ሁለተኛው ላሢዮም ናፖሊን 2-0 በመርታት ኤ.ሢ.ሚላንን በአንዲት ነጥብ ልዩነት በቅርብ መከተሉን ቀጥሏል። በጎል አግቢነት ስምንት አስቆጥሮ የሚመራው የኢንተሩ ካሜሩናዊ ሣሙዔል ኤቶ ነው።

የፈረንሣይ ሻምፒዮና ከ 13 ግጥሚያዎች በኋላም የጠበበ የብዙ ክለቦች ፉክክር እንደሰመረበት ነው። ስታድ ብሬስት በ 22 ነጥቦች በአንደኝነት ይመራል፤ ሊል ሁለተኛ፤ ሞንፔልዬር ደግሞ ሶሥተኛ ነው። በሌላ በኩል በአንደኛውና በ 12ኛው መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት አራት ብቻ በመሆኑ የሻምፒዮንነት ዕድል ያላቸው ክለቦች ብዙዎች እንደሆኑ ይቀጥላሉ። በአንጻሩ በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶ በአስተማማኝ አሥር ነጥብ ልዩነት መምራቱን ሲቀጥል በኔዘርላንድ ሊጋም አይንድሆፈን የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ኤንሼዴና አያክስ አምስተርዳም በመሽነፋቸው አመራሩን መልሶ ለመያዝ በቅቷል።

BdT Berlin Marathon Haile Gebrselassie mit neuem Weltrekord
ምስል AP

ሃይሌ ገብረ-ሥላሴ ከሣምንት በፊት ያደረገውን የስንብት ውሣኔ በማጠፍ ወደ አትሌቲክሱ ውድድር መድረክ ሊመለስ ነው። ሮይተርስ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ሃይሌ ቀደም ያለ ውሣኔውን የቀየረው ሰንበቱን ወለጋ ውስጥ በተካሄደ ሩጫ አኳያ ነው። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደግሞ ሃይሌ ለለንደኑ ኦሎምፒክ መዘጋጀቱን እንደሚቀጥል ዘግቧል። የኔዘርላንድ ተወላጅ የሆነው ማኔጀሩ ጆስ ሄርመንስ በፊናው በዚህ ሣምንት ከሃይሌ ጋር ተገናኝቶ በመነጋገር አትሌቱን ሃሣብ ለማስለወጥ እንዳቀደ ትናንት አመልክቶ ነበር።

ሃይሌ ከሣምንት በፊት በጉልበት ሕመም ምክንያት የኒውዮርኩን ማራቶን አቋረጦ ከወጣ በኋላ ድንገት ከስፖርቱ መድረክ ስንብት ማድረጉን ማስታወቁ አይዘነጋም። ሄርመንስ ለጀርመኑ ዕለታዊ ጋዜጣ ለፍራንክፉርተር-አልገማይነ-ሣይቱንግ ሲያስረዳ የቀድሞውን የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን፤ እንዲሁም የዓለም የማራቶን ክብረ-ወሰን ባለቤት ለመሳብ የሚያደርገው ጥረት እንደሚሳካለት ተሥፋውን ገልጾ ነበር። ለሃይሌ የሃሣብ ለውጥ ከወዲሁ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያድርግ አያድርግ ግን ለጊዜው የሚታወቅ ነገር የለም።

ትናንት በተካሄደ የፓሪስ-ኦፕን ፍጻሜ ጨዋታ የስዊድኑ ሮቢን ሶደሪንግ ጌል ሞንፊልስን በማሽነፍ ፈረንሣዊ ተጋጣሚው በአገሩ ለድል ለመብቃት የነበረውን ሕልም ከንቱ አድርጎ አስቀርቶታል። ሶደሪንግ በትናንት ድሉ የብሪታኒያውን ተወላጅ ኤንዲይ መሪይን በመፈንቀል ወደ አራተኛው ቦታ ከፍ ሲል በሣምንት ጊዜ ውስጥ ለንደን ላይ ለሚጀመረው ለዓመቱ ማጠቃለያ ውድድር ራሱን አጠናክሯል።

በተረፈ የያዝነው ሣምንት አጋማሽ የደቡብ አፍሪቃው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ዓመት በተለያዩ አስደናቂ ግጥሚያዎች የሚጠቃለልበትም ነው። ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል ብራዚል ከአርጄንቲና፤ ጀርመን ከስዊድን፣ እንግሊዝ ከፈረንሣይና እንዲሁም ስፓኝ ከፖርቱጋል በፊታችን ረቡዕ ምሽት በዓለም ዙሪያ አያሌ የቴሌቪዥን ተመልካችን እንደሚማረኩ የሚጠራጥር የለም።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ