1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 9 2003

በዛሬውም ዝግጅታችን እንደተለመደው በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የእግር ኳስ ሻምፒዮና ላይ በሰፊው እናተኩራለን።

https://p.dw.com/p/QsxE
ምስል picture alliance/dpa

ሣምንቱ በዓለምአቀፉ የረጅም ርቀት ሩጫ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቶች ቀደምት ሆነው የታዩበትም ነበር። ከዚሁ ሌላ ካታር ላይ የሚካሄደው የእሢያ የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ለአስተናጋጇ አገርም የቀና ሆኖ እየተራመደ ሲሆን በስዊድን ደግሞ ባለፈው ሣምንት የተጀመረው የዕጅ ኳስ የዓለም ሻምፒዮና ቀጥሏል።

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር እንጀምርና በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን የሁለት ክለቦች የበላይነት በሰፈነበት ፉክክር በዚህ ሣምንት ባርሣ ከሬያል ማድሪድ የተሻለው ነበር። ኤፍ.ሢ.ባርሤሎና ማላጋን 4-1 ሲረታ አመራሩን ወደ አራት ነጥቦች ከፍ ሊያደርግም በቅቷል። ለቡድኑ ከአራት ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው ደግሞ ድንቁ ዴቪድ ቪያ ነበር። ባርሤሎናን በተለይ የጠቀመው የቅርብ ተፎካካሪው ሬያል ማድሪድ ከዝቅተኛው ክለብ ከአልሜይራ ጋር ባካሄደው ግጥሚያ 1-1 በሆነ ውጤት መወሰኑ ነው።
ባርሣ ዘንድሮ በሁሉም የሊጋው ውድድሮች፤ ማለትም በሊጋው ሻምፒዮና፣ በሊጋው ጥሎ ማለፍ ዋንጫና በአውሮፓ ውድድሮች 28 ግጥሚያዎችን ሳይሸነፍ በማሰለፍ የክለብ ክብረ-ወሰንን አስመዝግቧል። ክለቡ ከፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ 19 ግጥሚያዎች በኋላ አሁን በ 52 ነጥቦች ሊጋውን የሚመራ ሲሆን ሬያል በ 48 ሁለተኛ፤ እንዲሁም ዘጠኝ ነጥቦች ወረድ ብሎ ቪላርሬያል ሶሥተኛ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደግሞ ማንቼስተር ዩናይትድ ምንም እንኳ በሰንበት ግጥሚያው ከቶተንሃም ሆትስፐር ባዶ-ለባዶ ቢለያይም ለዚያውም ሁለት ግጥሚያዎች ጎለውት በአመራሩ ቀጥሏል። ማኒዩ በ 21 ግጥሚያዎች 45 ነጥቦችን ሲሰበስብ ሁለተኛው ማንቼስተር ሢቲይም 23 ጊዜ ተጋጥሞ እኩል ነጥብ ነው ያለው። ማንቼስተር ሢቲይ ባለፈው ቅዳሜ ዎልቨርሃምፕተን ዎንደረርስን 4-3 ሲያሸንፍ ዘንድሮ ብርቱ የዋንጫ ባለቤትነት ተፎካካሪ የሚሆን እየመሰለ ነው። እርግጥ የመከላከል ብቃቱን እንደ ማጥቃት ችሎታው ሁሉ ማጠናከር ይኖርበታል።

አርሰናል ዌስት-ሃም-ዩናይትድን 3-0 አሸንፎ በ 43 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን ቼልሢይም ብላክበርን ሮቭርስን 2-0 በመርታት በ 38 ነጥቦች አራተኛ ነው። በተረፈ ሊቨርፑል ከኤቨርተን 2-2፤ በርሚንግሃም ሢቲይ ከኤስተን ቪላ 1-1፤ ሰንደርላንድ ከኒውካስል ዩናይትድ 1-1፤ ዊጋን አትሌቲክ ከፉልሃም 1-1፤ ሁሉም ግጥሚያዎች በእኩል ለእኩል ውጤት ተፈጽመዋል።

Flash-Galerie Bundesliga 14.01.2011 1. Bayer 04 Leverkusen Borussia Dortmund
ምስል dapd

በዚህ በጀርመን ቡንደስሊጋ በውድድሩ መጀመሪያ ማንም ያልጠበቀው ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ለሰባተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን በያዘው ዕርምጃ አሁንም የሚያቆመው አልተገኘም። ቡድኑ በመልሱ ዙር የመጀመሪያ ግጥሚያው በቅርብ ተፎካካሪው በሌቨርኩዝን ሜዳ በፍጹም የበላይነት 3-1 ሲረታ አመራሩን በ 12 ነጥቦች ለማስፋት በቅቷል። ለቡድኑ ከሶሥት ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው ኬቪን ግሮስክሮይትስ ነበር፤ እና ደስታውም ወሰን አልነበረውም።

“ስኬታችን በቀላሉ አርኪ ነው። ይህን በመሰለ ቡድን ውስጥ መጫወቱ እጅግ በጣም ያስደስታል። ከመጀመሪያዋ ደቂቃ አንስተን ጥሩ ስንጫወት ያሸነፍነውም በአግባብ ነው”
ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ሁለተኛውም ፍራንክፉርትን 3-0 ያሽነፈው ሃኖቨር ሲሆን ይሄው ክለብ ባለፈው የውድድር ወቅት ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ከማቆልቆል የተረፈው ለጥቂት እንደነበር ሲታወስ በጣም የሚያስገርም ነው። በዚሁ የተነሣም ሁለተኛዋን ጎል ያስቆጠረው ክሪስቲያን ሹልትስ ስኬቱ ቡድኑ በጥሩ አቅጣጫ እየተራመደ መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ነው የገለጸው።

“በጥሩ መንገድ ላይ ነው የምንገኘው። እርግጥ በዛሬው ጨዋታ ፍራንክፉርትም ቀድሞ ሊመራ በቻለ ነበር። ከዚህ አንጻር ሁሉም ነገር እንዳሰብነው የተሳካ አልነበረም። ከውጤት አንጻር ግን 3-0 ግልጽ ነገር ነው። እናም በዚሁ የተነሣ አሁን ሁለተኛው ቦታ ላይ በመድረሳችን ተደስተናል”

በሌላ በኩል በመጀመሪያው ዙር እንደ ዶርትሙንድ ብዙውን ጊዜ ጠንካራ የነበረው ማይንስ በሽቱትጋርት 1-0 በመሽነፍ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ሲንሸራተት የቡንደስሊጋው ሬኮርድ ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን ደግሞ ከቮልፍስቡርግ 1-1 በመውጣት ከአመራሩ ይብሱን መራቁ ግድ ሆኖበታል። በወቅቱ ከዶርትሙንድ የሚለዩት 16 ነጥቦች ናቸው። በተቀረ መንሸን ግላድባህ ከኑርንበርግ 0-1፤ ብሬመን ከሆፈንሃይም 2-1፤ ካይዘርስላውተርን ከኮሎኝ 1-1 ተለያይተዋል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ቀደምቱ ኤ.ሢ.ሚላን ከሌቼ 1-1 በመለያየት አመራሩን ወደ ስድሥት ነጥቦች ለማስፋት የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ቢሆንም ከሃያ ግጥሚያዎች በኋላ በ 41 ነጥቦች አንደኛ ነው። ናፖሊ ከፊዮሬንቲና ባዶ-ለባዶ ቢለያይም በ 37 ነጥቦች ሁለተኛ ሲሆን ሶሥተኛው ላሢዮ ደግሞ ሣምፕዶሪያን 1-0 በመርታት ከናፖሊ ጋር በነጥብ እኩል ለመሆን ችሏል። ሮማ አራተኛ፤ ጁቬንቱስ አምስተኛ፤ ኢንተር ሚላን ስድሥተኛ!

የፈረንሣይ ሻምፒዮና እንደጠበበ የቀጠለ ሲሆን አሁንም አንደኛውን ክለብ ከሰባተኛው የሚለዩት አምሥት ነጥቦች ብቻ ናቸው። በሰንበቱ ግጥሚያዎች ሊል ኒስን 2-0 በመርታት በ 35 ነጥቦች አመራሩን እንደያዘ ሲቀጥል ለዚያውም ገና አንድ ግጥሚያ ይጎለዋል። ፓሪስ-ሣን ዠርማን፣ ስታድ ሬንስና ኦላምፒክ ሊዮን ደግሞ ሁሉም የየበኩላቸውን ግጥሚያ ሲያሸንፉ ከሊል አንዲት ነጥብ ብቻ ወረድ ብለው በእኩልነት ይከተላሉ። ከመጀመሪያው ቦታ በሁለት ነጥቦች የሚርቀው ኦላምፒክ ማርሤይ ሲሆን አምሥተኛ ነው። በተቀረ በፖርቱጋል ሻምፒዮና የፖርቶ የብቻ ጉዞ ባለበት ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ አትሌቶች ሰንበቱን ሕንድ ውስጥ በተካሄደው የሙምባይ ማራቶን ሩጫ በወንዶችና በሴቶችም አሸናፊ በመሆን ግሩም ውጤት አስመዝግበዋል። በወንዶች ግርማ አሰፋ ግሩም በሆነ የሁለት ሰዓት ከዘጠኝ ደቂቃ 54 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ጸጋዬ ወልዴ ሶሥት መቶኛ ሤኮንድ ብቻ በመዘግየት ሁለተኛ ሆኗል። ሶሥተኛ ፓትሪክ ሙሪዩኪ ከኬንያ፤ ታሪኩ ጂፋር አራተኛ፤ እንዲሁም ሃይሌ ገመዳ አምሥተኛ!

በሴቶች ኢትዮጵያዊቱ ኮረን ጀሊላ በሙምባይ ማራቶን ፈጣን ጊዜ ስታሽንፍ ከሁለት እስከ ሰባተኛው ቦታ ድረስም በመከታተል የገቡት በሙሉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸው። የሙምባይ ማራቶን በኢትዮጵያና በኬንያ አትሌቶች ፉክክር የኢትዮጵያውያኑ ጥንካሬ የጎላበት ነበር። አንድ ሣምንት ቀደም ሲልም በኔዘርላንድ የኤግሞንድ ግማሽ ማራቶን አየለ አብሸሮና አበበች አፈወርቅ በየፊናቸው ለድል መብቃታቸው አይዘነጋም።

US OPen Tennis Championship Roger Federer Schweiz 2010 Flash-Galerie
ምስል picture-alliance/dpa

ስዊድን ውስጥ በአራት ምድቦች ተከፍሎ በመካሄድ ላይ ባለው የዕጅ ኳስ የዓለም ሻምፒዮና ውድድር እስካሁን በተካሄዱት ግጥሚያዎች ታላላቁ ቡድኖች ጥንካሬያቸውን ሲያስመሰክሩ ታናናሾቹም ለስንብት እየተቃረቡ ነው። በምድብ ሁለት ውስጥ አይስላንድ፣ አውስትሪያ፣ ኖርዌይ፣ ጃፓን፣ ሁንጋሪያና ብራዚል በሙሉ ወደፊት የመግፋት ዕድላቸውን ገና እንደጠበቁ ሲሆን በምድብ ሶሥት በአንጻሩ አልጄሪያ፣ ሩሜኒያና አውስትራሊያ ከወዲሁ ያለቀላቸው ነው የሚመስለው።

ዴንማርክ፣ ሰርቢያና ክሮኤሺያ ግን በእኩል አራት ነጥቦች በፉክክራቸው ቀጥለዋል። በምድብ አራት ውስጥ አስተናጋጇ ስዊድን፣ ፖላንድና ደቡብ ኮሪያ የምድቡ ቁንጮዎች ሲሆኑ በምድብ አንድ ዋነኛ ፉክክር ጀርመንና ያለፈው ዋንጫ ባለቤት ፈረንሣይ ዛሬ ማምሻውን ይጋጠማሉ። ጀርመን በመጀመሪያዎቹ ሁለት ግጥሚያዎቿ ግብጽንና ባህሬይንን በፍጹም የበላይነት ብታሽንፍን ፈረንሣይን ለመርታት ግን የቡድኑ አከፋፋይ ሚሻኤል ክራውስ እንደሚለው በተለይም በመከላከል ረገድ ብርቱ ጥረትን የሚጠይቅ ነው።

“ቡድኑ ሊሸነፍም የሚችል ነው። ሆኖም ግን ስፓኞችን በቀላሉ መመልከት የለብንም። የጨዋታውን ውጤት ለመለየት እርግጥ በመጀመሪያ እያንዳንዱ ግጥሚያ መካሄድ አለበት። ይሁን እንጂ ወደ ሜዳ የምንገባው በታላቅ በራስ መተማመን ስሜት ነው”

በአርጄንቲናና በቺሌ ከ 9,500 ኪሎሜትር በላይ ርቀት ባቋረጠው በዘንድሮው 33ኛ ራሊይ-ዳካር የመኪና እሽቅድድም የካታሩ ዘዋሪ ናሰር-አል-አቲያህና የጀርመን አበሩ ቲሞ ጎትሻልክ አሸናፊ ሆነዋል። የካታሩ ዘዋሪ የድሉን መንፈስ ከአገሪቱ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነትና ተሥፋ ጋር አያይዞታል።

“ይህ ለካታር ትልቅ ነገር ነው። አሁን ራሊይ ዳካርን እንዳሸነፍነው በ 2022 ደግሞ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን እናሸናለን። ግሩም ነበር የዛሬው ድል ለካታር!”
ባለፈው ቅዳሜ በተጠናቀቀው ውድድር ሁለተኛ የወጡት ደግሞ የደቡብ አፍሪቃው የፎልክስ-ዋገን-ቱዋሬግ ዘዋሪ ጂኒዬል-ዴ-ቪነርስና ጀርመናዊው ዲርክ-ፎን-ሢትሤቪትስ ናቸው።

በቴኒስ የአውስትራሊያን-ኦፕን የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያዎች ከወንዶች ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ እንደተጠበቀው ሮጀር ፌደረር፣ ኤንዲይ ሮዲክና ጌል ሞንፊልስ፤ እንዲሁም ከሴቶች ካሮሊን ቮዝኒያችኪና ማሪያ ሻራፖቫ ወደ ተከታዩ ዙር አልፈዋል። ያለፈው ውድድር የውንዶች አሸናፊ ፌደረር እንደነበር የሚታወስ ነው።

ዘገባችንን በእግር ኳስ ለማጠቃለል ካታር ውስጥ በሚካሄደው የእሢያ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር አስተናጋጇ አገርና ኡስቤኪስታን የምድብ አንድ ማጣሪያቸውን በስኬት በማጠናቀቅ ለሩብ ፍጻሜ አልፈዋል። በምድቡ የመጨረሻ ግጥሚያዎች ካታር ኩዋይትን 3-0 ስትረታ፤ ኡስቤኪስታን ደግሞ ከቻይና ጋር 2-2 ተለያይታለች። ኡዝቤኪስታን በሰባት ነጥቦች የምድቡ አንደኛ ስትሆን ካታር ደግሞ ከመጨረሻዎቹ ስምንት አገሮች አንዷ ለመሆን የበቃችው በሁለተኝነት ነው።

ለለንደን የ 2012 ዓ.ም. የኦሎምፒክ ጨዋታ በሚደረገው የሴቶች እግር ኳስ ማጣሪያ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ ውስጥ ባካሄደው ግጥሚያ ባዶ-ለባዶ ተለያይቶ ተመልሷል። የመልሱ ጨዋታ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው በሁለት ሣምንት ጊዜ ነው። እናም ቡድኑ ለስኬት እንዲበቃ በዚህ አጋጣሚ ከልብ እንመኛለን።

መሥፍን መኮንን