1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 14 2003

የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የእግር ኳስ ውድድርና አትሌቲክስ ዛሬም በስፖርት ዝግጅታችን ሰፊውን ቦታ የሚይዙት የስፖርት ዓይነቶች ናቸው።

https://p.dw.com/p/R2pB
የዶርትሙንድ ጎል አግቢ ሉካስ ባሪዮስምስል AP
IAAF Athletik Weltmeisterschaften
ምስል picture alliance/dpa

ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች

በአትሌቲክስ እንጀምርና ኬንያዊቱ አትሌት ሜሪይ ካይታኒ ባለፈው አርብ በተባበሩት አረብ ኤሚሮች ግዛት በዱባይ በተካሄደ የሴቶች ግማሽ ማራቶን ሩጫ አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ለማስመዝገብ ችላለች። ካይታኒ ራሷ ከሁለት ዓመታት በፊት በዚህ ርቀት የዓለም ሻምፒዮን እንደነበረች ሲታወስ አሁን በ 35 ሤኮኖንዶች ያሻሻለችው የአገሯ ልጅ ሎርናህ ኪፕላጋት በ 2007 ዓ.ም. ኢጣሊያ ውስጥ አስመዝግባ የነበረውን ፈጣን ጊዜ ነው። የፈጀባት ጊዜ አንድ ሰዓት ከአምሥት ደቂቃ ከ 55 ሤኮንድ! ካይታኒ ባለፈው ዓመት የኒውዮርክ ማራቶን ሶሥተኛ መውጣቷም ይታወሣል። ኬንያዊቱ አትሌት በፊታችን ሚያዚያ ወር የለንደን ማራቶን ለመሳተፍም የምታቅድ ሲሆን ያለፈው አርብ ግማሽ ማራቶን የአቅም መፈተሻ ጭምር መሆኑ ነበር።

በትናንትናው ዕለት ጃፓን ውስጥ ተካሄዶ በነበረ የዮኮሃማ የሴቶች ማራቶን ሩጫ ደግሞ የአገሪቱ ተወላጆች ዮሺሚ ኦዛኪና ሬሚ ናካዛቶ በመከታተል ለአሸናፊነት በቅተዋል። የ 29 ዓመቷ ዮሺሚ ከ 38ኛው ኪሎሜትር በኋላ ተፎካካሪዎቿን ጥላ ስትሄድ ሩጫውን የፈጸመችው ግሩም በሆነ የሁለት ሰዓት ከ 23 ደቂቃ 56 ሤኮንድ ጊዜ ነበር። የፖርቱጋሏ ማሪሣ ባሮሽ ሶሥተኛ ስትወጣ ጃፓናዊቱ ካኦሩ ናጋዎ አራተኛ፤ እንዲሁም የፖላንዷ ካሮሊና ያርዢንስካ አምሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል።

ባለፈው ቅዳሜ በብሪታኒያ-በርሚንግሃም ተካሂዶ በነበረው የአዳራሽ ውስጥ ግራንድ-ፕሪ አትሌቲክስ ውድድር ከሶማሊያ የመነጨው የእንግሊዝ ዜጋ ሞ ፋራህ በ 5000 ሜትር የአውሮፓን የአዳራሽ ውስጥ ክብረ-ወሰን አሻሽሏል። የ 27  ዓመቱ አትሌት  ሩጫውን በ 13 ደቂቃ ከ 10.60 ሤኮንድ ሲፈጽም ሁለተኛ የሆነው አሜሪካዊው  ጋለን ሩፕ ነበር። በ 1,500 ሜትር ደግሞ ኬንያዊው አውጉስቲን ቾጌ አሸንፏል።  ሞ ፋራህ ፓሪስ ላይ ከሁለት ሣምንት በኋላ በሚካሄደው የአውሮፓ የአዳራሽ ውስጥ ሻምፒዮና ያለፈውን የሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ድሉን ለመድገም እንደሚወዳደር ይጠበቃል።

ሌላው የአትሌቲክስ ዜና የደቡብ አፍሪቃ የሴቶች የ 800  ሜትር ሩጫ የዓለም ሻምፒዮን ካስተር ሤሜኒያ በጾታ ባሕርይዋ አሻሚነት ለአንድ ዓመት ያህል ከቦዘነች በኋላ ባለፈው ሰንበት በስኬት ወደ ውድድሩ መድረክ ተመልሳለች። ሤሜኒያ በዚያው በደቡብ አፍሪቃ በተካሄደ የ 800 ሜትር ሩጫ ያሸነፈችው ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ተፎካካሪዎቿን በመምራት ነው። አትሌቷ ባለፈው መስከረም የኮመንዌልዝ ጨዋታ በጀርባ ሕመም ምክንያት ውድድሩም ማቋረጧ ይታወሣል። ሤሜኒያ በተለይም በፊታችን ነሐሴ ወር ደቡብ ኮሪያ ውስጥ በሚደረገው የዓለም ሻምፒዮና ውድድር የምታተኩር መሆኗን አስታውቃለች።

Lionel Messi
ሊዮኔል ሜሢምስል AP

የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች እግር ኳስ

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ካለፈው ሣምንት አጋማሽ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ሽንፈቱ በኋላ የመታወክ ዝንባሌ የታየበት ባርሤሎና ዘግይታ በተገኘች ግብ አትሌቲኮ ቢልባኦን እንደምንም 2-1 በማሸነፍ የአምሥት ነጥቦች አመራሩን እንደያዘ ሊቀጥል ችሏል። ዘግይታ የተገኘችውን ሁለተኛና ወሣኝ ግብ ያስቆጠረው የቡድኑ አርጄንቲናዊ ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ነበር። ባርሣ አሁን ከ 24 ግጥሚያዎች በኋላ 65 ነጥቦች ሲኖሩት ሌቫንቴን 2-0  የሽኘው ሬያል ማድሪድ በብቸኛ ተፎካካሪነት በቅርብ ይከተላል። ባለፉት ሣምንታት መንገዳገድ የታየበት ቪላርሬያል በአንጻሩ በዚህ ሰንበትም ከማላጋ በ 1-1 ውጤት ሲወሰን ሶሥተኝነቱን በቫሌንሢያ መነጠቁ ግድ ነው የሆነበት።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰንበቱ የኤፍ-ኤ.፤ ማለትም የፌደሬሺኑ ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ውድድር የተካሄደበት ነበር። ዳዊት ጎልያድን መፈታተኑ በተለመደበት የዋንጫ ውድድር አምሥተኛ ዙር ትናንትም እንደቀድሞው አስደናቂ ውጤት መታየቱ አልቀረም። ይሄውም ዝቅተኛው ክለብ ሌይተን-ኦሪየንት ከፕሬሚየር ሊጉ ቀደምት ቡድን ከአርሰናል ጋር ዘግይቶ ባስገባት ጎል እኩል ለእኩል 1-1 መውጣቱ ነው።                                  
ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ ክሮውሊይ-ታውንን 1-0 ሲረታ መጪ ተጋጣሚው አርሰናል ይሁን ወይም ኦሪየንት ለመለየት የግድ መጠበቅ ይኖርበታል። ትናንት በወጣው የፌደሬሺኑ ዕጣ መሠረት በመጪው ሩብ ፍጻሜ የሚጋጠሙት የተቀሩት ክለቦች ስቶክ ሢቲይ ከ ዌስት ሃም ዩናይትድና ከበርንሌይ አሸናፊ፤ የማንቼስተር ሢቲይና የኤስተን ቪላ አሸናፊ ደግሞ ከኤቨርተን ወይም ከሪዲንግ፤ እንዲሁም በርሚንግሃም ሢቲይ ከቦልተን ወንደረርስ ይሆናሉ። በነገራችን ላይ ዘንድሮ ብዙም ያልቀናው ቼልሢይ በኤቨርተን ከውድድሩ ከወዲሁ ተሰናብቷል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ አመራሩን በተመለከተ በዚህ ሰንበትም የተለወጠ ነገር የለም። ሶሥቱም ቀደምት ክለቦች የየበኩላቸውን ግጥሚያዎች በማሸነፍ ሲወጡ ዶርትሙንድ ሣንት ፓውሊን 2-0 በመሸኘት በአሥር ነጥብ ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። በፊታችን ሰንበት ከጀርመኑ ሬኮርድ ሻምፒዮን ከባየርን ሙንሺን ጋር የሚጋጠመው የዘንድሮው አመርቂ ክለብ ከወጣት ተጫዋቾቹ አንዱ ኬቪን ግሮስክሮይትስ እንደሚለው ከሆነ ወደ ሙንሺን የሚያመራው በሙሉ ልብ ነው።

“እንደገና ፈጣንና ትግል የተመላበት ጨዋታ ነው ያሳየነው። በዚሁ ደጋፊዎቻችንን እንደገና አስደስተናል ብዬ አስባለሁ። ግን አሁንም ገና ያልረካ ካለ ምን ለማድረግ እንደሚቻል አላውቅም። ሁሉም በቡድኑና በክለቡ ሊኮሩ ይገባል። እናም ወደ ሙንሺን የምንጓዘው በአሥር ሺህ ያህል ደጋፊ ታጅበን ሲሆን ግሩም ትግል እንደምናደርግና እንደምናሸንፍም አልጠራጠርም”

ዶርትሙንድን በርቀትም ቢሆን በሁለተኝነት የሚከተለው ሌቨርኩዝን በትናንቱ ሰንበትም ጠንክሮ በመጫወት ሽቱትጋርትን 4-2 ሲያሸንፍ ባየርን ሙንሺንም ማይንስን 3-1  በመርታት ሶሥተኝነቱን አስከብሯል። በቡንደስሊጋው ተዋረድ ላይ  የመጨረሻው የሆነው መንሸን ግላድባህ ደግሞ ምንም እንኳ ከ 18ኛ ቦታው ባይነቃነቅም ትናንት በአዲስ የስዊስ አሠልጣኙ በሉሢየን ፋብር አመራር ሻልከን 2-1 በማሽነፍ ጥቂትም ቢሆን ነፍስ ዘርቷል። በሌላ በኩል ያለፉት በርካታ ዓመታት ጠንካራ ክለብ ብሬመን ከአንደኛው ዲቪዚዮን ለይቶለት እንዳይወርድ ከሣምንት ሣምንት ይበልጥ እያሰጋ ነው። ቡድኑ በሃምቡርግ 4-0 ሲቀጣ በተለይም አብዛኛውን ጊዜ በድን ሆኖ መታየቱ ስኬቱን ለለመዱ ደጋፊዎቹ ብቻ ሣይሆን ለአሠልጣኙ ለቶማስ ሻፍ ጭምር ግራ የሚያጋባ ነበር።

“የሚያሳዝን ሆኖ ባለፉት ጥቂት ግጥሚያዎች ያደረግነውን ገንቢ ዕርምጃ ዛሬ ያሳየነው በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ብቻ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርገን ነው የተውነው። እናም ጥቃቱን ለመከላከል በቂ የራስ መተማመን ሊኖረን አልቻለም” 

ብሬመን በዚሁ ሽንፈቱ ወደ 14ኛው ቦታ ሲያቆለቁል ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ለመውረድ ከሚያሰጋቸው ክለቦች የምትለየው በወቅቱ አንዲት ነጥብ ብቻ ናት። እናም በሚቀጥሉት ሣምንታት ብርቱ ትግል ይጠብቀዋል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኤ.ሢ.ሚላን ቬሮናን 2-1 በማሸነፍ በ 55 ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ሲቀጥል ናፖሊም ካታኛን 1-0 በመርታት ሶሥት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛ እንደሆነ ነው። ኢንተር ሚላንም እንዲሁ ካልጋሪን 1-0 በማሽነፍ በሶሥተኛው ቦታ ላይ ሊቆናጠጥ ችሏል። ላሢዮ በ 48  ነጥቦች አራተኛ ሲሆን በውድድሩ ሂደት አራቱም ክለቦች ሻምፒዮን የመሆን ዕድል አላቸው። በተቀረ በፈረንሣይ ሊል፣ በስኮትላንድ ሤልቲክ፤ በኔዘርላንድ አይንድሆፈን፣ በፖርቱጋልም ፖርቶ አመራራቸውን እንደያዙ ቀጥለዋል።

Andy Roddick beim Wimbledon-Finale 2009
ምስል AP

ዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድሮች

በአሜሪካ የሜንፊስ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድር የአገሪቱ ተወላጅ ኤንዲይ ሮዲክ ካናዳዊ የፍጻሜ ተጋጣሚውን ሚሎሽ ራኦኒክን ለተመልካች እስትንፋስ በሚያሳጣ ትግል የተመላው ጨዋታ 2-1 በማሽነፍ ለሰላሣኛ ድሉ በቅቷል። በብዌኖስ አይርስ ኦፕን ፍጻሜ ደግሞ የስፓኙ ኒኮላስ አልማግሮ ትናንት የአርጄንቲናውን ሁዋን-ኢግናሢዮ-ቼላን 6-3, 3-6, 6-4 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በሣምንት ውስጥ ለተከታታይ ሁለተኛ ድሉ በቅቷል።

በቦጎታ የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያም የስፓኟ ላውርድስ ዶሚንጌስ ፈረንሣዊቱን ማቲልድ ጆሃንሰንን ስታሸንፍ በዱባይ ሻምፒዮና ደግሞ የዴንማርኳ ካሮሊን ቮዝኒያችኪ ሩሢያዊት ተጋጣሚዋን ስቬትላና ኩዝኔትሶቫን በለየለት 6-1, 6-3  ውጤት ረትታለች። ካሮሊን ቮዝኒያችኪ በወቅቱ በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቷ ስትሆን የትናንቱ ድሏም እስካሁን 13ኛው መሆኑ ነው። በተረፈ በማርሤይ ኦፕን ፍጻሜ የስዊድኑ ሮቢን ሶደርሊንግ የክሮኤሺያ ተጋጣሚውን ማሪን ቺሊችን 2-1 አሸንፏል።

ዘገባችንን በእግር ኳስ ለማጠቃለል የያዝነው ሣምንት የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር የሚካሄዱበትም ነው። ወደ ሩብ ፍጻሜው ለማለፍ በሚደረገው ውድድር ነገ ኮፐንሃገን ከቼልሢይና ኦላምፒክ ሊዮን ከሬያል ማድሪድ የሚጋጠሙ ሲሆን በማግሥቱ ደግሞ ኦላምፒክ ማርሤይ ከማንቼስተር ዩናይትድ፤ እንዲሁም ኢንተር ሚላን ከባየርን ሙንሺን ይገናኛሉ። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ባርሤሎና ባለፈው ሣምንት በአርሰናል 2-1 ሲሽነፍ በኖው-ካምፕ ስታዲዮሙ በሚያካሂደው የመልስ ጨዋታ ብርቱ ፈተና ነው የሚጠብቀው። በገዛ ሜዳው በቶተንሃም ሆትስፐር ለተሽነፈው ኤ.ሢ.ሚላንም ቢሆን የመልሱ ግጥሚያ ቀላል የሚሆን አይመስልም።

መሥፍን መኮንን         
        

ሂሩት መለሰ