1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 20 2003

የዘንድሮው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ባለፈው ምሽት በርሊን ላይ በደመቀ ስነ-ስርዓትና ግሩም የመክፈቻ ግጥሚያ ተጀምሯል።

https://p.dw.com/p/RW4A
ምስል picture-alliance/dpa

በምድብ-አንድ መክፈቻ ግጥሚያ ያለፈው ዋንጫ ባለቤት ጀርመን በበርሊኑ የኦሎምፒክ ስታዲዮም ካናዳን 2-1 ስታሸንፍ ጅማሮዋ የሰመረ ነው የሆነው። ባልተለመደ መጠን 75 ሺህ ተመልካች በተገኘበት ስታዲዮም ለጀርመን ጎሎቹን ያስቆጠሩት በአሥረኛዋ ደቂቃ ላይ ኬርስቲን ጋረፍሬከስና በ 42ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሤሊያ ኦኮይኔ እምባቢ ነበሩ። የካናዳ ብሄራዊ ቡድን ምንም እንኳ ወደመጨረሻው አንዲት ጎል ቢያስገባም ከሽንፈት ሊያመልጥ አልቻለም። በዚሁ ምድብ ውስጥ ቀደም ሲል ዚንስሃይም ላይ በተካሄደ ሌላ ግጥሚያ ፈረንሣይ ናይጄሪያን 1-0 ረትታ ነበር። የውድድሩ ዝግጅትና የደመቀ አጀማመር የሴቶች እግር ኳስ ተቀባይነት እያደገ መሄዱን የሚያሳይ ሲሆን የዶቼ ቬለ የጀርመንኛ ፕሮግራም ዘርፍ የስፖርት ክፍል ባልደረባ ቮልፍጋንግ ፋን ካን እንደገለጸው ይሁንና ሂደቱ በተለይም ከወንዶች እግር ኳስ ደረጃ ለመድረስ ገና ብዙ የሚቀረው ነው።

“ዝግጅትን በተመለከተ እርግጥ ጀርመን በምታዘጋጀው ውድድር ሁሉም ነገር ስኬታማ መሆኑ የተለመደ ነገር ነው። እና ከዚህ አንጻር አሁንም በሴቶቹ የዓለም ዋንጫ መክፈቻ ላይ ችግር አልነበረም። ከዚሁ ሌላ የሴቶችን የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ማዘጋጀት የጸጥታው ሁኔታ በሌሎች ታላላቅ ውድድሮች ወይም በወንዶች የዓለም ዋንጫ የተለመደውን ያህል ከባድ አይደለም። በሌላ በኩል ከስፖርቱ አንጻር ጥሩ አጀማመር ነው የታየው። በተለይ በመጀመሪያው ሰንበት የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በመጫወቱ የተነሣ ጉጉቱ ከፍተኛ ነበር። እንግዲህ ሁኔታው እንዴት እንደሚቀጥል የጀርመን ቡድን የማይጫወትባቸውን የሚቀጥሉትን ቀናት አይቶ መታዘቡ ግድ ነው። ለማንኛውም የሕዝቡ ፍላጎት ከ 2006 የወንዶች የዓለም ዋንጫ ጊዜ ያነሰ ነው የሚሆነው”

እርግጥ የወቅቱን ውድድር ከወንዶቹ የዓለም ዋንጫ ማነጻጸር አይቻልም። ግን በሌላ በኩል የተመልካቹ ጉጉትና ፍላጎት መጨመር በአደባባይ በሰፊው ነው የሚንጸባረቀው። በሌላ አነጋገር እስካሁን በሴቶች የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ይህን ያህል ድምቀት የታየበት ጊዜ ጨርሶ አይታወስም።

“ይሄ እርግጥም እስካሁን አልታየም። ግን በ 2006 የወንዶች የዓለም ዋንጫም ቢሆን በዚህ በጀርመን የሆነው በተመሳሳይ ውድድሮች የታየና የተጠበቀ አልነበረም። በታላላቅ ዝግጅቶች ላይ በዕለታዊ ኑራቸው ለስፖርት ብዙም ስሜት የሌላቸውን ሁሉ ማሰባበቡ የጀርመን የተለየ ባሕርይ የሆነ ነው የሚመስለው። እርግጥ የሴቶች እግር ኳስ ሁኔታ በተለይም በጀርመን ባለፉት ዓመታት በጣሙን ተሻሽሏል። በሕጻናትና ወጣት ሴቶች ዘንድ ያለው ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነው። እግር ኳስ ለመጫወት ባላቸው ፍላጎት ክለቦችን የሚቀላቀሉት ቁጥር በሰፊው ነው የጨመረው። እርግጥ ክለቦቹ አቅሙ ስለሌላቸው ሁሉንም ለመቀበል ከማይችሉበት ደረጃ ነው የደረሱት። በጥቅሉ ካለፉት ዓመታት ሲነጻጸር ፍላጎቱ እያደገ ነው የመጣው”

Dossierbild 2 Frauenfußball WM 2011
ምስል AP

ጀርመን በሶሥተኛ ዋንጫ ሕልም

በስፖርቱ ላይ ስናተኩር ጀርመን የሁለት ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ናት። ብሄራዊ ቡድኗ አሁን ደግሞ በአገሩ ዋንጫዋን ለሶሥተኛ ጊዜ ለማግኘት በተለየ ስሜት መነሳሳቱ የማይጠበቅ ነገር አይደለም። ቮልፍጋንግ ፋን ካን እንደሚያምነው የጀርመን ቡድን ቢቀር ለግማሽ ፍጻሜ የሚደርስ ነው። ግን ለዋንጫው በሚደረገው ትግል ብራዚልን የመሳሰሉ ሌሎች ተፎካካሪዎችም አሉ። እና ጉዞው ለአስተናጋጇ ለጀርመንም ቢሆን ቀላል አይመስልም።

“እንግዲህ አንዱ የጀርመን ቡድን ታላቅ ጥንካሬ ከሌሎቹ ተወዳዳሪዎች ሲነጻጸር በአካል ጽናት የተሻለ ሆኖ መገኘቱ ነው። የጀርመን ተጫዋቾች በሌሎቹ ላይ እንደሚታየው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ትንፋሽ አያጥራቸውም። በአጨዋወትም ቢሆን ጠንካሮች ናቸው። ግን ሌሎች ብራዚል፣ አሜሪካ ወይም ስዊድን አብረው ሊቋቋሙ ይችላሉ። እርግጥ የአካል ጥንካሬ ነው በመጨረሻ ወሣኝ የሚሆነው። እኔ በበኩሌ የጀርመን ቡድን ለግማሽ ፍጻሜ እንደሚደርስ አምናለሁ። ከዚያ ወዲያ ያለውን የሚወስነው ደግሞ የተጋጣሚው ማንነትና በተወሰነ ደረጃም ዕድል ነው”

ዓለም ባለፉት ዓመታት ውስጥ ካፈራቻቸው ታላላቅ ሴት ተጫዋቾች መካከል ከብዙ በጥቂቱ ከብራዚል በዓለም ድንቅ ተጫዋችነት የተመረጠችውን ማርታንና የጀርመኗን ጎል አግቢ ቢርጊት ፕሪንስን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ተጫዋቾች አሁንም በውድድሩ የሚካፈሉ ሲሆን በተለይ በጀርመን ብሄራዊ ቡድን ውስጥ አንጋፎቹን በአዳዲሶች የመተካት የትውልድ ለውጥ እየተካሄደ ነው።

“በመጀመሪያው የጀርመን ጨዋታ ባለፈው ምሽት በቡድኑ ውስጥ የትውልድ ለውጥ እየተደረገ መሆኑን ለመታዘብ የቻልን ይመስለኛል። ቢርጊት ፕሪንስ፣ ኢንካ ግሪንስና ኬርስቲን ጋረፍሬከስ ሶሥቱም ከሰላሣ ዓመት ዕድሜ በላይ ናቸው። ጊዜያቸው እያከተመ ነው። ቢርጊት ፕሪንስ ጥሩ ጨዋታ አላሳየችም። እናም ተቀይራ ወጥታለች። እንግዲህ ከዚህ የዓለም ዋንጫ በኋላ ወጣቶቹ ተጫዋቾች ለምሳሌ ኪም ኩሊክ፣ ሢሊያ ኦኮይኔ ወይም ባቢ የአዲሱ ትውልድ ገጽታዎች ይሆናሉ። የብራዚሏን ማርታን በተመለከተ ገና 25 ዓመቷ በመሆኑ ሁኔታው የተለየ ነው። ከቢርጊት ፕሪንስ ስትነጻጸር ገና ወጣት ተጫዋች ናት”

የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፕሬዚደንት ሤፕ ብላተር በወቅቱ በጀርመን የሚካሄደውን የሴቶች የዓለም ዋንጫ ውድድር ዝግጅት በሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ሲሉ ነው ያወደሱት። በእርግጥም ውድድሩ ቢቀር በዚህ በጀርመን ከመቼውም ይበልጥ የሕብረተሰብን ትኩረት መሳቡ ጎልቶ ነው የሚታየው። እና በዚሁ የሴቶች እግር ኳስ ወደ ከፍተኛ ደረጃ መሸጋገር መያዙ ይሆን? የዶቼ ቬለው ቮልፍጋንግ ፋን ካን የወንዶችን እግር ኳስ ያህል ክብደት ለማግኘት ገና ጊዜ ይወስዳል ባይ ነው።

“እርግጥ የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ውድድር ለሴቶች እግር ኳስ ትልቅ የወደፊት ዕርምጃ እንደሚሆን አያጠራጥርም። እዚህ ላይ በጣም እርግጠኛ ነኝ። ግን ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ እንደ ወንዶች እግር ኳስ ይሆናል ብሎ መጠበቁ ትክክል አይመስለኝም። እንበል በጀርመን ቡንደስሊጋ በሴቶች ግጥሚያዎች ጊዜ በአብዛኛው ባዶ የሆኑት ስታዲዮሞች ባንዴ ጢም ብለው ሊሞሉ አይችሉም። ፍላጎቱ እያደገ መሄዱ ግን የሚታይ ነው። ከዚህ ቀደም እንዳሁኑ የዓለም ዋንጫ የሴቶች እግር ኳስ በዓለም ዙሪያ በቴሌቪዥን ወደ ሁለት መቶ አገሮች የተሰራጨበት ጊዜ የለም። ግን ከዛሬ ወደ ነገ ሁሉም ነገር የተሻለና ግዙፍ ይሆናል ብሎ መጠበቅ አይቻልም”

ለማንኛውም ጀርመን በሚቀጥሉት ሶሥት ሣምንታት የሴቶች የእግር ኳስ መድረክ ሆና ትሰነብታለች። አስተናጋጇ አገር የዋንጫ ባለቤት ለመሆን ከበቃች ደግሞ ቢቀር የጀርመን የሴቶች እግር ኳስ ገናና እየሆነ ለመሄዱ አንድና ሁለት የለውም። ዛሬ በምድብ ሁለት የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን የሚያካሂዱት ጃፓን ከኒውዚላንድና ሜክሢኮ ከእንግሊዝ ናቸው።

Logo CONCACAF
ምስል APTN

ኮንካካፍ

በእግር ኳሱ ዓለም እንቆይና ሜክሢኮ ባለፈው ቅዳሜ የዘንድሮዋ የሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ እንዲሁም ካራይብ እግር ኳስ ማሕበራት ኮንፌደሬሺን የኮንካካፍ ወርቃማ ዋንጫ አሸናፊ ለመሆን በቅታለች። የሜክሢኮ ብሄራዊ ቡድን በ 23 ደቂቃዎች ውስጥ በዩ.ኤስ.አሜሪካ 2-0 ከተመራ በኋላ ውጤቱን ቀይሮ 4-2 መርታቱ ታዛቢዎችን በጣሙን ነው ያስደነቀው። ሜክሢኮ ታላቅ ተሰጥኦ ያላቸው በርካታ ወጣት ተጫዋቾች ማፍራቷ አገሪቱ በመጪው ብራዚል ውስጥ በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር ወደ ከፍተኛ ቦታ እንድትደርስ ሊያደርግ የሚችል ነው። በዚህ በአውሮፓ ዴንማርክ ውስጥ በተካሄደው ከ 21 ዓመት በታች የአውሮፓ ሻምፒዮና ደግሞ ስፓኝ በፍጻሜው ግጥሚያ ስዊትዘርላንድን 2-0 በማሽነፍ ለድል በቅታለች። በአንጋፋ ቡድኗ የአውሮፓና የዓለም ዋንጫ ባለቤት ለሆነችው ለስፓኝ ይሄው የሰንበቱ ድል በዓይነቱ ሶሥተኛው መሆኑ ነው።

Formel 1 Sebastian Vettel Großer Preis von Europa Valencia
ምስል dapd

ፎርሙላ-አንድ፣ አትሌቲክስ

ወጣቱ ጀርመናዊ የፎርሙላ-አንድ ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል ትናንት ስፓኝ-ቫሌንሢያ ላይ በተካሄደው የአውሮፓ ግራንድ-ፕሪ እሽቅድድም በአስደናቂ ሁኔታ በማሸነፍ በስምንት ውድድሮች ለስድሥተኛ ድሉ በቅቷል። የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ሁለተኛ ሲሆን ሶሥተኛ የወጣው የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር ነው። ፌትል በአጠቃላይ ነጥብ በ 186 የሚመራ ሲሆን እኩል 109 ነጥቦች ይዘው የሚከተሉት የብሪታኒያው ጄሰን ባተንና ማርክ ዌበር ናቸው።

በፊታችን ነሐሴ ወር ደቡብ ኮሪያ ዴጉ ውስጥ ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማለፍ በተካሄደ የጃሜይካ ሻምፒዮና ቬሮኒካ-ካምፕቤል-ብራውን እንደተጠበቀው በመቶና ሁለት መቶ ሜትር ሩጫ አሸናፊ ሆናለች። በወንዶች ሁለት መቶ ሜትር ስቲቭ መሊንግስ ሲያሸንፍ በአንድ መቶ ሜትር ደግሞ አሣፋ ፓውል ቀዳሚ ሆኗል። በሣምንቱ አትሌቲክስ አሳዛኙ ዜና አሜሪካዊው የእጭር ርቀት ኮከብ ታይሰን ጌይ ታፋው ላይ በገጠመው ጉዳት ከአሜሪካ ሻምፒዮና በግማሽ ፍጻሜው መሰናበቱ ነው።
በዚሁ ዓለም በጉጉት የጠበቀው በታይሰንና በዩሤይን ቦልት መካከል የሚደረግ የመቶ ሜትር ፉክክር ዕውን አይሆንም። በሌላ በኩል የእንግሊዟ የማራቶን የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ፓውላ ሬድክሊፍ ባለፈው ዓመት ልጅ ከወለደች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በፊታችን መስከረም የበርሊን ማራቶን እንደምትሳተፍ ባለፈው ሰንበት አስታውቃለች። የ 37 ዓመቷ እንግሊዛዊት በመጪው ዓመት የለንደን ኦሎምፒክ ለመሳተፍም ታስባለች።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ