1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 8 2004

ያለፈው ሰንበት የዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ የዳያመንድ-ሊግ ውድድር የተፈጸመበትና በሞዛምቢክ አስተናጋጅነት የተካሄደው አሥረኛው የመላው አፍሪቃ ጨዋታ በስኬት የተጠቃለለበትም ነበር።

https://p.dw.com/p/RmcN
ምስል dapd

የዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ የዳያመንድ-ሊግ ውድድር ባለፈው አርብ ምሽት በብራስልስ ተጠቃሏል። በአጭር ርቀት ሩጫ በተለይም በመቶና ሁለት መቶ ሜትር አይለው የታዩት አዘውትሮ እንደተለመደው ሁሉ የጃሜይካና የአሜሪካ አትሌቶች ነበሩ። በወንዶች አንድ መቶ ሜትር ጃማይካዊው ዩሤይን ቦልት በአስደናቂ 9.76 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ የአገሩ ልጆች ኔስተር ካርተርና ሌሮን ክላርክ ሁለተኛና ሶሥተኛ ሆነዋል። በሁለት መቶ ሜትርም ጃማይካዊው ዮሃን ብሌከ እጅግ ፈጣን በሆነ ጊዜ የአሜሪካ ተፎካካሪውን ዋልተር ዲክስን በሁለተኝነት አስከትሎ ሲያሸንፍ ሶሥተኛ የወጣው ሌላው ጃማይካዊ ኒክል አሽሜድ ነበር። ብሌክ በዚሁ ርቀት ወደፊት የዩሤይን ቦልት ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆን በውጤቱ አስመስክሯል።

በሴቶች አንድ መቶ ሜትር አሜሪካዊቱ ካሜሊታ ጄተር አንደኛ ስትወጣ ጃማይካዊቱ ቬሮኒካ ካምፕቤል-ብራውን ሁለተኛ፤ እንዲሁም ኬሊይ ባፕቲስት ከትሪኒዳድ ሶሥተኛ ሆናለች። በሴቶች መቶ ሜትር መሰናክል ሩጫ ደግሞ አራት የአሜሪካ አትሌቶች በቀደምትነት ተከታትለው በማሸነፍ ፍጹም ልዕልና አሳይተዋል። በአራት መቶ ሜትር ሩጫ በወንዶች የቤልጂጉ ዮናታን ቦርለ ሲያሸንፍ በዚሁ ርቀት በሴቶች ለድል የበቃችው የቦትሱዋናዋ አማንትሌ ሞንቾ ናት። በወንዶች 800 ሜትር የኬንያው የዓለም ሻምፒዮን ዴቪድ ሩዲሻ ሲያሸንፍ የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ ሙሐመድ አማን ባልተጠበቀ ሁኔታ ኬንያዊውን አስቤል ኪፕሮፕን ከኋላው በማስቀረት ሁለተኛ ሆኗል። ይህ ያልተጠበቀ ግሩም ውጤት ነው።

በሴቶች 1,500 ሜትር የአሜሪካ ተወዳዳሪ ሞርጋን ኡሴኒይ አንደኛ ስትሆን የሞሮኮዋ ማሪየም ሤልሱሊና የባህሬይኗ ማሪያም-ዩሱፍ-ጀማል ሩጫውን በሁለተኝነትና በሶሥተኝነት ፈጽመዋል። ለኢትዮጵያ ምሽቱ ቀና ሆኖ የታየው በተለይም በመካከለኛው ርቀት ሩጫ ነበር። በ 5000 ሜትር ኢማነ መርጋ ሁለት ኬንያዊ ተፎካካሪዎቹን ቶማስ ሎንጎሲዋንና ቪንሴንት ቼፕኮፕን ከኋላው አስቀርቶ ሲያሸንፍ ታሪኩ በቀለም አራተኛ ወጥቷል። በአሥር ሺህ ሜትር ደግሞ ድሉ በማያሻማ ሁኔታ የቀነኒሣ በቀለ ነበር። ኬንያዊው ሉካስ ሮቲች ሁለተኛ ሲወጣ ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመው የአሜሪካው ተወዳዳሪ ጋለን ሩፕ ነበር። ቀነኒሣ አሥር ሺህ ሜትሩን በ 26 ደቂቃ ከ 43.16 ሤኮንድ ጊዜ ሲያቋርጥ ይህ በዘንድሮው የውድድር ወቅት ፈጣኑ መሆኑ ነው።

ቀነኒሣ በቀለ በብራስልሱ ምሽት ባሣየው ሩጫ ታፋው ላይ ደርሶበት ከነበረው የአካል ጉዳት በሚገባ ያገገመ ይመስላል። ድንቁ አትሌት በቅርቡ የዴጉ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በጉዳቱ የተነሣ ከበርሊን ሁለት ዓመታት በኋላ የአሥር ሺህ ሜትር ክብሩን ለማስጠበቅ ሳይችል መቅረቱ አይዘነጋም። ሩጫው ገና አሥር ዙሮች ቀርተውት ሳለ ውድድሩን አቋርጦ መውጣት ግድ ነበር የሆነበት። ለማንኛውም ወደ አትሌቲኩ መድረክ በስኬት መመለሱ እጅግ የሚያስደስት ነው። በተረፈ በሴቶች የሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ሩጫ ሩሢያዊቱ ዩሊያ ዛሩድኔቫ ስታሸንፍ ከኢትዮጵያ ሶፊያ አሰፋ አራተኛ፤ እንዲሁም ሕይወት አያሌውና መቅደስ በቀለ ስድሥተኛና ሰባተኛ ወጥተዋል።

በእንግሊዝ ትናንት በተካሄደው ግሬት-ኖርዝ-ራን ሩጫ ደግሞ በሴቶችና በወንዶችም ኬንያውያን ባለድል ሆነዋል። በወንዶች ያሽነፈው ማርቲን ማታቲ ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ በ 2005 ዓ.ም. አስመዝግቦት የነበረውን የ 59 ደቂቃ ከ 5 ሤኮንፍ ክብረ-ወሰን በዘጠኝ ደቂቃዎች ሲያሻሽል በሴቶችም ሉሢይ ካቡ በግሩም ጊዜ ለድል በቅታለች።

የመላው አፍሪቃ የስፖርት ውድድር

ሞዛምቢክ ውስጥ ለሁለት ሣምንታት የተካሄደው የመላው አፍሪቃ ሁል-ገብ የስፖርት ሻምፒዮና ትናንት ከዋና ከተማይቱ ከማፑቶ ወጣ ብሎ በሚገኘው የዚምፔቶ ብሄራዊ ስታዲዮም በደመቀ ስነ ስርዓት ተፈጽሟል። የሞዛምቢኩ ፕሬዚደንት አርማንዶ ጉዌቡዛ ውድድሩ በይፋ መጠቃለሉን የገለጹት የተሳታፊዎቹ 51 ሃገራት ልዑካን 42 ሺህ ተመልካቾችን የሚይዘውን ስታዲዮም ለመጨረሻ ጊዜ በሰልፍ ካደመቁ በኋላ ነበር። ከአራት ዓመታት በኋላ መጪውን የመላ አፍሪቃ ውድድር የምታስተናግደው የኮንጎ ብራዛቪል የስፖርት ሚኒስትር ደግሞ በስፍራው በመገኘት የአፍሪቃን ከፍተኛ የስፖርት ሸንጎ ሰንደቅ ዓላማ ተረክበዋል።
ሞዛምቢክ ዝግጅቱን በገንዘብ ችግር በተወችው በዛምቢያ ፈንታ መተካቷ ሲታወስ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲሳካ ማብቃቷ የሚያኮራት ነው። እርግጥ ውድድሩ በሂደቱ የቅንጅት ጉድለትና የተመልካች እጥረት የጎላበት ሆኖ መሰንበቱ መጠቀስ ይኖርበታል። ዝግጅቱን ተወት አድርገን በስፖርቱ ላይ ስናተኩር ውድድሩን በታላቅ ስኬትና የበላይነት የፈጸመችው ደቡብ አፍሪቃ ናት። ደቡብ አፍሪቃ በ 61 የወርቅ፣ 55 የብርና 40 የናስ ሜዳሊያዎች፤ በጠቅላላው በ 156 ሜዳሊያዎች ቀደምቷ ስትሆን ናይጄሪያ በ 98 ሁለተኛ እንዲሁም ግብጽ በ 66 ሶሥተኛ ሆነዋል።

በቡድን ስፖርት ጋና በወንዶች እግር ኳስ ደቡብ አፍሪቃን በፍጹም ቅጣት ምቶች በለየለት ፍጻሜ ግጥሚያ 5-3 ለማሸነፍ በቅታለች። ደቡብ አፍሪቃ መደበኛው ጊዜ ሊያበቃ አራት ደቂቃዎች ቀርተው ሳለ 1-0 ስትመራ ያሸነፈች መስሎ ታይቶ ነበር። ሆኖም ጋና ውጤቱን በማስተካከል ጨዋታው እንዲራዘም ለማድረግ ችላለች። ጋና በመላው አፍሪቃ ውድድር ለሴቶች ፍጻሜም ስትደርስ ድሏን ድርብ ማድረጉ ግን አልተሳካላትም። በካሜሩን 1-0 ተሸንፋለች። በቅርጫት ኳስ ደግሞ አስተናጋጇ ሞዛምቢክ ከናይጄሪያ ጋር ባካሄደችው ጠንካራ የፍጻሜ ግጥሚያ 62-57 ስትሸነፍ የመጨረሻው ወርቅ ሜዳሊያ የመሰብሰብ ዕድል ለጥቂት አምልጧታል። ግብጽ በአንጻሩ በቴኒስና በዕጅ ኳስ አሸናፊ ሆናለች። በሴቶች የዕጅ ኳስ ፍጻሜ ደግሞ አንጎላ ኮንጎ ብራዛቪልን ለማሸነፍ በቅታለች።

Flash Galerie Bundesliga Schalke Bayern
ምስል dapd

እግር ኳስ፤ ቡንደስሊጋ/አውሮፓ

በከፊል ገና በጅምሩ ላይ በሚገኘው በአውሮፓ ክለቦች ብሄራዊ ሻምፒዮና ባየርን ሚዩኒክና ማንቼስተር ዩናይትድ በድል ጉዟቸው በመቀጠል አመራራቸውን ሲያጠብቁ በኢጣሊያ ደግሞ ናፖሊ ኤዲንሶን ካቫኒ ባስቆጠራቸው ሶሥት ጎሎች ያለፈውን ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ኤ.ሢ.ሚላንን በመሸኘት የሤሪያ-አ ቁንጮ ሆኗል። በስፓኝ ሬያል ማድሪድ በሌቫንቴ ሲሸነፍ ተፎካካሪው ባርሤሎና በአንጻሩ ኦሣሱናን 8-0 በመቅጣት አሰናብቷል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ እንጀምርና ባየርን ሚዩኒክ ባለፈው ሰንበት በፍጹም የበላይነት ሻልከን 2-0 ሲያሸንፍ ዘንድሮ በማንም የማይገታ እየመሰለ ነው። ቨርደር ብሬመንና መንሸንግላድባህ ደግሞ ከስድሥት ግጥሚያዎች በኋላ ሁለት ነጥቦች ዝቅ ብለው ይከተላሉ። ያለፈው ሻምፒዮን ዶርትሙንድ በአንጻሩ በመጨረሻዎቹ አምሥት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ጎሎችን በመልቀቅ በሃኖቨር 1-2 ተሸንፏል። በመሆኑም እንደ ቡድኑ ተከላካይ እንደ ኔቨን ሱቦቲች ሁሉ ተጫዋቾቹ መቆጨታቸው አልቀረም።

“ይህ ዕድለ-ቢስነት ነው። ከ 85 ደቂቃዎች በላይ እኛ ነበርን የተሻልነው ቡድን። በዚሁ ጊዜ ውስጥ ብዙ ስናጠቃ ተጋጣሚያችን ወደ በራችን እንዲጠጋ ብዙም ዕድል አልሰጠነውም ነበር። ግን በመጨረሻ በሁለት የቸልተኝነት ስህተቶች ጨዋታው ከዕጃችን እንዲወጣ አድርገናል። አዎ፤ እግር ኳስ እንዲህ ነው። በመጨረሻዎቹ አምሥት ደቂቃዎች የተፈጸሙ ሁለት ስህተቶች ለሽንፈት አብቅተውናል”

ዶርትሙንድ በዚሁ ሽንፈት ወደ 11ኛው ቦታ ሲያቆለቁል መልሶ ቀና ለማለት በመጪዎቹ ሣምንታት ብርቱ ትግል የሚጠብቀው ነው የሚመስለው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰንበቱ ታላላቆቹ ሁለት ክለቦች እርስበርስ የተገናኙበት ነበር። ማንቼስተር ዩናይትድ በዚሁ በዘንድሮው ውድድር ወቅት አምሥተኛ ግጥሚያ በኦልድ-ትሬፎርድ ስታዲየሙ ቼልሢይን 3-1 በማሸነፍ ሻምፒዮንነቱን ለመጠበቅ ቆርጦ የተነሣ መሆኑን አስመስክሯል። ጎሎቹን በመጀመሪያው አጋማሽ ናኒና ዌይን ሩኒይ ሲያስገቡ የቼልሢይን ብችኛ ጎል ያስቆጠረው ደግሞ የስፓኙ ፌርናንዶ ቶሬስ ነበር። እስካሁን በአምሥት ግጥሚያዎቹ በሙሉ ያሸነፈው ማንቼስተር ዩናይትድ የከተማ ተፎካካሪውን ማንቼስተር ሢቲይን በሁለት ነጥቦች ብልጫ አስከትሎ የሚመራ ሲሆን ቼልሢይ አምሥት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሶሥተኛ ነው።

የስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ውድድር ገና በሶሥተኛ ሣምንቱ ላይ ሲሆን የመሃል ተጫዋቹ ሣሚ ኬዲራ ተቀጥቶ ከሜዳ የወጣበት ሬያል ማድሪድ በእር ሰው በሌቫንቴ 1-0 መሸነፉ ግድ ሆኖበታል። ባርሤሎና በአንጻሩ ኦሣሱናን 8-0 በመቅጣት ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ሊል ችሏል። በወቅቱ ቫሌንሢያና ሬያል-ቤቲስ በዘጠኝ ነጥቦች ተከታትለው ሊጋውን የሚመሩ ሲሆን ባርሣ ሶሥተኛ ነው፤ ሬያል ደግሞ ወደ አምሥተኛው ቦታ አቆልቁሏል። በተረፈ በኢጣሊያ ሊጋ ናፖሊ፣ በፈረንሣይ ኦላምፒክ ሊዮን፣ በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን ኤንሼዴ፤ እንዲሁም በፖርቱጋል ፖርቶ በወቅቱ የየሊጋቸው መሪዎች ናቸው።

Sport US Open Tennis Novak Djokovic Flash-Galerie
ምስል dapd

ቴኒስ/የቅርጫት ኳስ/ቡጢ

ባለፈው ሰንበት በተካሄዱ የዓለም የቴኒስ ዴቪስ-ካፕ የቡድን ግጥሚያዎች ከብዙ በጥቂቱ ሰርቢያ በአርጄንቲና 2-3 ስትረታ ስፓኝ ፈረንሣይን 4-1፤ ሩሢያ ብራዚልን 3-2፤ ክሮኤሺያ ደቡብ አፍሪቃን 4-1 አሸንፈዋል፤ አውስትራሊያና ስዊስ ደግሞ 2-2 ተለያይተዋል። ሌላው ሊቱዋኒያ ውስጥ ሲካሄድ የቆየው የቅርጫት ኳስ የአውሮፓ ሻምፒዮና ደግሞ ትናንት ባለፈው የውድድር ወቅት አሸናፊ በስፓኝ ቀጣይ ድል ተጠናቋል። ስፓኝ እንደገና ለዚህ ክብር የበቃችው ፈረንሣይን 98-85 በማሸነፍ ነው። ሩሢያ የውድድሩ ሶሥተኛ ስትሆን አራተኛዋ ደግሞ ማንም ያልጠበቃት ማቄዶኒያ ናት። የሚቀጥለው የአውሮፓ ሻምፒዮና ከሁለት ዓመታት በኋላ ስሎቫኪያ ውስጥ ይካሄዳል።

በቡጢ ለማጠቃለል አሜሪካዊው ፍሎይድ ሜይዌዘር ጁኒየር ላስ ቬጋስ ላይ ከአገሩ ልጅ ከቪክቶር ኦርቲስ ጋር ባካሄደው ግጥሚያ በዝረራ በማሸነፍ አዲሱ የዓለም ቡጡ ካውንስል የዓለም ሻምፒዮን ሊባል በቅቷል። ሜይዌዘር ያሸነፈው ተጋጣሚውን አከራካሪ በሆነ ሁኔታ በአራተኛው ዙር ከጣለ በኋላ ነው። ሻምፒዮኑ ከ 16 ወራት ቆይታ በኋላ ወደ ውድድሩ መድረክ ሲመለስ እስካሁን በ 42 ግጥሚያዎች አንዴም አልተሸነፈም።

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ