1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 27 2004

በዓለም ላይ ታላላቅ ከሚባሉት የረጅም ርቀት ሩጫ ውድድሮች አንዱ የሆነው የኒውዮርክ ከተማ ማራቶን ትናንት በኬንያና በኢትዮጵያ ድል ተፈጽሟል።

https://p.dw.com/p/RvEC
አቤል ኪሩዊምስል dapd

በወንዶች ሁለቱ ኬንያውያን ጄፍሪይ ሙታይና ኤማኑዌል ሙታይ በቀምትነት ተከታትለው ሲያሸንፉ ጸጋዬ ከበደና ገ/እግኢአብሄር ገ/ማርያም ደግሞ ሶሥተኛና አራተኛ ሆነዋል። እዝቂያስ ሲሣይም ሩጫውን በዘጠነኝ’ነት ለመፈጸም ችሏል። በውድድሩ ባለፈው መስከረም ወር ከሁለት ሰዓት አራት ደቂቃ በታች የነበረውን የሃይሌ ገ/ሥላሴን የዓለም ክብረ-ወሰን ያሻሻለው ኬንያዊ ፓትሪክ ማካዉና የሁለት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮን አቤል ኪሩዊ በሩጫው አልተሳተፉም። ቢሆንም ጄፍሪይ ማታይ ትናንት ያሽነፈው ለኒውዮርክ ማራቶን ፈጣን በሆነ ሁለት ሰዓት ከአምሥት ደቂቃ ከስድሥት ሤኮንድ ጊዜ ነበር።
ጠንካሮቹ የኬንያ ማራቶን ሯጮች ለለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፎ በፌደሬሽናቸው ለመመረጥ በመካከላቸው ብርቱ ፉክክር እንደሚጠብቃቸው ከወዲሁ ጎልቶ እየታየ ነው። በሴቶች ደግሞ የኒውዮርኩ ማራቶን ድል የኢትዮጵያ ሆኗል። በዚሁ ሩጫ ባለፈው መጋቢት ወር የሮማን ማራቶን ለተከታታይ ሶሥተኛ ጊዜ ያሽነፈችው ፍሬሕይወት ዳዶ ቀዳሚ ስትሆን በዚያው በኒውዮርክ የምትኖረው ብዙነሽ ደባ ደግሞ ሁለተኛ ወጥታለች። ሩጫውን እንዳለፈው ዓመት ሁሉ በሶሥተኝነት የፈጸመችው ኬንያዊቱ የለንደን ማራቶን ሻምፒዮን ሜሪይ ካይታኒይ ነበረች።

ዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ደግሞ የዓመቱን ድንቅ አትሌቶች ለመምረጥ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን ባለፈው አርብ የዕጩዎች ዝርዝሩን ይፋ አድርጓል። በወንዶች የጃማይካ የአጭር ርቀት ሩጫ ከዋክብት ዩሤይን ቦልትና ዮሃን ብሌክ እንዲሁም የኬንያው የ 800 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ወጣቱ ዴቪድ ሩዲሻ ሲታጩ በሴቶች ለምርጫ የተሰየሙት ደግሞ የኒውዚላንዷ ቫሌሪ አዳምስ፣ የኬንያዋ ቪቪያን ቼሩዮትና የአውስትራሊያዋ ሤሊይ ፒርሰን ናቸው። የዓመቱ ስፖርተኞች የሚመረጡት በሣምንቱ መጨረሻ እንደተለመደው ሞናኮ ላይ በሚካሄድ የዓለም አትሌቲክስ ምሽት ላይ ነው።
ዓለምአቀፉን የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ካነሣን ተቋሙ ደምቡን በጣሱ በሁለት ስፖርተኞች ላይ እገዳ መጣሉን በሣምንቱ መገባደጃ ላይ አስታውቋል። እነዚሁ በደቡብ ኮሪያው የዴጉ የዓለም ሻምፒዮና ወቅት የተከለከለ አካል አጎልባች መድሃኒት መውሰዳቸው የተረጋገጠባቸው አትሌቶች የፖርቱጋሏ ሣራ ሞሪየራና የደቡብ ኮሪያዋ ሊም-ሄ-ናም ሲሆኑ በጊዜያዊነት የታገዱት ለሁለት ዓመት ጊዜ ነው። ባለፈው ነሐሴ ወር የዴጉ ሻምፒዮና ወቅት በጠቅላላው በ 468 አትሌቶች ላይ የሽንት ምርመራ ተደርጎ ነበር።

Fußball Bundesliga Bremen Köln
ምስል picture-alliance/dpa

እግር ኳስ፤ አውሮፓ/ቡንደስሊጋ

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሰንበቱ በተለይም የክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሆኖ ሲያልፍ ማንቼስተር ሢቲይና ባየርን ሙንሺንም በግንባር ቀደምነት ወደፊት መገስገሳቸውን ቀጥለዋል። በስፓኝ ላ-ሊጋ የትናንቱ ዕለት በተለይም ለኦሣሱና አስከፊ ሆኖ ነው ያለፈው። ቡድኑ በሬያል ማድሪድ 7-1 ሲቀጣ ክሪስቲያኖ ሮናልዶም በአንድ ጨዋታ ለአራተኛ ጊዜ ሶሥት ጎሎች በማስቆጠር የሬያል የድል ዋስትና መሆኑን እንደገና አስመስክሯል። የተቀሩትን ጎሎች ያስቆጠሩት አንሄል-ዲ-ማሪያ፣ ጎንዛሎ ሂጉዌይንና ፔፔ ነበሩ። ሬያል ማድሪድ በትናንትናው አስደናቂ ድሎ ሊጋውን በሶሥት ነጥቦች ብልጫ ለመምራት በቅቷል። ከ 11 ግጥሚያዎች በኋላ 28 ነጥቦች አሉት።

ባርሤሎና ደግሞ ከቢልባዎ 2-2 ሲለያይ በ 25 ነጥቦች ሁለተኛ ነው። ለባርሣ ሁለቱን ጎሎች ሤስክ ፋብሬጋስና ሊዮኔል ሜሢ ሲያስቆጥሩ ክለቡ እስካሁን አንዴም ሽንፈት ሳይደርስበት ሊቀጥል በቅቷል። ቫሌንሢያ ሌቫንቴን 2-0 ረትቶ በ 24 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን በውድድሩ መጀመሪያ ሣምንታት በቁንጮነት ጉድ አሰኝቶ የነበረው ሌቫንቴ በዚህ ሽንፈቱ በአንዲት ነጥብ ተበልጦ ወደ አራተኛው ቦታ ማቆልቆሉ ግድ ነው የሆነበት። በተቀረ ጌታፌ ከአትሌቲኮ ማድሪድ 3-2፤ ኤስፓኞል ከቪላርሬያል 0-0፤ ሣራጎሣ ከጊዮን 2-2፤ እንዲሁም ማዮርካ ከሤቪያ ባዶ-ለባዶ ተለያይተዋል። በጎል አግቢነት ሊጋውን የሚመራው 14 ያስቆጠረው ሊዮኔል ሜሢ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አምሥቱም ቀደምት ክለቦች ግጥሚያዎቻቸውን ሲያሸንፉ ከአሰላለፍ አንጻር ብዙም የተለወጠ ነገር የለም። ማንቼስተር ሢቲይ ኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስን 3-2 ሲያሸንፍ በአምሥት ነጥቦች ልዩነት አመራሩን እንደያዘ ቀጥሏል። ክለቡ ከ 11 ግጥሚያዎች በኋላ በጠቅላላው 31 ነጥቦች ሲኖሩት ለሰንበቱ ድል ዋስትናው የነበረው በተለይም የቦስናው ኮከብ ኤዲን ጄኮ ነው። ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን ማንቼስተር ዩናይትድም ሰንደርላንድን 1-0 በመርታት በ 26 ነጥቦች ሁለተኛ ሲሆን ኒውካስል ዩናይትድም ኤቨርተንን 2-1 በመርታት አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ በሶሥተኝነቱ ቀጥሏል። ቼልሢይ ብላክበርን ሮቨርስን 1-0 አሸንፎ አራተኛ ሲሆን አምሥተኛው ቶተንሃም ሆትስፐር ነው። በጎል አግቢነት ሆላንዳዊው የአርሰናል አጥቂ ሮቢን-ፋን-ፐርዚ 11 አስቆጥሮ ይመራል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ባየርን ሙንሺን ትናንት የመጨረሻውን አውግስቡርግን 2-1 በመርታት አመራሩን ወደ አምሥት ነጥቦች ሊያሰፋ በቅቷል። ይሁንና ተከላካዩ ዳኒየል-ቫን-ቡይተን እንዳረጋገጠው ድሉ የተገኘው በቀላሉ አልነበረም።

“የመጀመሪያው አጋማሽ ለኛ ጥሩ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ተጋጣሚያችን እንዲጠነክር ነው ያደረግነው። በሚገባ አልታገልንም፤ አንዳንድ ስህተቶችንም ሰርተናል። እናም ለድል ለመብቃት በሁለተኛው አጋማሽ ሂደት ውስጥ በትልቅ ትክረት መጫወት ነበረብን”
ያም ሆነ ይህ ባየርን ከ 12 ግጥሚያዎች በኋላ አሁን ሊጋውን በ 28 ነጥቦች ይመራል። ሻልከ ከሃኖቨር በ 2-2 እኩል ለእኩል ውጤት በመወሰኑ ከሁለተኛው ወደ አምሥተኛው ቦታ ሲያቆለቁል ቮልፍስቡርግን በጎል ፌስታ 5-1 አከናንቦ የሸኘው ዶርትሙንድ በቦታው ተተክቷል። ብሬመንና መንሸንግላድባህም ከዶርትሙንድ በነጥብ እኩል ሲሆኑ ሶሥተኛና አራተኛ ሆነው ይከተላሉ። ግላላድባህ በርሊንን 2-1 ሲረታ ብሬመንም ኮሎኝን በደመቀ ጨዋታ 3-2 በማሽነፍ ነበር ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ሊል የቻለው። ቡድኑ ከእረፍት በፊት ሁለት-ለባዶ ከተመራ በኋላ ሶሥቱንም ጎሎች በማስቆጠር ለድል ያበቃው ድንቅ ተጫዋቹ የፔሩው ተወላጅ ክላውዲዮ ፒሣሮ ነበር።

“በውጤቱ በጣም ደስተኛ ነኝ። ጨዋታው በአጀማመሩ ለኛ ጥሩ አልነበረም። በዚሁ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ባለመጫወታችንም ሁለት ጎሎች ይገቡብናል። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ጥሩ በመጫወት ጎሎች ስናስቆጥር በመጨረሻም ለአሸናፊነት በቅተናል”

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር መጪው ቅዳሜ ደግሞ ቀደምቱ አራት ክለቦች እርስበርስ በቀጥታ የሚፈታተሹበት በመሆኑ በተመልካቾች ዘንድ በተለየ ጉጉት ነው የሚጠበቀው። አንደኛው ባየርን ሙንሺን ዶርትሙንድን የሚያስተናግድ ሲሆን ግላድባህ ደግሞ የብሬመን ተጋጣሚ ነው። በጎል አግቢነት የባየርኑ ማሪዮ ጎሜስ በ 13 የሚመራ ሲሆን የብሬመኑ ክላውዲዮ ፒሣሮ በ 11 በቅርብ ይከተለዋል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኡዲኔዘና ላሢዮ ጁቬንቱስን በሁለት ነጥብ አልፈው አልፈው በእኩልነት የሊጋውን አመራር ሲይዙ በፈረንሣይ ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን በሶሥት ነጥቦች ልዩነት ቀደምት ሆኖ እንደቀጠለ ነው። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶና ቤንፊካ እኩል 24 ነጥቦች ይዘው መፎካከራቸውን ሲቀጥሉ በኔዘርላንድ አልክማር በስድሥት ነጥቦች ልዩነት እንደመራ ነው። በግሪክ ደግሞ ፓናቴናኢኮስ አቴን አመራሩን ከኦሎምፒያኮስ ፒሬውስ መንጠቁ ተሳክቶለታል።

Petra Kvitova Wimbledon Siegerin
ምስል dapd

ቴኒስ

ቼክ ሬፑብሊክ ትናንት ሞስኮ ላይ በተካሄደ የፌደሬሺን-ካፕ ፍጻሜ ግጥሚያ ሩሢያን በአጠቃላይ 3-2 ውጤት በመርታት ባለድል ሆናለች። ቼክ ሬፑብሊክ ከቀድሞዋ ቼኮዝሎቫኪያ ዘመን ከ 1988 ዓ.ም. ወዲህ በዚህ ውድድር አሸናፊ ስትሆን ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። አገሪቱን ለትናንቱ ድል ያበቁት ሉሢ ራዴንካ፣ ክቬታ ፔሽከና የወቅቱ የቼክ ቀደምት ተጫዋች ፔትራ ክቪቶቫ ናቸው። ከዚሁ ሌላ በትናንቱ ዕለት ስፓኝ ውስጥ በተካሄደው የቫሌንሢያ-ኦፕን ፍጻሜ ግጥሚያ የአገሪቱ ተወላጅ ማርሤል ግራኖለርስ የአርጄንቲናውን ሁዋን ሞናኮን በማሸነፍ በዚህ ዓመት ሁለተኛ ለሆነው ድሉ በቅቷል።
በነገራችን ላይ ሁዋን ሰንበቱን በደረሰበት የትከሻ ጉዳት የተነሣ ከፓሪስ ማስተርስ ውድድር ወደ ኋላ ማሸግሸጉ ግድ ሆኖበታል። በስዊትዘርላንድ-ባዝል ደግሞ ሮጀር ፌደረር ጃፓናዊ ተጋጣሚውን ካኢ ኒሺኮሪን በመርታት በስድሥት ዓመታት ውስጥ አምሥተኛ ድሉን ለማስመዝገብ ችሏል። ፌደረር በአገሩ የአዳራሽ ውስጥ ፍጻሜ ግጥሚያ ያሽነፈው በለየለት 6-1, 6-3 ውጤት ነው።

ወደ እግር ኳሱ ስፖርት መለስ እንበልና በያዝነው ሣምንት መጨረሻና በተከታዩ አጋማሽ ላይ በርከት ያሉ ዓለምአቀፍ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ከነዚሁ መካከል በጥቂቱ ለመጥቀስ ኢጣሊያ ከመጪው የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር አዘጋጅ ከፖላንድና ከኡሩጉዋይ ትጋጠማለች። ኔዘርላንድ ደግሞ ከስዊስና ከጀርመን የምትገናኝ ሲሆን በተለይም ሃምቡርግ ላይ በጀርመን አስተናጋጀት የሚካሄደው ግጥሚያ በትልቅ ጉጉት የሚጠበቅ ነው። ሁለቱ አገሮች በእግር ኳስ ብርቱ ተፎካካሪዎች ሲሆኑ በአውሮፓው ዋንጫ ማጣሪያ ሂደት አንዴም አለመሸነፋቸው ተደምሮ ግጥሚያውን ይበልጥ የክብር ጉዳይ ያደርገዋል። ጀርመን ከኔዘርላንድ ቀደም ሲልም የሌላዋ የአወሮፓ ዋንጫ አዘጋጅ የኡክራኒያ እንግዳ ናት።

ጀርመንን ካነሣን ጀርመናዊው የዩ.ኤስ.አሜሪካ ብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ ዩርገን ክሊንስማንም አቅም ፍተሻ ለማድረግ የተነሣው በዚሁ በአውሮፓ ነው። የአሜሪካ ቡድን በፊታችን አርብ ከፈረንሣይ ከዚያም አራት ቀናት ዘግየት ብሎ ከስሎቬኒያ ጋር ይጋጠማል። የክሊንስማን ዓላማ ለ 2014 የብራዚል የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሚቀጥለው ዓመት ለሚጀመረው ማጣሪያ ቡድኑን ማዘጋጀትና ብቁ ማድረግ ነው። ለዚህም በአውሮፓ ጠቃሚ ልምድ መቅሰም እንደሚችል አንድና ሁለት የለውም። ፈረንሣይ በበኩሏ ከአሜሪካ ሌላ ከቤልጂግም ትጋጠማለች።
ብራዚል ደግሞ ለወዳጅነቱ ግጥሚያ ወደ አፍሪቃና ወደ ፋርስ ባሕረ-ሰላጤ አካባቢ መዝለቁን ነው የመረጠችው። ብራዚል ከፊታችን ሐሙስ ጀምሮ ከጋቦን፣ ከግብጽና ከካታር ትጋጠማለች። ከፌደሬሺኑ ለመረዳት እንደተቻለው የአንዴው የዓለም ድንቅ ተጫዋች ካካና የሬያል ማድሪድ የክለብ ባልደረባው ማርቼሎ በአካል ጉዳት የተነሣ ቡድኑ በሚቀጥሉት ዘጠኝ ቀናት በሚያካሂዳቸው ግጥሚያዎች አይሳተፉም።

ከወዳጅነት ግጥሚያዎች ባሻገር ብራዚል ውስጥ በ 2014 ዓ.ም. ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በደቡብ አሜሪካ የሚደረገው ማጣሪያ ደግሞ በፊታችን አርብና ቅዳሜ በአራት ግጥሚያዎች ይጀመራል። እነዚሁም አርጄንቲና ከቺሌ፤ የደቡብ አሜሪካው ሻምፒዮን ኡሩጉዋይ ከቦሊቪያ፤ ቬኔዙዌላ ከኤኩዋዶርና ፓራጉዋይ ከፔሩ ይሆናሉ። በደቡብ አሜሪካው ማጣሪያ ምድብ ውስጥ የሚፎካከሩት ብራዚል በአስተናጋጅነት በቀጥታ በማለፏ ዘጠኝ ሃገራት ብቻ ናቸው።
በመጨረሻም ዘንድሮ በማግሬብ አገሮች መካከል በሚለይለት የአፍሪቃ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ትናንት በመጀመሪያው ግጥሚያ የሞሮኮው ዋክ ካዛብላንካና የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ባዶ-ላባዶ ተለያይተዋል። የመልሱ ግጥሚያ ቱኒዚያ ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን ኤስፔራንስ በደጋፊዎቹ ፊት መጫወቱ ምናልባት ሊጠቅመው የሚችል ነው።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ