1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ቀዉስ፤ የኢጋድ ዉሳኔና እንድምታዉ

ሐሙስ፣ ግንቦት 13 2001

ሼክ ሸሪፍ ያላቸዉ በጣም ትንሽ ጊዜ ነዉ።ብዙ ጊዜ አልተረፋቸዉም

https://p.dw.com/p/HukT
ኢጋድ

21 05 09

የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (IGAD ) የሚንስትሮች ምክር ቤት የሶማሊያን ደፈጣ ተዋጊዎች በሐገሪቱ ሽግግር መንግሥት ላይ የሚፈፅሙትን ጥቃት አዉግዘዋል።ትናንት አዲስ አበባ ዉስጥ ተሰብስበዉ የነበሩት የስድስቱ ሐገራት ሚንስትሮች በሶማሊያና የሶማሊያ ሸማቂዎችን ታስታጥቃላች ባሏት ኤርትራ ላይ አለም አቀፍ ማዕቀብ እንዲጣልም ጠይቀዋል።ኤርትራ የኢጋድን ዉሳኔ ዛሬ አጣጥላ ነቅፋዋለች።የሶማሊያንና የአካባቢዉ ሐገራትን አቋም በተመለከተ Interenatinal Crisis Group በተሰኘዉ የፖለቲካ ጥናት ተቋም የሶማሊያ ጉዳዩ ልዩ ባለሙያ ረሺድ አብዲን ነጋሽ መሐመድ አነጋግሯቸዉ የሚከተለዉን ዘገባ አጠናቅሯል።

የአለም አቀፍ ድጋፍ አለዉ የሚባለዉ የሼኽ ሸሪፍ ሼኽ አሕመድ መንግሥት በሃያል ጠላቶቹ ተፈጥርቆ ሲያጣጥር እዉቅና የሰጠዉ-ትልቅ አለም-ጣሩን ከማዳመጥ ባለፍ-እስካሁን ያለዉ እንጂ ያደረገዉ የለም።የአካባቢዉ ሐገራትም ረሺድ አብዲ እንደሚሉት የሶማሊያን እቅልቂት ፍጅት ለማስቆም የተከሩት የለም።የግጭቶችን ምክንያትና መፍትሔ የሚያጠናዉ አለም አቀፍ ጥናት ተቋም-ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የሶማሊያ ጉዳይ አዋቂ ረሺድ አብዲ እንደሚሉት የአካባቢዉ ሐገራት ለመፍትሔ በርግጥ ዘግተዋል።በትናንቱ ዉሳኔያቸዉ ግን ቢያንስ አንድ ትልቅ ጉዳይ አንሰተዋል።ጦር መሳሪያ።
«እንደሚመስለኝ ይሕ (ዉሳኔዉ) ወደ ሶማሊያ የሚገባዉ የጦር መሳሪያ ትልቅ ችግር እንደሆነ አካባቢዉ መረዳቱን ለመጀመሪያ ጊዜ በግልፅ ያመለከተ ነዉ።ይሕ ወደ ሶማሊያ በሚገባዉ ጦር መሳሪያ ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ወደ ማድረጉ የሚያመራ ከሆነ በጣም ጥሩ ነዉ።ያም ሆኖ አንዳዱ ለምሳሌ የበረራ እገዳ እንዲጣል የተጠየቀዉን ገቢራዊ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነዉ።ምክንያቱም የበረራ እገዳዉን ማን ያስከብራል የሚል ጥያቄ ያስከትላልና።»

የኢጋድ ሚንስትሮች የሶማሊያን ደፈጣ ተዋጊዎች ታስታጥቃለች ባሏት ኤርትራ ላይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጦር መሳሪያ እገዳ እንዲጥ ጠይቀዋል።ረሺድ አብዲ ጥያቄዉ ሰሚ ማግኘቱን ይጠረጠራሉ።ጥያቄዉ ግን በኤርትራ አንፃር አንድ መልዕክት ያስተላልፋል።
«እንደሚመስለኝ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ በኤርትራ አንፃር የያዘዉን አቋም እያጠናከረ ሳይመጣ አልቀረም።ይሁንና በኤርትራ ላይ የምጣኔ ሐብት ወይም ሌላ ጠንካራ ማዕቀብ ከሚጥልበት ደረጃ ደርሰናል ብዬ አላስብም።እዚያ ደረጃ ገና የደረስን አይመስለኝም።»

የኤርትራ ፕሬዝዳት ኢሳያስ አፈወርቂን የኢጋድን መግለጫ-ዉሳኔ «የሲ አይ ኤ ሴራ» ብለዉታል። ተሰብሳቢዎቹን ደግሞ «ቀጣፊዎች»

የኢጋድ ሚንስትሮች ከመሰብሰባቸዉ በፊት የአዉሮጳ ሕብረት አቻዎቻቸዉ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥትን እንደሚደግፉ አስታዉቀዋል።ኢጣሊያ ትናንት-ሊቢያ ደግሞ ዛሬ ተፋላሚዎችን አናደራድራለን-ብለዋል።ላንዲት ሶማሊያ አንድ ችግር-ብዙ ስፍራ ብዙ መትሔ እየተጠቆመ ነዉ።የሶማሊያ ችግርም-እሱዉ ነዉ-ይላሉ ረሺድ አብዲ።

«ከሶማሊያ ግጭት ድቀቶች አንዱ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ የጋራ አቋም አለመያዙ ነዉ።ሁሉም በየሚመስለዉ መንገድ ሥልታዊ ጥቁም የሚያስከብርበትን እርምጃ ነዉ-የሚወስደዉ።እንደ ኢትዮጵያና ኤርትራ የመሳሰሉት የአካባቢዉ ሐገራት ብቻ ሳይሆኑ ሩቅ ያሉት አዉሮጳ እና ዩናይትድ ስቴትስ ሳይቀሩ የሶማሊያን ግጭት ለየራሳቸዉ ጥቅም ሊያዉሉት ነዉ-የሚሹት።»

Somalia Präsident Sheik Sharif Achmed
ብዙ ጊዜ አልተረፋቸዉምምስል ap

ሆነና በአስራ-ዘጠኝ አመት ላአስራ-አምስተኛ ጊዜ የተሰየመዉ የሽግግር መንግሥቱ ይበረክት ይሆን? ረሺድ አብዲ-አይ-አዎም ነዉ-መልሳቸዉ።

«እንደዚሕ አይነቶቹን እርምጃዎች ባዘገየናቸዉ ቁጥር-ሁኔታዎች እየተበላሹ መሔዳቸዉን ማንም ይገነዘበዋል።ሼክ ሸሪፍ ያላቸዉ በጣም ትንሽ ጊዜ ነዉ።ብዙ ጊዜ አልተረፋቸዉም።እንደሚመስለኝ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ከአማፂያኑ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሆነ-አይነት ድርድር ካልጀመረ ሁሉም ነገር ይበለሻል።»

ICG

ነጋሽ መሐመድ/ሂሩት መለሰ